ብርድ ብርድ ይለኝና እራሴን ለመቆጣጠር እስከ ማልችልበት ድረስ አቅም ያሳጣኛል።ድንገት ጉልበቴ ድክም ይልና ሰውነቴ ሁሉ ይዝላል። በነዚህ ምክንያቶች ብዙ ጊዜ በየሆስፒታሎቹ ተመላልሻለሁ። በግሌም መድሃኒቶችን እየገዛሁ እውጥ ነበር። ቢበዛ ለሦስት ቀን ሕመሙ ታገስ ይልልኝና እንደገና ደ ተመልሶ በሽታዬ ያገረሽብኛል። ቢቸግረኝ ለአንዱ የልብ ጓደኛዬ ነገርኩት። ለምን ኤች አይቪ አትመረመርም አለኝ፡፡
በወቅቱ የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ ይሰጥ የነበረው መቅድም ኢትዮጵያ ሄደና የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ በደሜ ውስጥ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚያስችለኝን ምርመራ አደረኩ።በእርግጥ ለበሽታው ተጋላጭ በመሆኔ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ ላይገኝ ይችላል የሚል ዕምነት አልነበረኝም።ሆኖም ያኔ የምርመራ ውጤት ወዲያው አይገለፅም ነበርና ተመርምሬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ።ይሄ ወቅት በፍፁም አይዘነጋኝም። ዓመተ ምህረቱ 1998 አካባቢ ሲሆን ወሩ ደግሞ የካቲት የሚባለው መዘዘኛ ወር ነበር።
ይህን ሁሉ ታሪክህን የምትዘረዝረው አንተ ማነህ ለምትሉኝ እያዩ አወቀ እባላለሁ። ዘንድሮ 48ኛ ዓመቴን ጨርሼ 49ንኛውን ለመቆናጠጥ ዳር ዳር እያልኩ ነው። ቫይረሱ በደሜ በመገኘቱ ምክንያት 16 አመታት በሙሉ ፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት እየወሰድኩ ኖርያለሁ።ከዚሁ ጎን ለጎንም ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ ትምህርት በመስጠት ላይ እገኛለሁ።በሕይወት እስከቆየሁ ድረስም ይሄው ሆኖ ነው የሚቀጥለው።ወጣትነቴን በጭንቀት ነው ያሳለፍኩት። ቢሆንም ብዙ ጓደኞቼ በቫይረሱ ምክንያት የገቡበት ጉድ ጓድ ከመግባት ድኜ ታሪኬን ለእናንተ ለማካፈል ያቆየኝን ፈጣሪዬን ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡
ወዳጆቼ ታሪኬ እንዲህ ነው። ተወልጄ ያደኩት በደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ ውስጥ ሲሆን መጠጥ የለመድኩት ገና በታዳጊነቴ ነው።ልማዴ የትምህርት ጊዜየን አባክኖብኛል።በመጠጡ ምክንያት ለትምህርት የምሰጠው ትኩረት በመቀነሱ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችለኝ ነጥብ አላመጣሁም።በዚህ ምክንያት ገና በአፍላ ዕድሜዬ ሥራ አጥ ሆንኩና የወላጆቼ ጡረተኛ ለመሆን ተገደድኩ፡፡
ይሄ ደግሞ በእጅጉ ተስፋ እንድቆርጥ አደረገኝ።በሱሱ የበለጠ እንድገፋበትና ዝሙተኛ እንድሆንም ምክንያት ሆነኝ።ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለመጠጣትም መሥራት ነበረብኝና ያገኘሁትን ሥራ እሰራ ነበር።በርካታ የጉልበት ሥራዎችን ስሰራ ቆይቻለሁ።ሁለትና አንድ ዓመት የሚቆዩና የሚያልቁ የፋብሪካ ሥራዎች እየሰራሁ እድሜን ስገፋ ቆይቻለሁ፡፡
1991 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ዘመዶቼ ጋር የመጣሁትም ይሄንኑ ሥራ ተማምኜ ነበር።ሥራውን ሰርቼ ብገባም ከዝሙተኛና ከጠጭነት የሚያወጣ የባህርይ ለውጥ አላደረኩም። አዘውትሬ የተለያዩ ሴት አዳሪዎች ጋር መሄድ፤ በጉልበትም ሆነ በሌላ ቦታ ካገኘኋቸው ሴቶች ጋር ወሲብ መፈፀሜን አጠናክሬ ቀጠልኩበት፡፡
ለሰባት ዓመታት በሰራሁበት በአንድ ፋብሪካ ውስጥ በጥበቃ ሥራ መቀጠሬና የወር ደሞዝተኛ መሆኔ ከድርጊቴ እንድቆጠብ ከማድረግ ይልቅ እንድገፋበት ሳያደርገኝ አልቀረም።በኤች አይቪ ቫይረስ ለመያዝ ምልክት የሆነው ሕመም የጀመረኝም እዚህ ፋብሪካ ውስጥ በጥበቃ ሥራ እሰራ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ አልዘነጋውም።የተለያዩ ምርመራዎችን አድርጌ መድሃኒት ብወስድም በሽታዬ አልታወቀም።የታወቀው በቅርብ በጓደኛዬ አማካኝነት በቀጥታ የኤች አይቪ/ኤድስ ምርመራ ካደረኩ በኋላ ነው።ይሄ ቀን በፍፁም አልዘነጋውም፡፡
ዕውነታው ምጠብቀውና በውስጤ ያለ ቢሆንም አምኜ ልቀበለው አልቻልኩም። ደጋግሜ በተለያዩ ቦታዎች የኤች አይቪ ኤድስ ምርመራ አደረኩ።ባይገርማችሁ ከሰባት ጊዜ በላይ ደጋግሜ ተመርምሪያለሁ።ግን ሁሉም ጋር ቫይረሱ በደሜ ውስጥ እንዳለ ነው የተነገረኝ።እንደምንም ራሴን አሳመንኩና በመጀመሪያ ቫይረሱ በደሜ ውስጥ መኖሩን ወደ አረጋገጠልኝ መቅድም ኢትዮጵያ ተመልሼ ሄድኩ።ህመሜም ተባብሶ ነበር።
ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሪፈር ላከኝ።ሆስፒታሉ የተለያዩ ምርመራዎችን አደረገልኝ። በምርመራው የቲቪ በሽታ ተገኘብኝ። ለ20 ተከታታይ ቀናት የቲቪ መድሃኒት ስወስድም ቆየሁ።ከዚህ በኋላም በቀጥታ ፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት መውሰድ ጀመርኩ።በበሽታው ሰውነቴ በጣም ተጎሳቁሎና አቅሜ ራሴን መቆጣጠር እስኪሳነኝ ድረስ ተጎድቶ ስለነበር ለሁለት ወራት ያህልም በመቅደም ኢትዮጵያ የሚሰጠውን ወተት እየጠጣሁ እንዲሁም ራሴን የተለያዩ ምግቦችን በመመገብ ሳገግም ቆየሁ።በዚህም ከሞት አፋፍ ላይ ተመልሼ ይሄው ዛሬ ላይ ታሪኬን ለእናንተ ለመንገር በቃሁ።
ክብር ይግባውና ለፈጣሪዬ አሁን ላይ በአንድ የኤች አይቪ ኤድስ ጥምረት ማዕከል ውስጥ በኬዝ ማናጀርነት እየሰራሁ የራሴ ገቢና ወራዊ ደሞዝ ተከፋይ ሆኜ ለመኖር በቅቻለሁ።እንደኔው ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ከሚገኝ ሴት ጋርም በትዳር ተጣምሪያለሁ። አንድ ልጅም ለመውለድ በቅተናል። ደስ የሚለው የወለድናት ልጅ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርገውን ሕክምና በአግባቡ ተከታትላና መድሃኒት ወስዳ ስለወለደቻት ከቫይረሱ ነፃ ነች፡፡
በመሆኑም ቫይረሱ በደማችን መኖሩ በሕይወታችን ላይ እንቅፋት ሳይሆንብንና ተፅዕኖ ሳያደርግብን እንደማንኛውም ሰው በሰላም እየኖርን እንገኛለን።ቫይረሱ በደማችን በመኖሩም የቀረብን ነገር የለም።ዕድሜ ለፀረ ኤች አይቪ መድሃትና እኛም ቫይረሱ በደሙ ከሌለው የሕብረተሰብ ክፍል እኩል እንኖራለን።እኛ ቫይረሱ በደማችን ውስጥ የሚገኝ ወገኖች ቫይረሱ በደሙ ከሌለበት የሕብረተሰብ ክፍል የምንለይበት አንድ ነገር እንዳለ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ።እሱም የምንኖረው ለሌሎች ጭምር መሆኑ ነው።እናም አሁን ላይ በዙርያዬ ያሉት ወዳጆቼና ብዙ ሰዎች መድሃኒት ባልተገኘለት በኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ እንዳይያዙ እያደረኩ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ።በመጨረሻም ከጤና በላይ ምንም ነገር የለምና ጤናችሁን ጠብቁ በማለት ሃሳቤን እቋጫለሁ፡፡