አቶ ኢሳያስ ጂራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን ለቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ በድጋሚ ተመረጡ። ፕሬዚዳንቱ ከ138 ድምጽ 94ቱን በማግኘት ነው በድጋሚ የተመረጡት።
14ኛው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል። ጉባኤው የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ለመተካትም መርጧል።
ሽኩቻዎች በበዙበት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በእጩነት በቀረቡት አቶ ኢሳያስ ጂራ፣ አቶ መላኩ ፈንታ እና አቶ ቶኪቻ አለማየሁ መካከል ፉክክሩ ጦፎ ከርሟል። መራጮች በሰጡት ድምጽ መሰረትም ከ138 ድምጽ አቶ ኢሳያስ ጂራ 94 ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል። አቶ መላኩ 27፣ አቶ ቶኪቻ 17 ድምጽ አግኝተዋል።
ከምርጫው መካሄድ ሳምንታት አስቀድሞ እስከ ዋዜማው ድረስ ከፍተኛ ውዝግቦችና አለመግባባቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል። ይህ ሁኔታ ቀጥሎም በምርጫው ወቅትም የተለያዩ ውዝግቦችን ፈጥሯል። በተለይም የአፋር ክልልን ወክለው በቀረቡት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አሊሚራ መሀመድ ጋር ተያይዞ ውዝግቦች ተስተናግደዋል። እጩው ለአራተኛ ጊዜ ለተመራጭነት መቅረባቸውን ተከትሎ አስመራጭ ኮሚቴው ሠርዟቸው እንደነበር ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ክልሉ ጉዳዩን ጉባኤው ላይ በአጀንዳነት በማቅረብ አቶ አሊሚራ በእጩነት እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምጽ ተወስኖ ነበር። ነገር ግን አስመራጭ ኮሚቴው ተወካዩ በስራ አስፈጻሚ ምርጫው ላይ በተመራጭነት እንደማይካተቱ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ውዝግቡ ተነስቷል። የጉባኤ ህግን ባልተከተለ ሁኔታ የተነሳውን ውዝግብም የፊፋ ተወካዮች ጣልቃ በመግባት ምርጫው እንዲቀጥል አቅጣጫ ሰጥተዋል። ይህንን ተከትሎም አስመራጭ ኮሚቴው የእጩውን ክልከላ ምክንያት አብራርተዋል።
በዚህም በካፍ ህግ መሰረት አንድ እጩ ከ3 ጊዜ በላይ መመረጥን የማይፈቅድ መሆኑን ተከትሎ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻው መሆኑን ይደነግጋል። በመሆኑም አስመራጭ ኮሚቴው በጉባኤው የተወሰነውን ማስቀጠል እንደማይችል አስታውቋል። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከወራት በኋላ ደንቡን በማሻሻል የማሟያ ምርጫ ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁሟል።
አቶ ኢሳያስ ጂራ በድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎም፤ “ደስ ብሎኛል ትልቅ የቤት ስራ እንደተሰጠኝ ነው የማስበው። ጉባኤው ትንሽ በሰራሁት ነገር በዚህ ደረጃ እውቅና በመስጠቱ ደስ ብሎኛል። የሚቀጥሉት አራት ዓመታት ያቀድናቸውንና የጀመርናቸውን ነገሮች፤ በተለይም የተቋም ግንባታ፣ የብሄራዊ ቡድን፣ እንደ ልጆቼ በማያቸው የፓይለት ፕሮጀክትና የሴቶች እግር ኳስ ላይ እየተሰሩ ያሉ ጉዳዮችን ለማስቀጠል ትልቅ የቤት ስራ ተሰጥቶኛል። ለዚህም አመሰግናለሁ” በማለት ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየት ሰጥተዋል።
አቶ ኢሳያስ አክለውም፣ “ለቀጣዮቹ አራት አመታት እንድንመራ ትልቅ የቤት ስራ ነው የተሰጠን ፣ ለሀገር የሚጠቅሙንን ሃሳቦች ለመቀበል ሁሌም ክፍት ነን ወደኋላ አንልም። ለመመረጥ ብዬ መራጩን ማታለል አልፈልግም ከመንግስት ጋር በመቀራረብ በተለይም የባህርዳር ስታዲየም በቶሎ የሚጠናቀቅበትን መንገድ እንፈልጋለን። ውጪ የሚጫወተው ብሔራዊ ቡድናችን በሀገር ውስጥ ሲጫወት መመልከት እንደ ሁላችሁም እኔም ናፍቆኛል፣ እሱ ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ነገር ግን የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል። ውሸት አልወድም ዋሽቼ ትዝብት ላይ መውደቅ አልፈልግም ፣ ትናንት በከተማው የተደረጉ ነገሮች ተገቢ ያልነበሩ እና ወደፊት ሊቀሩ የሚገባቸው ተግባራት ናቸው። በጎንዮሽ ድምፅ ለማግኘት የሚደረጉ ነገሮች መልካም አይደለም ፈጣሪ ልብ ይሰጣቸው ፣ ደጋፊዎቼ እንኳን ደስ አላችሁ ኢሳያስ ቂመኛ አይደለም “ በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ለመወዳደር 32 እጩዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 9ኙ ሴቶች ናቸው። በተሰጠው ድምጽ መሰረትም ሀቢባ ሲራጅ ከአዲስ አበባ 101 ድምጽ፣ ፋይዛ ረሻድ ከሶማሌ በ65 ድምጽ፣ ብዙአየሁ ጀምበሩ ከድሬዳዋ 63 ድምጽ በማግኘት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ሊመረጡ ችለዋል።
Addisu….sidama
Dr.Dagnachew…..Amara
Sherefa……Debub
Murad……Hareri
Aser……Benishangul
ከሀቢባ ሲራጅ፣ ፋይዛ ረሻድ እና ብዙአየሁ ጀንበሩ ጋር በመሆን ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን በመጨረሻ እጩነት ከተወዳደሩት 12 ወንድ እጩዎች ውስጥ ሙራድ አብዲ ከሃረሪ፣ሸረፋ ደለቾ ከደቡብ፣ ዳኛቸው ነግሩ (ዶ/ር)ከአማራ፣አዲሱ ቃሚሶ ከሲዳማ፣ኡጁሉ አዳይ ኙበሪ ከጋምቤላ፣ አሰር ኢብራሒም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ መመረጥ ችለዋል። በመጨረሻም ለምክትል ፕሬዚዳንትነት በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ መካከል በተካሄደው ምርጫ፤ ዶክተር ዳኛቸው ነገሩ በአብላጫ ድምጽ ሊመረጡ ችለዋል።
ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ የፊፋው ተወካይ በምርጫው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለፕሬዘዳንቱና ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን በማስተላለፍ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማሳደግ እገዛቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የካፍ ተወካዩም ለተመራጮቹ መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014