“ታሪክ ማለት የሰው ልጅ ስለ ራሱ የሚያውቅበት ግላዊ ዕውቀት ነው… ሰዎች ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ለማወቅ የሚያስችለው ብቸኛው ፍንጭ ሰዎች ከዚህ ቀደም የሠሩት ሥራ ነው። ስለሆነም የታሪክ ዋነኛው ፋይዳ ̔ሰው ምን ሠራ?҆ የሚለውን ለእኛ ለሰው ልጆች ማስተማርና በዚህም ‛ሰው ምንድነው?҆ የሚለውን እንድናውቅ ማድረግ ነው” ይለናል አር. ጂ. ኮሊንግውድ የተባለ የታሪክ ሊቅ። አባባሉ የታሪክን ትክክለኛ ምንነትና ፋይዳ በሚገባ የሚያመላክት ነው።
ምክንያቱም አላዋቂዎችና የትንሽነትና ታህተ ሰብዓዊነት፣ የአጥንት ቆጠራና የኢ-ምክንያታዊና ግዑዛዊ መንገኝነት ፖለቲካ መስራችና አቀንቃኝ የሆኑት ትሕነግና መሰሎቻቸው እንደሚሉት ታሪክ ተራ ተረት ተረት ሳይሆን የፈለጉትን ማድረግና መሆን እንደሚቻል ሰዎች በተግባር መሆናቸውንና መቻላቸውን የሚያረጋግጡበት መንገድ ነው። ታሪክ ዛሬን ከትናንትናና ከወደፊቱ ጋር የሚያገናኝ፣ የአሁኑና መጭው ትውልድ መሆንና ማድረግ እንደሚቻል በወሬ ሳይሆን በድርጊት የሚማርበት ህያው የድርጊት ቤተ ሙከራ ነው።
ይህንን የታሪክ እውነታ ይዘን የሃገራችንን ታሪክ ስንመረምር እጅጉን ደስ የሚያሰኝና የሚያኮራ የታሪክ እውነትን እናገኛለን። ምክንያቱም ታሪካችን ሁሉ የአሸናፊነትና የመቻል ነውና! ከጥንት ከቅድመ ዓለም ጀምሮ እስከ የቅርብ ዘመኖቹ አድዋና የፋሽስት ወረራ ለሦስት ሺ ዓመታት በኢትዮጵያ ነጻነት ላይ ደጋግማ የዘመተችው ኢጣሊያ፣ አስራ ስድስት ጊዜ ሞክራ አስራ ስድስት ጊዜ የተሸነፈችው ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ፣ በኦቶማን ቱርክም ሆነ በዚያድባሬዋ ሶማሊያ… ክብሯንና ነጻነቷን ለመድፈር በሞከረ ማንኛውም ኃያል ነኝ ባይ ወይንም እብሪተኛ ምድራዊ ኃይል ኢትዮጵያ በታሪኳ ተሸንፋ አታውቅምና። ምክንያቱም እኛ ማድረግ ፈልገን ያልቻልነው፤ የተሸናፊነት ታሪክ የለንምና!
ታሪክ አሸናፊነትን በተግባር የምንማርበት የመቻል ቤተ ሙከራ ነው፣ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ማድረግ የቻሉትን እኛም ማድረግ እንችላለንና እኛም ዛሬ የገጠሙንን ፈተናዎች ሁሉ እያሸነፍን በመቻል ጎዳና ላይ እንገኛለን። ለዚህ ደግሞ ከገዛ ማህፀኗ ተወልዶ “ክብሯን ረግጨ በኃይል አንበርክኬ እኔ ብቻ እገዛታለሁ፣ ካልሆነ አፈርሳታለሁ” ብሎ በወጋን አሁናዊው ጠላታችን ትሕነግና ሌሎች ተባባሪዎቹ ላይ እያስመዘገብን የምንገኘው ድል አንዱ ማሳያ ነው። በአያሌ መሰናክሎችንና የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን ሴራ አሸንፈን ከሰሞኑ በድል ያከናወንነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሊትና ሁለተኛ ተርባይን የኃይል ማመንጨት ሥራም ሌላው የአሸናፊነታችን ትልቅ ማረጋገጫ ነው።
የአሸናፊነት፣ የነጻነትና የጀግንነት አኩሪ ታሪካችን ሁለ ነገራችን የተመሰረተበት፣ ማንነታችን የተገነባበት ሥጋና ደማችን፣ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን አጠቃላይ ሕዝባዊ ሥነ ልቦናችን የተሠራበት፣ በየትኛውም ጊዜ የማይለወጥ፣ በማንኛውም ጊዜ የማያስስ የታላቋ ሃገራችን የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ሥሪት ነው። እኛም አሁን እንደአባቶቻችን በማሸነፍ ላይ እንገኛለን። ከምንም በላይ ታሪክ ሥነ ልቦና ነውና አባቶቻችን ባወረሱን የአሸናፊነት ሥነ ልቦናና የመቻል ውርስ በዚህም በዓለም ላይ ተከብረው እኛንም አስከብረው እንደኖሩ ሁሉ፤ በክብር ኖረው በክብር እንዳኖሩን ሁሉ እኛም ከሃዲውንና ዋናውን አሁናዊ የህልውና ጠላታችን ትሕነግን ጨምሮ የክብራችንና የነጻነታችን ጠላት የሆኑ ማናቸውንም የዘመናችንን ጠላቶች በማሸነፍ እንደአባቶቻችን በክብር መኖር ጀምረናል። እንደአባቶቻችን አንድ ላይ ተባብረን ጠላቶቻችን በመመከትና የታላቅነት መንገዳችንን ዓባይን እየገነባን በአንድነት ወደአሸናፊነት ወደታላቅነት ወደዓባነት እያመራን እንገኛለን።
የአሸናፊነታችንና የድላችን ሁሉ ሚስጥር ደግሞ አንድነታችን ነው። እጅግ የቅርቡንና በዓለም ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የሰው ልጅ ፍጡር ዘንድ እንድንከበርና እንድንኮራ ያደረገንን አንዱንና ዋነኛውን የነጻነትና የክብር ታሪካችን በማሳየነት በማንሳት ልጀምር። እብሪተኞች እንደ ሰው የማይቆጥሩት የጥቁር ህዝብ “ምንጊዜም የበላይ ነን” ብሎ የሚያምነውን የነጭ ወራሪ በጦር ሜዳ ገጥሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፍንና እናም ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን ከዚያም አልፎ ለመላው ሰው ልጆች ሁሉ የሰውነት ክብርን ያጎናጸፈውን አኩሪ ታሪክ የሠራነው በአንድነታችን ነው። ይህም አንድነታችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ለመላው የሰው ዘር በሙሉ፣ ከራሳቸው ከነጭ ዘር የተገኙ ጭቁን ህዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ምክንያት፣ ድል አመላካች፣ የአሸናፊነት ምልክት እንድንሆን አድርጎናል።
እንደአንድ ልብ የመከረ ልባችን፤ በአንድነት የቆመ ኢትዮጵያዊ ምርኩዛችን፣ የተባበረ ክንዳችን ሁልጊዜ የአሸናፊነታችንና የክብራችን የታላቅነታችን ምንጭ ነው። እናም በአሁኗ ኢትየጵያ የምንገኝ እኔና የእኔ ትውልድ ጀግንነታችንና ኩሩነታችንን አስጠብቀን ለመቀጠል እንደ አባቶቻችን በአንድነት መመከትና በጀግንነት ዋጋ በመክፈል የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅብናል። ልክ የህልውና ጠላታችን ትሕነግን በተባበረ ክንድ አዋርደን እንደመለስነው፣ ልክ በተባበረ ክንድ ዓባይን በራሳችን አቅም እየገነባንና ድል እየተቀዳጀን እንደምንገኘው በአንድነት መቆም ስንችል ነው እንደ አባቶቻችን አኩሪ ታሪክ መስራት የምንችለው። በዚህ መንገድ ነው ወደቀደመ የታላቅነት የ “ዓባይነት” ታሪካችን መመለስ የምንችለው።
በተከፋፈለ ግንጥል ማንነታችን ሳይሆን በሙሉ ኃያል ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ኢትዮጵያዊ ክብራችንን ዝቅ የሚያደርጉ ነገሮችን ሁሉ እንደ አባቶቻችን በጀግንነት ታግለን በድል መወጣት ስንችል ነው እኛም በኩራት ኢትዮጵያም በክብር መኖር የምትችለው። ትውልዱ እንደቀደምቶቹ አባቶቹና እናቶቹ ጀግና ነኝ ለማለትና ኩሩ ሆኖ ለመገኘት በምኞት ሳይሆን እንዲህ እንደአሁኑ በተግባር ማድረግ የሚገባውን አድርጎ መገኘት፤ የራሱን ዘመን ሥራ ሠርቶ ጀግንነትን ፈጽሞ እንደ አያት ቅድመ አያቶቹ፣ እንደ እናት አባቶቹ አኩሪ ታሪክ ፈጽሞ በኩራት በክብር ለመኖር የሚያስችለውን ታሪክ አድርጎና ሆኖ መገኘት አለበት። በዓባይ ላይ ያሳየነውን ኢትዮጵያዊ አንድነት አጠናክረን ከቀጥልን ደግሞ አሸናፊነትን ብቻ ሳይሆን የጥንቱን ዓባይነታችን የማንጎናጸፍበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። ኢትዮጵያም ዛሬም ጠላቶቿን አሸንፋ በክብርና በነጻነት ከፍ ብላ ትኖራለች! በዓባይ አንድ ሆናለች፣ በአንድነቷም ዓባይ ሆና ለዘላለምም በክብር ትኖራለች!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም