ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በጥንታዊቷና ከሁለት ምዕተ ዓመት በላይ የኢትዮጵያ መዲና ሆና ባገለገለችው የጎንደር ከተማ የተፈጠረው ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር አንደኛው ነው፡፡ ለከተማው የንጹህ የመጠጥ ውሃ መጠን በቀን 70 ሺህ ሜትር ኪዩብ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት እየቀረበ ያለው 13 ሺ ሜትር ኪዩብ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ካለፈው የሰኔ ወር ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች 90 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ፍጆታቸውን የሚያገኙት ከዝናብ ውሃ መሆኑን ችግሩን አስመልክቶ ከሁለት ሳምንት በፊት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በክልሉ መንግስትና በከተማው ነዋሪዎች መካከል በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ ተገልጿል። በመሆኑም በከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ማግኘት ፈታኝ እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር በከተማዋ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር በመጀመሩና ችግሩ የከፋና አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ ጉዳዩ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ በበጀት የተደገፈ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥበትም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባም በተመሳሳይ እንደ ጎንደሩ የከፋ ባይሆንም ከፍተኛ የውሃ እጥረት ችግር መኖሩ ይታወቃል፡፡ ሳምንት ጠብቀው ውሃ የሚያገኙ የመዲናችን ነዋሪዎችና አካባቢዎች(ሰፈሮች) በርካታ ናቸው፡፡ የአፍሪካ የውሃ ማማ በምትባል አገር መጠኑ ይለያይ እንጂ ከአርብቶ አደር እስከ አርሶ አደር፣ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከቆላ እስከ ደጋ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ እጥረት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ችግር መሆኑ ለሰሚው ግራ ነው ከማስባል አልፎ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያስገድድ ነው፡፡
በሌላ በኩል ውሃ አሽገው የሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፣ እንደ አሸን እየፈላ ነው ቢባል ይቀላል፡፡ ይሁን እንጂ የታሸገ የንግድ ውሃ ዋጋም እንደሌሎች ሸቀጦች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ በእርግጥ እዚህ አገር ያልተወደደ ነገር የለም፡፡ ዳቦ አንድ ከብር ተነስቶ አስር ብር ደርሷል፣ እንጀራም እንደዚሁ…ሽንኩርት…ዘይት…ነዳጅ …አሁን ደግሞ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገባ የሚመስል ውሃ፣ የእግዜር ውሃም እየተወደደብን ነው፡፡ እየተወደደ ብቻ ሳይሆን እያጠረ ነው፡፡ የተወደደውማ የንግዱ የታሸገ ውሃ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ነገር አንድ ታዋቂ የፀረ አዲስ ዓለም ሥርዓት አንቂ በአንድ ወቅት የጻፈውና በአንድ ወቅት ያነበብኩትን ፅሁፍ ደግሜ እንዳስታውሰው ያደርገኛል፡፡
ግማሽ ሊትር ውሃ አስራ ሁለት ብር፤ አንድ ሊትር አስራ ሰባት ብር፣ ሁለት ሊትር ውሃ ደግሞ ሃያ አምስት ብር ገብቷል፡፡ አስቡት እንግዲህ የአፍሪካ የውሃ ማማ በሆነችው የአፍሪካ መዲና ላይ አንድ ብርጭቆ ውሃ አስር ብር ሲሸጥ፤ ለዚያውም ሳንፈልግ በግዴታ፡፡ ምክንያቱም በብዙ የመዲናችን(የአገራችን ተመሳሳይ ነው) ሬስቶራንቶች ተመጋቢው የእግዜር ውሃ የማግኘት መብት የለውም፣ ምግቡ እንዳያንቀው መጠጣት የሚችለው የታሸገ ውሃ ገዝቶ ነው፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ አስገድደው ሲሸጡልን፡፡ ታዲያ ይኼ በእርግጥም የብዙሃኑ መሆኑ ቀርቶ ውሃም እንደ ውስኪ የሃብታሞች ብቻ ወደ መሆን እየተሸጋገረ አይደለም ትላላችሁ? እውነቴን እኮ ነው፡፡ እስኪ እኔስ የመንግስት ሰራተኛ በመሆኔ ቢያንስ ድሃ በሚለው ምድብ ውስጥ ስለሆንኩ እንደምንም ብዬ ግማሽ ሊትር ውሃ በአስራ ሁለት ብር ገዝቼ ልጠጣ እችላለሁ፡፡ ቆይ ከእኔ ያነሰ ገቢ ያላቸውስ፤ ማለቴ ይች አገር እኮ ከድሃም ያነሰ “የድሃ ድሃ” የሚባሉ ዜጎች የሚበዙባት አገር ናት፡፡ ታዲያ ቢቀር ቢቀር ውሃም “ጥቁር ውሃ”ም ይወደድብን እንዴ?
እናም “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እንዲል ያገሬ ሰው እዮሃኪም ሃጎፒያን የተባሉ የፀረ አዲሱ ዓለም አንቂ እንደሚሉት የእኛዎቹ ውሃ ሻጭ ቱጃሮችም የዓለም አቀፉ “ውሃን በሞኖፖል የመያዝ” ሴራ አካል እንዳልሆኑ በምን እርግጠኛ እንሆናለን፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ውሃን በግል ይዞታ ስር የመቆጣጠርና የህዝብ ቁጥርን በፍጥነት የመቀነስና ዓለምን ለራሳቸው ብቻ በሚመች መልኩ አፍርሶ ለመስራት ከመጋረጃው በስተጀርባ እየተካሄደ ያለ ድብቅ አጀንዳ አለ፡፡ ሴራው የኃያላን አገራት መንግስታት ድጋፍ ያለው መሆኑንም ተሟጋቹ በመረጃ ይከራከራሉ፡፡ በዓለም ባንክ ስር የሚተዳደረው “ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን” በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን በብድርና በእርዳታ መልክ የሚሰጥ በተለይም በድሃ አገራት የውሃን የግል ይዞታነት ለማስፋፋት ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በዓለም ላይ ትልቁ የገንዘብ ምንጫቸው መሆኑንም በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡ እናም ተራው የዓለም ህዝብ በአንድነት ሆ ብሎ ተነስቶ ካልተቃወመውና ካላስቆመው በስተቀር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕቅዳቸው እንደሚሳካ ያስጠነቅቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ላይ የውሃን የግል ይዞታነት የሚቃወሙ ድምጾች እየተበራከቱ መምጣታቸው የመጥፋት አደጋ ለተጋረጠበት ብዙሃኑ የዓለማችን ምስኪን ህዝብ መልካም ዜና ነው ይላሉ እዮሃኪም ሃጎፒያን፡፡ ዓላማቸውም ይኸው ነው የውሃ አቅርቦት በእነሱ ቁጥጥር ሥር ይውላል፣ ገንዘብ የሌለው ብዙሃኑ ድሃ የሚጠጣው ውሃ ስለማያገኝ በውሃ ጥም፣ የሚታጠብበትና ንጽህናውን የሚጠብቅበት ውሃ ስለማይኖረው በወረርሽኝ በሽታ እንዲያልቅ ማድረግ፤ ከዚያም እንደተመኙት “በሃብታሞች፣ ለሃብታሞችና የሃብታሞች ብቻ የሆነች አዲስ ዓለም መፍጠር(Realizing their dream of creating the New World Order)”!
ለዚህም ከሁለት ዓመት በፊት የዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ባካሄደበት ወቅት ከህንድና ከአሜሪካ የተውጣጡ የውሃ የግል ይዞታን የሚቃወሙ ፀረ ኮርፖሬታውያን ዓለም አቀፍ ጥምረቶች “የዓለም ባንክ በታዳጊ አገራት ላይ በልማት ስም ውሃ በግል ይዞታ ሥር እንዲውል የሚያደርገውን ዘመቻ እንዲያቆም እንጠይቃለን” በማለት በግልጽ ደብዳቤ መጠየቃቸውና ለዓለም ህዝብ መልዕክት ማስተላለፋቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡
እናም ብዙሃኑ ድሃ ህዝብ ኮርፖሬታውያኑ ከቃጡበት ጥፋት ራሱን በፍጥነት መታደግ ከፈለገ ከላይ እንደተጠቀሱት የህንድና የአሜሪካ የጋራ ጥምረት አባላት በንቃት ሊታገል ይገባል፡፡ ሰፊው ህዝብ እንዲህ በአንድነት ሆ ብሎ ከተነሳና ከተባበረ ደግሞ ለሰው ልጆች ሕይወትና ደህንነት ሁሌም ከኮርፖሬታውያኑ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው እኩይ ሴራቸውን በድፍረት እያጋለጡና በፅናት እየታገሉ የሚገኙት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት አርበኞችና የመብትና የደህንነት ተሟጋቾች ከጎኑ ናቸው፡፡ እናም የቀድሞው የጦር መኮንን ሚስተር ኢዮሃኪም ሃጎፒያን ግሎባል ሪሰርች ላይ በጻፉት ጽሁፋቸው “ምስኪኑ ድሃ ወገኔ ሆይ ራስህን ለማዳን ጊዜው አሁን ነው፡፡ በተባበረ ክንድህ ፈጥነህ የጥፋት ሴራ አክሽፍ!” የሚል የሕይወት አድን ጥሪ ለዓለም ህዝብ ያስተላልፋሉ፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014