ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የረገጠ ታዳጊ የዛሬው የመነሻ ታሪካችን ነው:: ታዳጊው ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ተወልዶ ከባህርማዶ ያደገ ነው:: ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አዲስ አበባን እየጎበኘ ያለ ታዳጊ:: የክረምቱ ዝናብ እየዘነበባቸው የታክሲ ወረፋ የሚጠብቁ ሰዎችን ተመልክቶ ግር የተሰኘ:: ለግርታው መፍትሔን ፍለጋ እናቱን “እማማ እኒህ ሰዎች ለምንድን ነው የቆሙት?፤ ለምንስ ወደየቤታቸው አይሄዱም? ለምን ቆመው በዝናብ ይመታሉ? ብሎ ጠየቀ:: የእናቱ ምላሽ ትራንስፖርት እየጠበቁ መሆኑን መንገር ነበር::
ታዳጊው ፊት ላይ ጥልቅ ኀዘን ይነበባል:: በዝናብ የሚደበደቡ ሰዎችን እያዩ ሳይጭኑ ማለፍ ይቸግረውና “ለምን የሚያልፉት ሰዎች ሁሉም እየጫኑ አይሄዱም?፤ ለምንስ እኛም ሰው አንጭንም?” ብሎ ይጠይቃል:: እናትም የማያውቁትን ሰው የመጫንን አደገኛነት ለማስረዳት ትሞክራለች:: ልጁ ጥያቄውን በመቀጠል “የሚጭኑትስ ታክሲዎችሽ አደገኛነቱ አይመለከታቸውም እንዴ?” ብሎ ይጠይቃል:: እናትም “እነርሱማ ስራቸው ስለሆነ ነው” ትላለች:: እሺ “መንግሥት ለምን መኪና እንዲያገኙ አያደርጋቸውም?” ሌላ ጥያቄ:: እናቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ያን የማድረግ አቅም እንደሌለው ባለመሰልቸት ትመልስለታለች:: ታዳጊውም የኢትዮጵያን መንግሥት እርሱ ከመጣበት የአሜሪካ መንግሥት ጋር በማነጻጸር “የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን እንደ አሜሪካ መንግሥት አቅም ያለው አልሆነም?” ብሎ ይጠይቃል:: የእናት ምላሽ አሁንም ይቀጥላል::
እናትና ልጅ የጀመሩትን ጨዋታ ሳይጨርሱ እቤታቸው ደረሱ:: እቤታቸው ደርሰው መክሰስ እየተመገቡ እያሉ በተከፈተው ዜና በኢትዮጵያ ውስጥ ለርሃብ ስለተጋለጡ ዜጎች ዜና ይሰማል:: ሰዎች የሚበሉት አጥተው የሚሞቱበት ሁኔታ ይበልጥ የታዳጊውን ልብ ነካው::ታዳጊው በሚያውቀው ኮልታፋ አማርኛና እንግሊዝኛ እየደባለቀ የሚያገኛቸውን ሰዎች በሙሉ “እንዴት ሰዎች የሚበሉት ያጣሉ?፤ እንዴት ሰው በዝናብ እየተደበደበ መኪና ይጠብቃል?፤ እንዴት ሰዎች መኖሪያ ቤት አጥተው በአንድ ቤት ውስጥ ታጭቀው ይኖራሉ?” ወዘተ እያለ ይጠይቃል::
ታዳጊው ሁሉም ሰው ስለሚያነሳው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ደግሞ ሌላው ግርምትን ፈጥሮበታል:: ሁሉም ችግሩን ወደ ሌሎች ሰዎች መጠቆም ላይ ያተኮረ መሆኑን ይረዳል:: በአብዛኛው ችግሩ ወደ መሪዎች፤ ወደ ፖለቲካ ሰዎች ያነጣጠረ ሆኖ ይቀርብለታል:: ችግሩን ወደ ሌላ በመጠቆም ያስረዱት ሰዎችን ዘላቂ መፍትሔው ምንድን ነው ብሎ ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ሊያሳምነው አልቻለም:: የችግር አተያያቸውም ሆነ የመፍትሔ ጥቆማቸው ሊያሳምነው አልቻለም::
