ኢትዮጵያ የቱባ ባህሎችና የአኩሪ ታሪኮች አገር ስለመሆኗ ዓለም መስክሯል:: ከቱባ ባህሎቿ መካከልም ባህላዊ ምግቦቿ ይጠቀሳሉ:: የባህላዊ ምግብ አይነቶቹ፣ አዘገጃጀታቸውና የአመጋገብ ሥርዓታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው:: የየዘመኑ ትውልድም ይህንኑ አኩሪ ባህል እየተቀባበለ እዚህ አድርሶታል::
በዛሬው የስኬት ገጻችንም የሲዳማ ባህላዊ ምግብን በሆቴላቸው በማዘጋጀት ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ታዋቂነትን ያተረፉ እንግዳ ይዘን ቀርበናል:: እንግዳችን ብዙም ከቤት ውስጥ ፍጆታ ውጭ ማለፍ ሳይችል ዘመናትን ያስቆጠረውን ይህን ባህላዊ ምግብ ወደ አደባባይ ሲያወጡ ነገሮች አልጋ ባልጋ አልሆኑላቸውም::
ከቤተሰብ ጀምሮ በአካባቢው ማሕበረሰብ ጭምር ተቃውሞ ገጥሟቸውም እንደነበር ያስታውሳሉ:: ለመጀመሪያ ጊዜ የምግቦቹን ስም ዝርዝር በሜኑ ላይ በማውጣት ለደንበኞች ሲያቀርቡ ችግር ገጥሟቸውም ነበር:: ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባህላዊ ምግብ በቤት ውስጥ ከእናቶቻችን ውጭ እንዴት ይቀርባል፤ በሚል ለጊዜው ተፈትነዋል::
እርሳቸው ግን ፈተናዎቹን በማለፍ ባህላዊ ምግቡን በሆቴላቸው እያቀረቡ ይገኛሉ፤ በዚህ ብቻም ሳይወሰኑ በውጭው ዓለም የማስተዋወቅ ራዕይ ሰንቀው እየሠሩም ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅት ግን ባህላዊ ምግቦቹ ተወዳጅና ተፈላጊነታቸው እየጨመረ እንደመጣም ይገልጻሉ::
እንግዳችን ወይዘሮ አዝርዕት አየለ ይባላሉ፤ በሃዋሳ ከተማ የአዚ ባህላዊ ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው:: በሲዳማ ክልል ቦና አካባቢ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ አዝርእት፤ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚሁ አካባቢ ተከታትለዋል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሀዋሳ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል:: የኮሌጅ ትምህርታቸውን ቢጀምሩም ብዙ አልገፉበትም፤ ከዛ ይልቅ ውስጣዊ ፍላጎታቸው ለምግብ ዝግጅት ያደላ ነበርና የምግብ ዝግጅት ትምህርት ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል::
የምግብ ዝግጅት ትምህርታቸው በዘመናዊ የምግብ አሰራር ላይ ትኩረት ያደረገ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን ባህላዊ ምግብ በተለይም የሲዳማ ባህል ምግብ ማዘጋጀት ይማርካቸዋል:: ‹‹ስለሲዳማ ባህላዊ ምግብ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል›› የሚሉት ወይዘሮ አዝርእት፤ ‹‹እጅግ ጣፋጭና ለጤና ተስማሚ፤ ቀምሶ የማያውቀው ማንም ሰው ቢመገበው አዲስ የማይሆንበትና ምቹ ምግብ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ከእንሰትና ከእንስሳት ተዋጽኦ፤ ከቦቆሎና ከአጃ ነው የሚዘጋጀው:: በዋናነት የእንሰት ተዋጽኦን ቆጮና ቡላን በመጠቀም በተለያየ አዘገጃጃት ተሰናድቶ ለተመጋቢዎች እንዲቀርብ የሚደረግ ነው::
እንሰት ተፍቆ ቆጮ ይዘጋጃል:: ቆጮው ይጨመቅና ተነፍቶና ተበጥሮ ከጸዳ በኋላ እንዲበስል ይደረጋል:: የበሰለው ቆጮም በተለያየ መልኩ ለምግብነት ይዘጋጃል:: ቂቤ ተጨምሮ ቡሪሳሜ፣ ጩካሜና ኦሞልቾ የሚባሉ ባህላዊ የምግብ አይነቶች ተዘጋጅተው ባማረ መልኩ ለተመጋቢዎች ይቀርባሉ::
