የትምህርት ዘመኑ አልቆ ተማሪዎች ከሰፈራቸው ተገናኝተው እየተጫወቱ ነው።የክረምቱ ጉም፤ ዝናቡ፤ የልጆቹ ከፍተኛ የጨዋታ ፍላጎት፤ የጎርፉ ድምጽ ወዘተ ልዩ ስሜት የሚፈጥሩባቸው አባት ደግሞ በሰፈሩ ውስጥ ይገኛሉ።እኒህ አባት በበጋ ወቅት “ምነው ክረምቱ በመጣና ሰፈሩን ሕይወት በዘሩበት” በማለት ልጆች በልዩ ሁኔታ የሚደምቁበትን ክረምትን ይናፍቃሉ።ሰፈሩ ሕይወት የሚኖረው ለእርሳቸው ልጆች ቀኑን ሙሉ ሲሯሯጡና ሲጫወቱ ማየት ነው።
እንሆ ክረምት ሆኖ አዛውንቱ ከዘራቸውን ይዘው ቤታቸው በር ላይ ካላቸው ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ፊትለፊታቸው ባለው ሜዳ ውስጥ የሚቦርቁትን ልጆች ይመለከታሉ።ሲጫወቱ ነፍሳቸውን አያውቁም፤ የልጅነት ጨዋታ።ቀኖች እየጨመሩ ሲሄዱ ሁሉም ልጅ ወደ ራሱ መስመር ውስጥ ገብቶ ይበታተናል፤ ልጆቹ ዛሬ እርሱን አያውቁም።በሕይወት የዓላማ ጉዞ ምናልባትም ነገ በተለያየ ጎራ ሆነውም የሚፋለሙ ሊሆኑ ይችላሉ።በምናባቸው አዛውንቱ የእርሳቸውን ዘመን የልጅነት ጓደኞቻቸውን እያሰቡ ነጎዱ።በሕይወት ጉዞ በተለያየ አቅጣጫ የተመመውን የእርሳቸውን ትውልድ።
አዛውንቱ ከእለታት በአንዱ ቀን ከፊታቸው የሚቦርቁትን ልጆች ሰብሰው አብረዋቸው ማውራት ፈለጉ።ከልጆቹ መካከል ከጫዋታው ውስጥ የእርሳቸውን የልጅ ልጅ ተጣሩ፤ “ዱጩ፤ ዱጩ” እያሉ ተጣሩ።“ዱጩ” እርሳቸው የልጅ ልጃቸውን የሚጠሩበት የቤት ስሙ ነው።ዱጩ “አቤት አባቴ” ብሎ እየሮጠ ወደ አያቱ ቤት ሄደ።“እስኪ ልጆቹን ሁሉ ወዲህ ጥራለኝ” አሉት።“እንዴ ምነው አባ፤ አንተም ወደቤት ግቡ ብለህ ጨዋታችንን ልታቋርጠን ባልሆነ?” አለ።አዛውንቱም “አይደለም ዱጩ ለሌላ ጉዳይ ነው” በማለት ምላሽ ሰጡት።ዱጩም የተሰጠውን ትእዛዝ ተከትሎ በጨዋታው እብድ ያሉትን ልጆች ተጣራ።አንዳንዶቹ ከጨዋታው ስልተቋረጡ ተነጫነጩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ምን ይሆን ብለው ወደ አባባ ዘንድ ፈጠኑ።
አባባ ምን ሊሏቸው እንደሆነ ጓጉተው ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ እያለ አባባ ጋር ደረሱ።አባባም “እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ በመጀመሪያ ማንን ልጠይቅ አሉ?” ሁሉም “እኔን፤ እኔን” እያሉ እጃቸውን አወጡ፤ ልክ እንደ ትምህርት ቤት።አዛውንቱም “ቆይ ተረጋጉ እንጂ ከእድሜ ትንሹ ማንነው? ከእርሱ ጀምረን ወደ እድሜ ትልቁ እንሄዳለን” ብለው ሁሉንም በእድሜ ቅደም ተከተል አሰለፏቸው።
