በብሔርና በሃይማኖት ስር የተጠለሉ ነገር ግን ሃይማኖት መርህም ሆነ የየትኛውም ብሔር ባህል ከሚያዘው በጎ ተግባር ውጭ አገራቸው ላይ የሚያሴሩ ተበራክተዋል:: በሃይማኖትና ብሔር ተጠልለው ስውር አጀንዳቸውን የሚያስፈፅሙ፤ ከእምነቱ አልያም ብሔሩ ጋር ፈፅሞ የሚቃረን ተግባር ላይ የሚገኙ ናቸው:: ከላይ ሲታዩ የመጠሊያዎቹ ዋንኛ ጠባቂ ይመስላሉ:: ከእነሱ በላይ ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ ከእነሱ በላይ ለብሔራቸው ተሟጋች ፈፅሞ ያለ አይመስልም::
ነገር ግን እነርሱ በዚያ ተሸሽገው እኩይ ተግባር የሆነ አላማቸውን ያስፈፅማሉ:: አገር ላይ ያሴራሉ፣ ህዝብን ይከፋፍላሉ፣ በማስመሰል የተካኑ ናቸውና በለበጣቸው ከህዝብ ያገኙት ድጋፍ ተመርኩዘው ህገወጥነትን ያንሰራፋሉ:: እነዚህ በሁለቱ ጥላዎች ስር ተጠልለው አገርን የሚያምሱ አስመሳይ የመጋረጃ ጀርባ ተዋናዮች ተው ልንላቸው ይገባል::
በብሔር አልያም በሃይማኖት ለእነሱ መጠቀሚያ ብቻ ናቸው:: በእርግጥ አንድም ሊሆኑ አይችሉም:: አማኝ መስሎ በእምነት ጥላ ስር ያደባው ተው ተግባርህ ትክክል አይደለም ሲባል “እምነቴ ምናምን ስለሆነ ነው” የሚል መሸፈኛ ያቀርባል:: የብሔረሰብ ተቆርቋሪ መስሎ ተንኮል የሚሸርበው ስራህ ህገ ወጥ ነው:: ሲባል “ብሔሬ እንዲያ ስለሆነ ነው፤ የተወነጀልኩት” የሚል ውሃ የማያነሳ ምክንያት ይደረድራል:: እነዚህ ጉዶች ሃይማኖት አልያም ብሔር ለማስመሰል የሚጠለሉባቸው እንጂ ከእነሱ ተግባር ጋር አይታረቁም::
ዛሬ ኢትዮጵያችን ከውስጥና ከውጭ ኢትዮጵያ ሆና እንዳትቆም በሚፈልጉ አካላት ሴራ ተወጥራለች:: አገራችን ከምንጊዜውም በላቀ የዜጎችዋ አብሮነት የልጆችዋ ተገንነት የምትፈልግበት ወቅት ላይ ነች:: ታዲያ በዚህ ሁሉ ትግልና ወሳኝ ወቅት ነው፤ እነዚህ አስመሳዮች አገር ላይ ደባ የሚፈጽሙት:: በራሱ ውስጣዊ መሻት ላይ የተመረኮዘ እኩይ ምግባሩን ለመወጣት በመጋረጃ ተሰውሮ ደባ ይሰራል:: ይህ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ ሊጋርጡ ከሚያስቡ የውጭ ጠላት ጋር የሚደረግ ስውር ተልዕኮ ማሳያ ነው::
በነገራችን ላይ እነዚህ የመጋረጃው ጀርባ ሴረኞች የቆሙት ለህዝብ አልያም ለእምነት ነፃነት አይደለም:: ብዙውን ጊዜ እነዚህ ውስጥ ውስጡን የሚያሴሩት ከባዕድ የተቀበሉትን ተልዕኮ ለማስፈፀም ነው:: ስለምን ጓዳ ጎድጓዳችን ሊበረብር ለመጣ ጠላት ማንነታችንን አንትቦ ያለንን ቀምቶ ለሚሄድ ባዕድ ዓላማ መሳካት የአገር ልጅ በአገሩ ላይ ሊያሴር ይቻለዋል:: ዛሬ ላይ ይህቺን ታላቅ አገር አገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እልህ አስጨራሽ ትግል የሚያደረጉት ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንን ተግባር የሚያንኳስሱ ትናንሽ ኢትዮጵያዊያን በርክተዋል::
በዚህች ታላቅ አገር የሚኖሩ ትንንሽ ሀሳብ አራማጆች የኔ በሚሉዋቸው ብሔሮቻቸው ስር ተጠግተው አገር የማያሻግር ሀሳብ ይወረውራሉ:: ህዝብን የሚያጋጭ፤ አብሮነትን የሚንድ አሳሳች መረጃ ያቀብላሉ:: ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን እኩይ ተግባር ይከውናሉ::
የሌላኛው አስመሳይ መመሸጊያ ደግሞ ወዲህ ነው:: ህዝብ የሚሳሳላቸው እምነት ተቋማት:: ጅማሮው ላይ አማኞችን እናንተ ብሩህ ናችሁ፤ እምነታችሁም ከሁሉ የላቀ ብሎ ይቀርብና ለስውር አላማው ያመቻቻል:: ቀስ በቀስ ለራሱ ዓላማና ግብ ማሳኪያ ይሆነው ዘንድ በማስመሰል የተንጠላጠለበትን መሰላል ይጠቀማል:: ከእምነትና አምልኮ ውጭ የራሱን ዓላማ በስውር ያራምዳል::
የዚህ አይነቱ አስመሳይ የእምነት ጥላ ተንተርሶ የሌላውን እምነት በግልፅ ያነውራል:: ሌሎች አማኞችን ያጥላላል:: አንዱ አማኝ በሌላው ላይ እንዲነሳ ያደርጋል:: በጎነት የሚሰብከው እምነቱ በጥላቻ ይሞላዋል:: ይህ ለሴራው ይሆነው ዘንድ ሌላውን የሚሰድብ የሚያንቋሽሽና አስተምሮትን በተሳሳተ መልኩ የሚያራምድ የጥላው ስር ሴረኛ ነው::
ኢትዮጵያ ከሁልጊዜ በተለየ መልኩ መፀንታ መቆም በሚገባት በዚህ ጊዜ፤ ከብሔርና ሃይማኖት ጥላ ስር ያሉ እነዚህ ሴረኞች ትልቅ ፈተና ናቸው:: በዚህ ወሳኝ ጊዜ እንኳን የሚፈልጉትን ከማድረግ አይቆጠቡም:: ህዝብን ባልረባ ነገር ከመከፋፈል ምዕመናን በትክክል ወደ አምላካቸው ተጠግተው ስለ አገራቸው ሰላም እንዲፀልዩ(ዱዓ) እንዲያደርጉ እድል ከመስጠት ይልቅ በሸረቡት ሴራ አማኝና እምነትን ፈተና ውስጥ ይጥላሉ::
እነዚህ የአገር ጠላቶች በግርግሩ ይበልጥ ላደናግር ያሉ ይመስላል:: አገራቸው ከሌለች፣ ነፃነትዋ ከተደፈረ፣ ማንነትዋ ከተናደ የተጠለሉበት ብሔርም ይሁን ሃይማኖት ነፃነት የሌላቸው መሆኑ እንኳን አልተረዱም:: እምነቱ ተጠግቶ የእኛ እምነት በሌሎች እየተበደለ ነው ብለው አማኙን ያሳምኑታል፤ ብሔሩን የተጠጋው ደግሞ እኛ የምንበደለው እገሌ በመሆናችን ነው ብለው ያሳምፁታል::
እነዚህ ተጠላዮች ወይም አስመሳዮች በአማኞቹ ቶሎ አይለዩም:: ስለዚህም ሳይታወቁ ከፍ ያለ ጉዳት በህዝብ ብሎም በአገር ላይ ያደርሳሉ:: አስጠላዮቹም ወይም የተጠለሉበት ሃይማኖትም ሆነ የኔ ብለው ለዓላማቸው መሳኪያ የተለጠፉባቸው ብሔራቸው በእነዚሁ እጅጉን ይጎዳሉ፤ በሴራው ይጠቃሉ:: አንዴ አይናችን ገልጠን ብናያቸው ጥላውን ገፈን ማንነታቸው ብንመረምረው እነዚህ የጥላው ስር ሴረኞች ባዶነታቸውን በተረዳን ነበር::
ፈፅሞ ለብሔራቸው መብት የማይሰሩ መሆናቸው፤ ለእምነታቸው ያላደሩ አስመሳይ እንደሆኑ ፍንትው ብሎ በታየንም ነበር:: ይሄ ግን ጊዜ ይጠይቃል:: በተለይ በዚህ አገር በጠላት ተከባ ፈተናዎችዋ በዝተው ሁሉም በስሜት በሚፈርድበት ጊዜ ሜዳው ይመቻቸዋልና እውነት የያዙት አስመሳዮቹ ብቻ ይመስላሉ:: የተደበቁበት ታላቅ እምነት ወይም ብሔር ለእነሱ መከታ ለስውር ሀሳባቸው መደበቂያ ይሆናልና:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሁሉ ከፍ የምትል፤ ዘመንን የምትሻገር መሆንዋን አልተረዱም::
ህዝብ ቆም ብሎ እነዚህ ማጋለጥና ተው ሊላቸው ይገባል:: የሚነግሩትን ሰምቶ ለምን? ብሎ ማስላት እንዴት ብሎ መመርመር ይገባዋል:: አማኝ ለእምነቱ ያደረ መልካም ነገርን አብዝቶ የሚተገብር ከወገኖቹ ጋር በፍቅር ያለውን የሚጋራ ሆኖ ሳለ፤ ስለምን? የሌሎችን እምነት ያንቋሽሻል? ለምንስ መልካም ነገር ከመስበክ ይልቅ የሌላው እምነት ተከታይ እየሰደበና በሌላው ላይ እየተሳለቀ ከአምላኩ ትዕዛዝ ተቃርኖ ይቆማል? አዎን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ይገባል::
እምነት በበጎ የሚያዝ ከመጥፎ ነገር የሚከለክል ሆኖ ሳለ ለሌሎች መጥፎ ሁኑ ሊል አይችልም:: ይሄኔ አማኙ መመርመር ይገባዋል:: አስመሳዩ ግን አማኝ ነኝ ብሎ፤ በእምነት ጥላ የተሸሸገ እንጂ በአምላካዊ በጎ ተግባር የታነፀ የእምነቱን ቀኖና የሚያከብር ለሰው ልጆች በጎ የሆነ አስተሳሰብ የለውም:: በሃይማኖት ጥላ ስር የራሱን ድብቅ አላማ ማስፈፀም ነው ግቡ:: በብሔሩ ተሸሽጎ ለድብቅ አላማው የሚያላዝነውም እንዲሁ::
የሁሉም እምነቶች መሰረት በጎነት የአማኞች ተግባርም መልካምነት ለሰው ልጆች ምቹ መሆንን ማስተማር ነው:: ለአገር አብሮ መቆም ለወገን ችግር መድረስ ተደጋግፎም ክፉን ጊዜ መሻገር እንደሚገባ መስበክ ነው ዋንኛ ግቡ:: ስለዚህም ነው በዚህ በጎ ጥላ ስር ያለውን መሰሪ መለየት የሚገባው::
ልክ እንደ እምነቱ ሁሉ በብሔሩ ጥላ ስር ያደሩ ለብሔሬ ተቆርቋሪ ነኝ፤ ለህብረተሰቤ ተሟጋች ብለው እራሳቸውን እላይ የሰቀሉ አስመሳዮች አሉ:: ተቆርቋሪ መሳይ ነገር ግን የተጠለሉበትን ብሔረሰብ የማይመስሉ ለእርሱም እውነተኛ አርነት የማይሰሩ መሆናቸው ነው ከባዱ ነገር:: ስለማህበረሰቡ የሚጨነቅ ስለወገኑ የሚቆረቆር ቂምና ጥላቻን በሌላው ላይ አይሰብክም::
ማህበረሰቡ ባህልና ወጉ በሌላው እንዲከበር የሌላን ማህበረሰብ ባህልና ወግ ማክበር ወሳኝ መሆኑን ይረዳል:: እነዚህ ተጠላዮች ግን ወከልንህ አልያም እኔ ለአንተ ቆምኩልህ ይበሉት እንጂ ተግባርና አካሄዳቸው ሁሉ ማህበረሰቡን ለእንግልት የሚዳርጉ የአብሮነት እሴቱን የሚሸረሽሩ የአገር ህልውናም የሚያናጉ ናቸው::
እነዚህ የሁለቱ ጥላ ስር ሴረኞች ዓላማ ግልፅ ነው:: የራሳቸውን እኩይ ዓላማ በተጠለሉበት ማንነት ውስጥ በመሰወር ማስፈፀም ነው:: ለእነዚህ መድኃኒት ደግሞ እኛ አንድ ሆነን ቆመን አንድነታችን ሊንድ እኛን መስሎ የሚቀርበንን ተው ማለት ነው:: በአገራችን ህልውና ላይ አደጋ ሊጥል የሚያሴርን መዋጋት እንደ ዜጋ የሁላችን ኃላፊነት መሆን ይገባዋል::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 /2014