የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት /ኢጋድ/ ቀጠና ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚታይበት መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ቀጣናው በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ የሚጠቃ መሆኑም ሌላው ችግር ነው። በቀጠናው የሚኖሩ ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብና ድህነት መጋለጣቸውም ይጠቆማል።
ንፁህ ውሃ፣ የባህር እና የባህር ዳርቻ አሳ እና ሌሎች የውሃ ሀብቶች የዚህን ቀጠና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ የልማት እድሎች ናቸው። የኢጋድ የባህር ዓሳ አስጋሪ ማስተባበሪያ መድረክ እ.ኤ.አ በመስከረም 2021 የተጀመረውም ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ ነው።
የዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍን ለማሳደግና በዚሁ ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከርም ኢኮፊሽ /ECOFISH/ ተሰኘና በምስራቅ አፍሪካ፣ደቡብ አፍሪካ እና ህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያለውን የዓሣ ሀብት ዘርፍ አቅም ተጠቅሞ የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብና ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚሰራና በዘርፉ ለቀጠናዊ ትብብር አዲስ መነሳሳትን የሚፈጥር ፕሮግራም ተቀርጾ በአውሮፓ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያም በኢጋድ ቀጠና የኢኮፊሽ /ECOFISH/ ፕሮግራም ተጠቃሚ ናት፤ የዓሳ ሀብትን በዘላቂነት በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በባሮ-አኮቦ-ሶባት እና በኦሞ ቱርካና ተፋሰስ ድምበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ሁለት ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ትገኛለች።
ዶክተር ዋሴ አንተነህ በኢጋድ ሴክሬቴሪያት የሪጅናል ፊሸሪ ማኔጅመንት የዓሳ አስተዳደር ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኢኮፊሽ /ECOFISH/ በአውሮፓ ሕብረት የሚደገፍና ወደ 28 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ በጀት የተያዘለት ትልቅ ፕሮግራም ሲሆን በሃያ ሁለት ሀገራት ላይ ይሰራል። ኢኮፊሽ / ከሚያንቀሳቅሳቸው ፕሮጅክቶች ውስጥ አንዱ የኢጋድ ቀጠና ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዚህ ቀጠና ያሉ ሁለት ሀገራት ማለትም ደቡብ ሱዳንና ኬንያ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ናቸው።
ለዚሁ ፕሮጀክት ከአውሮፓ ሕብረት አንድ ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለታል፤ አንደኛው ፕሮጀክት የሚካሄደው በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ድንበር የነጭ አባይ ገባር በሆነው በባሮ- አኮቦ- ሶባት ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር ላይ በሚገኘው የቱርካና ሃይቅ የሚካሄደው የኦሞ-ቱርካና ቤዚን ፕሮጀክት ነው።
የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማም በነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሀይቅ አካባቢ የሶስቱ ሀገራት ሕዝቦች የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት እንዲጠቀሙ በማድረግና ሁኔታዎችን በማመቻቸት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ማስቻል ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮጀክት ባሮ አኮቦና ኦሞ ቱርካና ላይ ያለች ሀገር እንደመሆኗ በሁለቱም ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች። በዚህም ከላይ ከመንግሥት ጀምሮ እስከ ታችኛው ማሕበረሰብ ድረስ፤ ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር ተካተውበት የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ የሚሉት ባለሙያው፣ እስካሁን ባለው ሂደትም የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ሃምሳ ከመቶ መድረሱንና ቀሪ ስራዎችም በቀጣይ እንደሚከናወኑ ይናገራሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት፤ በአሁኑ ጊዜ በዋናነት የዓሳ ሀብቱን የማስተዳደር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የዓሳ ሀብቱን በምን መልኩ በዘላቂነት መጠቀም እንደሚቻልም ተመሳሳይ ተግባሮች እየተናከናወኑ ናቸው።
