በእዝነ ህሊናችሁና በምናባችሁ የያሬድ ሹመቴ ግጥምና ዜማ የሆነውን፤ ታደለ ፈለቀ ማለፊያ አድርጎ ያቀናበረውን ግርማ ተፈራና ራሔል ጌቱ ሸጋ አድርገው ያዜሙትን “የእረኛዬ”ይዛችሁ ተከተሉኝ፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ድንቅ ስራ ቴዲ አፍሮ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን ዘመን ተሻጋሪ ስራ “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ከ10 ደቂቃ ባልበለጠ ክሊፕ በ”ማር እስከ ጧፍ” ማለፊያ አድርጎ ያበረከተልንን ስራ ያስታውሰናል። ያሬድ ሹመቴም በ48 ክፍሎች የተላለፈውን የአገራችንን ተከታታይ ድራማ ታሪክን የቀየረውን፤ ከዚህ በኋላ መነሻም መለኪያም ሆኖ የሚያገለግለውን “እረኛዬ”ን ከስድስት ደቂቃ ባልበለጠ ክሊፕ ቅንብብ አድርጎ አቅርቦልናል። እናመሠግናለን።
“የእረኛዬ” ተከታታይ ድራማ በአርትስ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ ባጅቶ ባለፈው አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ሲጠናቀቅ በአእምሮዬ ሁለት ምናባዊ አሻራዎችን አኖረ። የመጀመሪያዊ የአገራችንን ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ በኪን አዋዝቶና አስውቦ ያቀረበ፤ ሁለተኛው ደግሞ ላለምነው አገራዊ ምክክር ፍኖተ ካርታ የሚሆን ዳና ትቶልን መሔዱ። እንደ እናና የሚሰበስበንና የሚጠብቀን እረኛ የሚያስፈልገን ሰዓት ላይ ነንና ከዚህ አንጻር ዘመኑንም ሆነ ትውልዶችን የዋጀ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ወደ ተወሰኑ ሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ቢተረጎምና ቢተላለፍ ለአገራዊ ምክክሩ መልመጃና እርሾ ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም ሆነ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለደራሲዎቹና ተዋናዮች እውቅና ቢሰጧቸው ተገቢ ነው ብዬም አምናለሁ።
እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ትልቅ ጉዳይ፤ በቴሌቪዥን በአስር ሚሊዮኖች የሚገመት ተመልካች፤ በዩቲውብ ከሦስት ሚሊየን በላይ ሕዝብ የተከታተለውን ይሄን ፋና ወጊ ድራማ መጠናቀቅ አስመልክቶ፤ ሚዲያዎቻችን ዛሬም ከስብሰባ አዳራሽ፣ ከልማት ዘገባ፣ ከፕሮቶኮል ዜና፣ ከአኃዝ ፍቅር፣ የመሪን ጥላና ዳና ከመከተል ክፉ አባዜ ባለመላቀቃቸው “እረኛዬ”ን ከተለያየ ማዕዘን አንጻር በዘረፉ ሊቃውንት ሊያስተረጉሙልን፣ ሊያስበይኑልንና ሊያስተነትኑልን ሲገባ፤ እንደለመዱት ባላየ ባልሰማ አልፈውታል። ለከፈላቸው ዩኒቨርሲቲ ግን የተማሪ ምረቃ በቀጥታ በማስተላለፍ ከአለም የመጀመሪያ ናቸው። ይህ ክፉ አባዜና ከሳጥን ወጣ ብሎ ያለማሰብ መርገም ፊት ሊነሳ ይገባል። ሌላው “እረኛዬ”ን ስፖንሰር ለማድረግ ሲጓደዱ የነበሩ የግልም ሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በራሳቸው ሊያፍሩ፤ ስፖንሰር ያደረጉ ደግሞ በራሳቸው ሊኮሩ ይገባል። በቀጣይ ግን እንደ”እረኛዬ”ያሉ ታላላቅ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን የሚደግፍ ራሱን የቻለ ፈንድ ሊቋቋም ይገባል።
በebs የ”Tech Talk With Solomon” አዘጋጅና የ”ግርምተ ሳይቴክ” ደራሲ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ፤ “እረኛዬ! የኢትዮጵያችንን ጠቧንና ፍቅሯን፣ ለቅሶዋንና ሳቋን፣ የኋላዋንና የፊቷን፣ ስህተቷንና እርማቷን፣ ጨለማዋንና ብርሃኗን፣ ፍርሃቷንና ድፍረቷን፣ ሃዘኗንና ደስታዋን፣ ድካሟንና ብርታቷን፣ ጥፋቷንና ልማቷን፣ ውሸቷንና እውነቷን፣ ደዌዋንና ፈውሷን፣ ስብራቷንና ጥገናዋን፣ መካንነቷንና ወላድነቷን፣ መርገሟንና በረከቷን፣ ስቃይዋንና ፍሰሃዋን፣ ወከባዋንና እረፍቷን፣ ስቃይዋንና ሰላሟን፣ ድህነቷንና ባለጸግነቷን፣ በደሏንና ምህረቷን፣ ጥርጣሬዋንና እምነቷን፣ ቁዘማዋንና ሃሴቷን፣ መውደቅና መነሳቷን፣ ጠላቷንና ወዳጇን፣ ቂሟንና ይቅርታዋን፤ ማጣቷንና ማግኘቷን፣ ሞቷንና ትንሳኤዋን ቁልጭ አድርጎ አሳየን! ፍቅር ከጥላቻ፣ ምህረት ከህይወት፣ ይቅርታ ከቂም፣ ብርሃን ከጨለማ፣ በደልን መሸፈን ከበቀል ምን ያህል አብልጠው ሃያልና አሸናፊ እንደሆኑ በእረኛዬ ግዙፍ የተስፋ መስኮት ውስጥ ይታያሉ!፡፡ ድርሰቱ ለአገር መርህ ሊሆን የሚችል፣ መልዕክቱ በልቦና ቢያድር አገር የሚዋጅ፣ ሃሳቡ ቢተገበር ትውልድ የሚያድን፣ ትወናው እንደ ጥበብ ጥግ ተቆጥሮ ሁሌም የሚሞገስ፣ ደራሲያኑ፣ ተዋንያኑ፣ የሙዚቃና የፊልም ባለሞያዎቹም ክብር የሚያሰጣቸው ብቻ ሳይሆን የአገር ጀግኖች የሚያስብላቸው ነው!፡፡ እረኛዬ — የኢትዮጵያ የመዋጀት ተስፋ መስኮት! Great job Arts Tv World!” ሲል ገልጾታል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ቴውድሮስ ተክለአረጋይ እንዲሁ በፌስቡክ ሰሌዳው “የሚያስቀናው የእናና አሟሟት” በሚል ርዕስ፤ እኔ ከሕይወት በሞት እቀናለሁ። ከሞትም
አሟሟት ይዋብብኛል። የሰው ልጅ ወትሮም ለሞት የተፈጠረ ነው። እስከ ዘለዓለማዊው ሞት ባለው መንገድ ላይ ለአጭር ጊዜ እዚህ ዓለም ይኖራል። ይህ ዓለም ወደ ሞት የምናዘግምበት መንገድ እንጂ መኖሪያችን አይደለም። ችግሩ ግን መኖርን እንለምደውና ሞት ያስፈራናል። እናና ሞተች። በሞቷ ተዋበች። ምንም እንኳን ለሞቷ ምክንያት ሆኖ የመጣው የሌሎች ጠብ፣ የጉልበተኞች እርግጫ ሳሯን እናናን