ከቡላ ደግሞ ኮፋሜ፣ የቡላ ገንፎ፣ የቡላ ቂጣና ዱአሜ የሚባሉ ባህላዊ የምግብ አይነቶች ይዘጋጃሉ:: ከቦቆሎ የሚዘጋጁት ባህላዊ የምግብ አይነቶችም እንዲሁ የበቆሎ ቂጣ፣ ገፉማ፣ ገፉማ ጨንጨናሜና ሌሎችም ይጠቀሳሉ::
አብዛኛው የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ከእንስሳት ተዋጽኦና ከእንሰት ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደሆኑ የሚናገሩት ወይዘሮ አዝርእት፤ ከእንሰት የሚዘጋጁ ምግቦች ከፍተኛ መጠን ያለው ቂቤ የሚፈልጉና በእርጎና በአሬራ የሚበሉ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፤ በሲዳማ ባህላዊ ምግብ ውስጥ እንሰትና የእንሰሳት ተዋጽኦ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንደሆኑ ይናገራሉ:: ስጋም በስፋት በቆጮ እንደሚበላ አስረድተዋል::
በመንግሥት ሥራ ከሚተዳዳሩ ወላጆች የተገኙት ወይዘሮ አዝርእት፤ ተማሪ እያሉ ተምረው የመንግሥት ሠራተኛ መሆን ምኞታቸው ነበር:: ነገር ግን በንግድ ሥራ ያውም በምግብ ቤት ንግድ ከሚተዳደር ጋር ትዳር መመሥረታቸው የተማሩትን የምግብ ዝግጅት ይበልጥ እንዲያሳድጉት ምቹ ሁኔታ ፈጥረላቸው:: የባለቤታቸውን የምግብ ሥራ ንግድ እርሳቸው ትልቅ አቅም ሆነው ብዙ ርቀት እንዲጓዝም አድርገዋል::
ከዛሬ አስራ አምስት ዓመት በፊት የጀመሩት የምግብ ሥራ ዛሬ ላይ ታዋቂ የባህል ምግብ ቤት ሆኖ መቀጠል የቻለው ጠንክረው በመስራታቸውና የተለያዩ ፈተናዎችን ማለፍ በመቻላቸው እንደሆነም ይናገራሉ:: ሥራውን ሲጀምሩ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ነበር፤ የቤት ክራዩ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ ይመጣና ለማቆም ይገደዳሉ::
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሥራው እንደገና የተመለሱት ወይዘሮ አዝርእት፣ ሥራውን ይበልጥ አስፋፍተውና አጠንክረው በመሥራት ውጤታማ መሆን ችለዋል:: ለሥራ ትልቅ አክብሮት አላቸው:: ባለቤታቸውም ጠንካራ ሠራተኛና ሥራ አክባሪ እንደሆኑ ይመሰክራሉ::
በሆቴል ሥራው ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር ባለፈም 50 ለሚደርሱ ቋሚ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል:: ከሠራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትም የአሰሪና ሠራተኛ ሳይሆን፣ ቤተሰባዊ መሆኑንም ነው ያጫወቱን::
ወይዘሮ አዝርእት ይህንን ባህላዊ ምግብ ከሆቴላቸው በተጨማሪ በየአካባቢው ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አምነው እየሰሩም ናቸው:: በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በተለይም በሃዋሳ አካባቢና አዲስ አበባ ከተማም ጭምር ቅርንጫፍ ለመክፈት እየተዘጋጁ ናቸው፤ ለዚህም በየጊዜው ከደንበኞቻቸው የሚያገኙት በጎ ምላሽ ትልቅ አቅም እየፈጠረላቸው እንደሆነ ነው ያስረዱት:: ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ባህላዊ ምግብ ቤታቸው ለሚመጡ ደንበኞቻቸው ምግቡን በየአካባቢያቸው ለማቅረብ ዕቅድ አላቸው:: በሀዋሳ ከተማ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከናወኑም በጨረታ ተወዳድረው ባህላዊ ምግቡን ያቀርባሉ::