ከተሰበሰቡት መካከል በእድሜ ትንሹን ጠየቁት “ልጄ እያለቀ ባለው ዓመት ውስጥ ደስ ያለህ ነገር ምንድን ነው?” በማለት።ልጁም በልጅነት አንደበቱ “እኔ በጣም ደስ ያለኝ የልደት ቀኔ ሲከበር አክስቴ ከገጠር መምጣቷ ነው።ለእኔ ብላ ብዙ መንገድ ተጉዛ መምጣቷ በጣም ደስ ብሎኛል።ደግሞም ሳይክል ስለገዛችልኝ በጣም ደስ ብሎኛል”ሲል መለሰ።
ሁለተኛው ልጅ ደግሞ “አንተስ እያለፈ ባለው ዓመት ውስጥ በጣም ያስከፋህ ነገር ምን ነበር?” ሲባል ተጠየቀ፤ ልጁም “እኔ በጣም ያስከፈኝ አጎቴ ለጦርነት ሄዶ አለመመለሱ ነው።አጎቴ በጣም ይወደኛል ደግሞም አባባ እንደሚያውቁት አባቴና እናቴ ሲጣሉ የሚያስታርቃቸው እርሱ ነውና የእርሱ መሞት በጣም አስከፍቶኛል” ሲል መለሰ።
ሦስተኛው ልጅ ደግሞ “አንተ ደግሞ በዓመት ውስጥ ካደረከው ነገር ልዩ ስሜት የሚፈጥርብህ የቱነው?” ተባለ እርሱም “በዚህ ዓመት ውስጥ ደስ የማይሉ ነገሮችን አሳልፌያለሁ።ነገርግን በጦርነት ለተፈናቀሉ እኛ ተማሪዎች እንድናዋጣ ተጠይቀን አባቴና እናቴ በሰጡኝ ገንዘብ ፓስታ ገዝቼ መስጠቴ ደስ ብሎኛል።ደግሞም በትምህርቴ ጥሩ ውጤት ስላመጣሁም ደስ ብሎኛል።ከሁሉም በላይ ግን እኔ መማር ያለብኝ አንደኛ ለመውጣት ብቻ ሳይሆን የደረጃ ተማሪ ከመሆን ባሻገር የሰዎችን ችግር መፍታትን ግብ አድርጎ መንቀሳቀስ አስፈላጊ እንደሆነ ነው።ይህም አባቴ የመከረኝ ትልቅ ምክር ልቤ ውስጥ የተመዘገበበት ወቅት ስለነበረ ደስ ብሎኛል፡፡” በማለት ምላሽ ሰጠ።
የልጆቹ ደስታም ሆነ መከፋት ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያገናኝ ጉዳይ መሆኑን አዛውንቱ አስተዋሉ።ምድር ላይም የሰው ልጅ ምንያህል እርስበእርሱ የተሳሰረና ደስታውም ሆነ ሃዘኑ በአብሮነት ጉዞ ውስጥ መሆኑን አሰላሰሉ።የሰው ልጅ አቅዶ በመተግበር ውስጥ ያለው ጉዞው ትርጉም የሚሰራው ሰውን ማእከል አድርጎ ሲከናወን መሆኑን ከራሳቸው ጋር አወሩ።ኢላማም ሆነ ዓላማ የሚሳኩት ሰውን ይዞ ከሰው ጋር ተሆኖ ሲተገበር ብቻም እንደሆነ በሃሳባቸው ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ ሄዱ፤ ጊዜ ቢኖራቸው ወደፊት ሊኖሩ የሚወዱትን ኑሮም አሰቡ።ግን ብዙም ጊዜ እንደሌላቸው ያውቃሉ። የኢላማ እና የዓላማ ሕይወትን በመረዳት ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ግን ቀናት አያልቅበትምና ሊኖሩት ተመኙት።
ኢላማ
ለአደን የተሰማራ ሰው ኢላማውን አስተካክሎ አንዳች ድል ይዞ መመለስ ፈልጎ ወደ ጫካው ውስጥ ይገባል።ኢላማው በራሱ ዓላማ አይደለም፤ ዓላማው ኢላማው ሲሳካ የሚያሳካው ነው።ኢላማውን በትክክል ከሰነዘረ ፤ ኢላማውን መትቶ አውሬውን ከጣለና ባዶ እጁን ከተመለሰ አንዳች ችግር እንዳለበት ይቆጠራል።ምክንያቱም ሕይወቱን አስይዞ የተሰለፈበት የኢላማ ፍልሚያው አላማ ገድሎ መመለስ አይደለምና።
በሕይወት ጉዞ ውስጥ ሰዎች ኢላማ የሚያደርጉት ብዙ ነገር አለ።ጎበዝ ተማሪዎች ኢላማ አድርገው የደረጃ ተማሪ ለመሆን ያጠናሉ።ካሰቡበት ደረጃ ተንሸራተው ሲገኙ አንዳች የጎደላቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸዋል።በአንድ ወቅት በተማሪዎች የውጤት መቀብያ ቀን አንዱ ታዳጊ ተማሪ ስቅስቅ ብሎ ያለቅሳል።አንዳች ነገር እንደተፈጠረ እምባው ያሳብቅበታል።ምክንያቱ ደግሞ በአንድ ማርክ ተበልጦ ደረጃውን ማጣቱ ነበር።ኢላማ ያደረገው ነገር ነበርና ኢላማውን መምታት ባለመቻሉ የተፈጠረበት ሃዘን።
ከግለሰብ አልፎ የኢላማ ነገር በተቋማት ውስጥም ይሰራል።ተቋማት ግብ አስቀምጠው እያንዳንዱ ሰራተኛ እንደ ግለሰብ፤ ከእያንዳንዱ የስራ ክፍል እንደ ክፍል፤ ከአጠቃላይ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ኢላማ ይደረጋል።ኢላማውም ይሳካ ዘንድ የተለያዩ ተግባራት ይከናውናሉ።ኢላማ በአግባቡ ታልሞ ውጤት ሲመጣ ደስታ ይሆናል።ኢላማ የተደረገው ነገር ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ምክንያቱ ይገመገምና የማስተካከያ መንገድ ይቀየስለታል፤ በዚሁ መንገድ የኢላማ ጉዞ ይቀጥላል።
ኢላማ ማድረግን እንደ ባህል በአደጉት ሀገራት ዘንድ የተለመደ ነው።ጃፓኖች የማኔጅመንት ሳይንስ እንዲዳበር የአሰራር ማሻሻልን በየጊዜው በማድረግ ኢላማን መምታት የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረስ እንዲቻል ምሳሌ የሚሆኑ አሰራሮችን ለዓለም አስተዋውቀዋል።ኢላማን ትኩረት ያደረጉ በጥራት፣ በሰው ሃይል አስተዳደር፣ በንግድ አስተዳደር፣ በንብረት አያያዝ ወዘተ ውስጥ አሰራሮችን አስተዋውቀው ውጤታማም ሆነዋል።
አንባቢው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ኢላማን በማለም ልምድ ያለው ሊሆን ይችላል።አንዳንዱ ሰው የአዲስ ዓመት እቅድን በልኩ አቅዶ ተግብሮ ራሱን ገምግሞ የመሸለም ልማድም አለው።በሂደት ውስጥ ከዛሬ ነገን በስራ መቀየር።ኢላማ እዚህ ውስጥ ያለው ድርሻ ትልቅ ነው።ኢላማ የምናደርገው ነገር ግልጽ ነው።በቁጥርም፤ በስፋትም፤ በርዝመት ወይንም በሆነ አንዳች መለኪያ አማካኝነት የሚለካ ስለሆነ።
ኢላማ አድርጎ ቀኑን በሰዓት ከፋፍሎ የሚንቀሳቀስና ቅርጽ በሌለው አካሄድ ቀኖቹን ተቀብሎ የሚሸኝ ተመሳሳይ ውጤት ሊኖራቸው አይችልም።ተማሪው፣ አርሶአደሩ፣ ነጋዴው፣ ሰራተኛው ወዘተ በኢላማ ውስጥ ስራቸውን ያከናውኑ ዘንድ ይመከራል፤ በዚህ መንገድ የሚያከናውኑት ለውጤት ደርሰው ይታያል።ከፍ ያለው ጥያቄ ግን አላማ ነው፤ ከኢላማ የሚገዝፈው፤ የኢላማ ድምር ውጤት የሚገልጸው።በትውልዱ ውስጥ ቦታ የተነፈገ የሚመስለው በኢላማ ተሸፍኖ የሚኖረው፤ ዓላማ!
ዓላማ
‹‹ማርክ ትዋይን›› የተባለ አሜሪካዊ ፀሀፊ “በሕይወት ውስጥ ወሳኝ የሆኑት ሁለት ቀናት ሲሆኑ፤ አንደኛው የተወለድክበት ሌላኛው የሕይወትህን ዓላማ ያገኝህበት ነው” ይላል።ዓላማ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ቦታ በሚገባ የሚያሳይ አባባል ነው።
የስድብ ጥሩ ባይኖረውም “አላማ ቢስ” የሚል ስድብ የሰዎችን ስሜት የመንካት አቅሙ ከፍተኛ ነው።ማንም ሰው ዓላማ ቢስ እንደሆነ ተደርጎ እንዲቆጠር አይፈልግም።በዘመናት መካከል ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችበት ምዕራፍ ላይ ለመድረስ ያለፉ በርካታ ስልጣኔዎች ነበሯት።እያንዳንዱ ዘመን ይዞት የነበረው ስልጣኔ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ተጽፎ ከሚገኘው ባሻገር በእያንዳንዱ አካባቢ አሻራው ዛሬም ድረስ ይታያል።ኢትዮጵያውያን አንድ ሰው ዓላማ ብሎ የያዘውን ነገር ዳር በማድረስ ውስጥ የሚሰጡት ሙገሳ ወይንም አድናቆት የታሪካችን አካል ነው።ከዚህ አንጻር “አላማ ቢስ” የሚለው ቃል ለአንድ ኢትዮጵያዊ ስሜትን የሚጎዳ ቢሆን ሊገርመን አይችልም።
ቤተሰቦች ልጆቻቸው ትምህርትን በአግባቡ እንዲያጠኑ፤በአግባቡ እንዲከታተሉ ሲመክሩ ትምህርትን እንደ ዓላማ አድርገው በማቅረብ ነው።ሴት ልጅ ከሆነች ደግሞ ከዓላማዋ ሳትዘናጋ ትምህርቷን ዓላማ አድርጋ እንድትማር ትመከራለች።ለኃላፊነት ብቁ ሳይሆን ወደ ጾታዊ ግንኙነት መሄድም እንዲሁ ከዓላማ መስመር መሳት ተደርጎም ይቀርባል።አባቶቻችን በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ገብተው ሳይማሩ ከግልሕይወታቸው ተነስተው እስከ ሀገር ድረስ በዓላማ ውስጥ የመኖርን አስፈላጊነት ይገልጻሉ።
ባለንበት ዘመን ደግሞ ዓላማ የሚባለው ነገር ፈጽሞውኑ የጠፋ ነው ባንል እንኳን እየደበዘዘ የሄደበት ነው።ዓላማ እጅግ ጠቦ በየትም በኩል ተደርጎ ገንዘብ ላይ መድረስ የሚለው የሕይወት ዘይቤ የሰፋ ይመስላል።በስራ መንገድ ገንዘብ ላይ መድረስ የሚጠበቅ ቢሆንም ባልተገባ ስራ መድረስ እንዲሁም መነሻ ዓላማቸው ገንዘብ ባልሆኑ ዘርፎ እንደ ሃይማኖት፤ ፖለቲካ፤ ህዝብ አስተዳደር ወዘተ ከብዙሃን ጋር በሚሰጥ አገልግሎት ውስጥም ታልፎ ገንዘብ ጋር መድረስ ግብ ከሆነም ሰነባብቷል።ይህ ደግሞ ያሳዝናል።ዓላማን በገንዘብና በእውቅ ለመለካት የተሄደበት ርቀት ብዙ እንደሆነ በግልጽ የሚታይበት ወቅትም ነው።
መነሻችንን ዒላማ ያደረግነው በዒላማ ስሌት ዓላማ እየወደቀ ስላለ ነው።ገንዘብ የማግኘት ኢላማ ወይም ግብ ያለው ሰው በማንኛውም መንገድ አድርጎ ገንዘብ ጋር መድረስን ከሆነ የሚያስበው በመደበኛ ንግድ ገንዘብ ጋር ከመድረስ በኮንትሮባንድ መንገድ ላይ መሄድን ሊመርጥ ይችላል።በሙስና ገንዘብ ላይ መድረስን ኢላማ ያደረገ ሰው ካለበት አንድ ኃላፊነት ወደ ሚከተለው ሲያድግ ኢላማው በተጨማሪ ኃላፊነት ህዝብን ማገልገል ሳይሆን ለበለጠ ሌብነት ልምምድ ማድረግ ላይ ይሆናል።
የዒላማ ሕይወት በዓላማ ውስጥ ሲሆን፤ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን የሚያስረዱ አያሌ የማኔጅመንት ሳይንስ ጽንሰሃሳቦች አሉ።እውነታው ግን ዓላማ የለሽ በመሆን ውስጥ የበቀሉት ኢላማዎች ትርጉማቸው ማትረፍ እየመሰሉ መክሰር፤ ማግኘት እየመሰለ ማጣት፤ መገኘት እየመሰለ መጥፋት ነው።‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ›› ሊባል የሚችልባቸው ክስተቶች በየፌርማታው ከዓላማ አንጻር በዝቷል።ያለእጅ መንሻ ውጤት ማግኘት በማይታስብበት ዘመን ውስጥ ስንኖር በተለመደው መንገድ ወጥቶ የሚገባው ዓላማውን ለማሳካት በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆን አዋጭ እንዳልሆነ ያስባል።በዚህም ተስፋው እየተሸረሸረ ሊሄድ ይችላል።
የዓላማ ሕይወትን መኖር
ዓላማን ውስብስብ አድርጎ ከማቅረብ በቀላሉ “ሰዎችን ማእከል አድርገን ልንኖረው የተገባው ሕይወት” ብለን ልናየው እንችላለን።በምድር ላይ የምንኖረው ኑሮ በጊዜ የተገደበ መሆኑ እሙን ነው።ሰው በመሆናችን በውስንነት ውስጥም እንኖራለን።በዚህ ሁኔታ ምድር ላይ ስንኖር ዓላማ ትልቁ ስንቃችን ነው፤ ልንኖር የተገባውን ሕይወት ላይ ያደረስነው ውሳኔም ነው።
እንደ ግለሰብ በውስጣችን ያለውን ተሰጥኦ ተጠቅመን ልንኖር የምንፈልገውን ሕይወት ለመኖር እውቀትን ማእከል አድርገን ስንመላለስ እርሱ ዓላማ ነው።የዓላማ ሕይወት ራስን ፈልጎ በማግኘት ለሌሎች የሚመነዘር ማድረግ ነው።አንድ ሰው በቁጥር አንድ ቢሆንም ለራሱ በቂውን ጊዜ ሰጥቶ ራሱን ፈልጎ ባገኘበት ርቀት ለብዙዎች የሚመነዘር ሊሆን ይችላል።የዓላማ ሕይወት ሰዎች ግራ ተጋብተው በሚኖሩበት ሁኔታ ውስጥ የተረጋጋን ሕይወት እንድንኖር የሚረዳ ነው።ራስን ፈልጎ ማግኘት በውጤቱም ለሌሎች መድረስ ነውና፡፡
ሮበርት ኤፍ. ኬኒዲ “የሕይወት ዓላማ ነገሮችን መልካም ለማድረግ በሆነ መንገድ የምናደርገው አስተዋጾ ነው” በማለት ዓላማን ከራስ አጥር ባሻገር መመልከት እንደሆነ ይገልጹታል።ይህ ሲሆን ለውስጥ ጩኽት ምላሽ መስጠት፤ ከፈጣሪም ከተፈጥሮም ጋር ታርቆ የመኖር ሕይወትን ይከተላል።ተልእኮ አድርጎ የሚወሰድን ነገር ዳር ማድረስ የሚያስችል ሕይወትም ይሆናል።
በመቃብራችን ላይ የሚገኙ ሰዎች ምን አድርገን እንዳለፍን ቢያውቁ ደስ ይለናል።የተጣላን አስታራቂ፣ ተስፋ ላጡ ተስፋን መመለስ፣ የተራቡትን የሚያበላ፣ በስራው ታታሪ ሆኖ ብዙ የስራ እድል የፈጠረ፣ በስፖርቱ ዓለም ተጽእኖ ፈጥሮ ለሰዎች በስፖርት መዝናኛ ምክንያት ሆኖ ማለፍ ወይንስ ምን? ፒካሶ እንዲህ ይላሉ። ‹‹የሕይወት ትርጉም ስጦታህን ማወቅ ነው።የሕይወት ዓላማ ደግሞ ስጦታህን ለሌሎች መስጠት፡፡›› እናም ዓላማ በተቻለው መጠን ራስን ማእከል ከማድረግ ወጥቶ ሌሎችን የሚያስብ መሆን ነው።
አንድ ሰው ነግዶ ገንዘብ ማግኘት ቢፈልግ እንደ ዓላማ መያዝ ያለበት በሚሰራው የንግድ ስራ ሰዎችን የሚጠቅምበትን ነው።ለአርሶአደሩ የሆነ እቃ አቅርቦ የአርሶአደሩን ችግር ፈቶ ገንዘብ ማግኘት ሲሆን፤ ትርጉሙ እንዲሁ ነግዶ ገንዘብ ማግኘት ከሚል ዓላማ ይሻላል።ገንዘብ ማግኘት ኢላማ ሲሆን የሚሰራው ስራ የሚጨምረው እሴት ካለ ዓላማ ይሆናልም። ዛሬ በኢላማ ውስጥ በመኖር ብቻ ያልሞላነውን የሕይወት ጉዞ በዓላማ በመኖር ምልዑ እናደርገው ዘንድ እድል አለንና የተግባር እርምጃን ስለሰው ብለን እናድርገው።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014