ወንዞቹና ሃይቆቹ የሚገኙት በሀገራቱ ድንበር ላይ እንደመሆኑ የዓሳ ሀብቱን በመጠቀም ሂደት በዓሳ አስጋሪዎች መካከል ግጭቶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ያለው የዓሳ ሀብት ምርታማ መሆኑን ተናግረው፣ ከኬንያና ደቡብ ሱዳን አካባቢ ያሉ ዓሳ አስጋሪዎች ዓሳችን ወደ ኢትዮጵያ መጣ በሚል ድንበር ዘልቀው እያሰገሩ መሆናቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያውያን ዓሳ አስጋሪዎች ጋር ግጭት ይፈጠራል ይፈጠራል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ዋሴ ገለጻ፤ ከዚህ አንፃር እነዚህን ግጭቶች እንዴት ማስወገድ እንደሚቻልና የሶስቱም ሀገራት ዓሳ አስጋሪ ማሕበረሰቦች በጋራ ተስማምተው የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት መጠቀም እንዲችሉና የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ይህ ፕሮጀክት መንገዶችን ያፈላልጋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም የሁለትዮሽ ማእቀፎች ተዘጋጅተዋል። በነዚህ ማእቀፎች አማካኝነትም ሁለቱ ሀገራት ተገናኝተው በዓሳ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ በምን መልኩ ፖሊሲ መቅረፅና ስትራቴጂ ማውጣት እንዳለባቸው ይወያያሉ። በተመሳሳይ መልኩም እንደ እዚህ አይነት ማእቀፎች በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ተዘጋጅተው ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህ መሰረትም ወደ ማሕበረሰቡ በመውረድ ውይይቶች ተጀምረዋል። ማሕበረሰቡ የዓሳ ሀብቱን በሚገባ ማስተዳደር እንዲችልም ከየሀገራቱ መንግሥታት ጋር በመሆን ከሚቴዎች ተቋቁመዋል። ቀሪዎቹ ስራዎችም የሚሰሩት በሀገራቱ ከሚገኙ ዓሳ አስጋሪ ማሕረሰብ ጋር ነው። የዓሳ ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲያደርግ ለዓሳ አስጋሪዎች ሥልጠና ይሰጣቸዋል።
ባለሙያው እንደሚናገሩት፤ በድንበር ተሻጋሪ ወንዝና ሃይቅ አካባቢ ከፍተኛ የዓሳ ሀብት ያለ ቢሆንም፣ ከአካባቢው ሞቃትነት ጋር ተዳምሮ በቂ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ሀብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም። ለዚህም ነው ፕሮጀክቱን መቅረፅና የአካባቢውን ዓሳ አስጋሪ ማሕበረሰብ መደገፍ ያስፈለገው።
የአቅም ግንባታዎችን መስራት፣ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ዓሳ አስጋሪዎች የዓሳን ንፅህና ጠብቀው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማገዝ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እንዲችሉ መደገፍና ሌሎችም በቀጣይ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ስራዎች ይሆናሉ። አሁን ባለው ሁኔታም ወደማሕበረሰቡ መውረድ ተጀምሯል።
ጥርት ያለ መረጃ ባይኖርም በቅርቡ በወጡ ሪፖርቶች መሰረት በኢጋድ ቀጠና አካባቢ ባሉት ወንዞችና ሃይቆች 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን አሳ በዓመት ይመረታል። 85 ከመቶ ያህሉ የዓሳ ሀብትም የሚገኘው ከባህር ሳይሆን ከሀይቆቹና ወንዞቹ ነው። ባህር አካባቢ የሚመረተው ዓሳ ከ10 እና 15 ከመቶ አይበልጥም። ይመረታል ተብሎ የሚታሰበው አቅም ግን በዓመት ከ3 ሚሊዮን ቶን በላይ ነው።
ከዚህ አኳያ የቀጠናው ሀገራት እየተጠቀሙ ያሉት ገና አንድ ሶስተኛውን በመሆኑ ያለውን ዓሳ ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀም ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል። ለአብነት እንኳን በኢትዮጵያ በባሮ አኮቦ ወንዝ ያለው የዓሳ ሀብት ከፍተኛ ቢሆንም በሚገባ ጥቅም ላይ እየዋለ ባለመሆኑ እድሜያቸው ለምግብነት የደረሱ ዓሳዎች እየሞቱ ይገኛሉ። ለዚህም በቂ መሰረተ ልማት አለመኖርና አካባቢዎቹ ያለሙ መሆናቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ በዚህ ቀጠና በተወሰኑ ሃይቆች ላይ ዓሳዎችን ከልክ በላይ የማስገር ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። ይህም የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም ችግር ሆኗል። ከነዚህ ችግሮች አኳያ የዓሳ ሀብቱን ለማልማት በቂ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋትና ዓሳን በዘላቂነት ለማልማት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ማሕበረሰቡ ዓሳን የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብርም ብዙ መስራት የግድ ይላል።