ለእርሱ ትልቁ ችግር ሆኖ የሚሰማው ይህን ነባራዊ ሁኔታ ተቀብሎ መደበኛ ኑሮን መኖር መቻሉ ነው:: እንዴት ሰው እንዲህ ባለ ሕይወት ውስጥ በመደበኛነት ይኖራል፤ እንዴትስ ችግሩን ሁሉም ውጫዊ ያደርጋል፤ እንዴት እያንዳንዱ ሰው የራሱን የችግር አስተዋጽኦን ለመረዳት አይሞክርም እያለ ከራሱ ጋር ይሞገታል:: ታዳጊው እንግዳ:: በኖረበት አጭር እድሜው ውስጥ ችግርን እና አፈታቱን በሚያይበት አተያይ ውስጥ ሆኖ::
እናት በታዳጊው ልጇ የሚቀርብላትን የጥያቄ ጋጋታ ባለመስልቸት ትመልሳለች:: አሜሪካን ሀገር በስራ ተጠምዳ ለብዙ ጊዜ እናቱን ማግኘት የሚቸገረው ልጅ በአሜሪካን ሀገር ያለው የስራ ባህል ምንያህል ለአሜሪካኖች እድገት ወሳኝ እንደሆነ ተረዳ:: እናቱን እንደሚፈልግ ማግኘት ባለመቻሉ ቅር ይሰኝ የነበረው ታዳጊ ከእናቱ የትውልድ ሀገር ሁኔታ በደንብ ተረዳ:: ትክክለኛው አካሄድ የትኛው ነው ሲል ራሱንም ጠየቀ፤ የአሜሪካ ወይንስ የኢትዮጵያ::
ሰዎች ተገቢ የሆነ እረፍት ሊኖራቸው እንደሚገባ ቢያምንም በድህነት ተቆራምዶ በዚህ ደረጃ ከመገኘት ግን በማይመች ሁኔታም ውስጥ ጠንካራ ስራ ሰርቶ ነጻ መውጣት ይገባል ሲልም አሰበ:: መነሻው ግን ራሱ ሰው ላይ መስራት እንደሆነ ተረዳ:: የችግር አተያይም ሆነ የመፍትሔ አሰጣጥ ችግር ያለበት ሰው በሞላበት ሁኔታ እንዴት ዘላቂ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ሲል ራሱን ጠየቀ:: ከማልማት በፊት መልማት ያለበት ሰው ይቀድማል አለ:: ይህን ሁሉ ሰው ማልማት እስኪቻል ድረስ ብዙ ዓመት የሚፈጅ መሆኑን ተረዳና የማይመለከተው ነገር ውስጥ ገብቶ የሚጨነቅ መሆኑን ለራሱ ነገረ::
ለምቶ ማልማት፤
የልማት ጽንሰሃሳባዊ አረዳድ ሰፊ ትንተናን የሚፈልግ ነው:: ስለ ልማት ብዙ ተጽፎም ይገኛል:: በየአካባቢያችን የልማትን ቃል ተጠቅመው ገንዘብ የሚጠይቁ፤ ስብሰባ የሚጠሩ፤ ደንብን ጠቅሰው የሚጠይቁ ወዘተ አሉ:: ልማት ሲመረቅ መሪዎች ሪባንም ሲቆርጡ ተመልከተናል:: በተለይ በምርጫ ሰሞን የሚመረቁ የልማት አይነቶችና የሚቀመጡ የመሰረት ድንጋዮች አማላይ ሆነው እናያለን::
መሪው ሪባን በመቁረጥ የሚያስመርቀው ልማት በልማትነት ትርጉም ውስጥ ይዘልቅ ዘንድ ልማት በሰፈው የተዋሃደን ሊሆን እንደሚገባ ይነገራል:: ማሕበረሰብ በአካባቢው ያለውን ልማት የእኔ ነው ብሎ ተቀብሎ ተገቢን እንክብካቤ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው የሚለው ጥያቄ በልማት ዙሪያ የሚሰሩ አካላት ጥያቄ ከሆነ ሰነበተ:: ልማትን ዘላቂ ማድረግ ተደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ ነው:: ንድፈሃሳባዊ ትንታኔዎችን ማቅረብ ስለማንችል ጎልቶ የሚወጣውን ወሳኝ ነጥብ ግን እናንሳ፤ ለምቶ የማልማትን ሃሳብ::
የሰብዓዊ ምላሽ፣ ዘላቂነት ያለው ልማት እና ዘላቂነት ያለው ሰላም የማይነጣጠሉ መሆናቸውን አንቶኒዮ ጉተሬዝ ይናገራሉ /Humanitarian response, sustainable development, and sustaining peace are three sides of the same triangle:: ሦስቱን በአንድ ቃል ለመግለጽ ብናስብ ዘላቂነት ያለው ልማት ልንለውም እንችላለን:: ዘላቂ ልማት ደግሞ ዘላቂ አልሚ እንደሚፈልግ እናስብ::
