በሰፊ ህዝባዊ ንቅናቄና ድጋፍ የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የታየበት መቀዛቀዝ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን እንደሚያስከትል ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ጫናዎቹን ለመቀነስ ከተፈለገ ደግሞ በሙሉ አቅም ሥራን ማስቀጠልና ህዝባዊ ድጋፉን ማጠናከር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
የግድቡን እውን መሆን ተከትሎ ህዝቡ በገንዘቡም፣ በዕውቀቱም፣ በጉልበቱም፣ በሞራሉና በጸሎቱ ጭምር ሲረባረብበት እንደነበረ የሚያስታውሱት፣ የምሥራቅ ናይል የቴክኒክ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በዚህ መልኩ ህዝቡ ግድቡን በባለቤትነት መያዙም ለግድቡ የገቢ ምንጭ፣ ለዲፕሎማሲ ሥራውም አቅም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን ለማረም የተወሰደው ዕርምጃ በግድቡ ግንባታ ላይ መቀዛቀዝን አስከትሏል፡፡ እንደ አቶ ፈቅ አህመድ ገለጻ፤ ይሄን ዓይነት መሰረታዊ ለውጦች ሲከሰቱ መቀዛቀዙ የማይቀር ነው፡፡
ምክንያቱም በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ከነበሩት ሁለት ዋነኛ ኮንትራክተሮች ውስጥ የአገር በቀል ሆኖ ሲሠራ የነበረው ኮንትራክተር ወጥቷል፡፡ ይህ ሲሆንም ጥናት ይደረጋል፤ ውሳኔ ይወሰናል፤ በመጨረሻም ሥራ አቁሞ እንዲወጣና እርሱን የሚተካ ሌላ ኮንትራክተር ተቀጥሮ ሥራ እንዲጀምር ይደረጋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ደግሞ የግንባታ መቀዛቀዝ መከተሉ የግድ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ትላልቅ የግንባታ ሥራዎች መዘግየታቸው የታወቀ ነው፡፡
በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በተለይ ሥራውን ለማፋጠን ሲባል ፕሮጀክቱ በትይዩ ጥናት ዲዛየኑ እየተሠራ የቅድመ ኮንስትራክሽን ሥራዎች እንዲሠሩ ታቅዶ ወደሥራ የተገባ እንደመሆኑ፤ ውሃው ከሚወርድበት አካል ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሜቴክ ሥራውን በተያዘው የጊዜ ገደብና በተያዘው የጥራት ደረጃ አለማጠናቀቅ ለመዘግየቱ ጉልህ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡
ከሜቴክ ጋር የተያያዘውን ችግር በመፍታቱ ሂደት ደግሞ በኮንትራክተሩ በኩል ያለው ሥራ መከናወን ባለመቻሉ በግንባታው ላይ መቀዛቀዝን አስከትሏል፡፡ ሆኖም በተለያየ መልኩ እንደ አገርም ሆነ ዓለም የኢንጂነሪንግ ውጤት ተደርገው የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች ግንባታዎች መጓተት የተለመደ እንደመሆኑ፤ የህዳሴው ግድብም ከዚህ ተለይቶ መታየት አይገባውም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርገው ፕሮጀክቱ የህዝብ እንደመሆኑ የተፈጠሩ ችግሮች ለህዝቡ ግልጽ ሳይሆኑ በመቆየታቸው አሁን ላይ ችግሩ ሲታወቅና ችግሩን ለመፍታት በተደረገው ዕርምጃ ሂደት ላይ የግድቡ መቀዛቀዝ ሲከተል በህዝቡ ላይ የቅሬታ መንፈስ ማሳደሩ ነው፡፡
አቶ ፈቅአህመድ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ለፕሮጀክቶች መዘግየትና ለወጪ መዳረግ የሚጋብዙ ያልተጠበቁ (የፋይናንስ፣ የቴክኒክ፣ የፖለቲካና መሰል ጉዳዮች) ሁኔታዎች ይገጥማሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ የተጠና ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ላይ የተሠሩ ትላልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች (የጊቤ ሦስት ግድብ የተካተተበት) የተጀመሩበትን ጊዜ፣ እንዲጠናቀቁ በእቅድ የተቀመጠበትን ጊዜ፣ ሲጀመር ይወጣበታል ተብሎ የተገመተውን የገንዘብ መጠን፣ ግድቡ የተጠናቀቀበትና ሲጠናቀቅ የወጣበትን ገንዘብ የዳሰሰ ጥናት ተከናውኖ ነበር፡፡ ጥናቱም ከጊዜም ሆነ ከወጪ አኳያ በአማካኝ ከ40 እስከ 60 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ አመላክቷል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም በከርሰ ምድርም ሆነ በኮንትራርከር በኩል የገጠመው ችግር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ኢንጂነር ክፍሌ እንደሚናገሩት ደግሞ፤ የተፈጠረውን መጓተትና መጓተቱ የፈጠረውን ችግር ለማረም በተወሰደው ዕርምጃ ምንም እንኳን በግንባታው ላይ መቀዛቀዝ ቢታይም ፕሮጀክቱ ከሜቴክ ላይ መወሰዱ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ያገርን ኢኮኖሚ ያፋጥናሉ የተባሉትን ያክል፤ በስርዓት ካልተያዙ የአገርን ኢኮኖሚ የመጉዳት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በሌሎች አገሮችም ይሄው ታይቷል፡፡ መንግሥትም ይሄን ዕርምጃ ባይወስድ ኖሮ ፕሮጀክቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማናጋት አቅሙ ከፍተኛ ነበር፡፡ አቶ ፈቅ አህመድም ይሄን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዕርምጃው ባይወሰድ ከሚደርሰው ችግር ባለፈ፤ እስከአሁን ባለው መዘግየት በራሱ የሚደርስ ጉዳት ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ይህ ግድብ አልቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በዓመት እስከ አንድ ቢሊዬን ዶላር ገቢ እናገኛለን የሚል ነበር፡፡ የግድቡ ግንባታ በዘገየ ቁጥር በሙሉ ኃይሉ የሚያመነጭበት ጊዜም በዚያው መጠን ይጨምራል፡፡ ይህ ደግሞ አይደለም ይሄን ዓይነት ችግር ገጥሞት እያለ በጥናቱ መሰረት እንኳን ቢሆን አገሪቱ ለግድቡ ተጨማሪ ከ40 እስከ 60 በመቶ ወጪ እንድታወጣ ከማድረጉ ባለፈ፤ በእያንዳንዱ የዘገየበት ዓመት ያስገኝ የነበረውን የአንድ ቢሊዬን ዶላር ገቢ ያሳጣታል፡፡
አቶ ፈቅአህመድ እንደሚሉት፤ ግድቡ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ችግር እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ የህዝቡ ድጋፍ ከፍተኛ ነበረ፡፡ ህዝቡ ግድቡን በባለቤትነት ይዞት በሁለንተናዊ መልኩ ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጥ ነው የቆየው፡፡ ዲፕሎማሲውን ከማገዝ አኳያም ህዝቡ ትልቅ ሚና የነበረው ሲሆን፤ ይህ የህዝብ ድጋፍ ለግድቡ መፋጠንም አግዟል፤ ዲፕሎማሲያዊ ሥራውና ድርድሩም ለተደራዳሪዎች ትልቅ አቅም ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በግንባታው ሂደት የችግሮች መከሰት ብቻ ሳይሆን ችግሮችን ከህዝቡ ደብቆ ይዞ የተቆየበት አካሄድ ህዝቡ ቅር እንዲሰኝ አድርጓል፤ በመጨረሻ የተወሰደው ዕርምጃም ለግድቡ ሥራ መቀዛቀዝ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ምሑራኑ እንደሚሉት፤ ይህ የመቀዛቀዝ ሂደትና የህዝብ እምነት መሸርሸር ደግሞ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖዎች ያሉት ሲሆን፤ በተለይ የህዝቡ ድጋፍ በዚህ መልኩ ተቀዛቅዞ የሚቀጥል ከሆነ ለግድቡ ከሚሆን ፋይናንስ ጀምሮ እስከ ዲፕሎማሲ ሥራው ድረስ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም የህዝቡ ተነሳሽነት ወደቀድሞው መመለስ ይኖርበታል፡፡
ለዚህም አሳማኝ ተግባር በማከናወን የህዝብ ስሜት ለማስተካከል ትልቅ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ በዚህ መልኩ የህዝቡን ስሜትና ድጋፍ መመለስ ከተቻለ በፋይናንስ ብቻ ሳይሆን፤ በዲፕሎማሲው ጉልበት ስለሚፈጥር ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች አጀንዳ የማስቀመጥ፣ አቅጣጫ የማስያዝና ውጤቱንም እስከመወሰን የሚያደርስ ከፍተኛ አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ያለው የግድቡ ሥራ በዚሁ አኳያ መታየት ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
ወንድወሰን ሽመልስ