የልጅነት ሕይወታቸው ብዙም ፈተና የለበትም::ይህ አጋጣሚ ታዲያ ያን ጊዜ በመልካምነቱ ብቻ እንዲያስቡት አድርጓል::የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ግብርና ላይ ያረፈ በመሆኑ ያሻቸውን ከእፍታው እያገኙ አድገዋል::በተለይ የእረኝነት ውሏቸው ለእሳቸው ሥራ ብቻ አልነበረም::ይህ ዘመን ከሚያግዷቸው ላሞች ጡት ጉንጭ ሙሉ ወተት አስጎንጭቷቸዋል::
በየቀኑ በጉሮሯቸው የሚንቆረቆረው ትኩስ ወተት ዛሬ ከጥንካሬ አልፎ ልዩ ትዝታቸው ነው:: ይህ የልጅነት ዕድሜ ለአብዱልከሪም ሰይድ አንድም ከቤታቸው፣ ሌላም ደግሞ ከእድሜ እኩዮቻቸው የሚቦርቁበት ጊዜ ነበር::ይህን ባሰቡ ጊዜ ልጅነታቸው ይናፍቃቸዋል::ዳግመኛ ወዳለፉት መንገድ መመለስን ይመኛሉ::
የእሳቸው ልጅነት በልቶ ማደር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ማሰብን አስተምሯቸዋል::ነፍስ ካወቁበት ጊዜ አንስቶ ለቤተሰቡ ጉሮሮ የአቅማቸውን ማድረግ ልምዳቸው ነበር::አብዱልከሪም ልጅነትን አልፈው አዋቂ መሆን ሲጀምሩ ግን ማንነታቸው በውጣውረድ የሚፈተንበት ጊዜ ደረሰ::ወቅቱ ሁሉም እንደአቅሙ ተፍጨርጭሮ ለመኖር ዋጋ መክፈል ግድ የሆነበት ነበር:: ይህን ሲረዱ ችግርንና ሰርቶ የማደርን ዋጋ ቀምሰው አጣጣሙት::
የሚቻለው ያልተቻለ
አብዱልከሪም ተወልደው ያደጉት ራያ ውስጥ ‹‹ቅልሽ›› ከምትባል ቦታ ነው::በደስታ የተሻገሩት ልጅነት ለወጣትነት ቦታውን ሲለቅ አስቸጋሪውን ሕይወት የማየት አጋጣሚ ተፈጠረ::ጊዜው የዘመነ ደርግ ጦርነት ነበር:: በወቅቱ ለዚህ ዝግጁ አይደሉምና እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች በእሳት የሚማገዱበትን ፈታኝ ጊዜ ለማለፍ ቀያቸውን ሊለቁ ግድ ሆነ:: ከመሳሪያ ድምጽ ርቀውም ያገኙትን ሠርተው ለማደር ተመኙ::ይህ ውሳኔያቸውም ዝቅተኛ በሚባለው ሥራ እንዲሰማሩ አስገደዳቸው::
አብዱል ከሪም ጦርነቱን ሽሽት ከቀን ስራ ጀምሮ፣ ያልተሳተፉበት የስራ መሰክ አልነበረም::ከሰው እስኪለምዱ ፈተና ቢገጥማቸውም በልቶ ለማደር ጠንክሮ መስራት ግድ ነበር::በተለይ ዓመታትን በገፉበት የኮንስትራክሽን ሙያ የጉልበት ስራ መተዳደሪያቸው ሆኖ ዘልቋል::የዛኔ የለመዱት የጭቃ ቤቶች ግንባታ እስዛሬ የገቢ ምንጫቸው እንደሆነ ነው::
አንዳንዴ ጥጥ ከሚመረትበት አካባቢ ሲገኙ ከሪም የሥራ ዘርፋቸውን ቀይረው ይተጋሉ:: ኩትኳቶና ጥጥ ለቀማም እንጀራቸው ነበር::በተለይ በዚህ ሥራ ውጤታማ እንደሆኑ አይረሱትም ::ከሆዳቸው አልፈው የሚቆጥቡት ገንዘብ ጭምር ቋጥረውበታል:: ቆይቶም ወደ ንግዱ ዓለም ለመግባት ምክንያታቸው ነበር::
በዚህ ስራ መነሻ በኮንትሮባንድ ንግድ ከጅቡቲ አዲስ አበባ ተመላልሰው ጥሩ ጥሪት አስቀመጡ::ይህ አይነቱ ሥራ ስጋት የሞላውና የሚተማመኑበት አይደለም::በወቅቱ ግን ለእሳቸውና ለብዙዎች ቋሚ መተዳደሪያ ነበር::እንዲህ መሆኑ ከጉልበት ስራ እንዲላቀቁና ቤተሰብን እንዲያግዙ ረድቷቸዋል::