ልማት በገንዘብ ብዛት የሚመጣ አይደለም:: ብዙ ገንዘብ ያለው ሰው እንዴት ገንዘቡን መጠቀም እንዳለበት ካለማወቁ የተነሳ የሚገባበት ውድቀት በብዙ ማስረጃዎች ሊቀርብ የሚችል በገንዘብ ብዛት ብቻ የሚመጣ ልማት እንደሌለ የሚያሳይ ነው:: ልማት ድንጋይ መደርደር ብቻም አይደለም:: ቄንጠኛ ድንጋዮችን ደርድረው ዞር ሲሉ ቄንጠኛውን ግንባታ መጠበቅም ሆነ ማስጠበቅ በማይችል የሰው ሃይል የተከበበ ከሆነ ልማቱ ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ልማት ሲታሰብ አስቀድሞ መነሳት ያለበት ጉዳይ የሰው ሃይል ልማት ነው:: የሰው ሃይል ልማት መሰረታዊውን ልማት ለማከናወንም ሆነ ለማስቀጠል ወሳኙ መሳሪያ ሆኖ በተቀየሩ ሀገራት የታየ እውነት ነው:: በሰው ሃይል ልማት ላይ ለመስራት እንዲሁ የሚጠበቀው ጥልቀቱና ስፋቱ የታሰበበት መሆኑ የግድ የሚለው ለእዚህ ነው::
ለመንደርደሪያ የሚሆኑ ጥያቄዎችን በወጣቶቻችን ዙሪያ እናንሳ:: ወጣቶቻችንን ስናስብ ፈጥኖ ወደ አእምሮችን የሚመጣው ምን እንደሆነ እንጠይቅ:: አንባቢው ለራሱ ታማኝ ሆኖ እኒህን ጥያቄዎች ራሱን ይጠይቅ ምላሽም ይስጥባቸው:: ዛሬ ወጣቶቻችንን ስናስብ የምናስበው የለውጥ ሃይሎች ሆነው ወይንስ በቀንበር ውስጥ ሆነው የሚገኙ? ወጣቶቻችንን ስናስብ የምናስበው ስራ ለመፍጠር አቅም ያላቸው ወይንስ ተቀምጠው የሚጠብቁ? ወጣቶቻችንን ስናስብ የሚታየን ቤተሰብ መስርተው ፍሬያማ ሕይወትን ለመኖር ዝግጁ የሆኑ ወይንስ ውድ የሆነውን እድሜያቸውን ውሉ በጠፋበት መንገድ ውስጥ የሚያባክኑ? ወጣቶቻችንን ስናስብ የምናስበው ተጽእኖን ተቋቁመው ያለሙትን ለማሳካት የሚሰሩ ወይንስ እንዲሁ የሚባክኑ? እኒህ ጥያቄዎችን ይዘን የግላችንን ምላሽ ሰጥተን እንቀጥል:: የሰጠነው ምላሽ ከሚታየው ልማት በፊት ሊቀድም የሚገባውን የሰውን ልማት ማሰብ የግድ እንደሚል እንደሚያስረዳ ይታመናል::
እንደ ሀገር በስንዴ ራስን አለመቻል በብዙ መንገድ የጎዳን እንደሆነ ሲነገር እንሰማለን:: ከዚህ ጉዳትም ለመውጣት እንደ ሀገር እየተሰራ ያለው ስራ ፍሬያማ ሊሆን እንደሆነ በዜና ሲነገር ሁሉም ሰው ሀሴት ሲያደርግም እንዲሁ:: እዚህ ጋር ግን አንድ ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው:: እርሱም እንዴት እስከዛሬ በስንዴ ራስን መቻል ከባድ እንደሆነ የሚጠይቅ ጥያቄ:: በውሃ ሀብታም በሆነች ሀገር ውስጥ፤ ስንዴ ማብቀል የሚችል ሰፊ መሬት ባለባት ሀገር ውስጥ፤ በግብርና ዓመታትን ያስቆጠረ ልምድ ባላት ሀገር ውስጥ፤ እንዴት እንደ ሀገር የስንዴ ፍላጎትን ማሟላት ሳይቻል ቀረ? ታዳጊው ልጅ ያለንበት ሁኔታ የማይገባው ቢሆን እንዴት ይገርማል:: ቆም ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ከብዙ አንጻር ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆነ::
ሀገር እና ግለሰብ
ከኔልሰን ማንዴላ ንግግሮች መካከል አንዱን እናስቀድም:: በተጨባጭ ይህ ነው የሚባል የሃላፊነት ቦታ ያልተሰጣቸው ነገርግን ማሕበረሰብን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ስላደረጉ ወንዶችና ሴቶች መኖራቸው የተናገሩት ነው:: There are so many men and women who hold no distinctive positions but whose contribution towards the development of society has been enormous. ሀገርና ግለሰብን ስናገናኝ የምናስበው ግንኙነት የእውቅና ማማ ላይ የመውጣት አለመውጣትን አይደለም:: በእውቅና ማማ ላይ ሳይወጡ ባሉበት ሁኔታ ትርጉም ያለው ስራ የሚሰሩ ዜጎችን ማለታችን ነው::
የሰው ሃይላቸውን በግለሰብ ደረጃ ጠንካራ ማድረግ የቻሉ ሀገራት በተጨባጭ ጠንካራ ሀገር መገንባት ችለዋል:: ለምቶ ማልማት ሲታሰብ እያንዳንዱን ግለሰብ ጠንካራ አድርጎ መስራት ላይ አተኩረው ሰርተዋል:: እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ግለሰብ ትልቅን ማሰብ፤ ሃላፊነትን መወጣት፤ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መዝለቅ፤ ወዘተ ቢችል ለምቶ ማልማት ቀላል ይሆናል:: ከመጽሐፍት የምንረዳው ጠንካራ ሀገርን የፈጠሩ መርሆች እጅግ ውስብስብ አለመሆናቸውን ነው:: ቀላል የሆኑ፤ ነገር ግን በተጨባጭ መተግበር በቻሉ መርሆች ውስጥ አስቸጋሪ መንገድን ተጉዘው የሄዱ ወደ ውጤት ደርሰዋል:: እያንዳንዱ ግለሰብ ራሱን ጠንካራ አድርጎ ማቅረብን የሚጠይቅ ሥርዓት ባነበርን ቁጥር በድምር ውጤቱ ሀገር ጠንክራ ትገኛለች::
ለምቶ ማልማት ሲታሰብ ለአንድ ዜጋ የሚኖረን አተያይ ይወስነዋል:: አንዱ ዜጋ ምናልባትም እንደ አልበርት አንስታይን ዓለምን የሚያስደምም ፈጠራ ይዞ የሚወጣ ሊሆን ይችላል:: አንዱ ዜጋ ምናልባትም እንደ ሙሴ ሕዝብን ከባርነት ነጻ የሚያወጣ ሊሆን ይችላል:: አንዱ ዜጋ ምናልባት እንደ ማራዶና ታሪክ የማይረሳው የእግር ኳሱ ሜዳ ልዩ ፍጡር ተደርጎም ሊቆጠር ይችላል:: ጥያቄው ለአንዱ ዜጋ የሚሰጠው ትኩረት ነው፤ ራሱን ብቁ አድርጎ የመገኘትን አስፈላጊነት የሚያሳይ:: ከአንዱ ዜጋ ተነስቶ የሀገር ምስልን መቀየር::
በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተማሪዎች ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል የሚያደርጉት ጉዞ እንደሚታወቀው የተለመደ አሰራር ነው:: ተማሪዎች ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል እያለፉ የሚያደርጉት ጉዞ ግን በትልቅ የሀገር የዓላማ ምስል ውስጥ የተቃኘ መሆን አለመሆኑን ስንመለከት ክፍተትን እናስተውላለን:: ከክፍል አንደኛ እየወጣ የሄደ ልጅ ዲግሪውን በአስደናቂ ውጤት ይዞ ነገር ግን በሀገሩ ውስጥ ያለውን የማልማት ፈተና መቋቋም የማይችል፤ ከራስ ያለፈ እይታ የሌለው፤ ስለ ሀገር ያለው መረዳዳት የተጣመመ ከሆነ ትናንት የሄደበት የመገንቢያ ጊዜው ዛሬ ከእርሱ በሚጠበቀው ልክ እንዳይገኝ ያደርገዋል::
