የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፕሮፌሰር አታላይ አለም ይባላሉ። የተወለዱት ጎጃም በድሮ አጠራሩ አገዎ ምድር አውራጃ አንቀሻ ወረዳ ጃውቡታ ጊዎርጊስ በምትባል ገጠር ውስጥ ነው። እድሜያቸው ለትምህርት እስኪደርስም የወላጆቻቸውን ከብቶች ጠብቀዋል። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት እንጂባራ ከተማ ሲሆን፣ የተማሩትም በየእለቱ የአንድ ሰዓት ተኩል የእግር ጉዞ በማድረግ ነው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በባህር ዳር አሁን ጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመባል በሚታወቀው በአጼ ሰረጸድንግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
በወቅቱ እርሳቸው ተውልደው የተማሩበት አካባቢ የተማረ ሰው ብዙም አልነበረም። በዛ አካባቢ በጣም የተማረ ነው የሚባለው የአንደኛ ደረጃ መምህር ነበር። የእርሳቸውም ምኞት እንደእሱ መሆን ነበር። ይሁንና ምኞታቸው ሊሳካ አልቻለም። ላለመሳካቱ ምክንያት የሆነው ደግሞ በወቅቱ ይፈለግ የነበረው የእድሜ መነሻ 18 ዓመት ሲሆን፣ የእርሳቸው እድሜ ደግሞ 17 በመሆኑ ነበር። በእድሜያቸው ማነስ ምክንያት መምህር መሆን ሳይችሉ ቀርተው ሐኪም ለመሆን ተገደዱ።
መምህር የመሆን እድል ስላመለጣቸው ትምህርታቸውን መቀጠልና ማትሪክ ለመፈተን ወሰኑ። ይሁንና በዛሬው አጠራሩ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በወቅቱ ደግሞ ጎንደር ጤና ጥበቃ ኮሌጅ በዲፕሎማ ከሚያስተምራቸው ሶስት የትምህርት አይነቶች መካከል አንዱ በሆነው የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ተቆጣጣሪነት ኮርስ ተፈትነው እርሳቸው ብቻ ማለፍ ቻሉ፤ የመምህርነቱን ኮርስ በእድሜያቸው ማነስ ምክንያት አለማግኘታቸው ቢያስከፋቸውም ወደጎንደር አቅንተው ጎንደር ጤና ጥበቃ ኮሌጅ ለሶስት ዓመት ዲፕሎማ ተማሩ። ተመርቀውም ሞጣ ለአንድ ዓመት አገለገሉ። በወቅቱ የደርግ አገዛዝ ነበርና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆናቸው ብቻ ባጋጠማቸው ነቀፌታ ምክንያት ከሞጣ ተቀይረው ሀረርጌ ኤጀርሳ ጎሮ ተዛወሩ።
ትንሽ ቆይቶ ደግሞ እድገት በህብረት የሚባል ዘመቻ በመምጣቱ ወደ ጅግጅጋ ዘመቱ። ከዛ ሲመለሱ ቀደም ሲል አሰበ ተፈሪ የአሁኑ ጭሮ ከተማ የጤና ተቆጣጣሪ ሆነው ለአንድ ዓመት ሰሩ። ይህ ሲሆን፣ በግላቸው የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርትን ያጠኑ ነበር፡ ኮሌጅ እያሉም የ11ኛን ክፍል ትምህርት በተወሰነ መልኩ ሲማሩም ነበር። ስለዚህም ብቁ በመሆናቸው ከትምህርት ሚኒስቴር ተፈቅዶላቸው ማትሪክ እንዲፈተኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጠረላቸው። ተፈትነውም አለፉ። ከዚያም በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገቡ። በ1975 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሐኪም ሆኑ። በዚያው ዓመት ሐምሌ ላይ ተመረቁ። ከምረቃ በኋላ እጣ ሲያወጡ አዴግራት ሆስፒታል ስለደረሳቸው ወደዚያው ከአንድ ሌላ ጓደኛቸው ጋር አቀኑ።
በወቅቱ አዴግራትን ጨምሮ ትግራይ ጦርነት ውስጥ ነበረች፤ ይህም ጦርነት በደርግ፣ ሻቢያና ወያኔ አማካይነት የሚደረግ ነው። በመሆኑም በየቀኑ ከመቀሌ አዲግራት መኪና አይሄድም ነበር። ከአዲስ አበባ መቀሌ በአውሮፕላን ይኬድና በአንድ ወርና በሁለት ወር ደግሞ ኮንቮይ በአጃቢነት ወደአዲግራት ይሄዳል። እናም ዛሬ ኮንቮይ አለ ከተባለ መኪና የሚያዩበት ቀናቸው በመሆኑ በጣም ትልቅ የደስታ ቀናቸው ይሆን ነበር፤ በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት እዛ ሰሩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ቀደም ሲል በጤና ተቆጣጣሪነት የአራት ዓመት ልምድ ስለነበራቸው ያ ተቆጥሮላቸው በአንድ ዓመት ውስጥ አዲስ አበባ እንዲገቡ ተፈቀደላቸው። እኚህ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ የአዕምሮ ሐኪም ናቸው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ መምህርና ተመራማሪም ናቸው። ክእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ጭውውት እነሆ ለንባብ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ አማኑኤል ሆስፒታል ቢመደቡም ትንሽ አንገራግረው እንደነበር ይነገራል፤ ያለመፈልግዎ ምክንያትዎ ምን ይሆን? እስኪ ስለሱ ያጫውቱን?
