ዝናብና ብርድ ያንገበገባቸው የመጠጥ ቤቱ ደንበኞች ከምሽት ሱሰኞቹ ውጭ ሁሉም ወደየቤቱ በመግባቱ ግሮሰሪው ጭር ብሏል። ብዙም መጠጥ ቤት የማያዘወትረው ገብረየስ ገብረአምላክ ግን ከስድስቱ ሱሰኛ ጠጪዎች ተነጥሎ ጥግ ይዞ የጠርሙሱን ቢራ ብርጭቆ ላይ እየቀዳ እየተጎነጨ ይተክዛል። አካሉ እዛ ቢሆንም በሃሳብ ርቆ ሔዷል። ክልሎችን አቋርጦ ነጉዳል። ጭንቀቱን ፊቱ ያሳብቅበታል። አይኑን ቡዝዝ አድርጎ አንዴ ወደመሬት ፤ አንዴ ወደጣሪያው ያያል።
አይኑ ቢፈጥም እየተመለከተ ግን አይደለም፤ እያስተዋለም አይደለም። እያሰበ ያለው ጨካኞቹ ጭራቆች የተረፉለትን ጥቂት ዘመዶችን ሳያስቀሩ ሁሉንም በጦርነት ለማስፈጀት ነጋሪት እየጎሰሙ መሆኑን በመስማቱ ተሳቅቋል። ‹‹የነብር ዓይን ከፍየል፤ የፍየል ዓይን ከቅጠል እንደሚባለው ማንኛውም ፍጡር በሚወደው ላይ ያተኩራል። እነርሱ ድሎት እና ስልጣን ይወዳሉ። ከስልጣን ልነቅንቃችሁ የሚል ካለ ይተናነቃሉ። ይህ መለያ ባህሪያቸው ነው። ሕዝብ እነርሱን ወገኔ ቢላቸውም እነርሱ ግን ወገኔ የሚሉት የሰው ልጅን እና ሕዝብን ሳይሆን ልክ እንደነበሩ የሁልጊዜ ሃሳባቸው ፍየልን ወይም ልክ እንደፍየሏ ቅጠልን ብቻ ነው። የቀን የሌሊት ሃሳባቸው ድሎታቸው እና ምቾታቸው እንዳይጓል ብቻ ነው። የስልጣን ጥማት፤ ሱስ ላይ ነው።
ምቾታቸውን ለማስጠበቅ የሰው ልጅ ደም እንደጎርፍ ቢወርድ አያስጨንቃቸውም። የቅርባቸው ወገኔ የሚላቸው ሕዝብ በሰላም እየኖረ እየጠገበም ባይሆን እየቀመሰ፤ እየተማረና እየታከመ እነርሱ በልክ ከሚኖሩ ወገን እያስፈጁ በድሎት ተንደላቀው የህልም እንጀራ ስለሆነው ስልጣናቸው የምኞት ፈረስ ቢጋልቡ ይመርጣሉ። ካብ የማይገባ ድንጋይ ሆነው ለምንም እንደማይስማማና እንደማይመች ለዚህ ሥራ ይውላል እንደማይባል ከንቱ የሚቆጠሩ መናኛዎች ቢሆኑም ተስፋ አይቆርጡም። ዛሬም እነርሱን የሚፈራ ወይም እነርሱን አሁንም የሚወድና የሚያከብር በመኖሩ አሁንም በምኞት ዓለም ውስጥ በመዋኘት ላይ ናቸው። ይሄ አሁን ላይ ማብቃት አለበት።›› አለ ገብረየስ ለራሱ። ዞር ዞር ብሎ ሲመለከት በቅርቡ ማንም የለም። ይሄ ሃሳቡን ከጭንቅላቱ አልፎ በአንደበቱ ስለመለፍለፍ ስላለመለፍለፉ እርግጠኛ አልነበረም። ነገር ግን ዋናው ነገር የሰማው የለምና ደስ አለው።
በድጋሚ ከብርጭቆው ላይ ቢራውን ተጎነጨ። እንደገና በሃሳብ ባሕር ውስጥ ሰጠመ። ‹‹ ከፎከረ ይሻላል የጠረጠረ፤ እንዲሁ ቸኩሎ እነርሱን ደግፎ ጦርነት ውስጥ ከመግባት እና ስሕተት ውስጥ ከመውደቅ ይልቅ ነገሮችን መርምሮና ተከታትሎ በእውነት ላይ መድረስ አስፈላጊ ነበር። ግን እንዴት ይህ ሁሉ ሕዝብ ሴራቸውን መረዳት አቃተው? ›› አለና መልስ የሌለው ጥያቄ ለራሱ አቀረበ።
ለደቂቃዎች ጭንቅላቱ ውስጥ የሚመላለሰውን ሃሳብ ለማስቆም አይኑን ጨፍኖ በረዥሙ ተነፈሰ። መልሶ አይኑን ገለጠ። በራሱ የፀጥታ ዓለም ውስጥ ለመስጠም ተመኘ። አልሆነለትም፤ ተመልሶ ከሰመመኑ ወጣ። እንደገና ማብሰልሰል ቀጠለ። ቢተውት የማይተው የነፍስ ስቃይ። ‹‹እነዚህ መጥፎዎች መጥፎ ጓደኛ አጉል ልምድ ያስተምራል፤ ብዙውን ሰው አሳስተው አጉል ልማድ አስተማሩት። ‹ተገፍተናል የግድ ስልጣን ይገባናል፤ መሬታችንን ልንነጠቅ ነው› ብለው ወጣቱን ብቻ ሳይሆን ሽማግሌውን ሳይቀር ሁሉንም አታለሉት፤ አሳሳቱት። ከጦጣ ጋር የዋለች ጉሬዛ እህል ፈጅታ ትገባለች፤ እነርሱን አምኖ የተከተላቸው እህል እንደፈጀችው ጉሬዛ እነርሱን የሰሙ ሁሉ አገር ፈጁ፤ ንብረት አወደሙ፤ እኛን አሳቀቁ፤ እንድንሸማቀቅ አደረጉ። በገዛ ወገኖቻችን ድርጊት አፈርን ተሳቀቅን።›› አለ ለራሱ በድጋሚ።
ገብረየስ የልቡን ለሰው መተንፈስ ቢያቅተው ለራሱ መንገር በመቻሉ ተደሰተ። ራሱን ሁለት አድርጎ ሙግት ውስጥ ገባ። ‹‹ እነዚህ ሰዎች ሕዝባችንን ይዘው ማጥፋት እና መጥፋት ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሊመላ ሁለት ወር ብቻ ቀረ። በእነዚህ ዓመታት ስንቶች ሞተው ይሆን? ›› አለ። ‹‹በጦርነት ካለቀው ሌላ የልብ ሕመምተኛ፣ የደም ግፊት ወይም የስኳር መድሃኒት በቋሚነት በተከታታይ የሚወስዱ ስንት ሰዎች ሞተው ይሆን? ስንቱ ልጅ በመማሪያ ዕድሜው ሁለት ዓመት አቃጥሎ ይሆን? ስንቱ ከትግራይ ወደ ሌላ አካባቢ እሰደዳለሁ ብሎ በመንገድ ላይ ቀርቶ ይሆን? ይህንን ሁሉ የልጆቿን መከራ በማየት አንጀቷ ቆስሎ ሃዘን አድክሟት ወደ ጉድጓድ የገባች ስንት የትግራይ እናት ትኖር ይሆን?›› አለና አይኑን እንባ ሞላው። በወፍራም የእጁ ጣቶች የሁለቱንም አይኖቹን እንባ ሲያብስ ዘውዴ መታፈሪያ ወደ መጠጥ ቤቱ ገባ። ስላምታ ተለዋወጡ።
ዘውዴም ገብረየስም የመጠጥ ቤቱ በሰው አለመሞላት አስከፍቷቸዋል። በየምሽቱ ከሃምሳ እስከ ሰባ አንዳንዴም መቀመጫ እስኪጠፋ ሰማኒያ እና ዘጠና ሰው የሚተራመስበት ቤት ጭር በማለቱ እንደተለመደው ተራርቆ ከመቀመጥ ይልቅ ተቀራርቦ በአንድ ጠረጴዛ ላይ እየጠጡ ለመወያየት ፈልገዋል። ገብረየስ በሃሳብ ራሱን ከራሱ ጋር መሞገቱ ደስታ ቢሰጠውም እየፈጠረበት ያለው የሃዘን ስሜት ማስጨነቅ ስለጀመረው ለመቀጠል አልፈለገም። ዘውዴን ‹‹ተቀመጥ›› አለው። ዘውዴ አልተግደረደረም። ብዙ ጊዜ ገብረየስ ከሩቅ ያየውና ቀርቦ ማነጋገር እየፈለገ ሳያናግረው ስለቀረ ዕድሉን ለመጠቀም ፈጠን ብሎ ‹‹እሺ እቀመጣለሁ። አንድ ጓደኛዬም ይመጣል›› ብሎ ጠረጴዛውን በመጋራት በቀኝ በኩል ያለውን ወንበር ይዞ አስተናጋጅ ጠራ። እርሱም ቢራውን አዞ ተቀመጠ።