የማታ ማታ ግን የጀመሩት የኮንትሮባንድ ንግድ መጨረሻው አላማረም::በድንገት ከትልቅ ኪሳራ ጣላቸው::ይህ ክፉ አጋጣሚም ዳግመኛ ወደ ቀን ሰራው መልሶ ከቀድሞው ድካም አገናኛቸው::
አሁን አብዱል ከሪም ያላቸው ምርጫ በጉልበት ለፍቶ ማደር ብቻ እንደሆነ አውቀዋል:: በልቶ ለማደር፣ ቤተሰብን በተሻለ ለማገዝ ደግሞ ከቀን ሥራ አለፍ ያሉ ገቢዎች ሊኖሩ ያሻል::በኑሮ ከፍ ብሎ ለመለወጥም ሳይታክቱ ሥራ ማፈላለግ የግድ ነው:: ይህን ለማሳካት ያልሄዱበት መንገድ፣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም::
የነበሩበት ሁኔታ ግን ላሰቡት ሁሉ ዕድል አልሰጣቸውም::ለስራ ማልደው ቢተጉም የጉልበታቸውን በረከት ሊጠቀሙ አልቻሉም::የእሳቸው ኑሮ አፋር ‹‹ዳሳጊርታ›› ነውና በጦርነቱ ተጎድቷል::ሁሉም ጭንቀትና በፍርሃት እየኖረ ነው ::በዚህ ውስጥ ሆኖ ስራን ማሰብ ደግሞ ፍጹም አይታሰብም::
እሳቸው በጦርነቱ ቤት ንብረትን ከማጣት ባለፈ የዛሬን የዕለት ጉርስ መሙላት ተቸግረዋል::የባለቤታቸውን ጨምሮ የልጆቻቸውን ጉሮሮ የሚሞሉት በቀን ሥራ ከሚያገኙት ገቢ ነበር::ዛሬ ደግሞ ይህ መቀጠል አልቻለም::ጦርነቱ በአካባቢው የከፋ ጉዳትን አሳርፏል::አሁን ስራና ሰራተኛ ይሉት እውነት የሚሞከር አይደለም::የሚሰራም፣ የሚያሰራም የለም::በርካቶች ጉልበታቸውን ገብረው የላባቸውን ለማግኘት እየተፈተኑ ነው::
በዚህ ጊዜ አብዱልከሪምና ቤተሰቦቻቸው ጦም ማደር ልምዳቸው እየሆነ ነው::ሁሌም ግን ‹‹ነገ ሌላ ቀን ነው›› ሲሉ ተስፋ ያደርጋሉ:: እስከ ስምንተኛ ክፍል ፊደል የቆጠሩት አባወራ ይህ ዕውቀታቸው ብዙ እንደማያራምዳቸው ያውቃሉ::የእሳቸው ልምድ በጉልበታቸው ድካም፣ በላባቸው ወዝ ሰርቶ ማደር ነው::
ከአፋር ባህላዊ ቤቶች ጋር አጥርን አስውቦ ማሳመር የእጅ ጥበብን ይጠይቃል::አብዱል ከሪም በዚህ ሙያ የተካኑ ናቸው::ዛሬ ግን ፈላጊ አላገኙም::ስራ ባለማግኘታቸው በትምህርት ላይ ያሉ አምስት ልጆቻቸውን የሚያበሏቸው እያጡ ነው::ባለቤታቸው በየቤቱ እንጀራ እየጋገሩ ልብስ ያጥባሉ::በዚህ ገቢ ቤቱ ጥቂት ቢደጉምም ስራው እንደልብ የሚገኝ አልሆነም::እናም በእርዳታና አልፎ አልፎ በሚያገኝ ገንዘብ ብቻ ሕይወታቸው እየተንገዳገደ ቀጥሏል::
ችግር ያልፈታው ትዳር
አብዱል ከሪም ዛሬ ላይ የግራ ጎናቸው ሆና የልጆች በረከት ስለቸረቻቸው ሴት ብዙ ያስታውሳሉ::በአፋር ብዙ ዓመታትን ሲያሳልፉ ኑሯቸው በብቸኝነት ነበር:: እንዲህ መሆኑ ችግራቸውን የሚጋራቸው ሰው እንዳይኖራቸው አድርጓል::ወልዶ መሳምን ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው ቆይቷል::ሁሌም ሃሳባቸውን ለመሙላት በየአቅጣጫው ዓይናቸውን ማማተር ልምዳቸው ሆነ::እንዳሰቡትም አንዲት ጉብል ላይ ቀልባቸው አረፈ::ለመግባባት ጊዜ አልፈጁም::ጎጆ ቀልሰው ትዳር መሰረቱ ።