ፕሮፌሰር አታላይ፡– አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ክፍት ቦታ ያለንና የሐኪም እጥረት ያለው አማኑኤል ሆስፒታል ነው ፣ የምትመደበው እዛ ነው አሉኝ። እምብዛም የዘርፉ ፍላጎት ስላልነበረኝ የተወሰነ ጊዜ አንገራገርኩ። ይሁንና ገብቼ መስራት ጀምርኩ። እዛ ሆስፒታል ወደሶስት ዓመት ሰራሁ። እዛ እያለሁ እንግሊዝ አገር የትምህርት እድል አግቼ በአዕምሮ ሕክምና በማንቺስተር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዜሽን አድርጌ ወደአገሬ ተመልሼ እዛው አማኤል ሆስፒታል ተመደብኩ። በዚሁ ሆስፒታል በዳይሬክተርነት ወደ ስድስት ዓመት ያህል ሰራሁ።
በኋላም ወደሲወድን አገር ሌላ የትምህርት እድል ስላገኘሁ ወደዛው አቀናሁ። በዚያው ዘርፍ ሶስተኛ ዲግሪዬን ተምሬ ተመልሼም ወደአገሬ በመምጣት እዘዛው አማኑኤል ሆስፒታል መስራት ቀጠልኩ ። በወቅቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተባባሪ መምህርነት የአዕምሮ ሕክምና ነርሶችን አሰለጥን ነበር። ብዙ የምርምር ስራዎችን ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር ሆኜ መስራት የጀመርኩት እዛው ነው። ጥቂት ዓመት በዚህ መልኩ ከሰራሁ ቦሃላ ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ተዛወርኩ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጣሁ በኋላም በአዕምሮ ሕክምና ክፍል ውስጥ የድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍል ውስጥ የመጀመሪያው አስተባባሪ ሆኜ ትምህርት እንዲጀመር አስተዋጽኦ ማድረግ ችያለሁ። የድረ ምረቃውን ትምህርት የጀመርነው ጓደኛቼ ከሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዲሁም አሁን በሕይወት ከሌሉ ከዶክተር አብዱረሺድ ጋር ሶስት ሆነን ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬምበተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግያለሁ።
አዲስ ዩኒቨርሰቲ በተለየ መንገድ ሪፎርም ሲደረግ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እንዳዋቅር ኃላፊነት ተሰጥቶኝ እሱን በመምራት ኮሌጁን አቋቋምኩ። ኮሌጁን በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከመሩት ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙና የመጀመሪያው ነኝ።
ቀደም ባለው ጊዜ የአዕምሮ ህክምና በውጭ አገር ተምረው የመጡት ሐኪሞች ጥቂቶች ነበሩ። ስልጠናውን ሲጀምሩ ለጠቅላላ አገሪቷ የነበሩ ሐኪሞች 11 ነበሩ። አሁን ስልጠናውን ከጀመሩ ወዲያ እኛ ያሰለጠናቸው ሐኪሞች የተለያየ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሆነው ይህንኑ ትምህርት ማስተማር ጀምረዋል ።በአሁኑ ሰዓትም ቁጥራቸው ወደ 113 እና ከዚያ በላይ መድረስ ችሏል። በቅርቡ ወደ 130 እና 140 እናደርሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ጀምረዋል። ብዙ ምርምሮች ሰርተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ እዕምሮ ሕመምን በተመለከተ ብዙ ምርምሮች ተሰርተዋል። በዚህም ከአፍሪካ ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ኢትዮጵያ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
አዲስ ዘመን፡- በአዕምሮ ህመም ዙሪያ በምርምር የተገኙ ግኝቶች ምን ይመስላሉ?
