የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መልከ ብዙ ገፅታዎች የተላበሰ ነው። ዘመናትን በተሻገረው አገልግሎቱ ሙገሳም ወቀሳም እያስተናገደ ይገኛል። በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዲስ አበቤ ነዋሪዎች ጥያቄ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሆኗል። ወዲህ ደግሞ ባለስልጣኑ የነዋሪዎችን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ማስረጃዎችን ጭምር በማቅረብ ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ ይናገራል።
ለአብነት እንኳን በ2014 በጀት ዓመት የለገዳዲ ክፍል ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክትን በማጠናቀቅ 860ሺ የከተማዋን ነዋሪዎች የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል። ለዚህም አራት ቢሊዮን ብር በጀት የተበጀተለት እንደነበርና ከሁለት እስከ አምስት ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃን በየቀኑ መያዝ የሚችሉ የውሃ ጉድጓዶች ግንባታ የፕሮጀክቱ አካል ነበሩ ሲል ጥረት ማድረጉን አጋርቶናል። ይህ ለአብነት ይጠቀስ እንጂ ባለስልጣኑ እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑንም ያብራራል።
የባለስልጣኑን የኋልዮሽ ታሪክ እንደሚጠቁመው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት በ1893 ዓ.ም ነበር። ይህም የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነ ሰባት ዓመታት ዘግይቶ ነበር። የቧንቧ ውሃ አገልገሎት መጀመርን ተከትሎ አገልግሎቱን ማን ይስጠው የሚለውን መልስ መሻትም ግድ ነበር። በመጀመሪያ የሥራ ሚኒስቴር በመባል ይታወቅ የነበረው መስሪያ ቤት ይህን ኃላፊነት ሲወጣ ቆይቶ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1934 ዓ.ም የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት እንደገና ሲዋቀር ደግሞ ‹‹የውሃ ማደረጃ ዋና መስሪያ ቤት›› በሚል ስያሜ እንደ አንድ የሥራ ክፍል የውሃ አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል ተቋቋመ። እነዚህን ሂደቶች አልፎ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚል ስያሜ አግኝቷል።
ይህ ተቋም በአሁኑ ወቅት ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከምድርና ገፀ ምድር ውሃ በማፈላለግና በማልማት ውሃ እያቀረበ ነው። በዚህም በቀን ከ700ሺ ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ እያቀረበ ነው። ይሁንና የከተማዋ ዕለታዊ የውሃ ፍጆታ 1ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ገደማ ነው።
ለከተማው ነዋሪዎች የገፈርሣ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ፣ የለገዳዲ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ እንዲሁም የድሬ ግድብ ከፍተኛ ውሃ የማምረት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ሌሎች ጉድጓዶችና የከርሠ ምድር ምንጮች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ባለስልጣኑ ከእነዚህ በተጨማሪ ሌሎችንም እያለማ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ደፋ ቀና እያለ ስለመሆኑ ይነገራል።
በዛሬው ዕትማችን ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸው ጋር የባለስልጣኑን የአገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በ2014 በጀት ዓመት ዓበይት ክንውኖች ምንድን ናቸው?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኦፕሬሽን፣ ጥገና እንዲሁም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በየዓመቱ እያቀደ ይሠራል። በበጀት ዓመቱም በዋናነት ካሉ ግድቦች ጉድጓዶች ውሃ አሰራጭቶ በማምረት ረገድ 188 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ አምርቶ ለተጠቃሚዎች አሰራጭቷል። ይህም ከዕቅዱ 86 ከመቶውን ይሸፍናል።
አዲስ ዘመን፡- ለምን 86 ከመቶ ብቻ ሆነ?
