ካለፈው ዓመት አንስቶ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መካሄድ ከጀመሩ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የክለቦች ቻምፒዮና ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በታንዛኒያ እየተካሄደ ይገኛል።
አንድ ሳምንት ያስቆጠረው ይህ ውድድር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን ዛሬ ይስተናግዳል። ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ያለፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብም ከዩጋንዳው ሺ ኮርፖሬት ጋር ለፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማል፡፡ ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ በታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ እና በሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ጋር ይደረጋል፡፡
በታንዛኒያ አሩሻ አስተናጋጅነት ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ ክለቦች ቻምፒዮና ከቀጠናው የተወጣጡ ስምንት ክለቦችን በሁለት ምድብ ከፍሎ ሲያፋልም ቆይቷል፡፡ ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የሚያልፈውን አንድ ቡድን ለመለየት በሚያስችለው በዚህ ቻምፒዮና ዛሬ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ሶስቱንም የምድብ ጨዋታዎች በማሸነፍ የምድቡ ቀዳሚ ክለብ ሆኖ የጨረሰው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡድን ለፍጻሜ የሚያበቃውን ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ በመድረኩ የወከለውና የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ንግድ ባንክ በምድብ ሁለት የተደለደለውን የዩጋንዳውን ሺ ኮርፖሬት ያስተናግዳል፡፡
እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በዚህ ቻምፒዮና ላይም ድንቅ ብቃቱን እያስመሰከረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ዋሪየር ኩዊንስ ጋር በማድረግ 9 ለ 0 በሆነ ሰፊ ወጤት መርታቱ የሚታወስ ነው፡፡ በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም በተካሄደው ሁለተኛው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ደግሞ የቡሩንዲውን ፎፊላ ፒኤፍ 5 ለ 1 በማሸነፍ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ከምድቡ ማለፉን አረጋግጧል። በጨዋታውም አምበሏ ሎዛ አበራ 3፣ መዲና ዓወልና ናርዶስ ጌትነት ደግሞ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በቤንጃሚን ማካፓ ስታዲየም ከሩዋንዳው ክለብ ኤ ኤስ ኪጋሊ ጋር በነበረው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታም ንግድ ባንክ 2 ለምንም በማሸነፍ ምድቡን በአንደኝነት አጠናቆ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል። በዚህም የቻምፒዮናው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዋ ሎዛ አበራ 9 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ መሪነቷን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ መዲና ዓወል ደግሞ በ6 ግቦች ትከተላታለች፡፡
በቻምፒዮናው መርሃ ግብር መሰረትም የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎቹ በታንዛኒያ ብሄራዊ ስታዲየም በአንድ ሰዓት ልዩነት ይደረጋሉ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ከዩጋንዳው ሺ ኮርፖሬት እንዲሁም በታንዛኒያው ሲምባ ኩዊንስ እና በሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ መካከል ይደረጋሉ፡፡ ይህንን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው፤ ቡድኑ ሶስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፉ የተሰማውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል። አሰልጣኝ ብርሃኑ አክሎም ‹‹የቡድናችን የመጀመሪያው ግብ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ነበር፤ አሁን ደግሞ የመጨረሻውን ነጥብ ለማምጣት ዝግጁ ነን›› ማለቱን ካፍ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የንግድ ባንክ ተጋጣሚ የሆነው ሺ ኮርፖሬት በምድብ ሁለት 6 ነጥብ በመሰብሰብ ሁለተኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያለፈ ሲሆን፤ በሲምባ ኩዊንስ ከደረሰበት የ2ለባዶ ሽንፈት ውጪ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለ ክለብ ነው፡፡ ይህም አንድም ሽንፈት ያላስተናገደውና በአምናው ቻምፒዮና ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀው ንግድ ባንክ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። በምድብ አንድ ሁለተኛ ቡድን በመሆን ለዛሬው ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ኤኤስ ኪጋሊም ከምድብ ሁለት ቀዳሚ በሆነውና ጠንካራው ክለብ ሲምባ ኩዊንስ መፈተኑ አይቀሬ ነው፡፡
በውድድሩ ላይ ስምንት ቡድኖች ተካፋይ ሲሆኑ፤ በሁለት ምድብ ተከፍለውም የዋንጫ ፍልሚያቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመጀመሪያው ምድብ የተደለደሉት የኢትዮጵያውን ንግድ ባንክ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ጨምሮ፤ የዛንዚባሩ ዋሪየርስ ኩዊንስ፣ የብሩንዲው ፎፊላ ፒኤፍ እና የሩዋንዳው ኤኤስ ኪጋሊ ናቸው፡፡ በሌላኛው ምድብ ደግሞ የአዘጋጇ ሃገር ታንዛኒያ ክለብ የሆነው ሲምባ ኩዊንስ፣ የጅቡቲው ጋርዴ ሪፐብሊካን፣ የዩጋንዳው ሲ ኮርፖሬት እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ዬ ጆይንት ስታርስ ነበሩ፡፡ የፍጻሜ እና የደረጃ ጨዋታዎቹም በመጪው ቅዳሜ ነሃሴ 21/2014 ዓም እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014