‹‹ተረፍረፍ ያለ ነገር እወዳለሁ፤ ውስን ያለ ነገር አልወድም›› የሚሉት ወይዘሮ አዝርእት፤ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ያስደስታቸዋል:: ለመስጠት ደግሞ ውስን ያልሆነ ነገር እንዲኖራቸው ጠንክረው ሰርተዋል:: በሥራ የሚያምኑና ሥራ የሚያስደስታቸው ጠንካራ በመሆናቸውም እንደምንም ብለው ተፍጨርጭረው ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ችለዋል::
ማንኛውም ሰው ሥራ ሳይንቅ ተፍጨርጭሮ መሥራትና መለወጥ እንዳለበት ይመክራሉ:: በተለይም ሴቶች ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ የትኛውንም ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ:: እሳቸው አሁን የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፉ በማስታወስም፣ በንግድ ዓለም ውስጥ ኪሳራ፣ ማጣት ማግኘት ያጋጥማል፤ ነገር ግን ሁሉን ተቋቁሞ ማለፍ ያስፈልጋል ይላሉ:: ትናንት ምንም ያልነበረን እንደሆንን ሁሉ፣ ዛሬ ብናጣ ነገን ተስፋ በማድረግ በጥንካሬና በጥረት መሥራት አለብን ሲሉ ይገልጻሉ::
በተለይም ሴቶች የቱንም ያህል እንቅፋት ቢገጥማቸው ጠባቂ ከመሆን ተላቀው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተፍጨርጭረው መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ:: ሴት የራሷ ገቢ ካላት በነጻነት መንቀሳቀስና በራስ መተማመኗ እንደሚጎለብት ያምናሉ::
ለዚህም ቁጠባ ወሳኝ መሆኑን ነው የሚመክሩት:: ከራስ ተደብቆ መቆጠብ እንደሚቻል የሚናገሩት ወይዘሮ አዝርእት ከባለቤታቸው ጋር የጀመሩት የምግብ ቤት ሥራ ኪሳራ ሲያጋጥመው ለአንድ ዓመት ያህል ከሥራ ውጭ እንደነበሩ ያስታውሳሉ:: ወደ ሥራው ለመመለስ ግን እርሾ የሚሆን ብር ነበራቸው:: ይህም ቆጥበው ያስቀመጡት ባለቤታቸው የማያውቁት ዘጠኝ ሺ ብር ነበራቸው:: ከባለቤታቸው ደብቀው እንዲሁም ከራሳቸው ቀንሰው የቆጠቡት ይህ ገንዘብ እንደገና ለከፈቱት ሆቴል መነሻ ሆኗቸው ዛሬ የሚወዱትን የሲዳማ ባህላዊ ምግብ በስፋት መሥራት እንዲችሉ ምክንያት ሆኗቸዋል::
ባለቤታቸው የጀመሩትን የምግብ ሥራ አጠናክረው ያስቀጠሉት የአዚ ባህላዊ ምግብ ቤት ባለቤት ወይዘሮ አዝዕርት፤ ተወዳጅ የሲዳማ ባህላዊ ምግቦችን በማሰናዳት ዕውቅና አትርፈዋል:: በአዚህ ባህላዊ ምግብ ቤት የሚዘጋጀውን የሲዳማ ባህላዊ ምግብ የቀመሰ ማንኛውም ሰው ምግቡን አድንቆ እያመሰገነ ያለበት ሁኔታ ይበልጥ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል:: የሆቴል ቤቱ ተገልጋዮች ብቻም ሳይሆኑ እንግዶች ባህላዊ ምግቦቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ ስለመሆናቸው ግብረ መልስ እንደሚሰጧቸውም ወይዘሮ አዝርእት ይናገራሉ::
በቅርቡም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከባለቤታቸው ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመሆን ምግብ ቤቱን መጎብኘታቸውንና መመገባቸውንና በምግቡም ደስተኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ወይዘሮ አዝርእት አጫውተውናል::
ወይዘሮ አዝርእት፤ ባህላዊ ምግቡን በአገር ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀና ባህሉን የሚገልጽ ባለ ኮከብ ሆቴል ለመክፈት ዕቅድ አላቸው:: ሆቴሉም በአፍሪካ ትልቁና የቱሪስት መስህብ መሆን እንዲችል ታስቦ የሚሠራ እንደሆነና በቱሪዝም ዘርፉ ብዙ ሥራ መሥራት የሚጠበቅ እንደሆነም ጠቁመዋል:: ባህላዊ ምግቦቹ ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችሉ በመሆናቸው ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ አገር ለመላክ ምቹ ሁኔታ እንዳለ የገለጹት ወይዘሮ አዝርእት፣ እሳቸው ምግቦቹን እየላኩ እንደሆነም ይናገራሉ::
ለሚያሰናዷቸው ምግቦች ዋናው ግብአት የሆኑትን የእንሰት ውጤቶች የሚገዙት በሲዳማ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ለአብነትም ከበንሳ፣ ከቦና፣ ከአርቤ ጎና፣ ከኔራ እና ከሌሎችም አካባቢዎች እንደሆነ ተናግረዋል::
ባህላዊ ምግቡን ለውጭ አገር በስፋት በመላክ ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል እንሰት ላይ ብዙ መስራት አስፈላጊ ነው የሚሉት ወይዘሮ አዝዕርት፤ በአሁኑ ወቅት የእንሰት እጥረት እየተስተዋለ ስለመሆኑም ይናገራሉ::
ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ወደ ሥራው ሲገቡ የነበረው የእንሰት መጠንና ዋጋ ዛሬ ላይ ካለው ጋር ፍጹም የሚገናኝ እንዳልሆነ አመልክተው፣ የአንድ ጭነት ቆጮ ዋጋ በሶስትና አራት እጥፍ ከማደጉ በላይ እጥረት እየተከሰተ ይላሉ:: ከዚህ ቀደም እንሰትን ብዙ የሚጠቀም ሰው አልነበረም:: በየአካባቢው ከምግብ ፍጆታ አልፎ ለገበያ አይቀርብም ነበር የሚሉት ወይዘሮ አዝርእት፣ አሁን ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ:: ሰዎች በቦታው ላይ ጫትና የተለያዩ አትክልቶችን መትከል መጀመራቸውም ሌላው የእጥረቱ ምክንያት እንደሆነም ያብራራሉ::
ከዚህ ቀደም ለምግብነት የሚውለው እንሰት ተፍቆ ለረጅም ጊዜ ይቀመጥ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከብዙ ቆይታ በኋላ ለምግብነት ይውል እንደነበርም ያስታውሳሉ:: በአሁኑ ወቅት ግን በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ በመምጣቱ በቤት ውስጥ የዕለት ምግብ ከመሆን አልፎ በገበያው በእጅጉ እየተፈለገ ነው ይላሉ:: በዚህም ምክንያት እንሰቱ ገና ሳይደርስ ለገበያ እየወጣ ነው:: ይህ ደግሞ ጥራቱ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ:: ስለዚህ እንደቀድሞው ሁሉ እንሰት በየጓሮው በስፋት እንዲለማ በማድረግ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ያስገነዝባሉ::
የእንሰት ፍላጎት እየጨመረ ምርቱ ደግሞ እየተመናመነ የመጣ መሆኑን ተከትሎም ወይዘሮ አዝርእት በእንሰት ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፤ መሬት በኢንቨስትመንት ወስደው እንሰት በስፋት ለማልማት እየተዘጋጁ ናቸው:: ሌሎችም እንሰትን በማልማትና በመንከባከብ ሥራውን አስፍተው ቢሰሩ፤ በተለይም በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ባላቸው መሬት እንሰት ቢያለሙ በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መክረዋል::
‹‹እንሰት በጓሮው ውስጥ ያለው ሰው ምንም ቢሆን ለረሃብ አይጋለጥም›› የሚሉት ወይዘሮ አዝርእት፣ ከእንሰት የተለያዩ የምግብ አይነቶች የሚገኝ በመሆኑ በጓሮው እንሰት የተከለ አርሶ አደር ሌላው ቢቀር አሚቾ የተባለውን የምግብ አይነት በቀላሉ ለልጆቹ መመገብ እንደሚችል ያስረዳሉ:: በመጨረሻም እንሰት እንደ ሌሎች የምግብ አይነቶች ሁሉ እጅግ ተወዳጅና ጠቃሚ የምግብ አይነት መሆኑን ጠቅሰው፣ እንሰትን አብዝተን በማልማት ተጠቃሚ እንሁን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014