ወይዘሮዋ አንድ ጩኸት አላቸው፤ የሚጮኹት ደግሞ እንደፖለቲከኛ አሊያም ምሑር አይደለም። እንደእናት እንጂ። እኚህ ኖሮጂያዊ ኢትዮጵያዊት የሚጮኹት የየትኛውንም የኃይማኖት ተቋም እና የብሄረሰብ አጀንዳ ለማስፈጸም አይደለም። የመንግስትንም ሆነ የተፎካካሪውን ሐሳብ ለማራመድም አይፈልጉም። ቋንቋቸውም እንደዲፕሎማት ልቅም ያለ እንዲሆንም አይደክሙም። ነገር ግን እንደ እናት ጮኸው እንደ እናት መሰማትን ይሻሉ።
እንደ እናት ሆነው ለመጮህ ያስገደዳቸው ደግሞ አንድ ነገር በውስጣቸው ስላለ ነው፤ እርሱም ላለፉት ብዙ ዓመታት ለጣሩለት ለእርቅና ለሰላም ጉዳይ ጆሮ እንዲሰጠው ስለሚሹ ነው። በተለይም በኢትዮጵያ ብሔራዊም ፍትሃዊም እርቅ እንዲኖር በጽኑ ይፈልጋሉ። የኖርዌይ ዜጋ ቢሆኑም የትውልድ ሐረጋቸው የሚመዘዘው ከሚወዷት ኢትዮጵያ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረገው መልካም ነገር ልባቸው በሐሴት እንደሚዘል ሁሉ፤ መልካም ባልሆነው ነገር ደግሞ ክፍት ትክዝ ይላሉ። ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ስለጠፋው የንጹኃን ደም ግድ ይላቸዋል። ስለዚህም የሚፈልጉት በኢትዮጵያ ከልብ የሆነ ይቅርታና እርቅ ማውረድን ነው።
እኚህ የዛሬዋ የዘመን እንግዳችን ወይዘሮ ሰዋሰው ስለሺ ይባላሉ። የትውልድ እናት ለእርቅና ለሰላም ድርጅት ስራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ አስተባባሪ ናቸው። ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ፣ ለገሃር አካባቢ ሲሆን፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው። ከኢትዮጵያ ከወጡ ወደ ሶስት አስርት ዓመታት አልፏቸዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነ ጽሁፍ ዲግሪያቸውን በመማር ላይ እያሉ ነበር ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ ኖርዌይ ያቀኑት። በዚያም ኑሯቸውን ቢመሰርቱም ወደእናት ምድራቸው ኢትዮጵያ ግን ከመመላስ አልተቆጠቡም። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ አጠናቅረን አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- የእርስዎ ጩኸት እንደ እናት እንጂ እንደፖለቲከኛ፣ እንደምሁር ብሎም እንደኃይማኖተኛ አይደለም፤ የእናት ጩኸት ከጠቀሷቸው አካላት የሚለየው እንዴት ነው በሚለው ጥያቄ ጭውውታችንን እንጀምር?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- መልካም ነው፤ የእናት ጩኸት ርህራሄን ከተላበሰው ከእናትነት አንጀት የሚፈልቅ ነው። በሁሉም ብሔር ውስጥ ይህች እናት አለች። በሁሉም ኃይማኖትም ውስጥ ትገኛለች። የፖለቲከኛውም የምሁሩም ወላጅ ይህችው እናት ነች። እናትነት ሁሉም ዘንድ ውስጣዊ ስሜቱ አንድ ነው። የልጆቿን ክፉ ማየት አትሻም፤ ሃዘናቸው ያስከፋታል። ቁስላቸውም ይጠዘጥዛታል። ለዚህም ነው ‹‹የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ›› በሚል መርህ እናቶችን አካተን ለአገራችን ሰላም የበኩላችንን ለማድረግ ጩኸታችንን ለማሰማት እየጣርን የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን ‹‹የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ›› በሚል መርህ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፤ በቅርቡም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባሉበትም ውይይት ተካሂዷል፤ በዚህ መርህ የተካተቱት እነማ ናቸው? ዓላማውስ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ የሚል እንቅስቃሴ ጀምረናል። በዚህ የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ በሚለው ውስጥ ያለነው አስራ አንድ ድርጅቶች ነን። እነዚህ 11 ድርጅቶች የዓለም የእርቅና ሰላም ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ የኢትዮጵያውያንና የአሜሪካውያን የሰላም ትብብር ምክር ቤት፣ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የሴቶችና የልጃገረዶች ድጋፍ ኢትዮጵያ፣ ዲቦራ አብሪ የሴቶች አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ የሰላም እናቶች ማህበር፣ ምቹ ቤት መልቲ ሚዲያ፣ ተስፋ ኢትዮጵያ ወጣቶች፣ አሻጋሪ የበጎ አድራጊ ድርጅት፣ ቤዛ ኢንተርናሽናል የሴቶች ህብረት እና እኔ የምመራው የትውልድ እናት ለእርቅና ለሰላም ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የ11ዱም አስተባባሪ እኔ ነኝ።
አንደኛው ድርጅት የወጣት ድርጅት ሲሆን፣ እነርሱም ለስራችን በጣም የሚያስፈልጉን ሆነው አግኝተናቸዋል። ሁላችንም በተለያየ አቅጣጫ ይሁን እንጂ በሰላም እና በእርቅ ስራ ላይ በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጪ ስንሰራ ቆይተናል። የዚህም ስብስብ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያለን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እናቶች ነን። እናም ከዚህ በፊት በግል እና በተናጠል ስንሰራ የነበረውን ስራ በአሁኑ ወቅት ወደጋራ ስራ አምጥተን በአንድ አቋም እና በአንድ ዓላማ በመነሳሳት በአገራችን ላይ የበኩላችንን አሻራ ለምን አናስቀምጥም በሚል ነው የተነሳነው።
ስብስቡ ከተጀመረ ብዙ ጊዜ ያስቆጠረ አይደለም። ይሁንና ርቀት ሳይገድበን በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በኦንላይን እንዲሁም ሲቻል ደግሞ በአካልም ስንገናኝ ቆይተናል። በመጨረሻም ስምምነት ላይ በመድረሳችን አገራችን ካለችበት ከፍተኛ የሰላም ችግር መላቀቅ ስላለባት እንዴት እኛ እናቶች ዝም ብለን እንቀመጣለን? እንደ እናት አንድ ነገር ማድረግ አለብን፤ ይህንንም ለማድረግ ለመንግስትም፣ ለተፎካካሪውም፣ ለሚዲያውም፣ ለማህበረሰብ አንቂውም እንደ እናት ጥሪ ማቅረብ አለብን ብልን ነው፤ ሌላው ያስብነው አገራችን ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፈጣሪ የለም በሚል የማርኪስዝም ሌኒዚዝም ርዕዮተ ዓለም የተመራች አገር ነበረች። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከ95 በመቶ በላይ በሚያስብል ደረጃ በፈጣሪው የምናምን ህዝብ ነን።
