ምሁራን እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ ፈተናዎች ከሶስት ነገሮች ይመነጫሉ። አንደኛው ሀገሪቱ የምትገኝበት መልከአማድራዊ አቀማመጥ ስትራቴጂያዊ መሆኑ፤ በቀይባህር አቅራቢያ መገኘቷ በአካባቢው የሃይል የበላይነትን ለማመረጋገጥ በሚሹ አካላት ሁልጊዜም በትኩረት ውስጥ እንድትኖር የማድረጉ እውነታ። ሁለተኛው በዚህ ዘመን ተግዳሮቱ በግልጽ መታየት የጀመረው በአባይ ወንዝ ላይ ኢፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ለዘላለም ጸንቶ እንዲቆይ የሚፈልጉ ሀገራት የሚያደርሱት ጫና ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ በተፈጥሮ ሃብት መታደሏ ነው።
እነዚህ ሶስት የፈተና ምንጮች ሀገሪቱ ዘወትር በቀውስ አጀንዳ ውስጥ እንድትኖር አድርገዋታል።ለመልማት የምታደርገውም ጥረት በሌሎች ኃይሎች እንደስጋት እየታየ ከለውጥ መንገድ ለማደናቀፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም በተመሳሳይ መልኩ እየተደረገ ነው።
ኢትዮጵያውያንን በጀግንነት ታግለው ማሸነፍ እንደማይችሉ ስለሚያውቁ እነዚህ የውጭ ኃይሎች የውስጥ ባንዳዎችን በገንዘብ ገዝተው ሀገሪቱም የማመስ የቆየ ታሪክም አላቸው። ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ተቆራኝተው ኢትዮጵያን የደም ምድር ለማድረግ ዘወትር ሲሰሩ ይታያሉ። ከድሮ እስከ ዘንድሮ የታየውም ይህ እውነታ ነው።
በአለንበት ወቅት ለሀገሪቱ በጎ የማይመኙ፤ ኢትዮጵያ ከፍታ ስጋት የሚሆንባቸው እነዚህ ሀይሎች የህዳሴውን ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ሶሰት የሽብር ኃይላትን ምርጫቸው አድርገዋል።ህውሓት፤ ሸኔንና አልሻባብን።እነዚህ ሶስት ኃይላት ምንም የሚያስተሳስራቸውና አንድ የሚያደርጋቸው ነገር የለም። ሆኖም አንድ የጋራ አላማ ግን አላቸው፤ ለውጭ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያን ማፍረስ።
ይህንኑ አላማቸውንም ለማሳካት በሰሜን፤ በምስራቅና በምዕራብ ሀገሪቱ ክፍል ጦርነት በማወጅ እና ሀገሪቱን የግጭት ማዕከል በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው። በቀደሙት ጊዜያት በየቦታው በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል፤ አፈናቅለዋል፤ለስደት ዳርገዋል።
አሸባሪው ህውሓት ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ባስተዳደረባቸው አመታት ጸረ ኢትጵያዊ አቋም በመያዝ ጭምር ሀገሪቱ እንድትፈርስ ብዙ ሰርቷል። ዜጎችን በብሄር፤ በሃይማኖትና በቡድን በመከፋፈል እርስ በእርስ እንዳይተማመኑና ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዲያመሩ ያለ መታከት ሰርቷል። የሀገሪቱን አንጡራ ሃብት ያለ ርህራሄ በመዝረፍ በውጭ ባንኮች አከማችቷል።በዘረፈው ገንዘብም የሽብር ድርጊቶችን ለማስፋፋት በስፋት ተንቀሳቅሷል።
ይህ የሽብር ቡድን የዘረፈው ገንዘብ አልበቃ ብሎት ለውጭ ጠላቶች ያለውን ታማኝነት በግልጽ አንጸባርቋል። ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትወዛገብባቸውንና በግልጽ የተወረሱ መሬቶቿን ያለ ህፍረት የኢትዮጵያ ግዛቶች እንዳልሆኑ በመመስከር ከሃዲነቱን አረጋግጧል። ለሀገሩ ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ሲዋደቅ ከቆየው ከትግራይ ህዝብ ስነ ልቦና ውጭ ባንዳነቱን በገሃድ አሳይቷል። ከውጭ ጠላቶች የሚሰጠውንም ተልዕኮ ለመሳካት ከአሸባሪዎቹ ሸኔና አልሻባብ ጋር በማበር በተለያዩ አካባቢዎች በሽብር ተግባር ውስጥ ተሳትፏል።
ይህ እኩይ የሽብር ቡድን ኢትዮጵያ በጦርነት ደቃለች፣ በፖለቲካ፣ በጎሳና በሃይማኖት ተከፋፍላ ለመፈራረስ አንድ ሐሙስ የቀራት አገር ሆናለች ብሎ በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሟርት በማስነገር ጭምር የሀገሪቱ ገጽታ በብዙ እንዲበላሽ አበክሮ ሰርቷል።የህዳሴው ግድብ እንዲኮላሽም ስልጣን ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል። ለግድቡ የተዋጣውን ገንዘብ ለግል ጥቅሙ ከማዋል ጀምሮ በአደባባይ ከውጭ ጠላቶች ጋር ተመሳሳይ አቋም በማራመድ በህዳሴ ግድብ ላይ ጸረ ኢትዮጵያዊ አቋም ይዟል።
ቡድኑ በእብሪትና በማናለብኝነት በከፈተው ጦርነት ሽንፈትንና ውርደትን ተከናንቦ ዛሬ አንድ ጥግ ይዞ ቢገኝም በአገኘው አጋጣሚም ሁሉ የሽብር ድርጊቶችን ከማቀድና ከመተግበር፤ ሀገርና ህዝብን ወደ ከፋ ችግር የመክተት ምኞቱን እውን ከልማድረግ ተኝቶ የሚያድር አይደለም። በአሁኑ ወቅትም መንግስት የሰጠውን የሰላም እድል ከመጠቀም ይልቅ ቅድመ ሁንታዎችን በማስቀመጥ የትግራይን ወጣት ለዳግም እልቂት እያዘጋጀ ነው።
በኦሮሚያ ክልል በወለጋ አካባቢ ባለፉት አራት ዓመታት የደረሱ ግድያዎች በርካታ ናቸው። በርካታ ዜጎች የዘር ተኮር ግድያና መፈናቀል ተፈጽሞባቸዋል። ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም. መገባደጃ በወለጋ አካባቢ በርካታ ግፎች ተፈጽመዋል።
በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ላይ፤ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤል ወረዳ፤ በተገባደደው 2014 ዓ.ም በጥር 2014 ዓ.ም. ቄለም ወለጋ ጊዳሚ ወረዳ ፤ በቅርቡም በሰኔ ወር በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ እና በቄለም ወለጋ ሀዋ ገላን ወረዳ ንጹሀን ዜጎች በአሸባሪው ሸኔ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
አሸባሪው ሸኔ ምን አይነት አላማ የሌለውና የኢትዮጵያ ጠላቶች በሆኑ የውጭ ሃይላት ሳንባ የሚተነፍስ ዕኩይ ቡድን ነው። ዋነኛ ዓላማውም ከአሸባሪዎቹ ህውሓትና አልሻባብ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። አሸባሪዎቹ ህውሓትና ሸኔም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ድንበር ተሻግረው አለም አቀፍ አሸባሪ ከሆነው አልሻባብ ጋር ወዳጅነት መስርተዋል።ይህንኑ ተማምኖም የአልሻባብ ቡድን ኢትዮጵያ ላይ በቅርቡ የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሯል።
ከትላልቅ ከተሞች ውጪ በርካታ የሶማሊያ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ይህ ታጣቂ ቡድን፣ በሶማሊያ ውስጥ ያልተቋረጠ ከባድ የቦምብ እና የሸምቅ ጥቃቶችን በመፈጸም ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሆኗል።ለአገሪቱ ሕዝብና መንግሥት ከባድ የደኅንነት ፈተና እንደሆነም አለ።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት አልሻባብ ከህውሓትና ከሸኔ ጋር የፈጠረውን የሶትዮሽ ጥምረት ተገን አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሞክሯል። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው አሸባሪዎቹ ህውሓትና ሸኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ለባዕዳን አሸባሪ ሃይላት አሳልፈው በመስጠታቸውም የአልሸባብ ኃይሎች በሶማሌ ክልል አቶ በተባለው ቦታ ላይ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ሁለተኛው ጥቃት የፈጸመው በዬድ ላይ ነበረ። ሆኖም ጀግናዎቹ የምስራቆቹ አንበሶች አሳፍረው መልሰዋቸዋል። ለወሬ ነጋሪም ሳይተርፉም በመጡበት ቀርተዋል።
ቡድኑ በሶማሌ ልዩ ኃይልና በመከላከያ ሰራዊት ድባቅ ባይመታ ኖሮ የሶማሌ ክልልን በማለፍ ባባሌና በአርሲ አካባዎች በህቡዕ ከሚንቀሳቀሰው ሸኔ ጋር የመገናኘት አላማ ነበረው። ሆኖም ድንበሩን በፍጹም ለባዕዳን ኣሰላፎ የማይሰጠው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የሶማሌ ልዩ ኃይል ከ800 በላይ የአልሻባብ አባላትን ከመግደል ጀምሮ በአሜሪካ ጭምር በጥብቅ የሚፈለጉትን የቡድኑን መሪዎች በመግደል ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል።
ኢትዮጵያን የማመሱ ሶስትዮሽ ሰንሰለት በጀግኖቹ ኢትዮጵያን ተጋድሎ ተበጣጥሷል። የአሸባሪዎቹም ምኞት እንደጉም በኖ ጠፍቷል። ሶስተኛውም የውሃ ሙሌት ተከናውኗል፤ ሁለተኛውም ተርባይን ብርሃን መስጠት ጀምሯል።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም