መምህር ማሙሸት ለማ እባላለሁ። በሙያዬ መምህር ነኝ። በሙያው ከ25 ዓመት በላይ አገልግያለሁ።20 ዓመቱን በነፃ ነው ያስተማርኩት። የማስተማር ሥራውን ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት እያለሁ ጅምሬያለሁ። የምሰራው በግሌ ነው። በየቢሮዎች እየሄድኩና በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ አስተምራለሁ።በአካባቢዬም እየሄድኩ አስተምራለሁ። መነን አካባቢ የምኖር ሲሆን፤ በአካባቢው ያሉ ወጣቶች የኔ ተማሪዎች ነበሩ። አሁንም ልጅ ያለ አባት የሚያሳድጉትን አባትነትን ባልተካም የአባት የሚመስል ፍቅር ጭምር እየሰጠሁ አስተምራለሁ።
ሦስት ፈረቃዎች አሉኝ።ብዙዎቹ አራቱን ክህሎቶች ጨብጠው ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል። በቅርቡ ከወደ ትምህርት ሚኒስትር እንደሰማሁት ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ከ65 በመቶ በላይ ማንበብ እንደማይችሉ የተረጋገጠበትን ክፍተት ስሞላ ኖርያለሁ ብዬ አስባለሁ። በጥቅሉ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እየተማሩ ያሉ ፤ የተመረቁ ፤ሥራ የያዙ ተማሪዎች አሉኝ። ይሄን ማድረግ የቻልኩት በተለይ መኖርያ ቤቴን ክፍት በማድረጌ ነው። ባለቤቴም ሶፋዬ ይበላሻል ፣ ሳሎኔ ይቆሽሻልና መስትዋት በሬ ይሰበርብኛ አላለችም።
ብዙዎቻችን ቤታችን በትልቅ ብረት በር በአደገኛ ሽቦ፤ በዘበኛ፤ በኃይለኛ ውሻ እንዲሁም በዘበኛ ታጥሮ የሚጠበቅ ነው። ውስጡም በበርካታ ውድ ቁሳቁሶች ተሞልቷል። በውድ ዋጋ የተገዛ ሶፋ ወንበር፤ ቴሌቪዥንና በሌሎች ዕቃዎች አሸብርቋልም። እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ይዞም ተቆልፏል። ይሄ ለኔ እጅግ ሞኝነት ይመስለኛል። ባለቤቴም እንዲሁ ዓይነት ሀሳብ ነው ያላት። ምክንያቱም እኔም ሆንኩ እሷ ቤት የእግዚአብሄር ነው ሲባል እየሰማነው ያደግነው ። ይሄ በቀጥታ እግዚአብሄር መጥቶ ይቀመጥበታል ሳይሆን የእሱ ፍጡር የሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ነው ማለት እንደሆነ ለማናችንም አይጠፋንም።
እኔም ይሄ ነገ ከነሞላ ቁሳቁሱ ጥለነው የምንሄደው ቤታችንን ከሰው ይልቅ ለግኡዝ ነገር ክብር በመስጠት ቆልፈን በመኖራችን አላምንም። እንደኛ ላለ ደሀ አገር ቤት ክፍት መሆን ያለበት ለሰው ልጆች ነው ብዬ አስባለሁ። የሁሉም ማህበረሰብ እንደሆነም አምናለሁ። በተለይም ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢና ትውልድ አስቀጣይ ለሆኑ ልጆች ነው ባይ ነኝ ። ለዚህ ነው ክፍት ያደረኩላቸው። የኔም ቤት ከማንም አያንስም ። ውበቱና አሰራሩም ልዩና የተጨበጨበለት ነው። ዕምነበረድን ጨምሮ በውድ ቁሳቁስ ነው የተገነባው። ከሳሎን ጀምሮ እስከ ማዕድ ቤት ፤ መኝታ ቤት ያሉ ቁሳቁሶቹም ቢሆኑ ብዙዎቻችሁ ጋር እንዳሉት ሁሉ እጅግ ውድና ዘመናዊ ናቸው ።
አውቃለሁ በልጆች ሊሰበሩ፤ ሊበላሹና ሊቆሽሹ ይችላሉ ። እኔ ለአካባቢዬ ልጆች በሬን ክፍት አድርጌ ፤ ሳሎኔ ውስጥ ባለው ሶፋ ላይ ተንፈላሰው እንዲቀመጡ አንዴ እኔና ባለቤቴ መኝታ ቤት ፤ ሌላ ጊዜ ልጆቼ መኝታ ቤት፤ ሲያሻቸው ማዕድቤት፤ መታጠቢያ ቤት እንዲሯሯጡ የማደርገው እንደ እናንተ ይሰበርብኛልና ይበላሽብኛል የሚል ስጋት ሳይገባኝ ቀርቶ አይደለም።
አሁን ባለፈው ሳምንት እኔ በሬን ከፈትኩላቸው የአካባቢያችን ልጆች የሰባት ዓመቱና የሶስተኛ ክፍል ተማሪው ዶዶ በኃይል እየሮጠ መጥቶ በሩን ሳያንኳኳ ሲከፍተው በውስጥ በኩል በሩ ጋር ቆሞ የነበረውን የሶስት ዓመት ልጄን እግር ጋጠው። ግን ዶዶን በቁጣ ማስደንገጥም ሆነ ስለ ልጄ ጉዳት መናገር አልፈለኩም ። ይሄ የትኛውም ልጅ ሊሰራው የሚችል ጥፋት እንደሆነ ስለማውቅ የአብሥራን ቁጭ አድርጌ በር እንዴት እንደሚከፈት ከመክፈቱ በፊትም ማንኳኳትና ለመግባት የባለቤቱን ፈቃድ መጠየቅ እንደሚገባ አስረዳሁት። ዶዶ ራሱን በማግስቱ ቀይሮ በሳምንት ውስጥ ልጆች ሁሉ ወደ እኔ ቤት ሲገቡ በሩን እንዲያንኳኩና ፈቃድ እንዲጠይቁ በማድረግ አርአያ የሆነ ሥራ ሰርቷል።
አያችሁ አይደል ልጆች በፍጥነት እንዲህ ነው የሚለወጡት! እናም ታድያ በራችሁን ክፍት አድርጉላቸውና ዕድሉን ስጧቸው። እኔ ሁልጊዜ ትምህርት በመንገር ሳይሆን እርስ በእርስ በመነጋገር የምንማረው ነው የምለው ለዚህ ነው ። እርግጥ ነው ጥቁር ሰሌዳ ላይ እየለቀለቁ ልጆችን የሚጨቀጭቁበት ሳይሆን በሁለት መልኩ የሚያዩ መሆን አለበት። እርስ በእርስ መማማርያ ነው። እኔ ለዚህ ነው አንዱ ጥያቄ ሲጠይቀኝ ሌላው ተማሪ እንዲመልስለት ዕድል ምሰጠው ።
ትክክለኛ ትምህርት የሚባለው እንዲህ እንደኔ ተማሪ ዓይነት ፈጣን የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያመጣ ነው። ትምህርት የሚተገበር መሆን አለበት። ለዚህ ነው አራቱ ክህሎቶችን ማለትም ማንበብ፤ መፃፍ ፤መናገርና ማድመጥን በአማርኛና እንግሊዝኛ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ() ኢንፎርማል )ና በሦስት ፈረቃዎች ከፋፍዬ ለማስተማር የጣርኩት። ልጆች ነገ የተሻለ ቦታ ላይ መሆን የሚችሉት ደግሞ ዛሬ ላይ በተደረገላቸው ድጋፍ ነውና ሳልሳሳ የምደግፋቸውም በዚህ ምክንያት ነው።
ፍትህን ገና ከልጅነቱ ያልተማረ ልጅ ሲያድግ እንዴት ነው ፍትሃዊ የሚሆነው። ኢንጅነሩ ብረት ፤ዶክተሩ ኩላሊት ከሸጠ ዳኛው ፍትህ ካዛባ ፤እጅግ ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝና ፖቲከኛ ነው የተባለው በዘር በሚከፋፍል አስተሳሰብ ከገተጓዘ፤ ዜጎችን እርስ በእርሳቸው ካበላላ ፤ቄሱም ሆነ ሼሁና ፓስተሩ የተገላቢጦሽ የሚሰሩ ከሆነ ትምህርት መማር የቱጋር ነው። ይሄ ትምህርት አይደለም። የጎደለ ነገር አለ።በመሆኑም የሰው ልጅ ተገቢነት ያለው ትምህርት ሊኖረው ይገባል ባይ ነኝ። ልጆች ገና ከልጅነታቸው መልካም ነገሮችን ልምምድ ማድረግ አለባቸው። እኔ ልጆችን ሳሰለጥናቸውና በሬን ክፍት ሳደርግላቸው ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ ነገ ዓለምን የሚቀይሩ ጥቂት ሰዎች ለማፍራት ነው። አንዱ ልጅ 10 ልጅ ቢቀይር10 ልጆች በየፊናቸው ነገ 100 ዓለምን የሚቀይሩ ጥቂት ሰዎች ማፍራት እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ። ትላንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ልጅ ሆነው በሻሽ ነበሩ። ዛሬ ቤተመንግስት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንም ሆነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ሌሎቹ አገርን የቀየሩ ጥቂት ሰዎች ሁሉ ትላንት ልጅ ነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ እዚህ ጋር ናቸው ብለን ነው ልጆች ትምህርት ላይ መሥራት ያለብን። ሆኖም ታች ክፍለ ከተማ ቀበሌ እያልን ስንሄድ እንዲህ የሚያሰራ አመራር የለም። ለዚህም በአብነት የማነሳው ባለፈው የገጠመኝን ነው።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ 03/04 ቀበሌ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ጊቢዬ ውስጥ ባለው ቦታ ላይ ያሉኝን ዴስክቶፖች ተጠቅሜ የማስተምርበት አንዲት ክፍል ልስራ ብለው አበጀህ ብሎ እቅፍ አድርጎ ሊፈቅድልኝ ሲገባ ከለከለኝ። በቢሮክራሲ ምክንያትም የማስተማሪያ ጊዜዬን ሊያባክን 40 በመቶ አስፈቅድና እያለ ተስፋ አስቆረጠኝ። እናም እንዲህ አይነት ተገቢ ያልሆኑ አሰራሮች መቀየር አለባቸው ሳልል አላልፍም። እንደአገርም ይህ ነገር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለውናል። እኛም ምክራቸውና ተግባራቸው የሚበረታታ በመሆኑ ትኩረት እንስጠው በማለት አበቃን። ሰላም!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 /2014