ሀገርን ከእያንዳንዱ ግለሰብ ተነስተን መገንባትን ስናስብ ብቻ ቀላሉ ነገር ቀላል ሆኖ ሊታየን ይችላል:: ራስን በምግበ መቻል እንደ ሀገር ትልቅ ችግር የሆነበትን ምክንያትም ተረድቶ ለመፍትሔም መድረስ ይቻላል:: ዓለም በስንት ጉዳይ በብዙ እርቀት ከእኛ በራቀበት ሁኔታ የተገነባን ለማፍረስ፤ ወይንም ሸጦ ለግለሰብ ጥቅም ለማዋል የሚደረግ አተያይ ዝም ብሎ የመጣ ዝም ብሎም የሚጠፋም አይደለምና መፍትሔው የግድ ይላል:: አንድን ግለሰብ እንደ ግለሰብነቱ የሚሰራበት መስመር መዳረሻውን እያየ የሚሂድበት የመፍትሔ መንገድ::
ለምቶ ማልማት ሲታሰብ በእውቀትም ሆነ በእሴት የተገነባ አንድ ግለሰብ ያስፈልጋል ማለት ነው:: ለአንዱ ግለሰብ የሚሰጠው ትኩረት በቀነሰ ቁጥር ነገሮች አቅጣጫ ስተው ይገኛሉ:: በቀጣይ የሚኖሩ ማናቸውም ሀገራዊ ግቦች እንደታሰበላቸው ላይሆኑም ይችላሉ:: ከአንድ ምእራፍ ወደ ሌላ ምእራፍ የሚደረግ ሀገራዊ ጉዞም ውጤት ያለው ይሆናል:: ከዛሬው ወደተሻለው ምእራፍ እንጂ ከዛሬው ወደ ከፋ የመሄድ ጉዞም አይኖርም:: የመነሻ ታሪካችን ውስጥ የተመለከትነው ታዳጊ ጥያቄዎችም በቀላሉ መልስ ማግኘት ይችላሉ:: እኒህ ጥያቄዎች የሁላችንም ጥያቄዎች ሆነው ለከፍተኛ ስራ እንድንነሳሳ የሚያደርግ ግለሰባዊ ግንባታ ከሁሉ የቀደመው ነው:: ያስቀደሙቱ ተጠቅመዋል፤ ስፍራን ያልሰጡት በሌሎች ላይ ጥገኛ ሆነው ይኖራሉ:: ቤታችን ልንረዳው ያስጠጋነውን ሰው እድሜ ልኩን የሚበላውን እየሰጠን ከመርዳት እንዴት ሰርቶ የራሱን ገቢ ማመንጨት እንደሚችል ብንረዳው ብናሳየው የትኛው ይሻላል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ነው:: የመፍትሔው ጉዞ ግለሰቡ ባለው እውቀት፤ ክህሎት፤ እሴት ወዘተ ውስጥ መሆኑን ተስማምተን ሰፊ ቦታ ሊኖረው ስለሚገባ ግለሰባዊ እሴት እናንሳ::
በተጨባጭ አንዳችን ከሌላችን እንለያያለን:: እያንዳንዳችን ሕይወትን በምናይበት መንገድ፣ በባህሪያችን፣ ለጊዜ በምንሰጠው ቦታ፣ ወዘተ በብዙ መንገድ እንለያያለን:: ሁላችንም አንድ አይነት ሃሳብ በአንድ ጉዳይ ላይ ላይኖረን ይችላል:: አንድን ምስል ተመልክተን የየራሳችንን ትርጉም ልንሰጥ እንችላለን:: የሃሳብ፣ የሃይማኖት፣ የቅደምተከተል፣ የውሳኔ አሰጣጥ፣ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የአነጋገር ወዘተ ልዩነቶች አሉን:: ለእኛ የሚመቸን አይነት አለባበስ ለሌላው ሰው አይመቸውም ይሆናል:: ለአንዱ የተመቸው የምግብ አይነት ለሌላው አለርጂ ሊሆን ይችላል:: በብዙ ጉዳዮች ላይ መሰል ነገሮች ይኖራሉ:: በእሴት ዙሪያ የሚኖረን ልዩነትም እንዲሁ ነው::
መልካም የምንላቸው እሴቶች ዙሪያ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ መስማማት ያለው ነው:: መከባበር እሴት ቢሆን ማን ይጠላል:: መደማመጥ በተግባር ሆኖ ቢታይ ማን ይጠላል:: መረዳዳት ቢሆን ማን ይከፋዋል:: በግለሰብ ደረጃ እንዲተገበሩ የሚታሰቡ እሴቶች የሃይማኖትን አጥር አልፈው የሚያቀራርቡ ናቸው::
እሴትን ከእውቀት ጋር እና ከተዋሃደ ልምድ ጋር አቀናጅተን እንደ ሀገር በጋራ በምናየው ግብ ውስጥ አብሮ መፍሰስ መቻል ለምቶ ማልማት፤ ተገንብቶ መገንባት ላይ ያደርሰናል::
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014