ፕሮፌሰር አታላይ፡– ምርምሩን ያደረግነው በገጠርና በከተማ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ነው። ትኩረትም ያደረግነው የአዕምሮ ሕመም ምን ይመስላል? ስርጭቱስ እንዴት ይገለጻል? መጨረሻውስ ምንድን ነው? የሚለውን በስፋት አጥንተናል። ከዚህ አኳያ ጥናቱን ያጠናነው ቡታጅራ አካባቢ ነው ፣ ቃለ መጠይቅ የደረግንላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍ ያለ ቁጥር የነበራቸው ናቸው፤ ይህም ቁጥር በወቅቱ በዓለም አንደኛ የሆነ ነበር። ያን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ላይ በዚህ ልክ የተሰራ ጥናት አልነበረም። በወቅቱ የአዕምሮ ሕመምተኞችን ለመለየት የሚያስችለውን ጥናት ለማካሄድ ቃለ መጠይቅ ያደረግንላቸው ሰዎች ቁጥር ከ68 ሺ በላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ቡታጅራን የመረጣችሁበት ምክንያት ምን ይሆን?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ቡታጅራን የመረጥነው ቀደም ብሎ የተሰራ የህብረተሰብ ምርምር ማዕከላችን እዛ ስላለ ነው እንጂ የተለየ ምክንያት ኖሮን አይደለም። በእርግጥ በዚህ ሰዓት ከዚያም በላይ በስፍራው ተሰርቶ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ያገኘነው ግኝት አንዳንድ የጥናት ግኝቶች እንደሚያመለክቱት በታዳጊ አገሮች ላይ አንዳንድ የአዕምሮ አይነቶች ዝቅተኛ ናቸው፤ በአዕምሮ ሕመም የተያዙ ሰዎች ደግሞ የመዳን እድላቸው ከሌላው ከሰለጠነው ዓለም ይልቅ ከፍተኛ ነው የሚሉ ነበሩ። ነገር ግን የጥናታችን ግኝት እሱን አላሳየም፤ በተቃራኒው ነበር።
በቡታጅራ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት እንዲጀመር አድርገናል። አዲስ ሰው አሰልጥነን ለ12 ዓመት በቡታጅራ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዕምሮ ሕክምናው እንዲጀመር ያደረግን ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በመጀመሪያው የጤና ጣቢያ ውስጥ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት የተጀመረበት የቡታጅራው ነው። የተጀመረውም እኛ በወቅቱ እዛ ስለነበርን እዛ የነበሩ ነርሶችን አሰልጥነን ነው።
በጥናታችን ላይ በምርምር ያገኘናቸው ነገሮች በአብዛኛው ሕክምና ወስደው የሚያውቁ ከአስር በመቶ በታች ነበሩ። ለብዙ ዓመት የታመሙ ቢሆኑም ለሕክምና ግን አልሄዱም። ይህ አንዱ ግኝታችን ነበር። አስር በመቶ የሚሆኑት ወደ አማኑኤል ሆስፒታል አንዴ ወይም ሁለቴ መጥተው ሕክምና የጀመሩ ቢሆንም የእነርሱም ክትትላቸው ብዙም አልነበረም። ከእነርሱ ውስጥ ክትትል የነበራቸው አንድ ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆኑት ናቸው። ይህም አንደኛው ግኝታችን ነው።
ሌላው ደግሞ እያከምናቸው ለ12 ዓመት ከተከታልናቸው መካከል ብዙዎቹ የተሻለ ለውጥ አምጥተዋል፤ ትዳር የያዙ፤ ስራ የጀመሩ፤ ያቋረጡትን ስራ መልሰው መስራት የጀመሩ ነበሩ። ይህንን ለፖሊሲ አውጪዎችም ሆነ ለዓለም አቀፉም ማህበረሰብ አሳውቀናል።
የአዕምሮ ሕመም የሚገድል በሽታ አይደለም። ነገር ግን የሚገባውን ያህል ትኩረት ያላገኘ፤ መንግስትም በትክክል ያልተረዳው ነው። ነገር ግን የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ቀድሞ የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ነው። ይህንንም አሳይተናል። እድሜያቸው ከ20 እስከ 25 ዓመት ያጠረ ይሆናል። ምክንያቱም አንድ ጤነኛ ሰው የሚያደርገውን አይነት ጥንቃቄ ለራሳቸው ለማድረግ ስለሚቸገሩ መሆኑንም በጥናታችን አመላክተናል።
ሌላው የአዕምሮ ሕመምን ለማከም የተለየ ስፔሻሊስት ሳያስፈልገው ለተወሰኑ ጤና ጣቢያ አካባቢ ለሚሰሩ ሙያኞች ስልጠና ሰጥቶ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ማከምና መርዳት እንደሚችሉም አሳይተናል። የአዕምሮ ሕመም ደግሞ እንደማንኛውም ሕመም በየትኛውም የጤና ተቋም ሊታከም የሚችል ነው እንጂ የግድ አማኑኤል ሆስፒታል ወይም የተለየ ተቋም መሄድ የግድ አለመሆኑን አመላክተናል። በጥናታችን ያሳየነው እነዚህንና መሰል ግኝቶችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛውን ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ የአዕምሮ ሕመም ማለት አንድ ሰው ጨርቁን ጥሎ አሊያም ብቻውን እያወራ ሲሄድ ሲታይ ነው፤ የአዕምሮ ሕመም ማለት በዚህ የሚወሰን ነው?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- የአዕምሮ ሕመም ሲባል ለብዙ ሰው አንድ አይነት መገለጫ ያለው ይመስለዋል። በተለይ አንድ ሰው ቆሽሾና ጨርቁን ጥሎ እርቃኑ ሲሄድ ከታየና የሰውን ትኩረት በሚስብ መልኩ የሚሄድ ከሆነ አዕምሮውን አመመው ይባላል። ይህ አንድ አይነቱ ነው። ነገር ግን የአዕምሮ ሕመም ወደ 300 አይነት የሚጠጋ ነው። ደረጃውም አይነቱም መገለጫ መንገዱም ግን ለየቅል ነው። እንደዚያውም ሁሉ መነሻውም ለየቅል ነው። ለምሳሌ ስነ ሕይወታዊ ከሚባለው አንዱ አካላችን ላይ ከሚደርሱ ነገሮች የተነሳ የሚመጣ የአዕምሮ ሕመም አለ። ሌላው ማህበራዊ ሲሆን፣ ይኸውም ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት፣ ከአሰተዳደግ፣ ከሰላም፣ ከስደትና መፈናቀል፣ ከጦርነትና መሰል ነገሮች ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችል ነው። ልክ እንደሌላው የአካል ሕመም አይነት በላቦራቶሪ ምርመራ የሚገኝ አይነት ሕመም ሳይሆን በባህሪ ለውጥና በሚደረገው ንግግር እንዲሁም በሚኖር ግንኙነት ላይ ተመስርቶ በሚደረግ የምርመራ ዘዴ ነው።
እኔና ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ስንመጣ (በእርግጥ እሱ እኔን አንድ ዓመት ይቀድመኛል) በአገሪቱ ያለው ብቸኛው የአዕምሮ ሕሙማን ሆስፒታል አማኑኤል ነበር። አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ መስፍን ሲመጣ ያገኘው 500 ሕሙማንን ነበር። ነገር ግን በወቅቱ የነበረው አልጋ 360 ብቻ ነበር። 140 ያህል ሕመምተኛ ግን አልጋ አልነበረውም። ይህ ማለት በ1976 ዓ.ም ላይ ነው። በእርግጥ አሁን ብዙ ነገር የተሻሻለ ሆኗል። ይሁን እንጂ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት አያስደፍርም።
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎ ምኞት የነበረው በወቅቱ መምህርነት ነው፤ የሕይወት አቅጣጫዎ ባላሰቡት ዘርፍ ወደሕክምናው አምጥቶዎታልና በዚህ ይቆጫሉ? ወይስ የሚሰማዎት ሌላ ነገር አለ?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- በፍጹም አልቆጭም፤ እንዲያውም በጣም ደስ ነው የሚለኝ። እኔ የምረዳው ይህን መንገድ እግዚአብሔር እንደመረጠልኝ ነው። በመጨረሻም የሆንኩት ያው በዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው እንጂ መምህር ነው። እኔ ደግሞ መምህር መሆን በጣም የምወደው ስራ ነው።
በእርግጥ ሐኪም ከሆንኩ በኋላ በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ሐኪም ሆናለሁ ብዬም አላሰብኩም ነበር። እሱንም ቢሆን የገባሁት ተገድጄ ነው። አማኑኤል ላለመግባት አንገራግሬ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በመግባቴ እግዚአብሔርን የማመሰግንበት ነገር ሆኗል። ምክንያቱም ብዙ ሰዎችን ረድቻለሁ፤ ለብዙዎችም ምሳሌ ሆኛለሁ ብዬ እገምታለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በ1983 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ወታደሮችን ለማከም ወደአስመራ እንደሄዱ ሰማሁ፤ ዛሬም ደግሞ ከብዙ ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ጦርነቱ አልበረደም፤ የትናንቱም ሆነ የዛሬው ታሪካችን የሚያሳየው ያው ጦርነትን ነውና ጦርነት ከአዕምሮ ሰላም ጋር ያለውን መጣረስ ይንገሩን?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- በጣም የሚያሳዝነው ነገር እኛ በጦርነት ያደግን፤ በጦርነት ያረጀን ትውልድ ነን። እኔ ሞጣ ጤና ጣቢያ ውስጥ የጤና አጠባበቅ ተቆጣጣሪ ሆኜ ነው በ1966 ዓ.ም አብዮት ፈነዳ የተባለው። ከዚያ በፊት ታሪክ የሚያወሳውን ትቼ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን በአገራችን ላይ ኑሯችንም ሕይወታችንም ጦርነት ሆነ። ከሞጣ ወደሐረርጌ ተቀይሬ በምሰራበት ጊዜ እኛ ኮሚኒስት አገሮች ስንሆን ከሱማሊያ ጋር በጣም ትልቅ ጦርነት ተከፈተ። በወቅቱ በሱማሊያ ጦርነት ጊዜ አሰበ ተፈሪ ነበርኩ (የአሁኗ ጭሮ)። በወቅቱ ከባድ ነውጥ ነበር። ከዚያ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ።
በዚያ አካባቢ ወደዩኒቨርሲቲ የምንሄደው ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር እየተባለ ሰዎች ስለሚገደሉ በየጎዳናው አስክሬን እያየን ነበር። እኛም በተለያየ መንገድ እንጠረጠር ነበር። እኔ ለምሳሌ ምንም በማላውቀው ኢህአፓ ነህ ተብዬ በመጠርጠሬ አንድ ሁለቴ ታስሬያለሁ። በዚህ መልኩ እድሜያችንን የኖርነው በጦርነት ውስጥ ነው ማለት ይቻላል።
ጦርነት በአዕምሮ ላይ ያለው ተጽዕኖ በጣም ከባድ ነው። የነገን እቅድ ለማቀድ ሰላም ወሳኝ ነው። ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ካለ ሕይወት ትርጉም ያጣል። ያለተስፋ ደግሞ መኖር አይቻልም። ጦርነት ካለ ተስፋ ይቀጭጫል፤ ኑሮም የስጋት ይሆናል። መፈናቀሉ፣ ረሃቡ፣ ስደቱና ከቤተሰብ ውስጥ በጦርነት ሳቢያ የቅርብ የምንለውን ሰው ማጣቱ ሁሉ የሚፈጥረው ስሜት ከባድ ነው። የተስፋ መታጣትና የስጋት መንገስ ደግሞ ለአዕምሮ ጤና ጠንቅ ይሆናል።
በጦርነት ሳቢያ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው፣ የተለያየ የስነ ልቦና ጫና ያጋጠማቸው ሰዎች አዕምሯቸው በሰላሙ ጊዜ ከሚሆነው የበለጠ ተጋላጭነቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አገራችን እያለፈችበት ያለው ሁኔታ አሳዛኝ ነው። ጦርነት እና የአዕምሮ ሕመም በጣም ግንኙነት ያላቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ጭካኔ የተሞላበት ጦረኛ መሆን ምን አይነት አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም ነው?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ጭካኔ የተሞላበት ጦረኛነት ከአስተዳደግ፣ ከባህልና ከስብዕና ጋር የተገናኘ ነገር ነው። በስብዕናችን ውስጥ ብዙ አይነት ነገር አለ። ጭካኔ፣ ርህራሄ፣ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ቂመኝነት፣ ኩርፊያ፣ ሳቅ ይህ በአንድ ሰው ውስጥ ያለ የስብዕናው ክፍል ነው። ለምሳሌ ጭካኔው እንዲያመዝን ተደርጎ በጀግንነትና በአልሸነፍ ባይነት ስም እየሰጠን ልጆችን ከተቀረጽን ይህ ይዘውት የሚያድጉት ባህል ይሆናል። በተቃራኒው ርህራሄን፣ ፍቅርንና ደስተኝነትን ዋጋ እንዳለመስጠት ይሆናል። ዋና ነገር አሸናፊነትና የበላይነት ተደርጎ ሲወሰድ ስብዕና ይጠፋል። ከአራዊትም ያነሰ ባህሪ ይፈጠራል፤ የዱር አራዊት መሰሉን አይገድልም፤ አይበላም፤ እርስ በእርሱ የሚባለው ሰው ሆኗል። ይህ ግን ጨካኝነት ነውና ከእንስሳት ያነሰ ባህሪ እንዳይታይብን መልካሙን መውሰድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይም ሆነ በሰዎች አማካይነት የሚነገረው ፕሮፓጋንዳ በቅጡ መጠቀም ካልተቻለ የሰውን አዕምሮ በማጣመምም ሆነ ጨካኝ በማድረግ በኩል ትልቁን ድርሻ ይይዛልና እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ቴክኖሎጂው ብዙ ክፍሉ ጠቃሚ ስለመሆኑ እሙን። በዛው ልክ ደግ የሰውን አዕምሮ በክፋት ለማነሳሳት ሰፊውን ድርሻ ተጫውቷል እላለሁ። ለምሳሌ የስነ ልቡና ጦርነት የሚባል ነገር አለ። የስነ ልቦና ጦርነት ማለት በተቃራኒው ወገን ያለ አጥቂ በዛኛው በኩል ያለው ኃይል የበለጠ የገዘፈ አድርጎ ማሳየት ነው። ይህ ለተጠቂነት፣ ተስፋ ለመቁረጥና እጅ ለመስጠት አይነተኛ መሳሪያ ነው። ከዚህ የተነሳ ሰው መረጋጋት፣ እቅድ ማውጣት ከባድ ይሆንበታል። በተለይ የመረጃ ጫና አዕምሯችን ሊያስተናግድ ከሚችለው በላይ እየሆነበት ይመጣል። ከሚገባው በላይ ጭነት እንዲበዛበት ከተደረገ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ መረጃችን የተመረጠና የተመጠነ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በራስ እሴት ያለመጠቀም ነገር ወጣቱ ዘንድ ይስተዋላል፤ ሽማግሌዎች የሚሉትንም መስማት እንደሞኝ የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ተደርሷልና እዚህ ላይ መላው ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- የምዕራባውያኑ የባህል ወረራ ያመጣው ጣጣ ነው እላለሁ። ፈረንጆች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ልክ ነው ብሎ መቀበል በብዙዎች ዘንድ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ በሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ የኃይማኖት አባቶች ንግግራቸውና ተግባራቸው ለየቅል መሆኑ ነው። ሁሉም ቤተ ክርስትያንም መስጂድም እያለ ይሄዳል ይመጣል እንጂ እምነቱ በትክክል ገብቶት ለዛ እምነት የሚገዛ የለም ማለት ይቻላል፤ እንዲያውም የኢትዮጵያ ሕዝብ 97 በመቶ በፈጣሪው የሚያምን ነው ይባላል፤ በተግባር ሲፈተሽ ግን ሁኔታው የተለየ ገጽታ ሊኖረው ይችላል ። ይህ ደግሞ በደርግ የኮሚኒስት ሥርዓት ጊዜ እግዚአብሔር የለም በሚል የተዘራ ዘር ነው ብዬ አምናለሁ ። ይህም አሁን ላለው ልቅ አመለካከት መሰረት ጥሎ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስለጦርነት ያልዎት እሳቤ ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ጦርነት አውዳሚ ነው። ጦርነት በጦረኛው አስተሳሰብ ስላሸነፈ ማሸነፍ ይባል እንጂ በጦርነት ውስጥ ማሸነፍ የሚባል ነገር የለም። የሚገጥመው ኪሳራ ቡድኑ ካሰበው በላይ ነው። ስለዚህ ከእንስሳትም ያነሰ ሕሊና ያለን ካልሆንን በስተቀር እኔ ወንድሜንና እህቴን ገድዬ አሸናፊ ነኝ ብዬ መናገር ከስብዕና ጋር የሚሄድ ነገር አይደለም። በመሆኑም አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ጦርነትም ቢሆን አዋጭ ባለመሆኑ ወደሰላምና ድርድር መምጣቱ መልካም ነው የሚል አመለካከት አለኝ። ለሰላም ቅድመ ሁኔታ በመደርደር ይህ እና ያኛው ካልሆነ የሚባል ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። አሸናፊነት የሚመጣው በጦርነት ሳይሆን በሰላም መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ታማለች፤ ልትድን የምትችለው እንዴት ነው?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- በኦፕራሲዮን! መርዙን ለማውጣት ኦፕራሲዮን መደረግ አለባት። እሱም አሁን በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካይነት በእነ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የተጀመረው ጉዳይ ነው ሊያድናት የሚችለው። እግዚአብሔርም የሚወደው ሐሳብ ስለሆነ ከጦርነት ይልቅ መመካከርና መነጋገር ነው ሊያድነን የሚችለው ብዬ አምናለሁ። አሁን ማንም ያሸንፍ ማንም ከዚያ በኋላ መኖር አለ። አሸናፊው ስላሸነፈ ብቻ ልግዛህ ይላል፤ ተሸናፊውም ደግሞ ስለተሸነፈ ልበቀልህ ይላል እንጂ በጦርነት ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ ስር ነቀል ሰላምና የተረጋጋ ኑሮ ሊመጣ አይችልም።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ሄልዝ ያገኙትን ጨምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከተለያዩ ተቋማት በሥነ አእምሮ ሕክምና ዘርፍ ለአገሪቱ ባበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ሽልማት እንዳገኙ አውቃለሁ፤ ስለእሱ ያጫውቱን አስኪ?
ፕሮፌሰር አታላይ፡– የተሰጠኝ ሽልማት በአብዛኛው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰራሁት እና ካበረከትኩት አገልግሎት የተነሳ ነው። በተለይ የተሸለምኩት ሰዎችን በማከም፣ በመመራመር እና ጥናት በማድረግ በሰራሁት ስራ ነው። የመጀመሪያው ሽልማት የተበረከተለኝ ስታንሊ ፋውንዴሽን ቡታጅራ ላይ 68 ሺ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በተሰራው ስራ ነው። ሌላው ሽልማት ደግሞ በአዕምሮ ሕክምና ዘርፍ የድህረ ምረቃ በማስጀመራችን እና በማስተማራችን እንዲሁም ጥሩ ደረጃ ላይ በመሆናችን የእኛን የትምህርት ዘርፍ የመሰረቱ የኔዘርላድስ ዜጋ የሆኑ ሮበርት ጌል በሚባሉ ሰው ስም የሚሰጠውን ሽልማት እንደቡድን ወስደናል።
ሌላው በየዓመቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለተመራማሪዎች ሽልማት ይሰጣል፤ የእኛም ኮሌጅ እንዲሁ። በአንዱ ዓመት የዩኒቨርስቲውም የኮሌጁም በሰራሁት ምርምር ተሸላሚ ነበርኩ። ሌላው የአዕምሮ ሕክምና ማህበር ደግሞ በጠቅላላው በነበረኝ አገልግሎት በህክምናውም በማስተማሩም በምርምሩም እውቅና ለመስጠት ብሎ ሽልማት ሰጥተውኛል።
ሌላው የጤና አጠባበቅ ማህበር በየዓመቱ ሰዎች እየመረጠ ይሸልማል። በዚህም ከምርምርና ከስራዬ ጋር በተገናኘ የአንዱ ዓመት ተሸላሚ ነበርኩ። እኤአ በ2019 ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ እንዲሁ በየዓመቱ እየመረጠ ይሸልም ነበርና እሱ እስካሁንም ድረስ እንዴት ልመረጥ እንደቻልኩ ባልገባኝ ሁኔታ የተሸለምኩት ሽልማት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በኋላ ለአገርዎ ምን ማድረግ አስበዋል?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ከዚህ በኋላ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማማከሬን እቀጥላለሁ፤ ምርምሮችን ማድረግም እንዲሁ። ኅብረተሰቡን ባገኘሁት እድል ሁሉ ማስተማር እፈልጋለሁ። ከዚህ በተረፈ ምሳሌ የሚሆን ሽማግሌ መሆን እሻለሁ። በቤተ ክርስትያንም አካባቢ ጊዜ አጥሮኝ ያላደረግኳቸውን ነገሮች ለማድረግ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ካነሱት አልቀረ በቤተ በሙሉ ወንጌል አማኞች ክርስትያን በዝማሬ እንደሚያገለግሉ አውቃለሁ፤ አገልግሎትና የምርምር ስራዎን እንዴት ነው የሚያስኬዱት?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስትያን በ‹ሀ› ኳየር ውስጥ ለ15 ዓመታት በዝማሬ አገልግያለሁ። የእግዚአብሔርን ቃልም እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሰረት አካፍላለሁ፤ አንዳንድ ትምህርቶችንም በማዘጋጀት አገለግላለሁ። ስለዚህ በስራና በአገልግሎት መካከል መፋለስ አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖር ይሆን?
ፕሮፌሰር አታላይ፡- ማንሳት የምፈልገው ነገር በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የማየውና ልቤን የሚያሳዝነኝ ነገር ሁላችንም በሌላው ላይ ጣት ቀሳሪ ነን እንጂ እኛ የተሰጠነን ኃላፊነት በትክክል እየተወጣን አይደለንም። ስለዚህ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣታችን ላይ እናተኮር እንጂ በሌላው ላይ ጣታችንን ለመቀሰር አንጣደፍ እላለሁ። የየራሳችንን ኃላፊነት ለመወጣት ከሞከርን አገራችን የተሻለች ትሆናለች ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታና ስለፈቃደኛነትዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አታላይ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014