ሁለቱም ተያዩ፤ ዘውዴ ‹‹ከዚህ ቤት ውጭ ሌላም ቦታ የምንተዋወቅ መሰለኝ።›› አለ። አዎ! በትክክል አለ፤ ገብረየስ። ዘውዴ ‹‹የክፍለ ከተማው ሊቀመንበር ነበርክ? ›› ሲል ጠየቀው። ገብረየስ አልዋሸም፤ በትክክል እንዳወቀው ተረድቷል። ‹‹ አዎ!›› አለ። ‹‹ታዲያ አሁን የት ነህ? ›› የሚል ጥያቄ አቀረበለት በአንድ የመንግስት ተቋም ውስጥ እየሠራ መሆኑን ገለፀና መወያየት ቀጠሉ። ቀስ በቀስ ሳያስቡት የሰሞኑን የፖለቲካ ወሬ ውስጥ ገቡ።
ዘውዴ ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ ገብረየስ መቼም ትግራይ ዘመዶች አሉህ አይደል? ›› አለው። ገብረየስ ‹‹ይኑሩ አይኑሩ፤ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አላውቅም እንጂ መኖርስ ነበሩኝ።›› አለ። ዘውዴ በየጊዜው ውስጡ የሚመላለሰውን እና ግልፅ ያልሆነለትን ጥያቄ ለገብረየስ አቀረበ። ‹‹ እነዚህ በየጊዜው ጦርነትን ብቻ እያሰቡ ያሉ ሰዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ካወቅክ እባክህ ንገረኝ ? የሚፈልጉት ምንድን ነው? መቼም ኢትዮጵያን የመምራት ዓላማ ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም ምክንያቱም ይሄ በድጋሚ ሊሆን የሚችል አይደለም። ይህንን እነርሱም ጠንቅቀው የሚያውቁት ይመስለኛል። ትግራይን እንደ አገር መመስረትም ከሆነ በጦርነት እና ሰው በማስፈጀት ሊሆን የሚችል አይደለም። በዛ ላይ እንዴት ሕዝቡስ ልጁን ይሰጣል? በእርግጥ እኔ ያልገባኝ ቡድኑን እና ሕዝቡን የገባው ሊሳካ የሚችል ዓላማ ይኖራቸው ይሆን?›› አለ።
ገብረየስ በረዥሙ ተነፈሰና ትንሽ ዝም አለ። ቢራውን በስሱ ተጎንጭቶ መልሶ በቀስታ ብርጭቆውን አስቀመጠ። ወንበሩ ላይ ተደላድሎ ተቀምጦ ‹‹ ዓላማ የላቸውም፤ ግባቸው ምን እንደሆነ እንኳን ሕዝቡ እነርሱ ራሳቸው እርግጠኞች አይደሉም። ካልሰጡ አይሰደቡ እንደሚባለው የትግራይ ሕዝብ ልጁን እየሰጠ እየተሰደበ የታሪክ ተወቃሽ እየሆነ ነው። ዓላማ የሌለው ዝግጅቱ ያላማረ ግብዣ በኋላ ማስነቀፉ አይቀርም። ዓላማ ለሌለው እና ዝግጅቱ ላላማረ ድግስ ነጋሪት ሲጎሰም ከኋላ ሆኖ የሚያጨበጭብ ቢኖርም ግብዣው ያልተሟላ በመሆኑ በኋላ ተደናቅፎ መውደቅ ብቻ ሳይሆን ያለምንም ትርፍ እንደውም በብዙ ኪሳራ የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ መቅረት ይመጣል። ይሄንን ብዙ የትግራይ ተወላጅ ቢያውቅም እስከ አሁን ሙሉ ለሙሉ ጦርነቱን ማስቆም አልተቻለም።