ቢወስዳትም፣ እናና ለሞት ቅርብ ነበረች። እናና ለግል ሕይወቷ ጉጉ አልነበረችም። ለሌሎች ቤዛ የሆነ ሕይወት ነበራት። ብዙዎች የእናና ሞት አሳዝኗቸዋል። አበሳጭቷቸዋል። ውበቱም እሱ ነው። የእናና ሕይወት ለሞት ቅርብ ነው። እናና ሳትሆን ለ”እረኛዬ” መስዋዕት የሆነችው “እረኛዬ” ነው የተሰዋላት። ሁሉም ገጸባህሪያት ተሰብስበው ለእናና የመንፈስ ልዕልና ባርኔጣቸውን አንስተው ነው “እረኛዬ” የተጠናቀቀው። ማን ነው ከእንግዲህ በ”እረኛዬ” ድራማ ላይ ሀውልት ሆኖ የቆመው? እናና ናት። ምረጡ ብትባሉ ማንን መሆንን ነው የምትመርጡት? እኔ እናናን መሆንን እመርጣለሁ። በሕይወት ካሉት ይልቅ ለሌሎች ጥርሷን ነክሳ፣ ጉዳቷን አሳንሳ፣ እንደዚያ ምድር እስኪጠባት የምትሮጠዋ ሴት ቅዝዝ እንዳለች፣ ጉዳቷን ሌሎች እንዳይሰሙ ሕይወቷን በጥርሷ ነክሳ ሄደች።
እናና በሕይወት ብትኖር ለራሷ ካልሆነ ለእኛ ምን ይፈይድልናል? ብዙዎች አለን እኮ ለመኖር ለመኖርማ። ለማንም ምንም ሳናደርግ ምንም ሆነን የምንኖር። እናና ግን በሞቷ ከእኛ በላይ ትኖራለች። አብነት መንደር ውስጥ እያንዳንዱ ነዋሪ ልብ ውስጥ ሀውልት አላት። እሱ ነው ቁምነገሩ። መኖር ማለትም እሱ ነው፤ አለመሞት አይደለም። የእናና መንገድ መጨረሻው እንዲህ ነው። በሕይወት የሚሞቱበት ሳይሆን በሞት የሚኖሩበት ነው። የቴዎድሮስ (የቋራው)፣ የማርቲን ሉተር፣ የክርስቶስ አይነት የቤዛነት ሞት ነው ሞቷ። የሰሜን ሸዋዎቹ አባትና ልጅ ጀግኖች ሞትን እንረሳዋለን ? የእሸቴ ሞገስ ድምጽ ከጆሯችንስ ሆነ ከልባችን ይወርዳል? “ለዚህ ጀግንነትስ እንኳን ሞቱ” አላልንም? እኔ ብያለሁ። ከብዙ ሰው ሕይወት የእሸቴ የጀግንነት ሞት እንዳስቀናኝ አለ። ከመኖራቸው ሞታቸው ነው ልባችንን ከፍ ያደረገው። ለመኖር እኮ ባንዳም ሆኖ መኖር ይቻላል። “ እረኛዬ “ ላይ ለእኔ እጅግ የተዋበው አጨራረስ የእናና ሞት ነው። ሞት ትንሳኤ ነው። ሞት ፈውስ ነው ፤” ሲል ግሩም አርጎ ገልጾታል፡፡
የአማርኛው ቢቢሲ ደግሞ ሸጋ አድርጎ የሔሰበትን መጣጥፍ ላጋራችሁ፤ እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአርትስ ቴሌቭዥን በአራት ምዕራፎች በ48 ክፍሎች ሲተላለፍ ቆይቶ አርብ ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም. ተጠናቋል። ይህ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በአዜብ ወርቁ፣ በቤዛ ኃይሉ እንዲሁም በቅድስት ይልማ የተጻፈ ሲሆን፣ ያዘጋጀችው ደግሞ ከደራሲዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው ቅድስት ይልማ ነች። እነዚህ ሦሰት ደራሲያን ለፊልም ጽሁፍ እንዲሁም ዝግጅት እንግዳ አይደሉም። በስማቸው በርከት ያሉ ሥራዎች ሰፍረው ይገኛሉ። በጥምረት ግን ሲሰሩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። እረኛዬ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ መቼቱን ያደረገው ከከተማ ግርግር ርቆ፣ ሕይወት ስክን ብላ በምትፈስበት ገጠር ውስጥ ነው። ይህ አብነት የተሰኘ የገጠር መንደር በምናብ የተፈጠረ ነው። ይህች የገጠር መንደር ኢትዮጵያን እንድትመስል ተደርጋ ነው የተሳለችው። በዚህ መንደር በፍቅር ተሳስበው የሚኖሩ ዘመዳሞች እና ጎረቤታሞች ፍቅራቸውን የሚነቀንቅ ተቀናቃኝ መጥቶባቸዋል። ይህ ተቀናቃኝ ባለሀብት ነው። በሀብቱ ብዛት መሬታቸውን ሊነጥቅ የቋመጠ፣ ለዚህም በቀኝ በግራው፣ በፊት በኋላው ግለሰቦችን ያሰለፈ ነው። ይህ ባለሀብት የሚነጥቃቸው መሬት ይምሰል እንጂ ከመሬቱ ጋር የተሰፋ ማንነት፣ ባሕል እና ትውፊት አብሮ አለ። የአብነት መንደር ነዋሪዎች ይህንን የኖረ ባሕላቸውን፣ ማንነታቸውን ለመከላከል በገበሬ አቅማቸው ይውተረተራሉ፡፡
በድራማው የመጀመሪያ ክፍል ላይ የምናያቸው እና በኋላም በታሪኩ ውስጥ በተደጋጋሚ በአርዓያ ሰብነት የሚጠቀሱት አብዬ በቃሉ ከአካባቢው ሁሉ የተለዩ ግለሰብ ነበሩ። መለየታቸው ለመልካም ነው። ሕብረት ይወዳሉ፤ ድንበር አይፈልጉም። አገራዊ እውቀቶች ከአንዱ ሰው ወደ ሌለው እንዲተላለፉ አጥብቀው ይሻሉ። ለእርሱም ትምህርት ቤት ከፍተው የአብነትን ነዋሪዎች ያስተምሩ ነበር። ነገር ግን ልጃቸው ከጋብቻ ውጪ አርግዛ የሠርጓ ዕለት በመውለዷ በድንጋጤ ሕይወታቸው አለፈ። አገሬው ጉድ አለ፤ የአቶ በቃሉ ሕልም ተዳፈነ። ቤተሰቡ አንገቱን ደፋ። ልጃቸው ወጋየሁም ጨርቄን ማቄን ሳትል ሌሊቱን ማንም ወደማያውቃት አገር ተሰደደች።
የአብነት መንደር ወግ ባሕል ልማድ የተጣሰው ዋነኛ ተቆርቋሪ በሆኑት አብዬ በቃሉ ልጅ፣ ወጋየሁ ነው። በኋላ ግን የጠፋው ወግ ባሕል ልማድ በእርሳቸው የልጅ ልጅ እንደ አዲስ ሲያንሰራራ እንመለከታለን። በአንድ ማህጸን ያደሩት ዳዊት እና መንግሥቱ በተለያዩ ወላጆቻቸው እጅ ማደጋቸው፣ የተለያየ ባሕርይ እና ማንነት ሰጥቷቸው የማይግባቡ ዥንጉርጉሮች አድርጓቸዋል። ያደሩበት ማህፀን፣ ተካፍለው የጠቡት ጡት ያቆየላቸው እንጥፍጣፊ ፍቅር ያለ አይመስልም። እረኛዬ በእነዚህ ገፀ ባሕሪያት በኩል የአገርኛ እውቀቶች እንዲያብቡ፣ ባሕል ወግ ልማድ እንዳይጣስ፣ ፍቅር ይቅርታ የኑሮ አምድ እንዲሆኑ ደጋግሞ ይወተውታል።
በበርካቶች ዘንድ ትኩረትን ያገኘው ለዚህ ይሆን? ድራማውን የተከታተሉ ሁለት ግለሰቦች አነጋግረናል ይላል ቢቢሲ። ገሸሽ ያደረግነውን ማንነት ፍለጋ በእረኛዬ ድራማ ላይ የምናያቸው የማምረቻ መሳሪያዎቹ፣ አልባሳቱና ጌጣጌጦቹ፣ ወዘተ የራሳቸው የሆነ ቱባ ሥነ ውበታዊ ገጽታ አላቸው። በአሰራራቸው የአገርኛ ጥበብ አሻራ ታትሞባቸው ይገኛል። በድራማው ላይ የሚታዩት የሰላምታ ልውውጦች፣ የግብይት ልማዶች፣ የጋብቻ ሥርዓቶች፣ የአምልኮ ትውፊቶች፣ የለቅሶ ልማድ ሁሉ የየራሳቸው ውበትና መስህብ እንዲኖራቸው ተመልካችን እንዲያማልሉ ሆነው ተቀርፀዋል። በድራማው ላይ በእረኞች እና በኮማሪቷ ማስረሻ፣ የሚገጠሙ ግጥሞች የማኅበረሰቡን ማንነትና ስሜት ከማንጸባረቅ ትይዩ የቆሙ፣ ሥነ ጽሑፋዊ ቴክኒክ ተላብሰው የቀረቡ ናቸው። ይህም የማዝናናት ለዛቸውን አጉልቶ፣ አይረሴና ተጨባጭ አድርጓቸዋል። ድራማው አካብቶ ያቀርብልን የማኅበረሰቡ ጠቅላላ የተሞክሮ ዕውነታ ባሕላዊ ማንነትን የሚያጎሉ ቅርሶች የተዝናኖት ፋይዳ ጨምረውለታል። የደራሲዎቹ የተጠባቢነት አቅም ልኩ የሚመዘነው ደግሞ እነዚህን አጣጥሞ በማቅረብ ብቃቱ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የባላገሩ ቴሌቪዥን የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆነው ሲራክ ተመስገን ይናገራል።
የቲያትር እና የፊልም መምህር የሆነው አንተነህ ሠይፉ በበኩሉ፣ እረኛዬን የወደድንበትን ምክንያት ሲያነሳ አስቀድሞ የሚጠቅሰው መቼቱን ነው። በኢትዮጵያ የፊልም እና የተከታታይ ድራማ ታሪክ መቼታቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያደረጉ ሥራዎች በቀላሉ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እና ተወዳጅነት ማግኘታቸውን በማንሳት እረኛዬም ይህ እንደረዳው ይገልጻል። የዚህ ተከታታይ ድራማ ደራሲና አዘጋጅ የሆነችው ቅድስት ይልማ ቀዳሚ ሥራ የሆነው ‘ረቡኒ’ን በምሳሌነት ያነሳው አንተነህ፣ በተመሳሳይ መልኩ መቼቱን ገጠር በማድረጉ ተወዳጅነትን አትርፎ እንደነበር ያስታውሳል። አንተነህም ሆነ ሲራክ፣ እረኛዬ ተከታታይ ድራማ፣ ያነሳው ታሪክ ወደ ጥንታዊ ማንነት፣ ገሸሽ ወዳደረግናቸው ባሕላዊ እሴቶቻችን መመልከቱ በተመልካች ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘቱ አስተዋጽኦ ማድረጉ ላይ ይስማማሉ። አክለውም ታሪኩ የተዋቀረበት እና ገጸ ባህሪያቱ የመጡበት ዓለም፣ ከማኅበራዊ ከሌሎች እሴቶቻችን ጋር መሳ ለመሳ መሆኑ ተቀባይነት ለማግኘት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራሉ። ዳይሬክተሯም ገጸ ባህሪያቱ የተቀዱበት ማኅበረሰብን ማንነት ለማጉላት የተጠቀመችባቸው ነባር እሴቶችም አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንተነህ አክሎ ይገልጻል። ገጸ ባህሪያቱ በምናብ በተፈጠረ መንደር፣ አብነት፣ ልቦለዳዊ ኑሯቸውን መስርተዋል። የማኅበረሰቡን ኑሮ አይኑሩ እንጂ፣ ለኑሮው መስታወት ሆነው የራሱ የዕለት ተለት ገመና መልሶ እንዲመለከት አድርገውናል፡፡
