ከኳታሯ ዶሃ የጀመረው ዓመታዊው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 85 የሚሆኑ የኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮና የሜዳሊያ አሸናፊዎችን በተለያዩ 13 ከተሞች አፎካክሮ ሊገባደድ ደርሷል። ለአራት ወራት ያህል በበርካታ የአውሮፓ እንዲሁም በአንድ አንድ የሰሜን አሜሪካ፣ እስያ እና አፍሪካ ከተሞች በተለያዩ የአትሌቲክስ ዲሲፕሊኖች ሲደረግ የቆየው ይህ ውድድር ከቀናት በኋላ ይቋጫል። ዛሬ በቤልጂየም ዋና ከተማ ብራሰልስ የሚካሄደውን ውድድር ተከትሎ ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ በስዊዘርላንድ ዙሪክ የዳይመንድ ሊጉ አጠቃላይ አሸናፊዎች የሚለዩ ይሆናል።
ከመላው ዓለም የተውጣጡትና በተለያዩ ከተሞች ባደረጓቸው ውድድሮች ነጥቦችን ሲሰበስቡ የቆዩት የስፖርቱ ምርጥ አትሌቶች የመጨረሻውንና ወሳኙን ውድድር ዛሬ ያደርጋሉ። ለዚህም የሉዛኑ ሚሞሪያል ቫን ዳም ስታዲየም የመም እና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆኗል። 14 ዓይነት የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በሆኑት የአጭርና መካከለኛ ርቀት ውድድሮች ላይ ተካፋይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለዳይመንድሊጉ አጠቃላይ አሸናፊነት ወደሚያደርጉት ግስጋሴ ይበልጥ እንደሚጠጉ ይጠበቃል።
በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ3ሺ ሜትር መሰናክል እንዲሁም በ1ሺ500 ሜትር ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል። በዓመቱ መልካም የሚባል ብቃት እያሳዩ ያሉት እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች በሚካፈሉበት በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑ እርስ በእርስ የሚኖራቸው ፉክክር እንደሚበረታም ይጠበቃል።
በ3ሺ መሰናክል በኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ በማጥለቅ በርቀቱ አገሯን ያስጠራችው አትሌት የወርቅውሃ ጌታቸው ተወዳዳሪ ናት። የወርቅውሃ ሞናኮ ላይ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን፤ በወቅቱ የገባችበት ሰዓትም 9:06.19 ሆኖ ተመዝግቦላታል። የወርቅውሃ በርቀቱ ያላት ፈጣን ሰዓት ደግሞ 8 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ከ61 ማይክሮ ሰከንድ ነው። አትሌቷ ባላት ፈጣን ሰዓት ቀዳሚዋ ስትሆን፤ ከወቅታዊ አቋሟ ጋር ተያይዞም የዛሬውን ውድድር የማሸነፍ ዕድል እንደሚኖራት ይጠበቃል። ተፎካካሪዎቿም ቢሆኑ የሌላ አገር አትሌቶች ሳይሆኑ የአገሯ ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የሚገመተው።
ሌላኛዋ የውድድሩ ተጠባቂ አትሌት ደግሞ መቅደስ አበበ ናት። በኦሪጎን የወርቅ ውሃን ተከትላ በመግባት ለአገሯ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌቷ በዶሃው ዳይመንድ ሊግ ተካፋይ ነበረች። አትሌቷ 8 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ ከ08 ማይክሮ ሰከንድ የሆነ የግሏ ፈጣን ሰዓት አላት። ዘርፌ ወንድምአገኝም በዛሬው ውድድር የምትሳተፍ ሌላኛዋ ወጣት አትሌት ናት። አትሌቷ በሞናኮው ዳመንድሊግ ላይ የወርቅውሃን ተከትላ መግባት የቻለች ሲሆን፤ በማይክሮ ሰከንዶች ብቻ ተቀድማም 9:06.63 የሆነ ሰዓት አስመዝግባለች። ይህም በርቀቱን ያስመዘገበችው ፈጣኑ ሰዓቷ ነው።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፋት የሚካፈሉበት ሌላኛው ርቀት ደግሞ 1ሺ500 ሜትር ነው። በዚህ ውድድር ላይ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኘችው አትሌት ደግሞ ፍሬወይኒ ኃይሉ ናት። በዚህ ርቀት በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በዩጂኑ የዓለም ቻምፒዮና አገሯን የወከለችው ፍሬወይኒ የዲፕሎማ ባለቤት መሆኗ የሚታወስ ነው። በርቀቱ 3፡56፡28 የሆነ ሰዓት ያላት ይህች አትሌት የውድድሩ አሸናፊ ልትሆን እንደምትችል ይጠበቃል።
ለፍሬወይኒ ፈተና እንደምትሆን የምትጠበቀው አትሌት ደግሞ ድርቤ ወልተጂ ናት። ድርቤ በዛሬው ውድድር ከሚሳተፉ አትሌቶች ከፍሬወይኒ በማይክሮ ሰከንዶች የዘገየ ፈጣን ሰዓት ያላት ሆና የተቀመጠች ሲሆን፤ ባለፈው ወር መጀመሪያ በፖላንድ በተካሄደ የዳይመንድሊግ ውድድር በርቀቱ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር ጭምር ማሸነፍ የቻለች አትሌት መሆኗ ይታወቃል። ይህም ድሏን በድጋሚ ብራሰልስ ላይ ለማጣጣም እንደምትሮጥ ተጠባቂ አድርጓታል። አክሱማዊት እምባዬ እና አያል ዳኛቸውም በተመሳሳይ ከፍተኛ የአሸናፊነት ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል ናቸው።
በወንዶች በኩል ዛሬ በብራሰልስ የሚሮጠው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ነው። በ5ሺ ሜትር ርቀት የሚሮጠው አትሌቱ ከሁለት ወር በፊት ሮም ላይ በመሮጥ 12:52.10 የሆነ ሰዓት ነበር ያስመዘገበው። አትሌቱ በርቀቱ 12፡46፡79 የሆነ ሰዓት ያለው ሲሆን፤ በዛሬው ውድድርም ለማሸነፍ እንደሚሮጥ ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014