ጥንዶቹ በእኩል ለፍቶ አዳሪዎች ናቸውና ደስተኞች ሆኑ::አንዳቸው የሌላቸውን ሀብትና ገንዘብ ሽተው አልተገናኙም::ልፋታቸው የጋራ፣ ጥቅማቸው የትዳራቸው ሆኗል::
ንጹህ አየር በሚመላለስበት የአፋር ቤት የሚኖሩት ቤተሰቦች ዛሬም ከነችግራቸው ደስታ አልተለያቸውም::የአባወራው ወይዘሮ በቤቷ እንግዳ እንግዳ መጥቶ አይደለም እረፍት ይሉትን አታውቅም::እኛ በደረስን ጊዜ ግን ሕመም አሸንፏት ተኝታ ነበር::እንዲያም ሆኖ ቤት ያፈራው ለእንግዶች ይቀርብ ዘንድ ስትወተውት አስተውለናል::
ጥንዶቹ ከደጅ ውለው በቋጠሩት ገንዘብ ያቆሙት ትዳር ፍቅር የሞላበት እንደነበር ከሁኔታቸው ተረዳን::ሁሌም ችግር ባይጠፋም ውለው ሲገቡ እፎይ ይላሉ። አድረው ሲወጡ የሚመለሱበትን እያሰቡ ይጽናናሉ። በጎጇቸው ውስጥ ችግር ብቻ እንዳይነግስ ፍቅርና መተሳሳብ ፣ ሳቅና ጨዋታቸውን ያበረታሉ::
አብዱልከሪምና ትዳር ከተገናኙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬ እንደ ትናንቱ መስራት አልቻሉምና ችግራቸው ቀጥሏል::አሁን በጎጆ በረከት እየተዋዛ ተስፋ የሚሆናቸው አንዳች ነገር የለም::ጊዜያት እየተቆጠሩ ነጉደዋል::ለእነርሱ ግን አንዳች ጠብ ያለላቸው የለም:: በተለይ ባተሌዋ ወይዘሮ እንደቀድሞው ደፋ ቀና አለማለቷ እጅግ አሳስቧቸዋል::ቢያንስ የእርሷ ሥራ ቤቱን ለመደጎም ያስችል ነበር::የእርሳቸውም የሥራ ፍለጋ ጥረት የእለት ጉርሳቸውን መሙላት የሚችል አልሆነም::
አብዱልከሪም በአፋር በተከሰተው ጦርነት ብዙ ነገራቸው ተወስዷል::ተስፋቸው የጨለመ መስሎም ይታያቸው ይዟል::በተለይ አሁን ‹‹ተስፋ በሌለበት፣ ተስፋን ማለምለም እንዴት ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ ላይ ናቸው::ነገር ግን በትዳራቸው ፣ በፍቅራቸው ብርሃን ጨለማውን እንደሚገፉት ያምናሉና የቻሉትን ለማድረግ እየጣሩ ነው::
የአጋጣሚ ክፉ
ውሎ ለማደር፣ አድሮ ለመነሳት ያህል በቀጠለው ሕይወት ጦርነት ሲከሰት ይይዙት፣ ይጨብጡት ይጠፋል::ማንን ጥሎ ማንን ማዳን ፣ የቱን ይዞ የቱን መጣል እንደሚኖር ግራ ይገባል::ሆድን የሚሞላ ነገር በሌለበት ዓለም ድንገተኛ አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ደግሞ መከራ ብቻ ሳይሆን ሞትም ጭምር ይሆናሉ::የረሀብና ጥምን እውነታ ፣ የመለያየትን ጥግ ይህ ጦርነት በሚገባ አሳይቶ ፈትኗቸዋል:: 42 ኪሎ ሜትርን በእግራቸው ተጉዘው ጫካን ቤቴ ብለው ወራትን እንዲቆጥሩ ተገደዋል::
ከጫካ ኑሮ መልስ ወደቀያቸው ባቀኑ ጊዜ ጁንታው አንዳች ንብረት እንዳልተወላቸው አወቁ::ሕይወት ይቀጥል ዘንድ በባዶ ሜዳ ላይ የአፋር ጎጇቸውን ቀልሰው ሊኖሩ ተገደዱ::ያም ቢሆን ‹‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል›› አይነት ነው::በዚህም ትከሻቸው ከሸክም ባልወጣበት ወቅት ክፉውን አጋጣሚ መቋቋም ተሳናቸው::
ቤተሰቡን የሚያኖር ሥራ የለም ፤ የሚበላ የሚቀመስም እንዲሁ::በዚያ ላይ በርከት የሚለው ቤተሰብ በጠባቧ ቤት መኖር ጀምሯል:: ሕይወት በዚህ መልክ እየተጓዘ ነው:: ትንሽዋ ቤት ሰፊውን ቤተሰብ አስተቃቅፋ እንደነገሩ ታሳድራለች።
ለአብዱርከሪም ጉልበታቸው ማለት የቤታቸው ዋልታ ነበር። የእንጀራቸው ምንጭ፣ የመኖራቸው ትርጉም::ዓመታትን የተሻገሩበት ድልድይም ነው። ዛሬ ግን ይህን ማድረግ ከማይችሉበት ደርሰዋል::ቀድሞ የእሳቸውን እጅ የሚፈልጉ ዛሬ የሰው እጅ ናፋቂ ሆነዋልና አይፈልጓቸውም::ስለዚህም ቤተሰቦቻቸው በችግር ሊፈተኑ፣ ግድ ሆኗል::
ተስፋ መቁረጥ ደግሞ እርሳቸውን ፉክክሩ ውስጥ አያስገባቸውም::ሩጫና ትግል በሞላባት ዓለም ከችግር የተዳመረውን ድንገተኛ ሁነት ማጥፋት ካልተቻለ አደጋው የከፋ ነው::‹‹በቃኝ›› ብሎ መቀመጥም የባሰ ይጥላል::እናም ሥራ አገኙም፣ አላገኙም ማልደው መነሳትን የትግሉ አንዱ ማሳያ አድርገውታል:: አንዳንዴ የጉልበት ሥራ ሲገኝ ጥቂት ይሞክራሉ::ያም ሆኖ ከእጃቸው የሚደርሰው ገንዘብ ጥቂት ገንዘብ ጉዳይ አይሞላም::
ከቀን ስራው የሚመጣው ገቢ ቁራሽ ዳቦን ለሚሹት ልጆቻቸው ጉሮሮ የሚበቃ አይደለም:: ይህ እውነት ለአባወራውና ለእማወራዋ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው። ችግር እግሩን ተክሎ ገቢና ፍላጎታቸውን ሳይጣጣም ቀናትን እያስቆጠረ ይገኛል::ደግነቱ ልጆቻቸው ብርቱ ናቸው::አስቸግረው አያውቁም::ራበን፣ ጠማን ሳይሉ ያገኙትን ቀምሰው ያድራሉ::
አንዳንዴ የእርዳታ እህል ሲመጣና ከበጎ አድራጊዎች ስጦታዎች ሲገኙ ደስተኞች ናቸው ::ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ጎዶሏቸውን ይሞላሉ::ማገሩን አሮጌ ጨርቅ በወተፈው፣ ጣሪያው ሙሉ ዝናብ በሚያፈሰው ጎጇቸው ሆነውም ተስፋ አድርገው ይኖራሉ::
አብዱርከሪም ዛሬ
አሁንም ከእነ አቶ አብዱርከሪም መኖሪያ ውስጥ ነን ። ጊቢው እንደማንኛውም የገጠር ቤት አጥር ዞሮታል::በሩን ለመለየት አስቸጋሪ ይመስላል::እንግዶቹን የምትመራው ሴት በምታውቀው መልኩ ከፈተችልንና ወደውስጥ ዘለቅን::እንዲህ ባይሆን በቀላሉ ለመግባት እንደማንችል ግልጽ ነው::
ወደቤት በዘለቅን ጊዜ ባለቤታቸው በውስጥ፣ እርሳቸው ደግሞ መናፈሻ በሚመስለው የአፋር አጥር ቤት ውስጥ ጋደም ማለታቸውን ተመለከትን። በቤቱ የሚላስ የሚቀመስ እንደሌለ ያስታውቃል::ወይዘሮዋ በህመም እርሳቸው ደግሞ ስራ በማጣት ከቤት ውለዋል:: ይህ ደግሞ ዛሬም የቤተሰቡ ጓዳ በችግር እንዲፈተን አድርጓል ::በነገ ላይ ተስፋ ከመጣል ውጪ አማራጭም አልሰጣቸውም::ደከመኝ ካሉ ብዙ ነገሮች አብረው እንደሚጥሏቸው ያውቃሉና ለልጆቻቸው የተሻለ ነገር ለመስጠት ሥራ በአገኙበት አጋጣሚ ሁሉ ደፋ ቀና ይላሉ::ነገ ትናንት ሊሆን አይችልምና በነገ ፈረስ ዛሬን አይጋልቡም::ሁሌም ለእሳቸውና ለልጆቻቸው አዲስ ዓለምን ለመስጠት ይተጋሉ::