በድራማው ውስጥ የማኅበረሰቡን እንከን፣ ሠላም የማጣት፣ የመናቆር፣ ይቅር ማለት አለመቻል ፍጥጥ ብሎ እንዲታይ አድርጓል። ለዚህም እንቆቅልሽ ብሎ በመጠየቅ ከራስ መልስ እንደመጠየቅ አይነት ነው። ደራሲዎቹ በገጸ ባህርያቱ ሕይወት በኩል እንቆቅልሽ ብለው ይጠይቃሉ። ተመልካቹም ፍንጮቹን እየተከተለ የሕይወትን እንቆቅልሽ የመፍታት ድርሻን ይወስዳል። አንተነህ ይህንን ሃሳብ ሲያጠናክር “ወቅቱን የሚገልፁ፣ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን፣ በአደባባይ መተንፈስ መናገር የማይችለውን ነገር በድራማ መልክ ስለማንነታችን፣ ስለ እርስ በእርስ ግንኙነታችን ስለአናኗራችን አሁን ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ፣ በጥሩም ይሁን በመጥፎ ያነሳሳል” ይላል።
ላለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጥያቄ ነው ያለውን ድራማው ያነሳል፤ ሲራክም ሆነ አንተነህ በድራማው በኩል የራሳችን ገበና፣ ከአደባባይ ርቀን በማጀታችን የምናወራው ነገር ሲቀርብልን፣ መተንፈሻ ፉካ ሆኖን በማገልገል ተወዳጅነትን አትርፏል ይላሉ። ሲራክ አክሎም ዳይሬክተሯ ቅድስት አገሪቷ ያሉባትን ችግሮች፣ አገር በቀል በሆነ እውቀት ውስጥ መፍትሔ መፈለግን እንደ ስልት ይዛዋለች ይላል። የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የወንዶች ዓለም ነው በሚለው ሀሳብ አንተነህና ሲራክ ይስማማሉ። አብዛኞቹ ታሪክ ነጋሪዎችና ፀሐፊዎች ወንዶች በመሆናቸው በወንድ ዐይን ነው ዓለሙን የሚያሳዩን ይላል አንተነህ።
የምንኖረውን የአባታዊ ሥርዓት፣ በምንታደመው የጥበብ መድረክ ላይም የምናየው ሕይወት የወንዶች ምናብ ውጤት ነው በማለት ያክላል ሲራክ። “ዓለሙን፣ ሕይወትን፣ አገርን የሚተረጉሙት በወንድ መነጽር ነው” ይላል አንተነህ። የእረኛዬ ደራሲዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ ዕድል ነበራቸው። እንዲህ ሴቶች በድርሰትም በዝግጅትም ሰብሰብ ብለው መምጣታቸው እንደ እረኛዬ አይነት በሥርዓተ ጾታ ላይ ጥንቁቅ የሆነ ድራማ እንድናገኝ ረድቶናል ይላል ሲራክ። ለዚህም ነው የእረኛዬ ሴት ገጸባህሪያት የድራማው ደምና አጥንት ሆነው ነው የተሳሉት። የአብነት መንደር ሕይወት በጫንቃቸው ነው። የአብዬ በቃሉ አደራ በደም ሥራቸው ይፈሳል። የትምህርት ቤት ደጃፍ ባይረግጡም፣ የፊደል ዘር ባይለዩም ሕይወትን፣ በዙሪያቸው የተንሰራፋውን ዓለም በገባቸው ልክ የሚተረጉሙ እና እርሱንም አጽንቶ ለማቆም የሚታገሉ ናቸው። የእረኛዬ ሴት ገጸ ባህሪያት ለከተማ ሕይወት ባዳ ሆነው፣ የቀለም ዘር ሳይለዩ ለመብታቸው የሚቆሙ ናቸው የሚለው ደግሞ አንተነህ ነው።
