ታላቁ የህዳሴ ግድብ በህዝብ ተሳትፎ እውን እየሆነ የሚገኝ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። የዚህ ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይም ከተጣለ እነሆ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥም ግንባታው 66.26 ከመቶ ደርሷል። ለፕሮጀክቱ እውን መሆን እስካሁን የነበረው የህዝብ ተሳትፎም የላቀ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀዛቀዞች እንዳሉ ይነሳልና ባጋጠሙ ችግሮች ቀጣይ መፍትሔዎች ላይ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ መቀዛቀዝ ተስተውሎበታል የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ይደመጣልና በአሁኑ ወቅት ሕዝባዊው ተሳትፎ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ወይዘሮ ሮማን፡- መቀዛቀዝ አለ በሚል የተነሳው ዕውነት ነው። እርግጥ ነው ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም የነበረው ሕዝባዊ ተሳትፎ የተጋጋለና ብሔራዊ መግባባቱም ከፍተኛ እንደነበር ይታወቃል። ገቢ ማሰባሰቡም የብሔራዊ መግባባቱ ውጤት ነው። በዚህም በባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ማግኘት ተችሎ ነበር። በዘንድሮ ዓመት ደግሞ ከግድቡ የማመንጫ ጊዜ ከታሰበለት ጊዜ ወደኋላ መቅረትና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥራዎች መዘግየትን አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተሠጠው መግለጫ ሕዝቡን ለቁጣ ዳርጓል።
በተለይ መጀመሪያ ግድቡ ትልቅ ችግር እንደደረሰበት ምናልባትም እንደገና የመሥራት ያክል የሚመስል ምንም አዎንታዊና ሚዛናዊ ያልሆኑ ዘገባዎች በመገናኛ ብዙኃን መሰንዘሩ ህብረተሰቡ ግድቡ እንዲጠናቀቅና የሚጠበቁ ትሩፋቶች ዕውን እንዲሆኑ አጥብቆ በመሻቱ ለምን እንዲህ ይሆናል? የሚል መንፈስን ፈጥሮበታል። ይህም በሕዝባዊ ንቅናቄው ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ የባለቤትነት ደረጃ እንዳደርሰው ያሳያል። ጠያቂ መሆኑና እክሎች ሲመለከት ቁጣውን ማሳየቱ የሚጠበቅ ነው በሚልም ነው የተወሰደው። ይህንን መነሻ በማድረግም ዳሰሳ ጥናት አድርገን ነበር።
ከፍተኛ የቁጣ መንፈስ ባለበት ወቅት በተደረገው ዳሰሳ ጥናት ሕብረተሰቡ የሰጠው ምላሽ ግድቡ
መጠናቀቅ እንዳለበት የሚያሳይ ትልቅ ቁምነገርን ያዘለ ሆኖ ተገኝቷል። በወቅቱ ሕዝቡ በተለያየ መንገድ የሚያደርገው ድጋፍ መቀጠል አለበት ወይ? የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር። በዚህም 45 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው የሕብረተሰብ ክፍል አዎ መደገፍ አለበት የሚል ምላሽ ሰጥቷል። በድጋፉ መደረግ የሚያምኑት እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ችግር እንደገጠመ እናውቃለን፤ ግድቡም ዘግይቷል። ነገር ግን ምንም ችግር ቢገጥመውም መቀጠል ይኖርብናል›› ብለዋል።
የተቀሩት ደግሞ ግድቡ መገንባት አለበት እኛ ግን ምንም ድጋፍ አናደርግም የሚሉ ናቸው። በዚህም በመገናኛ ብዙኃኑ በነበረው ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ የተነሳም ‹‹ያደረግነው አስተዋጽኦ ባልተገባ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ እኛ አንቀጥልም መንግሥት ይቀጥልበት›› የሚለው ምላሽ ከፍተኛ ቁጥርን ይዟል። ሁለቱም ወገን ግድቡ ሕብረተሰቡ ባለቤት ሆኖ የሠራው እንደሆነ፣ በገጠመው ችግር እንደተቆጣ፣ ግን ደግሞ ማለቅ እንዳለበት እንደሚያምኑ ግን በምላሻቸው ማረጋገጥ ተችሏል። በማለቁ ላይም ልዩነት የላቸውም።