ጦርነቱም ቢሆን ሁሌም ችግር ብቻ እንደማይኖረው ያምናሉ::ከችግሩ ማዶ ብርቱነት አለ::በየቀኑ ጥንካሬ ይወለዳል::አዲስ የሆነ ነገን ለመፍጠር ጥረታቸው ይቀጥላል:: ችግር ተስፋቸውን ቢያጨልምም ቆይቶ እንደሚያነጋ ያውቃሉ::እንዴት ካሉ ደግሞ ባልተበገረ ተስፋ ውስጥ ሆነው በመሥራት ነው::በጦርነቱ የተፈጠሩ ችግሮችም ለእርሳቸው ተስፋ ፈንጣቂ የሚሆኑበት ጊዜን ያመጣል ብለው ያስባሉ::ምክንያቱም ጦርነቱ ያወደማቸው ዳግም ሲገነቡ ለቀን ሰራተኛው ከሪም ዕድልን ያመጣሉ::ቦታውን ከእርሳቸው ቀድሞ የሚፈናጠጥበት የለም::
‹‹እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው የጦር መሳሪያዎችን ድምጽ ባለመስማት ብቻ አይደለም::ችግር ቢከሰትም ለፍቶ ማደርና የእለት ምግብን ማግኘት ሲቻል ነው:: ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ ማለት ሳይሆን የፍትህ፣ የልማት፣ የአንድነትና የምድርን በረከት በእኩልነት መቋደስ ጭምር ነው::›› የሚሉት አብዱርከሪም፤ አሁን ያሉበት ሁኔታ በእጅጉ ያሳስባቸዋል::
ከሪም ተፈጥሮን እንኳን መጠቀም እንዳይችሉ ሆነዋል:: ለማረስ ቢሹም መሬቱ በፈንጅ ተሞልቷልና ሊረግጡት ያሰጋል::በየሰው ቤት ለመሥራትም የቀድሞው አይነት ዕድል የለም::ፍራቻ፣ ነግሷል::አሰሪ አካላትም በተለያዩ ምክንያቶች ከመግባት ተቆጥበዋል::እናም ከሪም ተስፋቸው አንድና አንድ ብቻ ሆኖ ያቺን የሰላም ቀን እየናፈቁ ነው:: መንግሥት በጦርነቱ የወደሙትን ዳግም እገነባለሁ ያለውን ቃል በተስፋ ይጠብቁታል::
እርሳቸው የቀን ሰራተኛና ግንበኛ በመሆናቸው ደግሞ ትልቅ እድል እንዳላቸው ተስፋ አድርገዋል::አካባቢያቸው ትልቅ ጉዳትን ካስተናገዱት መካከል የመጀመሪያው በመሆኑ በቅርቡ የሚጀመረው የትምህርት ቤት ግንባታ አንዱ የሥራ አማራጭ እንደሚሆን ያስባሉ:: የትምህርትቤት ግንባታው ደግሞ ገና ከአሁኑ ጅማሬው መልካም ሆኗል::እንዲህ መሆኑ ተስፋቸውን አለምልሟል::ከዚያ በኋላ በጉልበታቸው ድካም፣ በላባቸው ወዝ የቤተሰቦቻቸውን አንገት ቀና እንደሚያደርጉ ተስፋ አላቸው::
ጦርነት ለፍጥረታት ሁሉ መቅሰፍት ነው::የእጅን ፍሬ ያስጥላል፣ ሕይወትን ነጥቆ ሙሉ አካል ያሳጣል::እንዲህ በሆነ ጊዜ የንጹሃን ነፍሶች ከዛፍ እንዳሉ ወፎች ይመሰላል::ጎጇቸው ይፈርሳል::ሀብታቸው ይበተናል::አገር ቀያቸው ይወድማል::ይህ መልከ ብዙ መቅሰፍት ስደትና መፈናቅልን አስከትሎ መልካም ታሪክን ይሽራል::የአቶ አብዱልከሪምና ቤተሰቦቻቸው ሕይወትም በዚህ አይነቱ እውነታ የተቃኘ ነው::ነገ ያሰቡት ሞልቶ ሰላማቸው አስኪመለስ ያረፈባቸው ደማቅ ጠባሳ ምልክታቸው ሆኖ ይቀጥላል::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014