ወይዘሮ ሰርካለም፡– 86 በመቶ ብቻ የሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የጉድጓድ ውሃ መጠን መቀነስና የመሳሰሉት ለምርቱ መቀነስ በዋናነት የሚጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። ነገር ግን ከሁሉም ምክንያት እንደባለስልጣኑ ከፍ ብሎ ያየነው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ነው። ከ220 በላይ ጉድጓዶች፣ ሦስት ግድቦች እና ሁለት ማጣሪያ ጣቢያዎች አሉን። ሆኖም በእነዚህ ሁሉ ላይ ጀኔሬተር አናስቀምጥም። ሆኖም በጣም ትልልቅ የሆኑ 87 ዲዝል ጀኔሬተሮች አሉን። በእነዚህ ጀኔሬተሮች ብቻ በ2014 በጀት ዓመት 870 ሺህ ሊትር ነዳጅ ተጠቅመናል። ይህ የኤሌክትሪክ መቆራረጠን ለመቋቋም የተደረገ ጥረት ነው። ባለፈው ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ 220 ሊትር ብልጫ አለው። ይህ የሚያሳየው በበጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ከ2013 በጀት ዓመት አኳያ ከፍ ያለ መሆኑን ነው።
በፍሳሽ በኩል 38 ሚሊዮን 457ሺ 440 ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ አሰባስበንና አጣርተን አስወግደናል። 73ሺ የቤት ለቤት የዘመናዊ ፍሳሽ ቅጥያ ሥራ አከናውነናል። ይህም በዘመናዊ መንገድ ፍሳሽ በማሰባሰብ አጣርቶ ማስወገድ ሽፋን ከ31 ከመቶ ወደ 34 ከመቶ አሳድገናል። ይህም ማለት አብዛኛዎቹ በዘመናዊ መንገድ ወይንም በመስመር ፍሳሽ ማስወገድ ማለት ነው። 38 ትልልቅ ማጣሪያዎች አሉን።
ጎን ለጎን የውሃ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የለገዳዲ ቁጥር ሁለት የውሃ ፕሮጀክትን አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት ዋነኛ ዕቅድ የነበረ ነው። ይህ ፕሮጀክት 16 ጥልቅ ጉድጓዶች፣ 10 የውሃ ማጣሪያ ጋኖች እያንዳንዳቸው ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃን መያዝ የሚችሉ ናቸው። 180 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ 38 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድ ግንባታ እና ሁለት ግዙፍ ግፊት መስጫ ጣቢያዎችና ኤሌክትሮ መካኒካል በውስጡ የያዘ ነው። በቀን 86ሺ ሜትር ኪዩብ መስጠት የሚችልና 860ሺ የከተማዋን ነዋሪዎች የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ይህ ፕሮጀክት ታሳቢ ተደርጎ የተሠራው የጉለሌ እና የየካ ክፍለ ከተሞች ተራራማ አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በነዋሪዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዳለ ይገልፃል። ይህ ለምን ሆነ?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- በዋናነት በበጀት ዓመቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ተቋቁሞ 644ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ አምርቶ ለማሰራጨት ነው እቅዱ። ከእቅዱ ትልቁን ማሳካት ተችሏል። የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ይፋ ያደረገው ባይሆንም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት 4ነጥብ2 ሚሊዮን ነው ብለን ብናስብ፤ በቀን የሚያስፈልገው ውሃ 1ነጥብ2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው። ስለዚህ ያለን አቅምና ኅብረተሰቡ የሚፈልገው የውሃ ፍላጎት መካከል ልዩነት አለ። ስለዚህ ውሃውን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ስንል የፈረቃ መርሐ ግብር እንከተላለን።
