ወደ ዛሬው የመጣጥፌ ርዕሰ ጉዳይ ከማለፌ በፊት ስለ ሕወሓት ወቅታዊ ሁኔታ ባሰብሁና ባወጣሁ ባወረድሁ ቁጥር የሚከነክኑኝንና የሚያብከነክኑኝን ጉዳዮች ላነሳ ወደድሁ። የመጀመሪያው ተወደደም ተጠላም መንግስት ሕወሓትን በተለመደውና መደበኛ በሆነው የውጊያ፣ የፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ መንገድ ሳይሆን፤ በራሱ በሕወሓት የጨዋታ ሜዳና ሕግ ሊገጥመው ይገባል። ከመንግስትነት ባህሪው ብዙም ሳይወጣና ሳይርቅ።
በዝርዝር መተንተንና መሞገት ቢቻልም ምን ለማለት እንደፈልግሁ ግልጽ ነው። ሁለተኛው መንግስት ለአሜሪካና ለምዕራባውያን ግንኙነት ከሚጨነቅ፤ (ለዚያውም እንዲህ በተዳከሙበትና እነ ቻይናን የመሠሉ ማኩረፊያ ባሉበት፣) ለውስጣዊ አንድነቱና ለመረጠው ሕዝብ ቢጨነቅና ቢጠበብ ብዙ ያተርፋል። እስኪ ባለፉት ሶስት አመታት እነ አሜሪካንን ላለማስቀየም የሔድንበትን እርቀትና ያተረፍነውን እናስላው።
ሙሉ በሙሉ ባይባልም ከስረናል። የዓለም አቀፍና ውጭ ግንኙነት ስራችንን ከውጭ ወደ ውስጥ ከመስራት ይልቅ ከውስጥ ወደ ውጭ ስለመስራት ማሰብ አለብን። ታዋቂው የዓለም አቀፍና የውጭ ግንኙነት ሊቅ ሪቻርድ ሀስ እንደሚለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚጀምረው ከአገር ውስጥ ነውና። ሶስተኛውና ወሳኙ ነጥብ ሕወሓት ድርድሩንም ሆነ ጦርነቱን እንደፈለገ አስገድዶ እንዲጭንብን (dictate)መፍቀድ የለብንም። እየሆነ ያለው ይህ እንዳይሆን እሰጋለሁ።
ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት እና ክህደት ጨምሮ በውንብድና ዘመኑም ሆነ በአገዛዝነቱ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ክህደትና ዘረፋ መፈጸሙ፤ ሰሞኑን የነዳጅ ዘረፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ እንጂ ትላንት ወይም ዛሬ የተጀመረ አይደለም። እየተመለከትን ያለነው ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ፤ የጭካኔ ልምምድና የዘረፋ ዝግጅት ውጤትን ነው። ሕወሓት በውንብድና ዘመኑ ከአረብ አገራት እርዳታ ለማግኘት የወቅቱን የውጭ ጉዳይ ኃላፊውን አይተ ስዩም መስፍንን ስሙን ቀይሮ “ስዩም ሙሳ” ተብሎ እንዲጠራ ያደረገ መልቲና አጭበርባሪ ነው።
ሕወሓት ገና ስሙን ሳይቀይር ተሓህት/ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ/ይባል በነበረበት ወቅት ግገሓት/ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ከተባለው ከእሱ በፊት ተመስርቶ በኤርትራና በትግራይ አዋሳኝ መሬቶች ይንቀሳቀስ ከነበረው ድርጅት ጋር ውህደት ለመፈጸም ስምምነት ላይ ይደርሳል። ሁለቱ ድርጅቶች ውህደት ወደሚፈጽሙበት ምስራቅ ትግራይ ዘገብላ ወደሚባል ቦታ ሰራዊታቸውን ወስደው ካሰፈሩ በኋላ፤ የተሓህት_ሕወሓት አመራሮች ቀን ሲሸርቡት የዋሉትን ሴራ ለሰራዊታቸው በሚስጥር እንዲተላለፍ አደረጉ። እያንዳንዱ የተሓህት_ሕወሓት ታጋይ ከግገሓት ታጋይ ጋር ጥንድ ጥንድ እየሆነ እንዲተኛና ግገሓቶች እንቅልፍ ሲጥላቸው የሚደርሰውን ትዕዛዝ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ ይታዘዛል።
የግገሓት አባላትና አመራሮች እንቅልፍ እንደወሰዳቸው ሲረጋገጥ፤ ከጎናቸው የተኙት የተሓህት_ሕወሓት አባላት ትዕዛዝ ሲደርሳቸው እንቅልፍ ላይ የነበሩ የግገሓት አባላትን ከእነ አመራራቸው አንድ በአንድ በግፍ ጨፍጭፈው ጨረሷቸው። ለሕወሓት እርቅና ድርድር ማለት እንዲህ ነው። መርህና ሰብዓዊነት የሚባል ነገር አልፈጠረበትም። የሕወሓት ታሪክ በመላ የክህደትና የባንዳነት ታሪክ ስለሆነ ለአብነት ማንሳት አይቸግርምና ሌላ ላክል።
የትህነግ/ ሕወሓት መስራች ታጋይና የፓሊት ቢሮ አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ “ በተሰኘው ማለፊያ መፅሐፋቸው፣ “የሄጉ የድንበር ኮሚሽን ኢትዮጵያንና ኤርትራን ካከራከረ በኋላ ሚያዚያ 5 ቀን 1994 ዓ.ም ብይኑን ሲሰጥ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በኩል ከ70 ኪሎ ሜትር ካሬ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ግዛት ለኤርትራ ለመስጠት ወሰነ። ለኤርትራ በተሰጠው መሬት ውስጥ ለጦርነቱ ኃጢያት ተሸካሚ (ስኬፕጎት) የሆነችው ባድመ ስትካተት፤ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በታሪክ በኤርትራ በኩል ምንም የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቶበት የማያውቀውን የኢሮብ መሬት በከፊል … እነ ዓይጋን ፣ ወርዓትለን ፣ ዘገልባን ፣ ለኤርትራ ተወሰነ፡፡ ሕወሓት ግን ጥርሱን በነቀለበት ውሸትና ክህደት አይኑን በጥሬ ጨው ታጥቦ በጦርነት ያገኘነው ድል በሄጉ የድንበር ኮሚሽን የፍትሕ አደባባይ ተደገመ። ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነ። እንኳን ደስ አላችሁ ሲል በአደባባይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዋሸ። ካደ። በሰምዓቱ ደም ተሳለቀ።
በነገራችን ላይ አንዳንድ የሕወሓት ጉምቱ ባለስልጣት ወላጆች ሹምባሽና ባንዳ ናቸው። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያንን በስም ለመጥራት የሚጠየፉትና የሚጠሉት ለዚህ ነው። የሕወሓት የልቦና ውቅርም በዚህ የባንዳነት መንፈስ የታቀኘ ነው። ለዚህ ነው 123 ሚሊየን ሕዝብን የባሕር በር አልባ ያደረገው። የሶማሊያው የወቅቱ መሪ ሜጀር ጄኔራል ሲያድ ባሬ/ዚያድ ባሬ/በታላቋ ሶማሊያ የቀን ቅዠት የምስራቁን የአገራችንን ክፍል በ1969 ዓ.ም በወረረ ጊዜ ሕወሓት ወረራውን ደግፎ ከጎኑ የቆመው። በሞቃዲሾ ቢሮ ከፍቶም ይንቀሳቀስ ነበር። ከምስረታው የተጣባው ባንዳነት ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ከታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ጋር ሹምባሽ፣ ባንዳና አስካሪስ ሆነ አገራችንን ለማፍረስ ሌት ተቀን እየማሰነ ነው። የፈርኦን ፈረስ ሆኖ እየተጋለበ ነው። ለዚህ ውለታው የጦር መሳሪያ፣ የፋይናንስ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፕሮፓጋንዳ፣ የሚሰና የዲስ ኢንፎርሜሽን፣ ወዘተረፈ ድጋፍ እየተደረገለት ነው። ሰሞኑን ድንበር ጥሶ የጦር መሳሪያ ሲያጓጉዝ ተመትቶ የወደቀው አንቶኖቭም ሆነ ተሽሎክሉኮ ለሕወሓት የጦር መሳሪያ እያቀረቡ ያሉ አውሮፕላኖች የማን እንደሆኑ ለማወቅ ራዳሩን ማንበብ አያስፈልግም። ከአልሻባብና ከኦነግ ሸኔ ጋር የፈጠረው ግንባር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ገሀነምም ቢሆን እወርዳለሁ ያለው ቅርሻ አካል ነው፡፡
ለዚህ ነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ እግር እስኪቀጠን ቢታሰስ እንደ ሕወሓት ያለ ባንዳ፣ ከሀዲ፣ ዘራፊ፣ አሪዮስና አረመኔ የፖለቲካ ቡድን የለም የሚባለው። በዚህ ጊዜ በአለማችን የትኛውም ክፍል እንደ ትህነግ ያለ እፉኝት የፖለቲካ ስብስብ በዲያጎን ፋኖስ እንኳ ቢፈለግ አይገኝም። በአፍሪካም ሆነ በላቲን አሜሪካ አልያም በእስያ ከትህነግ ጋር በዘመነ ጓዴነት (ኮንቴምፓራሪስ) ሊነጻጸር የሚችል ምንም አይነት እኩይ ኃይል የለም። ለግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቁት እኩይ ተግባሮቹ ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። ገና ከምስረታው እንደሱ የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ ለመታገል ጫካ የገቡትን እንደ ኢህአፓ፣ ኢዲዩና የትግራይ ድርጅቶችን እንደራደር፣ ልዩነታችንን በውይይት እንፍታ እያለ እያግባባ እውነት መስሏቸው ለድርድር ሲመጡ አንድ በአንድ የጨረሰ አረመኔና ከሀዲ ስብስብ ነው።
እነ ስሁልን፣ ሙሴን፣ ሀይሎምንና ሌሎቹ በሀሳብ የተለዩትን እልፍ አእላፍ ታጋዮችንና ልጆቹን፤ በሰሜን እዝ፣ በመከላከያ ሰራዊታችን፣ በአገራችንና በሕዝባችን ላይ እንደፈጸመው ክህደት ከጀርባ ወግቶ ወይም በጥይት ደብድቦ የጨረሰ አሪዮስ ነው። ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የሀውዜንን ሕዝብ በገበያ ቀን በአውሮፕላን አስፈጅቶ ሙሾ የሚያወርድና የአዞ እንባ የሚያነባ የሀፍረተቢሶች ስብስብ ነው። በ77 ድርቅ ለትግራይ ሕዝብ የተላከ እርዳታን ሽጦ የጦር መሳሪያ የገዛ የማፍያ ስብስብ ነው። ባለፈው ረቡዕ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ግቢ ጥሶና ገልብጦ 12 ቦቲ ነዳጅ ወይም 570ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉን ስሰማ ያለገረመኝ ይህን የዘረፋ ማንነቱንና ከሀዲነቱን ጠንቅቄ ስለማውቅና ጥርሱን የነቀለበት ስለሆነ ነው።
በአዲስ አበባ ፒያሳ በኬቭ ካፌ በራድ ሻይ ፉት እያለ ሆነ በሌላ ቦታ ሆኖ ወደ “ትግል” ሜዳ ለመውጣት ሲወስንም ሆነ እንደወጣ ታሪክን፣ እውነትን፣ ሰንደቃላማን፣ አብሮነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን፣ ፍቅርን፣ ሰውነትን ፣ ፈጣሪን፣ ወዘተረፈ ሽምጥጥ አድርጎ ክዶ የራሱን የፈጠራ ትርክት ነው የነበረው። የአገሪቱን ታሪክ ወደ 100 አመታት አራክሶ፤ እውነትን ኅልቁ መሳፍርት በሌለው ውሸት ተክቶ፤ ሰንደቃላማን ጨርቅና የአንድ ሃይማኖት አርማ ነው ብሎ፤ አብሮነትን በመለያየት ቀይሮ፤ ሰብዓዊነትን በአረመኔነት ለውጦ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሳ ለንጥቆ ፤ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የአማራ ሕዝብና ኦርቶዶክስ ነው፤ ፈጣሪን ክዶ ራሱን ወደጣኦትነት ቀይሮ እስከመመለክ የደረሰ ወዘተረፈ የራሱን ተረክና እውነት በይኖ በራሱ ዓለም ሲዳክር የኖረ ስብስብ ነው
የእውነትን፣ አገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ የዜጋውን የልቦና ውቅርና የታሪክን ፈለግ ተከትሎ ርዕዮት ዓለም መንደፍ የማታገያ ስልት መትለም ሲገባው፤ በተቃራኒው እውነትን፣ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን፣ የዜጋውን ልቦና ውቅርና ታሪክ በድቡሽት ላይ ለተቀለሰ ማንፌስቶው እንዲመጥኑ እጃቸውን ጠምዝዞና አጣሞ እንደገና መበየኑ እና ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል በስሁት መንገዱ ልምምዱን መቀጠሉ ጎልማሳው ከሀዲ አድርጎታል። ከጥፋቱና ከዕድሜው የማይማር ልበ ቢስ አድርጎታል።
የከሀዲውን ማንነት ጠንቅቀው ለሚያውቁት የሰሜን ዕዝ ክህደቱና ጭፍጨፋ የሚጠበቅ ነበር። ለዚህ ነው እንደ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ያሉ ነባር ታጋዮች እና የሸዕቢያ ጉምቱ ሰዎች ትህነግን ከፍጥርጥሩ ጀምረው ስለሚያውቁት በዚህ አሳፋሪ ክህደት እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ያልደገነጡት። ያልተገረሙት። ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በድንጋጤ እጃቸውን በአፍ ያስጫነው ክህደቱም ሆነ ጭካኔው በአገሪቱ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅና ከሕዝቡ የስነ ልቦና ውቅር ፍጹም ያፈነገጠ መሆኑ ነው ።
ውርደትና ቅሌት ብርቁ ያልሆነው ሕወሓትን መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ 570 ሺ ሊትር ነዳጅ ዘረፈኝ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዓለም አሳጥቶታል። የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በሰጡት መግለጫ፤ ታጣቂዎቹ የፈጸሙትን ዝርፊያ በቦታው የነበሩ የመንግስታቱ ድርጅት እርዳታ ሰጪዎች ለማስቆም ቢሞክሩም አልተቻላቸውም፡፡ ድርጅቱ የተዘረፈው ነዳጅ የእርዳታ ምግብ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የሚውል ነበር፡፡
የሽብር ቡድኑ ነዳጁን በመዝረፉ ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፉ ሥራ እንደሚያስተጓጉለው እና ድርጅቱ የሕወሓትን ዝርፊያ አጥብቆ እንደሚያወግዘውም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኃላፊም ድርጊቱን አውግዘው የዘረፈውን ነዳጅ እንዲመልስ ጠይቀዋል። ባለፈው ዓርብ የዩኤስኤይድ ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር ይሄን የሕወሓት አብሮት የሸበተ ቅሌት አውግዘዋል። መቼም ሕወሓት እንደ ሰሞኑን ተዋርዶ አያውቅም።
ለትግራይ ሕዝብ ምንም አይነት እንጥፍጣፊ ግድ የሌለው ሕወሓት ካለ ጦርነት ሕልውና ስለሌለው፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥና ለስልጣን ጥሙ ሲል፤ ከትግራዋይ እናቶች የነጠቃቸውን ብላቴናዎች እንደገና መማገድ ጀምሯል። ለትግራዋይ ሕይወት የትንኝ ያህል ግድ የሌለው ሕወሓት፣ በሁለቱ ጦርነቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ትግራዋይን ማግዶ ማስጨፍጨፉ አልበቃ ብሎት ሌላ ዙር ጦርነት ከፍቷል። ማክሰኞ ለረቡዕ አጥቢያ ሲፈጽም የሰነበተውን ትንኮሳ ገፍቶበት በምስራቅ ግንባር ጥቃት ፈጽሟል ።
የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ታጣቂ ቡድን ሰሞኑን ሲፈጽም የሰነበተውን ትንኮሳ ገፍቶበት በምስራቅ ግንባር በቢሶበር ፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች በእለቱ ከሌሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል። በዚህም ቡድኑ የተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሷል። የፈጸመው ጥቃትም ሆነ እሱን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አስቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው። “ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንና መላው የጸጥታ ሃይላችን ከሽብር ቡድኑ የተሰነዘረውን ጥቃት በተቀናጀ መልኩ በድል እየመከቱት ይገኛሉ። የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከአሸባሪው ቡድን ለመጠበቅም ሁሉም የጸጥታ ሃይላችን በተጠንቀቅ መቆማቸውን የመንግስት የኮሙኒኬሽን ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በትንኮሳው ከገፋበት መንግስት አገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል። ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ቀድሞም በተካነበት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ስራ ራሳቸው ተንኩሰው ራሳቸው እየጮሁ ይገኛሉ ያለው መግለጫው፤ ለሰላም እጁን የዘረጋውን መንግስት በሃሰት በመወንጀል “ድርድሩ አስቀድሞ ከሽፏል” በሚል ለተለያዩ ወገኖች ጦርነቱ እንደማይቀር ሲያደርጉ የነበረውን ቅስቀሳ በማጠናከር የትግራይን ወጣት ዳግም ሊማግዱት በይፋ አውጀው ወደ ጦርነት እየተንደረደሩ ነው፡፡ ሰሞኑን ዓለም አቀፍ አጫፋሪዎቻቸው ካሸለቡበት ብቅ ብቅ ማለታቸውም የጦርነት ዝግጅቱን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የማጀብ አካል መሆኑ ግልፅ ሆኗል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ሕወሓት የሚያደርገውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ጠንካራ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ “በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የጥፋት ሃይል የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከትና ኢትዮጵያን የመበተን ግልጽ አላማ የያዘውን ይህንን የሽብር ቡድን የጥፋት ሙከራ ለማምከን በጋራ እንቁም ሲል መንግስት ጥሪውን አቅርቧል ።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ዛሬም ነገም የሰላም አማራጭ የመጀመሪያ መፍትሔ እንደሆነ መንግሥት ፅኑ እምነት አለው። አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በትንኮሳው ከገፋበት፤ መንግስት አገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል፡፡ ይህንን ለማስፈፀም ደግሞ መንግስትና መላው የፀጥታ ሃይላችን ከነሙሉ ብቃትና ቁመናቸው በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ሲል ገልጿል።
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014