በዚህ ሃሳብ ሲራክም ይስማማል። “በእረኛዬ ድራማ ላይ ልፍስፍስ ሴት አትታይም፤ ከወንዶች እኩል የምትገዳደር ሴት እናገኛለን” ሲል ያክላል። አንተነህ ሲያክልበት ደግሞ “ለእህቷ ለጓደኛዋ መብት የምትቆም ሴት… ልጆቿን ሕልውናዋን ለመመለስ የምትታገል ሴት… ቤቷን ብቻ ሳይሆን አካባቢዋን አጽንቶ ለማቆም የምትታገል እናት” ማየታችን በሴት ደራሲያን የመጻፉ ትሩፋት መሆኑን ያስረዳል። የድራማው ደራሲያን ሴት መሆናቸው ወንዶች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሲጽፉ የሚያጎዱሉት ነገር ቁጭት እና እልህ አለባቸው የሚለው አንተነህ፣ ጠንካራ ሴት ገጸ ባህሪያትን በመሳል ረገድ እንደተዋጣላቸው ይመሰክራል። ደራሲያኑ እንዲሁም ዳይሬክተሯ ሴቶች መሆናቸው “ለሚገባቸው ሚና የሚታመኑ ጠንካራ ገጸ ባህሪያትን” ጠንካራ ሴቶች እንድናይ አድርጎናል ሲል ይገልጻል። የእረኛዬ ሴት ገጸ ባህሪያት ከእነርሱ ሕይወት ይልቅ የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ሕልውና ያሳስባቸዋል።
በዋና ገጸ ባህሪይነት የተሳሉት ሴቶች ሁሉ ከራሳቸው በላይ ሰንደቅ ሆኖ የሚውለበለብ ዓላማ አላቸው። የእናና ገጸ ባህሪ ደግሞ ለሞቷ ሰበብ የሆነውን የጥቅም ፈላጊዎች ጠብ፣ ለመኖሪያ ቀዬዋ ነዋሪዎች ቀጣይ የጠብ ጥንስስ መነሻ እንዳይሆን በመመሸግ፣ መስዋዕት እስከመሆን ትደርሳለች። በእረኛዬ ድራማ ላይ የተሳተፉት ተዋንያንም ቢሆኑ ስምና ዝና ያላቸው፣ ክህሎትም ቢሆን ጠንቅቀው የተካኑ መሆናቸው ለተወዳጅነቱ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንተነህ እና ሲራክ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። “ከእረኛዬ ድራማ የተመቸኝ አንድ ነገር ቢኖር ገጸ ባህሪ አሳሳሉ እና ተዋናይ መረጣው ነው” ይላል ሲራክ።
እረኛዬ ድራማ “የደርቢ ስብስብ ይመስላል” የሚለው ደግሞ አንተነህ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በድራማው ላይ ወሳኝ ስፍራ የያዙት ተዋንያን ስምም ዝናም ያላቸው መሆናቸውን ነው። በእርግጥ በድራማው ላይ አዳዲስ ፊቶች የታዩ ቢሆንም እንደ አበበ ባልቻ፣ ሙሉዓለም ታደሰ፣ ድርብ ወርቅ ሠይፉ፣ ሳያት ደምሴ፣ ኩራባቸው ደነቀ፣ አማኑኤል ሐብታሙ፣ ቃልኪዳን ጥበቡ እንዲሁም ሠለሞን ቦጋለ ያሉ ተዋንያንን ማሳተፉ አድናቂዎቻቸውን ወደ ድራማው በመጥራት ረገድ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይጠቅሳል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተዋንያኑ የተወከሉበትን ገጸ ባህሪ በሚገባ መጫወታቸው፣ ተደራሲያንን ወደ ታሪኩ ጎትቶ በማስገባት ረገድ የላቀ ሚና እንደነበረው ያነሳል።
ብሔራዊ እርቅና መግባባት ለአገራችንና ለሕዝባችን ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19 ቀን 2014 ዓም