የዘንድሮ ሥራችንም ዳሰሳ ጥናቱን መሠረት በማድረግ የተቀዛቀዘው መንፈስ ለመቀየርና የሕብረተሰቡን አመኔታ ወደነበረበት ለመመለስ ያቀደ ነው። በዚህ መሠረት እስካሁን ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ተሳታፊ የሆኑባቸው የተለያዩ ሰፋፊ መድረኮች ተዘጋጅተዋል። መጀመሪያ የተደረገውም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የኤክትሪክ ኃይል በጋራ በመሆን ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሕዝባዊ አደረጃጀቶች፣ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ አካላትንና መሰል ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚሠሩ መሥሪያ ቤቶች ተቋማቱ በሠጡት ሰፊ መግለጫዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ጽሕፈት ቤቱ በመገናኛ ብዙኃኑ ተላልፈው በሕብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያስነሱና አመኔታውን የሸረሸሩ ጉዳዮችን መመለስ የሚያስችሉ መሰል መድረኮችን በስፋት የመፍጠር ሥራውንም አጠናክሮ እየሠራ ይገኛል። ሕዝብ አቅፈው የሚገኙ ሰፋፊ አደረጃጀቶች ጋር ሁሉ መድረኮች ተፈጥረዋል። ‹‹እንቀጥላለን!›› የሚሉ ሃሳቦችም ተገኝተዋል። በስብሰባው ላይም የአገሪቱን ሥልጣኔ የዳሰሰ፣ የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት አጉልቶ የሚያሳይና ካለፉት ችግሮች በመነሳት ግድቡ መጠናቀቅ እንዳለበት የሚያሳይ በአንድ ሰዓሊ የተሠራ የኪነጥበብ ሥራ ተበርክቷል። ከዲያስፖራ ጋር በነበረው መድረክም አንድ ግለሰብ ገቢ እንዴት ማሰባሰብ እንደሚቻል ፕሮጀክት ቀርፀው አቅርበዋል። ከዛም በኋላ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በተገኙበት መድረኮች ተካሂደዋል።
በየደረጃው ያለ አመራር ይህንን በሚገባ ደግፎ መንቀሳቀስ ይኖርበታል የሚል አቋም ተቀምጦበታል። ይህንን መሠረት በማድረግ በትኩረት እየሠራን ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት 484 ሚሊየን ብር ማሰባሰብ ተችሏል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በጣሙን አነስተኛ ቢሆንም ባለው ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ሕብረተሰቡ ድጋፉን እንዳላቋረጠ ግን ያመላክታል።
አዲስ ዘመን፡- በምላሽዎ እንደገለፁት በመገናኛ ብዙኃን ሲሠሩ የነበሩ ዘገባዎች የሕዝቡ ተሳትፎ ለመቀነሱ ዋነኛ መንስኤ ነው። ችግሩን ገምግማችሁታል ወይ? በምን መልኩስ ሊፈታ ይገባል ብላችሁ አቅጣጫ አስቀመጣችሁ?
ወይዘሮ ሮማን፡- መጀመሪያ የተሰጠው መግለጫ ሚዛናዊ ያልሆነ መግለጫ መሆኑን መገናኛ ብዙኃን ጋር በተፈጠረው መድረክ ውይይት ተደርጎ መግባባት ተደርሶበታል። በዚህ ብቻም ሳይሆን መገናኛ ብዙኃኑ ላይ በተለያዩ መንገዶች የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉም አይካድም። ይህንንም አቅርበናል። ከዚህ በኋላም እንዴት አድርገው ማረም እንደሚችሉና ሚናቸው ምን እንደሆነ ተግባብተናል። በመድረኮቹ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ መገናኛ ብዙኃኑ መልካም ተግባራትን ሲሠሩ እንደቆዩና ለብሔራዊ መግባባቱ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር በማንሳት ጎን ለጎን ደግሞ ችግሮችን ለይተናል።
እነዚህ ችግሮች ሲነሱም በወቅቱ ጽህፈት ቤቱ መረጃ የመስጠት ችግር እንደነበረበት አንስተዋል። በሩን ዝግ አድርጎ እንደነበር የተነሳበት ዋነኛ ምክንያትም እኛ መንግሥት ነን እንደ መንግሥት የተገለፀው ጉዳይ ምንድን ነው? በሚል ተረድተን ትክክለኛውን መረጃ አግኝተን መሄድ ስለነበረብን ነው። ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱም የገጠመው ችግር ምንድን ነው? እንዴትስ ነው የሚፈታው? በሚል ቀርቧል። በዚህም ችግሮቹ ተለይተው መፍትሔ ይሆን ዘንድ መንግሥት በጀት መድቧል። በተመሳሳይ አዳዲስ ኮንትራክተሮች በመቴክ ምትክ ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።
በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለቱም ተርባይኖች ማመንጨት እንዲጀምሩ ከዛም ደግሞ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የራሱ የሆነ በጀት እንደተመደበ ሁሉ ግልጽ አድርገናል። ስለዚህ መገናኛ ብዙኃን ከዚህ በኋላ ይህንን አስተካክለው እንዲቀጥሉ እየተደረገ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ግድቡን የተመለከቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
ፍዮሪ ተወልደ