ከዚህም የተነሳ ፈጣሪውን እንደሚያምን ሕዝብ ከፈጣሪው ጋር መታረቅ አለብን ብለን እናምናለን። ከዚህ የተነሳ ሁሉንም የኃይማኖት ተቋማት አነጋግረን ከፈጣሪ ምህረት እንድንለምን የሚል ተነሳሽነት ነው የያዝነው። በመጀመሪያ ምድራችን መታረቅ ያለባት ከፈጣሪዋ ጋር ነው። በአገራችን ውስጥ 50 ዓመታት ያህል የፈሰሰው ደም በምድሪቷ ላይ እርም ነው። ይህንን እርም እንዳላየ አይተን፣ እንዳልሰማ ሰምተን ብንሄድ ምህረት በምድራችን ላይ ሊመጣ አይችልም። ስለዚህ ፈጣሪ ምህረትንም ፍትህንም እንዲያመጣልን ይህንን የተደረገውን በደል አውቀን አምነን ገዳይም ሟችም እኛው እራሳችን ነንና ከፈጣሪ ጋር አስቀድመን መታረቅ አለብን።
ብዙ ጊዜ የእከሌ ብሔር የእነእከሌን ብሔር ገደለ ወይም ደግሞ የእነእከሌ ተፎካካሪ ፓርቲ የእነእከሌን ብሔር ገደለ በማለት ልክ እኛ ምንም እንዳላደረግን ሆነን ወደሌላው የመግፋት ችግር አለብን፤ አሁን ግን አገራችን ላይ በደረሰው ሁኔታ ግድያው አልፎ ተርፎ በመንደርና በቤተሰብ ውስጥ ገብቷል። ስለዚህ የገዳይም የሟችም እናት እኛው ነን። ችግሩን ለሌላ የምንሰጠው አይደለም። መከራውንም መውሰድ፤ ለመፍትሄውም መጋደል ያለብን እኛው እናቶች ነን። ለመፍትሔው በጋራ መቆም ይጠበቅብናል፤ ከዚህ በላይ ልጆቻችን እንዲያልቁ መፍቀድ የለብንም። ስለሆነም ልጆቻችንን እረፉ ማለት እንዳለብን ሁሉ እንዲሁ ልጆቻችንን የሚማግዷቸውን እረፉ ልንላቸው ይገባል። ከዚህ በኋላ እኛ እናቶች ምድሪቱ ትውልድ የሚጨነግፍባት እንድትሆን አንፈቅድም። ይህንን መከራ አይሆንም ስንልም እንደ እናት እንቆጣለን።
ከፈጣሪ ምህረት እንጠይቃለን ስንልም የደረሱብን በደሎች ቁጠኞች አድርጎናል፤ ሆደ ባሻ አድርጎናል፤ ቂመኞች አድርጎናል። ከዚህም አልፎ ተርፎ ለበቀል ያስሮጠናል። ስለዚህ ይህንን የማይበጀንን ነገር ትተን እኛም ራሳችን ከራሳችን ጋር መታረቅ አለብን ማለት ነው። እንደገና ከወንድማችን ጋር መታረቅ አለብን ብለን ነው ተነሳሽነቱን ወስደን እየተንቀሳቀስን ያለነው። መንግስትም በጉዳዩ ዙሪያ እንዲተባበረን እንሻለን። እስከ ዛሬ ልጆቻቸው ያለቁ እናቶች ዛሬም ያነባሉ። የትዳር አጋራቸውን በግፍ የተነጠቁ ሚስቶች ዛሬም ይቆዝማሉ። እናትና አባታቸውን በጭካኔ የተቀሙ ህጻናት ዛሬም ያለቅሳሉ።
ታዲያ ይህንን ፈተና እንዳልሰማና እንዳላየ ሆነን የምናልፈው እስከ መቼ ነው? ጉዳዩ የአንድ ወቅት የፖለቲከኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ማድመቂያ ሆኖ እስከመቼስ ይቀራል? ጉዳያቸው ተዳፍኖ ቢቀር የእነርሱ እንባና ሰቆቃ ከባድ ነው የሚሆነው። በመሆኑም ነው ለእነዚህ ሰዎች እውቅና ሰጥተን በደላችሁ በደላችን ነው፤ ሃዘናችሁ ሃዘናችን ነው ልንል የሚገባው። ምንም እንኳ የጠፋን ሕይወት መመለስ አሊያ መተካት ባንችልም በሕይወት ያጧቸው ቤተሰቦች ያጎደሉባቸውን ጎድለት እኛ እንደኢትዮጵያ ሕዝብ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገር ያለነው ካሳ ልንክሳቸው ይገባል ባይ ነኝ።
