ጢስ አልባው ኢንዱስትሪ ይባላል፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ፡፡ ኢንዱስትሪው ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑም በስፋት ይነገርለታል፡፡ ከዘርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ እያሰበሰቡ ያሉ አገሮች ተሞክሮም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ታሪካቸውን፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን ጠብቀውና ተንከባክበው፣ የቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማቶችን ገንብተው ብቻ አይደለም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሰሩት። ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ እንዲሁም ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥር ለማድረግም በትኩረት ይሰራሉ፡፡
ኢትዮጵያም በዚህ ጢስ አልባ ኢንዱስትሪ ለመጠቀም አቅዳ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በአስር አመቱ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ላይ የቱሪዝም ዘርፍ ከአምስቱ የእድገት ምሰሶዎች አንዱ ተደርጎ ተይዟል፡፡ ቀደም ሲል ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች ጋር ሆኖ ይሰራ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ አሁን ራሱን ችሎ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ለኢኮኖሚው እድገት ሲባል ዘርፉ ላይ በስፋት እንዲሰራ የሚያስችል እንደመሆኑም ለቱሪዝም ዘርፉ መጻኢ እድል ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አገሪቱ ለቱሪስት መስህብ በሆኑ ታሪኮች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች የታደለች ናት፡፡ ከበርካታ የታሪክ ቅርሶቿ መካከልም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት በመሳብ የሚታወቁት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልት፣ ገዳማት፣ የጎንደር አብያተ መንግስታት፣ በእስልምናው ሃይማኖት በኩልም የአልነጃሺ መስጂድ፣ እንዲሁም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የሀረሩ ጀጎል ግንብና የመሳሰሉት፤ ከማይደሰሱ ቅርሶቿ እንደ መስቀል ደመራ፣ ጥምቀት፣ እሬቻ፣ የኦሮሞ ገዳ ስርአት፣ ሻደይ፣ ሶለል ያሉ የልጃገረዶች ጨዋታዎች፣ በተለያየ መልክ የተደራጁ ቤተ ሙዚየሞቿ ይጠቀሳሉ፡፡
አገሪቱ ለቱሪዝም መስህብ የሚሆኑትን እነዚህን ሀብቶቿን በስፋት በማስተዋወቅ፣ ከተለያየ የዓለም ክፍሎች ቱሪስቶችንም ለመቀበል የሚያስችል አቅም ፈጥሮና ቱሪስቶችን በማስተናገድ ከዘርፉ ገቢ በማግኘት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ወሳኝ ነው፡፡
የቱሪስት መዳረሻዎች በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ነው የሚገኙት፡፡ እነዚህን መስህቦች የማስጎብኘቱ ሥራም ሆነ የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎቶችም በባለሙያ የሚካሄዱ አይደሉም ተብለው ይተቻሉ፡፡ ከተለያየ የዓለም ክፍል የሚመጣውን ቱሪስት ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎት አይሰጥም፤ በአጠቃላይ ኢንዱስትሪውን የሚመጥን ሥራ ገና አለመሰራቱ ይነገራል፡፡
በዚህና በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም መዳረሻ ሀብቷ የሚጠበቀውን ያህል ገቢ እንደማታገኝም በተለያየ ጊዜ ከሚወጡ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት በርካታ የማሰልጠኛ ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸው ይታመናል፡፡
በዚህ ረገድ ቀድሞ የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ደግሞ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ተብሎ የሚጠራው ተቋም ሙያተኞችን በማፍራት የረጅም ጊዜ ተሞክሮ አለው፡፡ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተመሰረተ ከ1969 ዓ.ም አንስቶ በሆቴል፣ በቱሪዝም በመደበኛና በተከታታይ መርሃ ግብር ባለሙያዎን አሰልጥኖ በማስመረቅ ሚናውን ሲወጣ እየተወጣ ነው፡፡ አጫጭር ስልጠናዎችንም በመስጠት ኢንዱስትሪውን እያገዘ ይገኛል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በቴክኒክና ሙያ የስልጠና መርሃግብር ሙያተኞችን በደረጃ ያሰልጥናል።
በ53 አመታት ጉዞው በከፍታና በዝቅታ ውስጥ ያለፈ ቢሆንም፣ ሙያተኛ ማፍራቱን ሳያቋርጥ እስካሁን ዘልቋል የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ይታሰብ፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የተለያየ ዘርፍ ውስጥ ያሰለጠናቸው ሙያተኞች መገኘታቸውን እንደ በስኬትነት ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ በ2002 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 174 በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል በሚል ተቋቋመ፡፡ ያ ጊዜ ግን በመካከለኛና ከመካከለኛ ከፍ ባለ ደረጃ ስልጠና ለመስጠት ምቹ አልነበረም፡፡ በዚህ አመት የአስፈፃሚ አካላትን በሚደነግገው አዋጅ መሠረት ወደ ቱሪዝም ኢንስቲትዩትነት ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡
የተለያዩ ዘርፎችም ተከፍተው ዘርፎቹንም ሶስት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ተመድበው እንዲመሩ መን ግሥት ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በበጀትም የተሻለ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ተጠሪነቱም ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሆኗል፡፡
ከፍተኛ አገራዊ ተልዕኮዎች የተሰጡት መሆኑንም አቶ ይታሰብ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለወጣቶች በተለይም ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ነው የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ በዚህ መንፈስ ኢንስቲትዩቱ በኢንዱስትሪው ውስጥ ሥራን ሊፈጥር የሚችል ስልጠና በመስጠት የዘርፉን ሙያተኞች እንዲያፈራ፣ በጥራትም በብዛትም በኢንዱስትሪው ላይ በጎ ተጽእኖ እንዲኖረው ነው ኢንስቲትዩቱ ይህ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሉ ያብራ ራሉ፡፡
ኢንስቲትዩቱ በዚህ ሁኔታ ባለሙያዎችን በማፍ ራት ተልዕኮውን እየተወጣ ቢሆንም፣ ኢንዱስትሪው ላይ ያሉት በስልጠና ክህሎት የሌላቸው መሆናቸው እንደሚተችና በዚህ ላይ ያላቸውን ሀሳብ እንዲሰጡን ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ይታሰብ ምላሽ ሲሰጡ በሚባለው ነገር እንደሚስማሙ ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ ከአራት አመት በፊት በአገሪቱ በማስጎብ ኘትና በሆቴል ኢንዱስትሪው ተሰማርተው በሚሰሩ ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ ሙያተኞች ምን ያህሉ በዘርፉ የሰለጠኑ እንደሆኑ፣ ተቋማቱም ለዘርፉ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡ ባካሄደው የጥናት ሥራ መለየቱን አስታውቀዋል፡፡ በጥናቱ መሰረትም በስልጠና የሙያው ባለቤት የሆኑት 26 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልገው በባለድርሻ አካላትም እምነት ተይዞ ለመተግበር ግንዛቤም ከፍ ማለት ስላለበት በዚህ ረገድም መሰራት እንዳለበት በኢንስቲትዩቱ እምነት ተይዟል፡፡ ዘርፉ እንደ ሌሎች የውጭ ንግዶች የውጭ ምንዛሬ ለአገር በማስገኘት ያለው ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፡፡
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለመጨመርም ዘርፉ በግንዛቤና በሰለጠነ የሰው ኃይል መታገዝ አለበት የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ በተለይም በባለሙያ መመራት አለበት በሚለው ላይ አጽንኦት ይሰጠዋል ብለዋል። ኢንስቲትዩቱም አቅሙን በማጎልበት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ፖሊ ቴክኒኮች ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው አይነት ስልጠና ኢንዲሰጡ በማደረግ ተልእኮውን እንደሚወጣም አስታውቀዋል፡፡ በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ በእውቀት በመመራት መሥራት ከተቻለ በመላ አገሪቱ የሰልጣኞችን ቁጥር በማብዛት ወደ ኢንዱስትሪው የሚቀላቀለውን ባለሙያ በብዛት ማፍራት ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ቱሪስቱን መሳብ የሚቻለው ባለው የቱሪዝም መዳረሻ ብቻ ሳይሆን፣ ከዘርፉ ጋር የሚሄደውንም አገልግሎት ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪነትን በመጨመር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ዝግጁነት ከዚህ አንጻር ምን እንደሆነ ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ይታሰብ ሲመልሱ፤ እንደ ውስንነት የሚወሰዱትን ለይቶ ወደፊት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
‹‹ያለውን የቱሪዝም ሀብትና አቅም በበቂ ሁኔታ አስተዋውቀን ጨርሰናል ወይንም ደግሞ በመላው ዓለም ያሉትን ደንበኞቻችንን ተደራሽ አድርገናል ብለን መናገር አንችልም፡፡ ስለዚህ የማስተዋወቅ አካሄዳችን ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታና ቱሪስቶችን ከመድረስ አኳያ በተለይም የቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ወደ እኛ ተቋም ስንመጣ ደግሞ ሶስት ዋና ዋና የሆኑ ኃላፊነቶች አሉብን የሚሉት አቶ ይታሰብ፣ አንዱ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል ከፍ አድርጎ ኢንዱስትሪው በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ማድረግ፣በሁለተኛ ደረጃ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጥናትና ምርምር በማማከር መፍታት ነው፤ ሶስተኛው ስልጠና መስጠት ነው፡፡›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
እንደ አንድ መንግሥታዊ ተቋም ኃላፊነታችን ከፍተኛ ነው፡፡ በተቻለ አቅም በኢንዱስትሪው ውስጥ ባለሙያዎችን ከፍ የማድረግ ሥራ እንሰራለን›› ይላሉ። የዘርፉን ክፍተት ለመሙላት ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በዚህ በኩልም ኢንስቲትዩቱ በጋራ ለመሥራት ከፌዴራል ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከክልል ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር መግባባት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደ ሚሉት፤ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከተለያዩ የዓለም አገራት ቱሪስቶችን በመሳብ ከዘርፉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ቱሪስቶቹ በሰለጠነ የሰው ኃይል የሚመራ የቱሪዝም መዳረሻ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል።
በዚህ ወቅት ከኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ቱሪስቱን ለጤና ችግር የማያጋልጠው ንጹህ አገልግሎት መስጠት ይፈልጋል፡፡ ለቱሪስቱ ከሆቴል ኢንዱስትሪው ይህን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ በዘርፉ ክህሎትና ግንዛቤ ያለው ባለሙያ ያስፈልጋል። ዘርፉ በሚፈልገው የሙያ ሥነ ምግባር እንዲመራና እንዲሰራ ማድረግ የግድ ነው፡፡
አገሪቱ ካሏት የቱሪስት መዳረሻዎች በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ተጨማሪ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ተገንብተዋል፤ ሌሎች መዳረሻዎችም እየተገነቡ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የሰልጠና ክህሎት ያለው ባለሙያ በብዛት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም አዳዲስ መዳረሻዎች ሲከፈቱ የሰው ኃይሉ ወደ አዲሱ የመፍለስ ሁኔታ ስለሚፈጠር ነባሮቹ ሊዳከሙ ይችላሉ፤ ይህን ክፍተት ለመሙላትም ዘርፉን የሚቀላቀሉ ባለሙያዎችን በስፋት ማሰልጠን ያስፈልጋል፡፡
በሆቴልና በአስጎብኝነት የሚሰለጥኑት ተቀጣሪዎች ብቻ አድርጎ መወሰድም እንደሌለበትም አቶ ስለሺ ያስገነዝባሉ፡፡ የራሳቸውን ሥራ ለመስራት የሚፈልጉትም ስልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች በግላቸው በቀላሉ መስራት እንዲችሉ ቱሪዝም ሚኒስቴር ያወጣው መመሪያ የሚፈቅድላቸው በመሆኑ የሚቀጠሩ ብቻ አይደሉም ስልጠናው የሚያስፈልጋቸው፡፡ አጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ልህቀቱ ለአገር ገጽታ ግንባታም አስተዋጽኦ እንዳለው መገንዘብና መረዳትም ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ከማድረግ አንጻር በቱሪዝም ሚኒስቴር በኩል ምን እየተሰራ ነው በሚል የጠየቅናቸው አቶ ስለሺ፤ ሚኒስቴሩ አዲስና ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት መፍጠሩን ይናገራሉ። በመዋቅሩ ልክ የሚፈለገውን የሰው ኃይል መመደብና ተጨማሪ የሚያስፈልግበት ቦታም ከገበያ አወዳድሮ መቅጠር ሲቻል መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህን ለማድረግ ደግሞ አንደኛ አሰልጥኖ ሙያተኞችን በማፍራት ረጅም አመት ልምድ ያላቸው ተቋማት ሙያተኞችን ማፍራታቸው ለዘርፉ ከፍተኛ ግብአት ይሆናል ይላሉ።
ሁለተኛ ደግሞ እንደ አገር የግልና የመንግስትን ጨምሮ ከሚያሰለጥኑ ተቋማት የሚወጡት ባለሙያዎች ከ30 በመቶ አይበልጡም ሲሉ ጠቅሰው፣ ከሆቴልና ቱሪዝም ውጭ ያለው የሰው ኃይል እንደሚበዛም ይናገራሉ፡፡ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የዘርፉ ሰራተኛ በዘርፉ ያልሰለጠነና በዘርፉ እውቀትና ልምድ የሌለው ወይንም ጉዳዩ የማይመለከተው መሆኑን አብራርተው፣ ይህ ሀይል ተገዶ ገብቶ እየሰራ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ዘርፉን ክህሎት ባለው የዘርፉ ባለሙያ ለማሟላት እስካልተቻለ ድረስ የተሻለ የአገልግሎት ጥራት ማምጣት አይቻልም። የዘርፉን የሰው ሀይል በማሰልጠን በኩል የስልጠና ተቋማት ሚና የጎላ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይ በሆቴል ኢንዱ ስትሪው ዘርፍ ላይ ባወጣው መመሪያ መሰረት ባለ ሆቴሎች ባለ ኮከብ ሆቴል ደረጃን ለማሟላት የሆቴል አገልግሎት ሰጪው ቢያንስ በኃላፊነት ደረጃ በቱሪዝም ወይንም በሆቴል የሰለጠነ የሰው ኃይል ካልቀጠሩ እውቅና አይሰጣቸውም፡፡ የኮከብ ደረጃም አያገኙም። በተመሳሳይ የሬስቶራነቶች አስተናጋጆችም የሰለጠኑ መሆን እንዳለባቸው መመሪያው ያዛል፡፡
ለሚወጡት አገር አቀፍ መመሪያዎች ትግበራ የንግድ ተቋማትም ሆኑ የግሉ ዘርፍ እንዳይቸገር የስልጠና ተቋማቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራታቸው አገሪቱ በዘርፉ ያስቀመጠችውን እቅድ ለማሳካትና የተሰነቀውን ተልዕኮ እውን ለማድረግ ይጠቅማል፡፡
የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ገና አገሪቱ ከገጠማት ጦርነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካጋጠመው የኮቪድ 19 ወረርሽን ድባብ የወጣ እንዳልሆነ አቶ ስለሺ ተናግረው፣ እንዲያም ሆኖ ግን መነቃቃቶች መፈጠራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ የቀጠና ቱሪዝም የሚባለው ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እየተሻሻለ መምጣቱን፣ ተቋርጠው የነበሩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችና ኤግዚቢሽኖች ወደ አገሪቱ መምጣት መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ እንቅስቃ ሴዎቹ በሚፈለገው ልክ ባይሆኑም፣ ቀድሞ ወደነበሩበት ለመመለስ መሰራት ይኖርበታል። ክልሎችን በማቀናጀት፣ በተለያየ አገር የሚገኙ አምባሳደሮችና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ጭምር በመጠቀም በአዲስ መልክ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በተለይም ወደፊት የሚጠበቁ እንደ መስቀል ጥምቀት ያሉትን በዓላት መሠረት ባደረገ መልኩ የቱሪዝም እንቅሰቃሴውን ይበልጥ ለማነቃቃት ከወዲሁ ሰፊ ሥራ ይሰራል፡፡
የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በውጭ ምግቦች አዘገጃጀት ካፈራቸው ባለሙያዎች አንዱ የሆነው መሐመድ ነስረዲን፤ ሙያውን ሳይንስ ነው ሲል ይገልጸዋል፡፡ ቱሪስቱ የሚሳበው በሚያየው ነገር ብቻ ሳይሆን፣ በሚመገበውም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ቱሪስቱ የሚፈልገውን ምግብ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ ወዶት እንዲመገበው በማድረግ በምግብ ዝግጅትም በአጠቃላይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚቻል ይጠቁማል፡፡
እርሱም በሰለጠነው ሙያ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅቷል። ወጣት መሐመድ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በጥሩ ውጤት ሲሆን፣ የዋንጫ ተሸላሚም ነው፡፡ እንዲህ የሚተጉ ሰልጣኞችና መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በመናበብ ከተሰራ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን እምነታችን ነው፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014