በደን የተሸፈኑ አረጓዴ ተራሮችንና የለመለሙ መስኮችን ማየት ያስደስታል፤ መንፈስን ያረካል፤ እንደ ስጋጃ የተነጠፈ አረጓዴ ደን ሲያዩት ያምራል፤ ቀልብን ይማርካል። በተለይ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ወይን፣ ፓፓያ፣ ብርቱካንና ቡና ባሉ ዛፎች የተሸፈነ ደን ከሆነ ደግሞ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል። ቋሚ የገቢ ምንጭ በመሆንም ያገለግላል። ደኑ የሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች የተካተቱበት ሲሆን ደግሞ ዝርያዎቹ ለመዳህኒት፣ ለፍራፍሬ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ወዘተ. ጉልህ ጠቀሜታ ያላቸው እንደመሆናቸው ፋይዳው የበለጠ እየጎላ ይመጣል።
በኢትዮጵያ በአረጓዴ የተሸፈኑ አካባቢዎችን ማየት ብርቅ መሆን ከጀመረ በርካታ አመታትን ተሻግሯል። በተለይ በስሜንና በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ችግሩ ጎልቶ ይታያል። ይህ ደግሞ አካባቢው ለተደጋጋሚ ድርቅ መከሰት፣ለመሬት መራቆትና ለምንጮችና ወንዞች መድረቅ በምክንያትነት ይጠቀሳል።
ችግሩን ለመፍታትም በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መካሄድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። ለዚህም ነው በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት የዛሬ አራት ዓመት የአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረግ የጀመረው። ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት በአረጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏም በቅርቡ ይፋ ተደርጓል።
በአራት ዓመታት በአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል መቻሉን የሚገልጹት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን፤ እስከ ነሀሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስም በአራተኛው አረጓንዴ አሻራ መርሀ ግብር ሰባት ነጥብ0 8 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል ይላሉ። ይህም የህዝብ ተሳትፎ ያስገኘው ትልቅ ስኬት መሆኑን ያስታወቁት።
በአሁኑ ጊዜ ያልተተከሉ አምስት መቶ ሚሊዮን ችግኞች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ቀሪ ችግኞችም በቀጣይ ዝናብ በሚጀምርባቸው የአገሪቱ ክፍሎች እስከ መስከረም ወር ድረስ እንደሚተከሉም ይጠቁማሉ። ችግኝ የመትከሉ ባህል በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርፆ የዘወትር ተግባር እስኪሆን ድረስ በቀጣይም በችግኝ ተከላው ላይ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
25 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያንም ችግኝ በማፍላት፣ የችግኝ ጉድጓድ በመቆፈር እና የተተከለውን በመንከባከብ መሳተፋቸውም ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት። የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ስኬታማነት ማሳያዎች ብለውም፥ ዘመቻው ሲጀመር 40 ሺህ ብቻ የነበሩት የችግኝ ማፍያዎች አሁን ላይ ወደ 121 ሺህ ማደጋቸውን፣ በዓመት 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞችን የማፍላት አቅም መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
የችግኝ ተከላው በስፋት በመላ አገሪቱ በየዓመቱ በተከታታይ በመካሄዱ ብዙ ለውጦች መገኘታቸውን፣ ከእነዚህ መካከልም የደን ሽፋን ማድጉን፣ የፍራፍሬ ዛፎች በየቦታው መተከላቸውን፣ የመሬት መሸርሸር እየቀነሰ መሄዱንና የግብርና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስትሩ በአብነት ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው አራተኛው የአረጓዴ አሻራ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት በአረጓዴ አሻራ ያስገኘችው ውጤት ስኬታማ ነው። የተተከሉ ችግኞች የአየር ንብረት ተፀእኖን በመቋቋምና የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
ጥቂት ሚሊዮኖች ችግኞችን መትከልን እንደ ድል በምትቆጥር ዓለም ላይ በአራት ክረምት 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓላማን ማሳካት እንደሚቻል አሳይተንበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሀገራችን አረንጓዴ ዐሻራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ ሁለት ወሳኝ እድሎችን ፈጥሯል ይላሉ። አንደኛው በትልቁ አስበን ከተባበርን በትልቁ ማሳካት እንደምንችል ምስክር ሆኖናል ፤ሁለተኛው ለብልጽግና መሠረት የሚሆን ባህል መፍጠር ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።
ችግኝ የመትከል ባህል ሲውል ሲያድር በምግብ ራሳችንን እንድንችል፣ ግድቦቻችን ዘላቂ ዝናብ እንዲያገኙ፣ ለም አፈራችን እንዳይሸረሸር ያደርጋም ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በሀገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠር ስኬታማ ቢሆንም፣ አሁንም ብዙ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል።
ባለፉትን ጥቂት ሳምንታት ብቻ በዓለም ዙሪያ የተስተዋሉት የጎርፍ አደጋ፣ የደን ቃጠሎ፣ ሀይለኛ ማዕበል እና ያልተለመደ ሙቀትን የመሳሰሉ ክስተቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ዓይነተኛ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል። የአፍሪካ ቀንድን ያጠቃው ድርቅም የዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳሉት፤ በኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ የውሃ ምንጮችን አድርቋል፤ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎችም የድርቅ አደጋን አስከትሏል ። አሁን ላይ ዓለም እየተሰቃየ ያለበትን ይህን ችግር ለመፍታት ከስብሰባዎች ያለፈ ተግባራዊ መፍትሄ መውሰድ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በ2011 ዓ. ም ላይ ተፋሰስን ለማልማት፣ የደን ሽፋኗን ለማሳደግ፣ ኢኮቱሪዝምን ለማስፋፋት እና የከተሞቿን የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን ጀምራለች። እንዲህ ዓይነቱ ተግባራዊ መፍትሄ በመውሰዱ ኢትዮጵያ ውጤታማ ሆና ትጠቀሳለች።
ሀገሪቱ ለአራት ዓመታት በዘለቀው ዘመቻ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ወጥና ብትነሳም፥ ዜጎቿ 25 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ካስቀመጡት ግብ በላይ ፈጸመዋል። ለችግኝ ተከላ የሚያስፈልጉ ቦታዎችን በመምረጡ እና ለተከላ በማዘጋጀቱ ረገድም የታየው እምርታም ሌላው የሚደነቅ ተግባር ነው። በዚህ ስኬት ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
አሁንም ብዙ ስራ ቢጠበቅም በሀገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠሩ ረገድ ዘመቻው እንደተሳካ ጥርጥር የለንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞች አሁን ላይ የአረንጓዴ ስፍራ አስፈላጊነትን ተረድተው ቦታ እያዘጋጁለት መምጣታቸው ለተፈጠረው አረንጓዴ ባህል ማሳያ ነው ብለዋል። ይህ አረንጓዴ ባህል ለቀጣዩ ትውልድም የሚቆይ መሆኑንም አንስተዋል።
አረንጓዴ ባህልን ከመፍጠር ባለፈ ዘመቻው ለ767 ሺህ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ያበረከተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉም ነው የተናገሩት። ይህ የኢትዮጵያ የችግኝ ተከላ ጥረት ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሰበብ የሆነውን የበካይ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ መሆኑን አስታውቀዋል።
የታዳሽ ሃይል በሆኑት የውሃ፣ ንፋስ፣ ፀሃይ እና የእንፋሎት የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የምታውለው መዋዕለ ንዋይም ሌላው የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በበኩሏ እየተወጣች የምትገኘው ሀላፊነት መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።
አፍሪካ ብሎም ዓለም ተፅዕኖው እየከፋ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እንዲህ ዓይነቱን ተግባራዊ መፍትሄ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይ የአፍሪካ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ላይ ለሚወያዩ ስብሰባዎች መዋዕለ ንዋያቸውን ከሚያፈሱ ይልቅ፥ ለችግኝ ተከላ ስራዎች እንዲያውሉ ጠይቀዋል። የአየር ፀባይ ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ከኮንፈረንስ እና ከጉባኤዎች ባሻገር ተጨባጭ ተግባርን የሚጠይቅ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ባለፉት ሳምንታት የታዩ ክስተቶች የአየር ፀባይ ለውጥ እየተከሰተ ስለመሆኑ ካላሳመኑን ሌላ ምንም ነገር ሊያሳምነን አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሀገራት ጎርፍ፣ ሰደድ እሳት፣ ኃይለኛ አውሎ ንፋስ፣ ያልተጠበቀ ሙቀት፣ በረሃማነት እና ሌሎች ከፍተኛ የአየር ፀባይ ለውጦች እየደረሰባቸው እንደሆነ ነው የገለጹት።
እነዚህ በተደጋጋሚ እና በከፍተኛ መጠን የሚከሰቱ የአየር ፀባይ ለውጦች በሰው ልጅ አኗኗር እና ጤና ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው። እዚሁ ቅርባችን የሚገኙ የምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እየተጠናቀቀ ባለው አመት ባገጠማቸው የአየር ፀባይ ለውጥ ለድርቅ መዳረጋቸውን፣ በሀገራችንም በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የአየር ፀባይ ለውጥ የውኃ ምንጮች እንዲደርቁ እና ድርቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
የአየር ፀባይ ለውጥ በሰው ልጆች ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ዛሬ እንደ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እውነታውን የምንኖርበት ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሰናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጠቁመው ፤ችግኞችን በስፋት ሁሌም መትከል የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ቁርጠኝነት እና ንቁ ተሳትፎን ይፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በሁሉም ደረጃ የሚገኙትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማንቀሳቀስ ውጤታማ የሆነችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርም የተፋሰስ ልማት ላይ አዎንታዊ ለውጥን ለማምጣት፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎችን ለማስፋት፣ የኢኮ-ቱሪዝምን ለማጠናከር እና ከተሞችን አረንጓዴ ለማልበስ ታስቦ የተጀመረ ነው።
ለዚህም በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለመላው ኢትዮጵያውያን በቀረበው ጥሪ መሠረት በችግኝ ተከላው ከ25 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ተሳትፈዋል። በዚህም በየዓመቱ ለመትከል ከታቀዱ ችግኞች በላይ በመትከል በአራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል።
የአየር ፀባይ ለውጥ ጫናን በጋራ ለመከላከል የአፍሪካ ሀገራት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የወሰደችውን ዓይነት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ውጤት የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አመልክተው፣ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በፍራፍሬ ችግኞች ላይ ማተኮር ይኖርብናል የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል። በቀጣይ የአረጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ለገበያ በሚውሉ ችግኞችና ጥራት ላይ በማተኮር ስንዴ ብቻ ሳይሆን እንደ ወይን፣ አቮካዶና ሻይ ቅጠል ያሉ ምርቶች በስፋት ለወጪ ገበያ ማቅረብ እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል ።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2014