የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአራት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎችን፤ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚያካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመርጥ ይታወቃል፡፡ ክልሎችም ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩ ሦስት ዕጩዎችንና 26 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ቀጣዮቹን ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ፌዴሬሽኑን የሚመሩት ዕጩዎች ቢመረጡ ስለሚያከናውኗቸው ሥራዎች ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡
ያለፉትን አመታት ፌዴሬሽኑን የመሩት አቶ ኢሳያስ ጂራ ስፖርቱን በድጋሚ ለማገልገል በድጋሚ ከክልላቸው ውክልና ያገኙ ሲሆን፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥትን በመወከልም የቀረቡት አቶ መላኩ ፈንታ ቢመጡ በፌዴሬሽኑ ስለሚያመጧቸው ለውጦች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን የወከሉት አቶ ቶኪቻ አለማየሁም በፕሬዚዳንትነት ቢመረጡ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ክልሎች ላይ ትኩረት ማድረግና ተጣምሮ መስራት እንዳለበት የገለጹት አቶ ቶኪቻ፣ ክልሎች የተጫዋቾች፣ የደጋፊዎች፣ የዳኞች እና የሌሎች ግብዓቶች ምንጮች እንደመሆናቸው ወደ 120 ሚሊዮን የተጠጋውን ሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ኃላፊነቶች ተከፋፍለው በጋራ መስራት የግድ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም ክልሎች ወደ ፌዴሬሽን የሚልኳቸውም ሆነ የሚቀጥሯቸው ሰዎች እግርኳሱን የተረዱ መሆን አለባቸው ይላሉ። ይህ ካልሆነ ግን ደካማ የክልል ፌዴሬሽኖች ባሉበት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላይ
ጠንካራ ሰው ቢኖር ዋጋ እንደማይኖረው ገልጸዋል። አሁን ባለው አወቃቀር የክልል ፌዴሬሽኖች በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላይ እምብዛም ደስተኛ አለመሆናቸውን እንዲሁም ከኃላፊነት አሰጣጥ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቅሬታ እንዳላቸው ካነጋገሯቸው የክልል ፌዴሬሽኖች መረዳታቸውንም አቶ ቶኪቻ ይጠቅሳሉ። ስለዚህም ይህን ጉዳይ በቅድሚያ መፍታትና አሠራሩንም ለመለወጥ እንደሚሠሩም ነው ያረጋገጡት።
ከፌዴሬሽኑ የገቢ ምንጭና ራስን ከመቻል አንጻርም ሊሠሩ ያቀዱትን በተመሳሳይ አንጸባርቀዋል፡፡ እግርኳሱን በገቢ ለማሳደግ መሠረታዊው ጉዳይ እግርኳሱ አሁን ባለበት ሁኔታ መሸጥ መቻል አለበት፤ ይህ ደግሞ ለውጭ አገራት ሳይሆን በቅድሚያ ለአገር ውስጥ መሸጥ አለበት ይህን የሚያደርገው ደግሞ ደጋፊ እና ጋዜጠኛ ነው። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በአገሪቷ ውስጥ የሚገኙ አቅም ያላቸው ትልልቅ ተቋማት ክለቦችን እንዲይዙ መጋበዝ እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡ ፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለውጥ ለማምጣት የመዋቅር ለውጥ ካስፈለገ አጥንቶ ተግባራዊ በማድረግ ወይንም ያለውን ሠራተኛ በማብቃት የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት አብራርተዋል።
በእግር ኳሱ በቂ መዋዕለ ንዋይ መፍጠር እንዳልተቻለ የሚያነሱት አቶ ቶኪቻ፤ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ፌዴሬሽኖቹ አሁንም ድረስ መንግሥት ላይ የተለጠፉ መሆናቸውን ማሳያ አድርገዋል። ለአብነት ያህልም የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ስታዲየም ካልገነቡ በቀር ስታዲየም መሥራት አይችሉም ብለዋል። ነገር ግን በፌዴራል ደረጃ ስታዲየም ቢገነባላቸውና ጠንካራ የክልል ፌዴሬሽኖችን መፍጠር ከተቻለ ከክልል ስፖርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ሌሎች ስታዲየሞችን ለአህጉራዊ ውድድር የሚያበቁ ሥራዎችን መሥራት ይችላሉ ባይ ናቸው።
ከስታዲየሞች ባሻገር በየክልሉ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የሚሆኑ የታዳጊ ማዕከላትም አስፈላጊ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ቶኪቻ፣ የተመረጡ ታዳጊዎች ገና ከስምንት ዓመታቸው አንስቶ በተጠና የጨዋታ መንገድ፣ በአመጋገብ ሆነ በሌሎች ሳይሳንዊ መንገዶች የተደገፉ ስልጠናዎችን ሊያገኙ እንደሚገባ አስረድተዋል። «እግርኳሱ እስካሁን በቂ ገንዘብ እየፈጠረ አይደለም፤ እንደ ሌሎች አገራት የኢትዮጵያ እግርኳስም ይህን የመፍጠር አቅም አለው፡፡ ታዳጊ ተጫዋቾች በብዛት መፍራት አለባቸው የትምህርት ቤቶች ውድድሮችም በተጠናከረ መልኩ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተመልሰው መካሄድ ይኖርባቸዋል። እግርኳስ ለመጫወት ምቹ ባልሆኑ ክልሎች ላይ እንደየአካባቢው ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ ውድድሮች መካሄድ አለባቸው። በተጨማሪም ስፖርቱን ይበልጥ ለማነቃቃት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ክለቦች መቋቋም ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ መደረግ ይኖርባቸዋል» በማለትም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግርኳስ ማህበር መስራች ትሁን እንጂ፤ አሁን ላይ በቂ ውክልና የሌላት መሆኑን ተከትሎ በዚህ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሠሩበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ «በተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያውያን በኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛል። በእግርኳሱም ይህን ከማድረግ የሚከለክል የለም። ኢትዮጵያውያን ካፍ ውስጥ በአመራርነት ከሌሉ ተጠቃሚነታቸውም ይቀንሳል። ስለዚህ ይህን በህብረት በመሆን ሌሎች አገራትን ማግባባት ያስፈልጋል፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ላለው አገር በካፍ ውክልና አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው። በሕዝብ ቁጥር ንጽጽር አነስተኛ የሆነችው ጅቡቲ እንኳን የተሻለ ውክልና አላት። በካፍም ሆነ በፊፋ በኃላፊነት ማገልገል የሚችሉ ሰዎች አሉ» በመሆኑም እነሱን ወደ ፊት ማምጣት ተገቢ እንደሚሆንም ፕሬዚዳንታዊ ዕጩው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ ለካፍ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ቃል ገብተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 /2014