በተመሳሳይ በቀጠናው ሀገራት መጠኑ ይነስ አንጂ የባህር ዓሳ ሀብትም ያለ ሲሆን፣ አብዛኛው የዓሳ ሀብት በወንዞችና ሃይቆች አካባቢ ያለ በመሆኑ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራው በዚሁ ላይ ነው።
የዚህን ቀጠና የዓሳ ሀብት በሚገባ ጥቅም ላይ ለማዋል አንዱ ችግር የአቅምና ትኩረት ማጣት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የዓሳ ሀብቱን ለመጠቀም በቂ የመሰረተ ልማት አለመኖር በመሆኑ በዚህ ላይ ብዙ መስራት ይጠይቃል።
ከድህነት ለመውጣትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም የቀጠናውን የዓሳ ሀብት በአግባቡና በዘላቂነት መጠቀም ያስፈልጋል። ይህንኑ ለማሳካትም ኢትዮጵያ በመጪው የአስር ዓመት የልማት እቅድ ውስጥ ይህን አካታ እየሰራች ትገኛለች።
በኢጋድ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ማናጀር ዶክተር እሸቴ ደጀን እንደሚሉት፤ በኢጋድ ቀጠና ከፍተኛ የዓሳ ሀብትና የመልማት አቅም ቢኖርም በአጠቃቅም ረገድ ሰፊ ክፍተት ይታያል። በተለይ ደግሞ የቴክኖሎጂ ድክመት ስላለ በውቅያኖስና በባህር ላይ የሚገኘውን የዓሳ ሀብት የቀጠናው አባል ሀገራት ብዙም እየተጠቀሙበት አይደለም።
አብዛኛው የኢጋድ ቀጠና ሀገራት የዓሳ ሀብት የሚገኘው ከወንዞች፣ ከሃይቆችና ዓሳ እርባታ በመሆኑና ትልቅ የዓሳ ሀብት ክምችት በነዚህ ሃይቆችና ወንዞች ውስጥ በመኖሩ ይህን ሀብት መጠቀም ከተቻለ ለቀጠናዊ ትስስርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
በምስራቅ አፍሪካ በተደጋጋሚ ድርቅ ቢከሰትም ድርቁ የውሃውን አካል ብዙም እንደማይነካው ዶክተር እሸቴ ጠቅሰው፣ በወንዝና በተለይ በሃይቆች ውስጥ ያሉ ዓሳዎችን በመጠቀም የተፈጠረውን የድርቅ ክፍተት መሸፈን ይቻላል ይላሉ። ከዚህ አንፃር የዓሳ ሀብቱ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ለዚህም የኢጋድ አባል ሀገራት ድርቅን ለመቋቋም የዓሳ ሀብቱን ማልማት አንድ አማራጭ እንዲሆን ድርጅቱ ፖሊሲ አውጪዎችንና ሌሎችንም በማማከር ላይ ይገኛል ብለዋል።
የፕሮግራሙ ማናጀር ዶክተር እሸቴ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በኢኮፊሽ ፕሮግራም በሚደገፉ ሁለት ፕሮጀክቶች ማለትም በባሮ-አኮቦ-ሶባት እና በኦሞ ቱርካና ተፋሰስ /ቤዚን/ የዓሳ ሀብቱን ለማልማት የአካባቢው ሁኔታዎች ተጠንተዋል። አንዳንድ ክፍተቶችም ተለይተው የመረብና ሌሎች ሙያዊ ድጋፎች ለማድረግ፣ በዓሳ አያያዝና አደራረቅ ላይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ለዚሁ ስራ የሚያስፈልጉ አንዳንድ የመሳሪያ ግዢዎችን ለመፈፀም ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ በርካታ ወንዞችና ሃይቆች ውስጥ በርካታ የዓሳ ሀብት በመኖሩ ይህ ሀብት መልማት ያለመበት ስለመሆኑ በስትራቴጂክ እቅድና በአስሩ ዓመት እቅድ ውስጥ ተካቷል። ከእነዚህ ወንዞች መካከል ከኢትዮጵያ የሚወጡ የጋራ ወንዞች አሉ። ሌሎች ሀገራትም በነዚህ የውሃ አካላት ውስጥ ያለውን የዓሳ ሀብት አልምተው መጠቀም ይፈልጋሉ።
ለዚህም በኢጋድ አዘጋጅነት በምስራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያሉት ሀገራት ተሰብስበው የዓሳውን ዘርፍ እንዴት አልምተው በጋራ መጠቀም እንዳለባቸው ምክክር አድርገዋል። በዚህም በዓሳ ልማት ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ ዘርፉን በዘላቂነት ለማልማት ተስማምተዋል። የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥም አድርገዋል። ይህም እያንዳንዱ ሀገር ያለውን የዘርፉን የማልማት አቅም አይቶ ወደተጨባጭ ስራ የሚገባበት ነው።
በኢጋድ ቀጠና ካለው የዓሳ ሀብት አቅም አንፃር ሀብቱን የመጠቀሙ ሂደት ገና በጅምር ላይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም በተመሳሳይ የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት የማልማት እንቅስቃሴ ገና አሁን ነው የተጀመረው ይላሉ። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የቀጠናው አባል ሀገራት የዓሳ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም ስብሰባ ማካሄዳቸውን፣ ከዚህ ስብሰባም በርካታ የዓሳ ሀብቱን ለማልማት የሚያስችሉ ጠቃሚ ነጥቦችን ማግኘታቸውን ያብራራሉ።
በቀጣይም ግብዓቶች እየተሰበሰቡ፣ ስትራቴጂዎች እየተቀረፁ፣ በሚቀረፁ ስትራቴጂዎች ላይ ደግሞ መሰራት የሚገባቸው ስራዎች እየተሰሩ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሃይቆች ላይ ያለውን እምቅ የዓሳ ሀብት በዘላቂነት በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠንካራ ስራዎች ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም የቀጠናው አባል ሀገራት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014