በዋናነት የከተማችን ሕዝብ እንዲገነዘብ የምንፈልገው ነገር አለ። የመጀመሪያው ከተማዋ የአፍሪካ መዲና እና የኤምባሲዎች መቀመጫ ናት። አየር መንገዳችንም ትልቁ ምስላችንና መለያችን ነው። የሚፈልጉት ውሃም ከፍተኛ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ነው። መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ የፌዴራል ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ባለኮከብ ሆቴሎችና የመሳሰሉት ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት አላቸው። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የከተማ አረንጓዴ ልማት፣ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶችም፣ የምናመርተውን ውሃ ይፈልጋሉ። ስለዚህ የፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ችግር ወደ ፈረቃ እንድንገባ አድርጎናል።
ነገር ግን በእኛ ግምገማ ትልቁን ጩኸት የሚያነሱት ኢ-መደበኛ ነዋሪዎች በተለይም የማስፋፊያ አካባቢ ያሉ ክፍለ ከተሞች፣ መንግሥት ለአረንጓዴ ልማትና ለመሳሰሉት ያስቀመጣቸውን ቦታዎችን ኢ-መደበኛ በሆነ ሁኔታ የተያዙ ቦታዎች ይህን ጥያቄን በተደጋጋሚ ያነሳሉ። አሁን ባለን አሠራር በመሰል አካባቢዎች የውሃ መስመር የለንም፤ ውሃ ለማቅረብና መስመሩን ለመዘርጋትም ነዋሪዎች ካርታ እና ፕላን ሊኖራቸው ይገባል። እንደ ዜጋ ደግሞ ውሃ ማግኘት አለባቸው። በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች የውሃ ሮቶ አስቀምጠንና በትልቅ ተሽከርካሪዎች ውሃ አመላልሰን እየሞላን ውሃ እንዲያገኙ እያደረግን ነው። ሌሎች ቦታዎች ግን መስመር ያላቸውና በሳምንት የሚያገኙት ምክንያቱ ከምንጩ የውሃ እጥረት ሲከሰት እና መብራት ሲጠፋ ፈረቃው ይዛባል። በመሰል አጋጣሚዎች በሳምንት አንድ ቀን ውሃ ሲያገኙ የነበሩት በሁለት ሳምንት የሚያገኙበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ይህ ሲሆን ግን እኛ የምናደርገው በተሽከርካሪ ውሃ ማቅረብ ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ መስመር ሊበላሽ ይችላል። በዋናነት የምናደርገው ግን ሰዎች ፈረቃቸውን እንዲያውቁ ነው። ቴክኒካል ችግሮች ሲገጥሙን ደግሞ በተቻለ ፍጥነት ለማስተካከል እንሞክራለን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠኑን ገልፀውልኛል። ስለዚህ የውሃ ምርት አቅርቦት ችግር አለ ማለት ነው?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- የውሃ ምርት እጥረት የለብንም። ምርት ማለት ባለ አቅም ማለትም ባሉ ጉድጓዶች እና የከርሰ ምድር የሚመረት ውሃ ማለት ነው። 220 ጉድጓች አሉን። ከገፀ ምድርም ለገዳዲ፤ ገፈርሳ ውሃ እናገኛለን። ለዚህም በቂ ኬሚካል አለን፤ ብዙ ጊዜም እጥረት አጋጥሞን አያውቅም። በመሆኑም ውሃም አክመን እናቀርባለን። ብዙ ጊዜም ኬሚካሉን ቀደም ብለን ገዝተን እንይዛለን። ስለዚህ ባሉን መሠረተ ልማቶች ውሃ እየተመረተ ነው። ነገር ግን ‹‹መሠረተ ልማቶቹ የሚያመርቱት ውሃ እና ከተማዋ የምትፈልገው ውሃ አይጣጣምም›› የሚለው ዋናው ሃሳብ ነው። ከተማዋ በቀን አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ትፈልጋለች። የእኛ 644 ሺ ሜትር ኪዩብ ነው። አዲስ የተመረተውን የለገዳዲን 86ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ስንጨምርበት 730 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው የሚሆነው። ስለዚህ አልተጣጣመም።
አዲስ ዘመን፡- አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣመም ማለት፤ የምርት እጥረት አለ ማለት አይደለምን?
ወይዘሮ ሰርካለም፡– አይደለም! የምርት እጥረት ሳይሆን የአቅርቦት እጥረት አለ። ምርት ማለት የሆነ ፋብሪካ የማምረት አቅም ኖሮት፤ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ አለማምረት ነው። ለምሳሌ 100ሺ ማምረት እየቻለ 50ሺ ካመረተ የምርት እጥረት አለ ይባላል። ምክንያቱም የማምረት አቅሙ 100ሺ ስለሆነ። በእኛ አግባብ ግን ያለማናቸው ጉድጓዶች ማምረት የሚችሉትን እያመረቱ ነው። ፍላጎቱ ግን ከዚህ በላይ ከፍ ያለ ነው። ሌሎች የውሃ ፕሮጀክቶች መጀመርና መከናወን አለባቸው። በእኛ አነጋገር የምርት እጥረት የለም፤ ግን በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ልዩነት አለ። እኛ የምረዳው፤ የምርት እጥረት ማለት ባለ አቅም አለማምረት ማለት ነው። እኛ ባለን አቅም እያመረትን ነው። አንተ የምትረዳው የምርት እጥረትና እኛ የምንረዳው የምርት እጥረት የተለያየ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ በመስመር ድፍርስ ውሃ እያጋጠመን ነው። ይህ ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታም አኳያ የኬሚካል እጥረት ሳይኖር አይቀርም ይላሉ። እርስዎ ከላይ በገለፁት ሀሣብ መሠረት ኅብረተሰቡ ተሳስቶ ይሆን?