በመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ፕሮግራም (ዩኤንኢፒ)ሀገራችን ኢትዮጵያን ለአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ከተጋለጡ 10 ሀገራት አንዷ መሆኗን ይገልጻል። መልሶ የአየር ንብረት ለውጥን ከማያባብሱ ዜጎች ተርታ ያሰልፋታል። ኢትዮጵያውያን በአማካኝ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ግሪንሀውስ ጋዝ 1.3 ሜትሪክ ቶን ወይም 1300 ኪግ ነው፣ በአንጻሩ የአሜሪካውያን 20ሺህ ኪግ፤ ኩየታውያን ደግሞ 60ሺህ ኪግ ግሪንሀውስ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ። የቻይናና የሕንድማ አይነሳ። ይህ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ለከባቢ አየር ሙቀት መጨመር እዚህ ግባ የሚባል ድርሻ የሌላቸው ሀገራት የበለጸጉ ሀገራት ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ ወደ ከባቢ አየር በለቀቁት ከፍተኛ መጠን ያለው ግሪንሀውስ ጋዝ በተፈጠረ የአየር ንብረት ለውጥና የከባቢ አየር ሙቀት የተነሳ ለተደጋጋሚ የዝናብ ዕጥረት ፣ ለድርቅና ርሀብ ተዳርገዋል።
ሀገራችን ከ1966 ዓም ጀምሮ በየአስር አመቱ ይጎበኛት የነበረው ድርቅ ከቅርብ አመታት ወዲህ በየአመቱ የሚከሰት ሆኗል። ዘንድሮ እንኳ በቦረና፣ በሱማሌና በደቡብ ክልል የተከሰተው ድርቅ በእንስሳትና በአርብቶ አደሩ ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጉዳት አይተናል። በመንግስት ርብርብ ድርቁ በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት ባያስከትልም የህልውናቸው መሠረት የሆኑ እንስሳቱ ላይ ግን የከፋ ጉዳት አድርሷል ። መጠኑ ቢለያይም እንደ 1966ቱ፣ 77ቱና 87 ሰዎች በርሀብ እንደ ቅጠል አልረገፉም። በአናቱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገቱን የሚመጥን ምርት ባለመመረቱ፤ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ሰፊ ክፍተት ባለመጥበቡ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ህወሓት በከፈተው ጦርነትና እዚህም እዚያም በተከሰቱ ቀውሶች፤ በኮቪድ 19ና ራሽያ ዩክሬንን በመውረሯ በተፈጠረ የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የተነሳ በከተሞች ሳይቀር ድምጽ አልባ ርሀብ ተከስቷል ። ኑሮው አልቀመስ ብሏል።
ሀገራችን ዛሬ ለምትገኝበት ውስብስብ ችግር በርካታ ምክንያቶችን መደርደር ቢቻልም ዋነኛዎቹ ግን ሁለት ናቸው። እነሱም አበክረን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አለመገንባታችን፤ የተፈጥሮ ሀብታችንና የሰው ኃይላችንን በአግባቡ አቀናጅተንና አልምተን አለመጠቀማችን ናቸው። ሰፊ ለም መሬት፣ አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ የከርስ ምድር ውሃ፣ ዝናብና ወደ 123 ሚሊየን ከሚገመተው ሕዝብ 70 በመቶው ወጣት ስለሆነ ከምግብ ዋስትና አልፈን የተትረፈረፈ ምርት አምርተን ኢንድስትሪውን፣ የአገልግሎት ዘርፉንና የውጭ ንግዱን ይዘን መነሳት እየቻልን ዛሬም እርዳታን የምንቀላውጥ መሆናችን አንገት ያስደፋል።
ከለውጡ ወዲህ ግን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ከግብርና ልማቱ ፣ ከአካባቢ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ጋር መሳ ለመሳ በማስኬድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልተጠበቀ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል። በ2025 ዓም ደግሞ የግሪንሀውስ ጋዝ ልቀቷን ወደ ዜሮ ለማውረድ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ። ባለፉት አራት አመታት 25 ቢሊየን ችግኞችን የተከለች ሲሆን የኤሌክትሪክ ፍላጎቷንም ከታዳሽ ኃይል ማለትም ከግድብና ከንፋስ እያገኘች ሲሆን በቀጣይም ከእንፋሎት ለማመንጨትም እየሰራች ትገኛለች።
አገራችን በታሪኳ ከፈጸመቻቸው እየፈጸመቻቸው ካሉ ግዙፋን ፕሮጀክቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አንድ ላይ ቢደመሩ የ” አረንጓዴ አሻራ“ን ያህል ክብደት አልሰጣቸውም። የህዳሴውም ሆነ የሌሎች ታላላቅ ግድቦች ህልውና እንዲሁ 80 በመቶ አገሬው ኑሮ የተመሰረተበት ግብርና እጣ ፈንታ የሚወሰነው ዛሬ በትጋት በምንከውነው የአካባቢ ወይም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ነውና። በቀደሙት ሶስት አመታት ከ18 ቢሊዮን በላይ አገር በቀል ችግኞችን ለዛውም ከሞላ ጎደል ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረጉ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች መትከል ተችሏል። ከተተከሉ ችግኞች መካከል እንደ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ አፕል፣ ፓፓየ፣ ሙዝ እንዲሁም ቡና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በአራቱም ዙር ከ90 ሚሊየን በላይ ሕዝብ በችግኝ ተከላው ተሳትፏል።
ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን፣ የአለም ሙቀት መጨመርን ወይም የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችን ለመፍታት የማይተካ ሚና አለው። ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና ጉድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ርሀብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሀ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት፣ ስራ አጥነት ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን፣ የጸጥታና የደህንነት ችግርን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል። ለዚህ ነው ችግኝ ተከላን የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ማስተር ኪይ ነው የምለው።
በየአመቱ በአገራችን ከ92ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ደን ይመነጠራል። ይጨፈጨፋል። በዚህ የተነሳ የደን ሽፋናችን ከ50 አመታት በፊት ከ35 በመቶ ከነበረበት ደረጃ ወደ ሶስት በመቶ አሽቆልቁሎ ነበር። ለዝናብ እጥረት፣ ለድርቅና ለከባቢ አየር ሙቀት ተዳረግን። በየአመቱ ምርታችን ከ10 በመቶ በላይ መቀነስ ጀመረ። በየአመቱ ከ35 እስከ 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይቀንሳል። ሆኖም ባለፉት አራት አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት በተከናወኑ የችግኝ ተከላና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የደን ሸፋኑን ወደ 17 በመቶ ማገገሙ ይበል የሚያሰኝ ነው።
የበጋ ስንዴ፣ የኩታ ገጠም ግብርናን ፣ በተወሰነ ደረጃ ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂና የሜካናይዜሽን እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመስራት፣ በተለይ ከአለፈው አመት ጀምሮ የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ግብ መጣሉ የአተያይ ለውጥ በማምጣቱ ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብርና ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል። ለዚህ ነው ተስፋ ሰጭ ጅምር እውቅና መስጠት የሚያስፈልገው።
ችግሮቻችንን ሁሉ ፈታተን፣ በታትነንና አገላብጠን ብንመረምራቸው አብዛኛዎቹ ከአንድ ቅርጫት የሚገኙ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ካለመንከባከብ፣ ካለመጠበቅና ካለማልማት ቅርጫት። የአለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የተፈጥሮ ሀብታችን እየተጎሳቆለ በመምጣቱ ማለትም መሬታችን የተራቆተ ፣ ዝናባችን የአጠረና የተቆራረጠ በመሆኑ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃችን በመመናመኑ ግብርናው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም።
በዚህ የተነሳ በግብርና ላይ የተመሰረተው የዜጋው ህይወት፤ የአገሪቱ ልማት ችግር ላይ ወድቋል ። ይህ የሀብት ውስንነትን ፈጥሯል። በዚህ የተነሳ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ከአመት አመት እየተባባሱ መጡ። እነዚህን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ የተፈጥሮ ሀብታችን እንዲያገግም ሌት ተቀን መሰራት አለበት። መሬት ማገገም፣ ውሃ መያዝ አለባት። ይህ ደግሞ እውን ሊሆን የሚችለው ችግኝ በመትከልና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስፋት በማከናወን ነው።“ አረንጓዴ አሻራ“ የበሽታውን ምልክት ከማከም ይልቅ መነሻውን በማያዳግም ሁኔታ የመፈወስ አቅም እንዳለው በማመን ነው፤” አረንጓዴ አሻራ ! “ የእንቆቅልሾቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ (ማስተር ኪይ) የምለው።
ለዚህም ነው 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ከቁጥርና ከአኃዝ በላይ በየአመቱ የሚከሰተውን ድርቅ፣ የበርሀማነት መስፋፋት፣ የአፈር መከላት፣ የዝናብ ዕጥረትና መቆራረጥ፣ የገጸና የከርሰ ምድር ውሃ መቀነስን በመከላከል፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ከተመጽዋችነት የመላቀቅ የማሪያም መንገዳችን፤ ሉዓላዊነታችን ሙሉኡ ማድረጊያችን፤ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማርሽ መቀየሪያ፤ አስተማማኝ ሰላም ማስፈኛችን፤ እውነተኛ አንድነትና እርቅ ማረጋገጫችን፤ ወዘተረፈ ስለሆነ አረንጓዴ አሻራ ከአኃዝ በላይ ከመሆኑ ባሻገር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉትም እንደ ሀገርና ሕዝብ ብቸኛ መዳኛችን ነው። የአራት አመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን መጠናቀቅ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ያስተላለፉት መልዕክትም የአረንጓዴ አሻራው 25 ቢሊየን ችግኝ ተተክሏል ከሚለው የአኃዝ ዜና በላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአራት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ መጠናቀቅን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ በአረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ከችግኝ ማፍላት እስከ እንክብካቤው 25 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን፤ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠር ስኬታማ መሆኑን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘገባ ያወሳል። ኢትዮጵያ የከተሞቿን የአረንጓዴ ሽፋን ለማሳደግ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻን መጀመሯን፤ ለአራት ዓመት በቆየው ዘመቻ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ወጥና ብትነሳም፤ ዜጎቿ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ካስቀመጡት ግብ በላይ ፈጽመዋል። የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው ሲጀመር 40 ሺህ ብቻ የነበሩት የችግኝ ማፍያዎች አሁን ላይ ወደ 121 ሺህ ማደጋቸውንና በዓመት ሰባት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ የማፍላት አቅም ላይ መደረሱን ፤ አረንጓዴ ባህልን ከመፍጠር ባለፈ ዘመቻው ለ767 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ያበረከተውን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦም ማንሳታቸውን የኤጀንሲው ዘገባ ያመለክታል።
ከዚህ ባለፈ ለችግኝ ተከላ የሚያስፈልጉ ቦታዎችን በመምረጡ እና ለተከላ በማዘጋጀቱ ረገድም የታየው ውጤት አበረታች መሆኑን፤ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከተሞች አሁን ላይ የአረንጓዴ ስፍራ አስፈላጊነትን ተረድተው ቦታ እያዘጋጁ መሆኑ ለተፈጠረው አረንጓዴ ባህል ማሳያ ነው። የአረንጓዴ አሻራ ባህል ለቀጣዩ ትውልድም የሚቆይ መሆኑን፤ በዚህ ስኬት ውስጥ የፖለቲካ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ቁልፍ ሚና መጫወቱን፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ በርካቶች መሳተፋቸውን፤ አሁንም ብዙ ሥራ የሚጠበቅብን ቢሆንም ንቅናቄው በአገሪቱ ፍሬ እንዳፈራ ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል።
ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት ብቻ በዓለም ዙሪያ የተስተዋሉት የጎርፍ አደጋ፣ የደን ቃጠሎ፣ ኃይለኛ ማዕበል እና ያልተለመደ ሙቀትን የመሰሉ ሁኔታዎች ለዓየር ንብረት ለውጥ ዓይነተኛ ማሳያዎች መሆናቸውን፤ የአፍሪካ ቀንድ ያስተናገደው ድርቅ የዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት መሆኑን፤ በኢትዮጵያም የዓየር ንብረት ለውጥ የውሃ ምንጮችን ማድረቁን በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎችም የድርቅ አደጋን ማስከተሉን፤ አሁን ላይ ዓለም እየተሰቃየ ያለበትን ይህን ችግር ለመፍታት ከስብሰባዎች ያለፈ ተግባራዊ መፍትሄ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማሳሰባቸውን ኤጀንሲው ዘግቧል።
ሀገሪቱ የታዳሽ ኃይል በሆኑት የውሃ፣ ንፋስ፣ ፀሐይ እና የእንፋሎት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የምታውለው መዋዕለ ንዋይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በበኩሏ እየተወጣች የምትገኘው ኃላፊነት መሆኑን፤ አሁንም ብዙ ሥራ ቢጠበቅም በአገሪቱ አረንጓዴ ባህልን በመፍጠሩ ረገድ ዘመቻው እንደተሳካ፤ አፍሪካ ብሎም ዓለም ተፅዕኖው እየከፋ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ልክ እንደ ኢትዮጵያ ተግባራዊ የአረንጓዴ አሻራን በመፍትሄነት ሊጠቀሙ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አረንጓዴ አሻራ የሕዳሴያችን ዋልታና ማገር ነው !
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም