በፍቅር ላይ የተመሰረተ ትዳራቸውን ለማቅናት ሁለቱም ደፋ ቀና የሚሉ ባልና ሚስት ናቸው። ፍቅራቸው ከቤት አልፎ ለሌሎች የሚታይ የተለየ አይነት ነው። ከማጣት እስከ ማግኘት በጋራ ያሳለፏቸውን ቀናት በትዝታ ማህደሮቻቸው በደማቅ ቀለም ፅፈዋል። መደጋገፍ መከባበራቸውን ለተመለከተ በአንድ ቋንቋ ሲናገሩ፤ በአንድ ልብ ሲጣመሩ ላየ ሁሉ “እውነትም ባልና ሚስት ከአንድ ምንጭ ይቀዳሉ” ሳይል አያልፍም።
ፀብ በቤታቸው ታይቶ አይታወቅም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከፍቅራቸው የተነሳ በሀሳብ አለመግባባት እንኳን ቢኖር ወደ ኩርፊያ ወደ ጭቅጭቅ ሳያድግ እዛው ላይ በአጭሩ ቋጭተው ወደ ነበረ ፍቅራቸው ይመለሱ ነበር። ለልጆቻቸው አርአያ የሆኑ፤ በመንገር ሳይሆን በመኖር ልጆቻቸው መልካም ስነ ምግባር ኖሯቸው እንዲያድጉ የሚያደርጉ ባልና ሚስት ነበሩ። ፍፁም ትህትናና ሰላም በቤታቸው የሰፈነ የሚያስቀና ፍቅር የነበራቸው ሰዎች ስለመሆናቸው የሚያውቃቸው ሰው በሙሉ ይናገሩላቸዋል። አይደለም ለረጅም ጊዜ ተለያይተው፤ በስራ ምክንያት እንኳን ቀን ሙሉ አብረው አለመዋላቸው የሚያነፋፍቃቸው አይነት ናቸው።
“ስስቴ ናት በሙሉ አይኔ አይቻት አላውቅም፤ አጠገቤ ሆና ትናፍቀኛለች። ሁለመናዋ በሕይወት መኖሬን የሚያረጋግጥልኝ እድሜዬ እንዲረዝም የምታደርገኝ ልዩ ፍጥረት ናት ይላል ባለቤቷ ስለ ሚስቱ በጠየቁት ቁጥር። የእሷም መልስ ይህንኑ ነው የሚመስለው ከሱ ተለይቼ መኖር የምችል አይመሰለኝም። ፈጣሪዬ ከእሱ ፊት ያድርገኝ” በማለት አክብሮቷን፤ በስስት ፍቅሯን ትገልፃለች።
ተወዳጇ ሴት
የደም ገንቦ ከሚባሉት ሴቶች መካከል ትመደባለች። ጨዋ ስራዋን፣ ትንሽ ትልቁን የምታከብር አይነት ሴት ናት። ይህች መልክና ፀባይ አሟልቶ የሰጣት ሴት ቤተሰቧን አክባሪ ትዳሯንም ወዳድ ናት። ቤተሰቡ ከእንቅልፉ ሳይነሳ ቀድማ ተነስታ ቁርሱን ቡናውን ስታደርስ ማንም አይስተካከላትም።
ከባለቤቷ ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት ለሰፈር ምሳሌ አድርጓቸዋል። ተወዳጅዋ እመቤት ፈፅማ ትዳሯን የምታከብር ለቤተሰቧ ሕይወት መቃናት ሌት ከቀን የምትደክም ጠንካራም ሴት ናት። የቤቷን ስራ ጨርሳ ወደ መስሪያ ቦታዋ ስትደርስ በዛም የተሰጣት ኃላፊነት ላይ ተግታ የምትሰራ ዘወትር አዲስ ነገር ለመማር የምትታትር ናት።
የስራ ቦታዋን እንደምትወድና እንደምታከበር አለባበሷ ምስክር ነው። ጥንቅቅ ያለ የቢሮ አለባበስ ለብሳ ነው በስራ ገበታዋ ላይ የምትገኘው። ኃላፊነቷን በፈገግታ ያለ ምንም መከፋት የምታከናውነው ይች ሴት አጠገቧ የደረሰ ባለ ጉዳይ በሙሉ ፊቱን ቀጨም አድርጎ ሲመለስ ታይቶ አይታወቅም።
በቁም ቅዠት ውስጥ የገባው አፍቃሪ
ፈገግታ ከፊቷ የማይጠፋውን ይህችን ሴት በልቡ ተመኘቶ አይኑን የጣለባት አንድ ሰው ነበር። ለቤት ለደጁ አድባር፤ ውብ ጠንቃቃ ሴትን አይቶ ማለፍ የከበደው ይህ ሰው ባለትዳር መሆኗን እስኪረሳ ድረስ በፍቅር አቅሉን ሳተ። እሷ የኔ ብቻ ናት በሚል የህልም ዓለም መዋኘት ከጀመረ ሰነባብተ።
ይህ ቅዠቱን እውን ለማድረግ የሌላ ሰው ሚስትን የተመኘው ይህ ሰው ለዚህች ቀና ልብ ላላት ባለቤቷን አክባሪና ታማኝ ሴት ሀሳቡን ያካፍላታል። ይህ ጉዳይ መሆን እንደማይችል በፍቅር ዓለም ከባለቤቷ ሌላ ሰው መመልከት የማትችል መሆኑን በትህትና ታስረዳዋለች። ጉዳዩ አልዋጥለት ያለው ይህ ሰው በምንም ተአምር ከእኔ ውጭ የሌላ ሰው መሆን አትችይም በማለት ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርስባት ጀመር።
በወጣች በገባች ቁጥር “ያንን ጉዳይ እንዴት አደረግሽው ?” በማለት መውጫ መግቢያ ያሳጣታል። ይህ ሰው ሀሳቡን እንዲቀይር ደጋግማ ወትውታውም ነበር። በምንም የቃላት ጋጋታ የማስረዳት ሙከራ ሀሳቡን አልቀይር ይላል። በማይሆን ፍቅር ልቡ ታወረ። ሆኖም እንዲህ አይነት ሰው ሊያጋጥም ይችላል ብላ በማሰብ ነገር ግን እርሷ ላይ እንዲወርድላት ሽማግሌም ልካበት ነበር።
ሆኖም ግን ልቡም አይኑም ታውሯልና የፈለኩትን ነገር በሀይል ማድረግ እችላለሁ በሚል አስተሳሰብ የግድ የእኔ መሆን አለብሽ ካለበለዚያ ግን በሕይወት አትኖሪም በማለት ያስፈራራት ጀመር። ሁልጊዜ ስለሚፎክርና ስለሚዝት ከወሬ ያለፈ ጉዳት ያደርስብኛል የሚል ሀሳብ ተሰምቷት አያውቅም ነበር።
ያልታሰበው የጭካኔ በትር
ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም ከረፋዱ አምስት ሰአት ከሰላሳ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታው ሳባ ሕንፃ ውስጥ በሚገኘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ ፋይናንስ ቢሮ ውስጥ ወይዘሮ መዓዛ ካሳ የተለመደ ስራዋን በተለመደው ትጋት እያከነወነች ነበር።
ከዚህ ቀደም የፍቅር ጥያቄ አቅርቦላት ባለትዳር እንደሆነች የገለፀችለት አቶ ጌታቸው ዓለምፀሐይ ክፍሉ ኮስተር ያለ ፊት በማሳየት ወደ እሷ አቅጣጫ ሲመጣ ተመለከተችው። ሆኖም እንደተለመደው ተናግሮ ዝቶና አስፈራረቶ ይሄዳል በሚል መንፈስ ዘና ብላ ተቀበለችው። ልክ እንደመጣ ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚጠይቃትና የፍቅር ጓደኛው ካልሆነች እንደሚገላት በቁጣ ነገራት። እሷ ደግሞ ባለትዳር እንደሆነችና የፍቅር ጥያቄውን መቀበል እንደማትችል ቁርጥ ባለ አማርኛ መለሰች። ይህንን አስረግጣ ብትገልጽለትም የግድ አብረው መሆን እንዳለባቸው ይወተውታታል። ምንም ለወጥ ለሌለው ሀሳብ ጊዜውን ማጥፋት እንደማይኖርበት ተናግራ ፊቷን ወደ ስራዋ መለስ አደረገች።
በቢሮው ውስጥ የነበሩ ሰዎችም የተለመደው ጭቅጭቃቸው ነው በሚል ለጉዳዩ ቁብ ሳይሰጡት ስራቸውን ያከናውናሉ።
ወይዘሮ መዓዛ ለፍቅር ጥያቄው ፈቃደኛ የማትሆን እንደሆነ የተረዳው አቶ ጌታቸው “ለምን ጥያቄዬን አልተቀበለችኝም?” በሚል ምክንያት ከዚህ በፊት እንደዛተው በጎኑ ደብቆ የያዘውን ቢላዋ በማውጣት በሥራ ገበታዋ ላይ እያለች ያባርራታል። ቢላዋ አውጥቶ እያባረራት ያለውን ሰው ለማምለጥ ከቢሮ ወጥታ ስትሮጥ ፍርሃት ያስተሳሰረው እግራ ተጠላልፎ ደረጃ ላይ ወደቀች።
በወደቀችበት ቀና ብላ በተማፅኖ አይን ተመለከተችው። እንዲተዋትም በፍርሃት ድምፅ ተማፀነችው። የተማፅኖዋን ድምፅ ከምንም ያልቆጠረው ይህ ሰው ምንም አይነት ርህራሄ ሳያሳይ በቀኝ እና በግራ ሆዷ ላይ ደጋግሞ በመውጋት የሆድ ዕቃዋ ወደ ውጭ ወጥቶ ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደርጋል።
ይህ ጉዳይ ይፈፀማል ብለው ያልጠረጠሩትም የስራ ባልደረቦች ሩጫውን ተከትለው የወደቀችበት ቢደርሱም ከጥቃቱ ሊያስጥሏት ሳይችሉ ይቀራሉ።
ይህን በማድረጉ እርካታ የተሰማው የሚመስለው ገዳይ ብዙም ሳያንገራግር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይውላል። በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ምንም አይነት የጥፋተኝነት መንፈስ ፊቱ ላይ እንዳልተነበበ በወቅቱ የነበሩት ሰዎች ይናገራሉ።
ግማሽ አካሉን በግፍ የተነጠቀው ባል
የወይዘሮ መአዛ ባል በሰላም ደህና ዋይ ብሎ ጉንጫን ስሞ የተለያትን የባለቤቱን ሞት የሰማው በስልክ ነበር። መጀመሪያ ሲሰማ ቀለድ መስሎት ነበር። ባለቤቱ መጎዳቷንና ሆስፒታል መሆኗን የነገረው ፖለስ እንዲረጋጋ አድርጎ የተፈጠረውን ሲያስረዳው የሰማውን ባለማመን ሰሜት እራሱን ስቶ ወደቀ። ከወደቀበት ደጋግፈው ያነሱት ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ሆስፒታል ሲደርስ ያች የዋህ ደግ የቤቱ ዋልታና ማገር ሚሰቱ ዳግም ላትመለስ አሸልባለች። ወጥታ እስከምትገባ የማታምነውን ቤቷን፤ ፍቅሯ ከእለት እለት የማይነጥፈውን ባሏን፤ በስስት በሙሉ አይኗ አይታቸው የማታውቃቸውን ልጆቿን እንደዋዛ በትና አለፈች።
ወደ እእምሮው ብዙ ሀሳብ መጣ የልጆቹን ሁኔታ አሰቦ እሷ የደፈነችው ትልቅ የቤት ሽንቁር ተከፍቶ ታየው። በሀዘን ተንቀጠቀጠ፤ የሚይዘው የሚጨብጠውን አጣ። እንባ የሀዘን መብዛት የሚመልሳት ቢሆን የባለቤቷ ሀዘን ብቻውን ከሞት መንጋጋ ፈልቅቆ ያስቀራት ነበር።
ያች የንጋት ፀሐይ ባለቤቱን፤ ያችን አብሮ አደግ እህቱን፤ የልጆቹን እናት ግማሽ አካሉን ያሳጠውን ሰው ምን ቢያደርገው መርካት እንደሚችል አያውቅም። ሀዘን የቦረቦረውን አንጀቱን አስሮ ከአይኗ ስር ልታጣቸው የማትፈልጋቸውን ልጆቿን እናትም አባትም እንደያጡ አቅሉን ሰብሰብ ማድረግ ጀመረ።
ምንም ይሁን ምን በወደድኩሽ ምክንያት የሚስቱን ሕይወት ያሳጠውን ሰው በህግ ፍትህ እንዲሰጠው እየተማፀነ ግራ በተጋባ ስሜት ተቆራምዷል። “ፍትህ ይሰጠኝ ፤ ህግ ይፍረደኝ….” እያለ ማንባቱን ማቆም ተስኖታል።
የፖሊስ ምርመራ
የተበዳዮችን እንባ ለማበስ ከህግ የበለጠ መቅጣት ማነጽ ማስተማር የሚችል የለምና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይህን አሰቃቂ ወንጀል የፈፀመውን ሰው በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ለዚህ ተግባር መንስኤ ያለውን በምርመራ አጣርቶ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በከባድ የሰው መግደል ወንጀል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦበታል።
በምርመራ ወቅት “የወደድኩሽ ጥያቄ አቀረብኩላት፤ እንቢ አለችኝ ገደልኳት” በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን የሰጠው ተከሳሽ በፖለስ ቁጥጥር ስር ሆኖ በምርመራ ላይ እያለ ከእስር ያመልጣል። ይህ ሰው ከባድና ዘግናኝ አሰቃቂ ወንጀል ፈፅሞ እንኳን ጸጸት አልተሰማውም ነበር። በጭካኔ የፈፀመው ወንጀል ሳይበቃው አሁንም ከአስር ቤት አምልጦ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ያስቻለው ጉዳይ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ በልባቸው የያዙት ፖሊሶች ባላሰቡት አጋጣሚ ከእጃቸው የወጣውን ወንጀለኛ ማፈላለግ ቀጠሉ። ምንም እንኳን በተከሳሹ ላይ የተደረገው ምርመራ ተጠናቆ ጥፋተኛ የሚያስብል ውሳኔ እንዲወሰነበት መዝገቡ ወደ አቃቤ ህግ ቢላክም ተከሳሹን ማግኘት አልተቻለም ነበር። ይሄ ተፈላጊ ወንጀለኛ በማምለጡ ምክንያት ክሱ በሌለበት እንዲታይ ተደርጓል።
ተከሳሹ ሆነ ብሎ የተሰወረ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በሚያሰማበት ጊዜ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ የመጠየቅ እና የመመርመር መብቱ ታልፎ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ማስረጃ በበቂ ሁኔታ ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመ መሆኑን አስረድቶ ውሳኔ ተሰጥቶት በተገኘበት እንዲያዝ ማዘዣ እንዲወጣ ጠይቋል።
ወንጀል ሰርቶ በሰላም መኖር የማይቻል መሆኑን ለማሳያ ፖሊስ ሌት ከቀን ባደረገው አሰሳ ከእስር ቤት ያመለጠውን ወንጀለኛ አድራሻውን በመቀያየር የተለያዩ የከተማይቱ ክፍሎች ሲዘዋወር ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጠቆማ መሰረት እግር በእግር ተከታትሎ ለፍርድ ሊያቀርበው ችሏል።
ውሳኔ
ወንጀለኛው ያልተገኘ በመሆኑ እንዲሁም መብቱን ጠብቆ የዐቃቤ ሕግን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበለ በመሆኑ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል። ይህ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ ወንጀለኛው በፖሊስ ቁጥጥር ስር በመዋሉ ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ውሳኔው ተፈፃሚ እንዲደረግ ብይን ተሰጥቷል። መዝገቡ ተዘግቶም ወደ መዝገብ ቤት ተልኳል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014