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- አዎ ስህተት ነው። በዋናነት ኬሚካል የሚፈልጉት ለገዳዲ፣ ገፈርሳ የመሳሰሉት ከገፀ ምድር የውሃ ምርት የሚሰጡን ናቸው። ለዚህ የሚሆን ኬሚካል እጥረት አጋጥሞን አያውቅም። ኬሚካል በበቂ ሁኔታ አለ። የዓለም የጤና ድርጅት የሚያስቀምጠውን መስፈርት በሚያሟላ ደረጃ አክመን ነው የምንለቀው። ነገር ግን አልፎ አልፎ የመስመር ብልሽት ሲያጋጥም በቅጽበት በቁጥጥር ስር የሚውል አይደለም። ጥቆማ ደርሶንና ባለሙያ ደርሶ እስከሚዘጋው ድረስ ውሃ በፍጥነት ግለሰቦች ቤት ሊደርስ ይችላል። ይሁንና መሰል ችግሮች ሲጋጥሙን ወዲያውኑ ዘግተን፤ መስመር ውስጥ ያለውን ውሃ ደግሞ ደፍተንና መስመሩን ጠግነን ንፁህ ውሃ ለተጠቃሚ እናደርሳለን። ከዚህም በተጨማሪ በየቀኑ 30 የሚሆኑ ናሙናዎችን እንወስዳለን። ይህም ከጉድጓዶች፣ ከግለሰቦች፣ ከማጠራቀሚያ ጣቢያዎች ናሙና ወስደን እንፈትሻለን።
ውሃው የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን ስለማሟላቱ፤ ጤናማ ስለመሆኑ ተጣርቶ ነው የሚሰራጨው። ነገር ግን ግለሰቦች አንዳንድ ነገሮችን ሲከውኑ ጭምር መስመር ይሰብሩና ባዕድ ነገር ከውሃው ሊቀላቀል ይችላል። ከዚህ በኋላ ቅሬታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ ጎርፍ ጉድጓድ ውስጥ ሊገባ ይችላል። ሆኖም በቅጽበት እናፀዳዋለን። ውሃ ማምረት እንደ ምግብ ፋብሪካ ነው። በመሆኑም ደረጃው ያልጠበቀውን ውሃ ለመልቀቅም ለማሰራጨትም አዋጁ አይፈቅድልንም፤ እኛም የምንጠቀመው ውሃ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣኑ የሚያከናውናቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶች ይፈጥናሉ፤ አንዳንዶች ለዓመታት ይዘገያሉ። ይህ ከምን የተነሳ ነው ?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- የተጓቱት የት ናቸው? እኛ ዘንድ ወይስ ሌላ ቦታ? በእርግጥ ይህ ዘገየ ብለህ ጠርተህ ያቀረብክልኝ ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ዘንድ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የሉም ማለት ነው?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- ምን መሰለህ፤ የውሃ ፕሮጀክቶች ከሌሎች በዋናነት የሚለየው የሚጠቀማቸው ግብዓቶች ‹‹ሸልፍድ›› ቀድሞ ተገዝቶ የሚቀመጥ አይደሉም። ለምሳሌ አንድ ግንባታ ለማከናወን ሲፈለግ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ቆርቆሮ የመሳሰሉትን ሄዶ ገዝቶ መጠቀም ይቻላል። የውሃ ፕሮጀክት ግን እንደዚያ አይደለም። የለገዳዲ ውሃ ፕሮጀክት እጥረት ስላለ እና በጣም በከፍተኛ ክትትል የተሠራ ነው። የውሃ ፕሮጀክት ትልቅ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል። ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር፤ መንግሥት ሁሉን በጀት ለውሃ በጅቶ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መተው አይችልም።
ሁለተኛው ደግሞ አብዛኞቹ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ናቸው። የውሃ ፕሮጀክቶች ጨረታው ወጥቶ ከዚያም ጨረታው ያሸነፈው አካል ተለይቶ ኤል.ሲ ‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ሊከፈትለት ይገባል። ‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ከተከፈተ በኋላ በዓለም ላይ ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ተብሎ ነው የሚመረተው። ምክንያቱም እዚህ የጥራትና ዲዛይን ሥራ ተሠርቶ በሚፈለገው ዲያሜትርና ስፋት ነው የሚታዘዘው። ይህም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ይወስዳል። ምርቱ ተመርቶ አገር ውስጥ እስከሚገባ ድረስ፤ ከተመረተ በኋላም ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ስለዚህ የውሃ ምርት ከሌሎች የሚለይበት አንዱ ይህ ነው። የውሃ ኢንቨስተመንት ውድ በመሆኑም በየጊዜው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዳይገቡ ያደርጋል። ጥቅም ላይ የሚውሉ አብዛኞቹ ግብዓቶችም በትዕዛዝ ተመርተው ወደ አገር የሚገቡ መሆናቸው ነው። አንዳንድ ፕሮጀክቶች ከመንግሥትም አቅም በላይ የሚሆኑ፤ የፋይናንስ አማራጭ የሚፈለግላቸውና ብድር የሚፈለግላቸው ይኖራሉ። በመሆኑም አበዳሪዎች ብድሩን እስከሚፈቅዱ ድረስ መጠበቅ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ችግሮች ከግምት ውስጥ አስገብቶ ስትራቴጂክ እቅድ ማቀድና ቀድሞ የሚጠበቅበትን ማከናወን የባለስልጣኑ ሥራ አይደለም እንዴ?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- ይህን ባለስልጣኑ እንዳላደረገ አንተ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እየጠየኩኝ ያለሁት በዚህ ላይ እርግጠኛ ለመሆንና፤ ኅብረተሰቡም መረጃውን እንዲያውቅ መሆኑ አልተረዱም?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- በጣም ጥሩ ነው። ለማንኛውም ‹‹ዩቲሊቲ›› በአደጉ አገራት የአምስት ዓመት እና አስር ዓመት አይያዝም። የ50 ዓመትም፤ የ100 ዓመትም ይይዛሉ፤ እኛ ድህነታችን ነው። እኛ እንደ ተቋም ጥናት ያካሄድንባቸው አሉ። ስትራቴጂክ ሆኖ መሄድ ይገባል ላልከው፤ እጃችን ላይ ሦስት ትልልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች አሉን። ከአገር አቅም ጋር ነው የምንሄደው። ለጥናት ሞልቶናል። እጃችን ላይ ገርቢ አለ ካጠናነውም ቆይቷል፤ ጥሩ እየሄደ ነው። አለልቱ ሲዳ-ሮቢ የሚባል አለ፤ ይህም ትልቅ ፕሮጀክት ነው። የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እየሠራን ነው። እነዚህን ሁሉ አጥንተን የተጠናቀቁ፤ ጥናታቸውም በዚህ አመት የሚጠናቀቅ አለ።
እነዚህ ትልልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ናቸው። ስለዚህ ‹ስትራቴጂካሊ› መንግሥትም እኛም ቀድመን አቅደን፣ አስጠንተን፣ ዲዛይኑን አጠናቀን ይዘን ፋይናንስ እየተፈለገላቸው የሚገኙም አሉ። ከውጭ አበዳሪዎቹ ለፕሮጀክቶቹ እንዲያበድሩን ፋይናንስ እያፈላለግን ያሉ ፕሮጀክቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የውሃ መስመር ሲባለሽና ለአንዳንድ አገልግሎቶች ባለሙያዎች በአግባቡ አያገለግሉም፤ ገንዘብ ይጠይቃሉ የሚሉና ሌሎች የሥነ-ምግባር ጥሰት ይነሳል። ባለስልጣኑ ምን ይላል?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- ባለሙያዎች ሳንቲም መጠየቅና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ እኛ ዘንድ ከወሬ ባለፈ የደረሰን ምንም ተጨባጭ ማስረጃ የለም። ይሁንና በወሬ ደረጃ እንሰማለን። ሆኖም ኮሚቴም አዋቅረን እስከታች ድረስ ወርደን ለማጣራት ስንሞክር ምንም ይህ ነው የሚለን የለም። በዚህ አጋጣሚ ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ የምንፈልገው ነገር መሰል ድርጊቶችን ከተመለከቱ በአስቸኳይ ካሳወቁን ለእኛ በቂ ነው። እኛ እንደዚህ ዓይነት ባለሙያዎች ካሉ የምንታገስበት ጫንቃ የለንም። በውሃ እጥረት ላይ የሥነ ምግባር ጉደለት ፈጽሞ አይመከርም። በጣም ከፍተኛ ፍተሻ እናደርጋለን፡ ነገር ግን በተጨባጭ አላገኘንም። አንዳንዴ ባለሙያዎች ፈረቃ ለመስራት ሲሄዱ ውሃ ሌላ አካባቢ ለማሰራጨት የሚመስላቸው አሉ። ሌላው በየመንደሩ ‹‹ፎካል ፐርሰን›› አለን። ውሃ በአግባቡ ስለመድረሱና ቴክኒሺያን በአግባቡ ስለመሥራታቸውም ግምገማ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- የ2015 በጀት ዓመት አንኳር እቅዶች ምንድን ናቸው?
ወይዘሮ ሰርካለም፡- ባለስልጣኑ በ2015 በጀት ዓመት በርካታ ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን የኅብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ያደርጋል። በበጀት ዓመቱም የትኩረት አቅጣጫዎችም ተለይተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የከተማዋን የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት ክፍተትን ሊቀንሱ የሚችሉ የተጀመሩ የውሃ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም በወቅቱ እንዲጠናቀቁ ማድረግ፣ የከተማዋን ፍሳሽ አገልግሎት ሊያሳድጉ የሚችሉ የተጀመሩ የፍሳሽ ልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሳኒቴሽን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ተቋማዊ የመፈጸም እና የማስፈጸም አቅም ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ለአዲስ አበባ የውሃ መገኛ የሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎችን የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
የውሃ ዕጥረት በሚታይባቸው የከተማዋ ኪስ ቦታዎች የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ በማከናወን እና በቀን እስከ 40 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በማምረት ከ400 ሺ በላይ ለሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በበጀት ዓመቱ መቶ ፐርሰንት እንዲደረስ ይደረጋል። ከ2014 በጀት ዓመት የዞሩ ከስድስት ጉድጓዶች ቁፋሮ ውስጥ የቀሪ አምስት ጉድጓዶች ቁፋሮ ሥራ መቶ በመቶ ማጠናቀቅ፣ የአማካሪ ቅጥር በመፈፀም ለጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ የጥናትና ሱፐርቪዥን ሥራውን መቶ በመቶ ማጠናቀቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
የተቋራጭ ቅጥር በመፈፀምም የ15 የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ (በተለያዩ ሎቶች) ሥራ ማከናወን፣ የተቋራጭ ቅጥር በመፈጸም የ31 ጉድጓዶች የፓምፕ አቅርቦትና ተከላ ሥራ ማከናወን፣ ለትራንስፎርመር አቅርቦት፣ ለመብራት ኃይል እና የትራንስፎርመር ተከላ ሥራ በመብራት ኃይል በኩል መቶ ፐርሰንት ክፍያ መፈጸም፣ የተቋራጭ ቅጥር በመፈጸም የአምስት ጉድጓዶች የመስመር ዝርጋታ እና ከሪዘርቫየር ጋር የማገናኘት ሥራ ማከናወን፣ የመስመር ዝርጋታ እና ተያያዥ የሲቪል ሥራዎች ማከናወንም ግብ ተደርገው የሚሠሩ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ በኮዬ ፈጬ አካባቢ ከዚህ ቀደም የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች በተለያዩ ምክንያቶች የቀነሰው የውሃ ምርት የመስጠት አቅምን ለመመለስ እና በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው በቀን 35 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ፕሮጀክት አሁን ካለበት 17 ከመቶ ወደ መቶ ፐርሰንት እንዲደርስ በትኩረት ይሠራል። ለትራንስፎርመር አቅርቦት አስፈላጊው ክፍያ ለመብራት ኃይል እና የትራንስፎርመር ተከላ ሥራ በመብራት ኃይል በኩል መቶ በመቶ ክፍያ መፈጸም፣ የዲዛይን፣ የመስመር ዝርጋታ እና ተያያዥ የሲቪል ሥራዎች በማከናወን በቀን እንዲሁም 35 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ሥርጭት ማስገባት ዋነኛ የትኩረት መስኮች ሲሆኑ፤ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 75ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ስርጭት ማስገባት ታሳቢ በማድረግ ባለስልጣኑ በትጋት የሚሠራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ መረጃ በዝግጅት ክፍላችን ሥም አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ሰርካለም፡- አመሰግናለሁ። ጥቅሙ የጋራ በመሆኑ በጋራ እንሠራለን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014