እባክሽ ያሏት ጎረቤት ትሆን እመቤት እንደሚባለው አንዳንድ ሰው ሲያከብሩት ኩራት ይሰማዋል። ሙቱልኝ ተሰውልኝ ይላል። የቡድኑም ነገር ተመሳሳይ ነው። ህዝቡን በሙሉ ለእኔ ምቾት ስትሉ ዋጋ ክፈሉ እያለ ነው። ህዝቡም እያንዳንዱ ሰው ዋጋ እየከፈለ ነው። እስከ መሰዋዕትነት በመድረስ ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል። አንዳንዱ ራሱ ሲሞት፣ አንዳንዱ አባቱ፣ አንዳንዱ ወንድም እህቱ አንዳንዱ እናቱ ሳይቀር በእነርሱ ፍላጎት በተጀመረ ጦርነት ምክንያት ሞተውበታል።
ቡድኑ ትግራዋይ በክፉ ረሃብና እርዛት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓል። ከእርዛት ክፉ ሱሪ ማጣት ከአካላት ክፉ የሆድ ጅማት እንደሚባለው ቡድኑ ትግራዮች ሱሪ ታጥቀው እነርሱን እንዳያስቆሙ ክፉ እርዛት እንዲያጋጥማቸው አድርገዋል። የትግራይ አካል ነን ቢሉም የቡድኑ አባላት በምንም መልኩ ከትግራይ ሕዝብ አይበልጡም። የትግራይ አካል ቢሆኑም ክፉ ጅማት ሆነው ከሕዝቡ ተነጥለው ከመውጣት ይልቅ ትግራይን ለማፍረስ ታጥቀው ተነስተዋል።
ዘመናቸውን ሁሉ በጦርነት ለማሳለፍ የወሰኑ ይመስለኛል። ምናልባት ዓላማ ከተባለ ዓላማቸው ሊሆን የሚችለው ይህ ብቻ ነው። ያደሩበት ጭቃ ከጭድ ይሞቃል ከተለመደው መጥፎ የሰዎችን ሕይወት ከሚቀጥፍ ተግባር መውጣት ተስኗቸዋል። ጦርነት እንኳን ለሕዝቡ ለእነርሱም ቢሆን የማይመች ቢሆንም የሚመች መስሎ ታይቷቸዋል። ለእነሱ ግን ይሄ ልክ ነው የስልጣን ማቆያ መንገድ አይደል። ወንድሜ እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን ማድረግ ይቻላል? ›› ሲል ገብረየስ ዘውዴ መታፈሪያ የጠየቀውን ጥያቄ በጥያቄ መለሰለት።
ዘውዴ በበኩሉ ‹‹ያደፈ በእንዶድ ይፀዳል፤ የጎለደፈም በሞረድ ይሞረዳል። ጭቃ ውስጥ ገብቶ በቅዝቃዜ ከመታገል፤ ይቅርታ ጠይቆ ፍርድን መጠበቅ እና ጥፋትን መቀነስ ሲገባ በጥፋት ላይ ጥፋት መደራረብ እንደልማድ መወሰዱ በምንም መልኩ የሚደገፍ አይደለም። እኛ በሃይማኖትም ሆነ በስነልቦና በብዙ መልኩ እርስ በእርስ የተጋመድን የማንለያይ ሆነን ስለምን በጦርነት ለመጠፋፋት መሳሪያ እንደምንሆን ግልፅ አይደለም። በእርግጥም ማንም ቢሆን የጦርነቱን ዓላማ የተረዳ አለ የሚል እምነት የለኝም። መፍትሔው ግን ምንም ሆነ ምን ጦርነት እንዳይቀጥል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው።›› አለው።
በዚህ ጊዜ ገብረየስ አቀረቀረ፤ ቀና ብሎ ብርጭቆውን አነሳና ቢራውን ከጠርሙሱ ወደ ብርጭቆ አንጠፍጥፎ፤ እያገላበጠ በብርጭቆ የተገኘችውን ቢራ ጨልጦ ጠጣ። መሃላቸው ዝምታ ሰፈነ። ዘውዴ ገብረየስ የሚለውን ለመስማት ጓጉቷል። ገብረየስ ውስጡ ጭንቀት በመኖሩ አካሉ ላይ የሚንበለበለውን እሳት ለማብረድ በረዥሙ ተንፍሶ ‹‹ምናለበት ጦርነትን ማስቆም አሁን እኔና አንተ እንደምንነጋገረው ቀላል ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር። ችግሩ ጦርነቱ መቆም የሚችለው በእኔ እና በአንተ ፍላጎት ሳይሆን፤ በሌሎች በሰው ሕይወት መጥፋት በሚደሰቱ ሰዎች ውሳኔ ነው። እርግጥ ቢዘገይም አሁንም ጦርነት ባይቀጥል የወደፊቱን ጥፋት የሚቀንስ በመሆኑ ተፈላጊ ነው። ግን በምን መንገድ ይቁም ከተባለ መልሱን መመለስ ከኔ አቅም በላይ ነው።›› ሲል ተነፈሰ።
ዘውዴ መታፈሪያ ወደ ደጃፍ እየተመለከተ ‹‹ ወዳጄ መጣ። እንደውም መልሱን እርሱ ይሰጠናል።›› በማለት ሰላምታ እየሰጠው መሳቅ ጀመረ። ተሰማ በበኩሉ ነገሩን ስላላወቀ ‹‹በቅድሚያ ጉዳዩ ይብራራልኝ።›› አለ። ዘውዴ ገብረየስን እና ተሰማ መንግስቴን አስተዋውቆ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እንዳይኖር ምን ይሠራ እያልን እየተጠያየቅን ነበር።›› አለው። ተሰማ ‹‹ እንግዲህ መንግስት ማንም ቢሆን ማን መወያየት እና መነጋገር እንችላለን። ከጦርነት ይልቅ ልማት ላይ እንረባረብ ለጦርነት ከበሮ ከመደለቅ ነጋሪት ከመጎሰም ይልቅ ፊታችንን ወደ ልማት እናዙር እያለ ነው። ነገር ግን ጦርነትን ስራ የስልጣን ማቆያ ያደረጉ ሰዎች ደግሞ ከልማዳቸው መውጣት አቅቷቸዋል። ስለዚህ መፍትሔው መንግስት ጋር ወይም ጦርነትን ልማዱ ያደረገ ቡድን ጋር ሳይሆን ሕዝብ ጋር ነው። ጦርነት የለመዱትን ‹ይህንን ክፉ ልማዳችሁን ተው፤ በቃነ፤ ይብቃችሁ፤ ከዚህ በላይ መሞት አንፈልግም› ማለት አለበት ካለበለዚያ ሌላ መፍትሔ ማግኘት በጣም አዳጋች ነው።›› አለ። ሶስቱም በዚህ ሃሳብ ቢስማሙም መቼ እና እንዴት ይህ ሊባል ይችላል የሚለው ላይ መግባባት ሲያቅታቸው ገብረየስ ‹‹ጉዳዩ ለይደር ይቆይ ከመጣሁ ስለቆየሁ ወደ ቤቴ ልሒድ።›› ብሎ ወጣ። እሱ ከግሮሰሪው ወጣ እንጂ ሀሳቡ ግን በግሮሰሪው ቤት ተጠንስሶ አብሮት ቀጠለ። ገና በእንቅልፍ ዓለም ጭምር ይብላላል። ምክንያቱም ሰላም አገር ላይ ካልሰፈነ የአእምሮም ሰላም የለማ፤ የሚያልቀው ህዝብ ነዋ። እና ምን እረፍት አለ የሚቆይ የሚቀመጥ ሀሳብ የለም። ሀሳብ ሰብሰብ ብሎ፤ አእምሮ አርፎና እረፍት አግኝቶ ሀሴት የሚያገኘው ጦርነቱ በልማት ሲተካ ነው። ሰው ሆዱ ብቻ ሳይሆን አእምሮም በልቶና ጠግቦ ሲያድር ነው። ካልሆነ ያው በሀሳብ መዋዠቅ፤ በቃ በሀሳብ መዋተት ነዋ !።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19 ቀን 2014 ዓም