የአካል ጉዳትም ሆነ የስነልቦና ጥቃት ለደረሰባቸው በተለይ ደግሞ የመከራውም የጦርነቱም ገፈት ቀማሾች ሴቶች ስለሆኑ እነርሱን እንደእናት ማየት አለብን። ይህን ለማድረግ መንግስት እንዲተባበረን እንፈልጋለን። እስከዛሬ ላለቀው ትውልድ አንድ ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ተብሎ በማወጅ ለ50 ዓመቱ ሰቆቃ ክዳን አበጅተን ወደኢዩቤሊዩ ዘመን እንድንመጣ እንሻለን። ይህንን ጥያቄያችንን ለመንግስት እናቀርባለን። ከዚህ በኋላ ምንም እንዳልተፈጠረ እያስመስልን መሄድ የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ በሚል ስያሜ የተመሰረተው ድርጅት በውስጡ ያካተታቸው አስራአንድ ድርጅቶችን እንደሆነ ገልጸዋል፤ የስብስባችሁ ስብጥር ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- የስብስባችን ስብጥር በተለያየ የእድሜ ክልል ያለንና የተለያየ ኃይማኖትን ያካተተ ነው፤ ለአብነትም ኦርቶዶክሶች፣ ሙስሊሞች፣ ካቶሊኮች፣ ፕሮቴስታንቶች ከዚህ በተጨማሪ የተለያየ ሙያ ባለቤቶች የሆንን አለን። እንዲሁም ከዚህ ቀደም የሰላም እናቶች በመሆን እርቅና ሰላም ይኖር ዘንድ በብዙዎች እግር ላይ ወድቀው ሲማጸኑ የነበሩ እናቶች በስብስባችን ውስጥ የተካተቱ ናቸው። ከዚህ በፊት በእርቅና በሰላም ስራ ላይ ልምድ ያላቸውም የሌላቸውም አሉበት። ያሰባሰበን ዋና ዓላማ እናትነት ነው። እንዳልኩሽ በስብስባችን ውስጥ ወጣቱንም አካተናል። ምክንያቱም ወጣቶች ሰላም ያለባት አገር ውስጥ መኖር አለባቸው ከሚል ነው። ስለዚህ እኛ እናቶች ልጆቻችንን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ከጎናቸው በመሆን መከራውን በመካፈልና የሕይወት ልምዳችንንም በማጋራት የማንም ለራሱ ፍጆታ ለሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት ማገዶ እንዳይሆኑ የበኩላችንን እንወጣለን።
አዲስ ዘመን፡- አባላቱ በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ያላችሁ እንደመሆናችሁ የመሰባሰባችሁና በጋራ መፍትሔ የማምጣታችሁ ጉዳይ እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– በየጊዜው እንሰበሰባለን። በአካል የመገናኘቱ እድል ያለን በአካል እንገናኛለን። በአካል መገናኘት የማንችለው ደግሞ በዙም እንሰበ ሰባለን። እኛ ዓላማችን ከአስራ አንዱ ባለፈ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በውጭ አገር ያሉትን ሌሎች እናቶችንም ማካተት ነው። ሁኔታዎች ከተመቻቹልን በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ ቢቻል በስታድየም ወይም በመስቀል አደባባይ ከተፈቀደልን ታላቅ ጉባኤ ለማድረግ አቅደናል።
ይህንን ጉባኤ ማድረግ የምንፈልገው እናቶች ተያይዘን ትውልድ እናስመልጥ በሚል ተነሳሽነት ነው። እግረ መንገደቻንን ደግሞ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ጥያቄያችንን ለመንግስት ለማቀረብ ነው። ባለፈው ጊዜ ባዘጋጀነው ጉባኤ በርካታ የመንግስትና የኃይማኖት መሪዎችም ተገኝተዋል። የተገኙ እነዚህ መሪዎች ከጎናችን እንደሚሆኑም ገልጸውልናል። በዚህም መሰረት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቢሮ ድረስ ሄደን አነጋግረናቸዋል። በወቅቱም ያሉን ነገር እኛ ወደእናተ ፈልገን መምጣት ሲገባን እናንተ ፈልጋችሁን መጥታችኋልና እናመሰግናለን ነው። በሚያስፈልገን ጉዳይ ሊረዱንም ቃል ገብተውልናል። ይሁንና በምን አይነት ሁኔታ ለመስራት እንደምንፈልግ ገና እቅድ እያወጣን ነው። በተመሳሳይ ደግሞ ታገኟቹኋላችሁ በተባልነው መሰረት ከቀናት በፊት የኢፌዴሪን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ለማግኘት ችለናል። በዚህም በጣም ደስተኞች ነን። እርሳቸውም ከጎናችን እንደሚሆኑ ቃል ገብተውልናል። በአገሪቱ ላይ ስላለው የሰላም ጉዳይ የሰላም ሚኒስቴር የሚመለከተው በመሆኑ ወደእነርሱም አቅንተን አነጋግረናቸው በነበረበት ወቅት በከፍተኛ ደስታ ከጎናችን እንደሆኑ ገልጸውልናል።
አዲስ ዘመን፡- ከሳምንታት በፊት ባካሄዳችሁት ስብሰባ እርስዎም እንዳሉት የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነርም ነበሩና በዋናነት ያካሄዳችሁት ውይይት ምን ነበር?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– የተሰባሰብነው የሰላም እናቶች የምንፈልገው የሰላም ጥሪ ማቅረብ በመሆኑ ይህን አስመልክተን ሐሳባችንን አቅርበናል። በተመሳሳይ በእነርሱ በኩልም ያለውን ሁኔታ ለመስማትም ነበር በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የጠራናቸው። በእርግጥ በወቅቱ በሙሉ የነበሩ የመንግስት ተወካዮች ከኃይማኖት መሪዎች በስተቀር እነርሱ የመጡት ራሳቸውን ወክለው እንደሆነ ነው የገለጹት። እኛ ደግሞ ራሱን ወክሎ የሚመጣውን ብቻ ሳይሆን መንግስትንም ወክሎ የሚመጣ አካል እንፈልጋለን። ለዚህም ነው በአሁኑ ወቅት የመንግስትን በሮች በማንኳኳት ላይ የምንገኘው። ነገር ግን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በጠራነው መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። በጉዳዩም በጣም ተነክተው ከጎናችን እንደሚቆሙ ቃል ገብተውልናል። ይሁንና ጉዳዩን ወደመንግስት ይዘው ሄደው የደረሱበት ውጤት ምን እንደሆነ አናውቅም። እንዲያም ሆኖ እኛ አሁንም ለመንግስት ጥያቄያችንን ማቅረብ እንቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፡- ወደመንግስት ያደረሳችሁት ጥያቄ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ቢታወጅ ከሚል ሌላ ምን ምን ጥያቄ አካታችኋል?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– ከጥያቄያችንም አንዱ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉትን የኢትዮጵያ እናቶች ለማስተባበር ድምጻችንን ማሰማት እንፈልጋለንና ሁኔታዎች ይመቻቹልን ነው፤ ምክንያቱም የመጀመሪያውን ጉባኤ ከሁለት ሳምንት በፊት ስናደርግ ሆቴል ተከራይተን ነው። እንዲህ ስናደርግ ግን ማናችንም የረባ አቅም ኖሮን አይደለም፤ ነገር ግን የአገር ጉዳይ ነው በሚል ተነሳሽነት እንጂ። በእርግጥ ደግሞ አካሄዳችን አገር እንዲረጋጋ መንግስትን እናግዝ በሚልም ነው። ስለዚህ መንግስትም እንደ ግል ጉዳዩ አድርጎ ድጋፍ እንዲያደርግልን እንሻለን፤ በምናደርጋቸው የተለያዩ ጉባኤዎችም አደራሾች እንዲመቻልን እንፈልጋለን። ድምጻችንን ወጣቶቻችንም እንዲሰሙል እንሻለን። ለጠፋው ትውልድ የአባቶችም ሃዘን አለበትና እነዚሁ የትውልድ አባቶችም ከጎናችን እንዲቆሙ እንፈልጋለን። በተለይ ወጣቶች በእነርሱ የወደፊት ሕይወት ላይ የተሻለ አሻራ ለማስቀምጥ በምንጥርበት ጊዜ በባለቤትነት ስሜት እንዲያግዙን እንሻለን። በጥቅሉ እኛ መንግስትን እናግዛችሁ እንጂ የገዥውንም ሆነ የተፎካካሪውን አጀንዳ ልናስፈጽም አይደለም ሩጫችን። ምክንያቱም በአገሪቱ ላይ ሕጋዊ የሆነ መንግስት አለ፤ ይህ መንግስት በሕጋዊ መንገድ ዜጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ነው። ታጥቆ የዜጋውን ደህነት ከሚጠበቀው ሕጋዊ መንግስት ወጭ ያለው አካል ግን እየበዛ ሕይወት እያጠፋ ሲሄድ እኛ እናቶች ዝም የሚያስብል ልብ ስለሌለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ የተፈለገበት ዋና ዓላማ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- ዓላማው በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ቁማር፣ የነበረው የፖለቲካ ጦስ ይህን ያህል ዓመት ሙሉ ትውልድ አሳጥቶናል። በእርግጥ እኛ የመቶ ዓመቱን ታሪክ ልንኖር አንችልም፤ የምንናገረው በእድሜያችን ያለውን ነው። እስካሁን ድረስ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው ትውልድ በመጨረስም ሆነ በማስጨርስ ተግባር ላይ የነበሩት እንጂ መንግስት ብቻ አይደለም። ምክንያቱም እነርሱ ወጣቱን ተነስ፤ ታጠቅና ጫካ ግባ ይላሉ፤ ወጣቱ ደግሞ ጫካ ሲገባ ሊገድልም ሊሞትም ነው። ይሁንና እኛ አሁን የሚንቀሳቀሰው በማንም ላይ ክስ የመመሰረት ዓላማ ኖሮን አይደለም። ማንንም ወደ ፍርድ አደባባይ የማመጣት እቅድም የለንም። ነገር ግን ጥፋት መንግስት ዘንድ ብቻ ነው ያለው ማለት አይቻልም። በ50 ዓመት ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም የየራሳቸውን ጥፋት አጥፍተዋል። ስለሆነም እነርሱም ይቅርታ እንዲጠይቁ ነው። በ50 ዓመት የገደብነው ዋናው ነገር አሁን ላይ እየታየ ያለው መከራ የዚያ ውጤት በመሆኑ ነው።
ስለዚህም የሃዘን ቀኑ ከዚህ በኋላ ትውልድ እንዳይረግፍ ለማድረግ ታስቦም ጭምር ነው። ለምሳሌ በውጪው ዓለም አንድ ሰው ሞተ ተብሎ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ይደረጋል። ብሔራዊ የሃዘን ቀን መታወጁ በተለያየ ምክንያት ሰዎች የሞቱባቸው አካላትን ሃዘናችሁ ሃዘናችን ነው ለማለት ጭምር ነው። ጎረቤት አስተዛዝኖት ይሆናል እንጂ እኛ በእነዚህ 50 ዓመታት ሕዝቡን ለቅሶ አልደረስነውም። እንደ አገርም ሆነ እንደ መንግስት እና ሕዝብ ሀዘኑን አልተጋራነውም። ሰዎች የሞቱት አገሬን ነጻ አውጣለሁ ወይም ብሔሬን ነጻ አወጣለሁ በሚል ጉዳይ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉን ያደረገው ከአገሩ አሊያም ከብሔሩ ጋር በተያያዘ ነውና የሞተባቸው ሰዎች ሃዘናችሁ ሃዘናችን ነውና ለዚህም እውቅና እንሰጣችኋለን ለማለት ነው።
ለምሳሌ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ መንበረስልጣን ሲመጡ እኛ ነን የገደልነው፣ አሸባሪዎች እኛ ነበርን እያሉ ሲናገሩ ነበር፤ እርሳቸው ገድለው አስረው ላይሆን ይችላል። ነገር ግን መንግስት የሰራው ስህተት ነው ብለው ነው ይቅርታ የጠየቁት። ልክ እንደእርሱ አይነት የአገሪቱ ርዕሰብሔር ያለፈውን የ50 ዓመቱን በደል መንግስትን ወክለው ይቅርታ ማለት ይችላሉ ማለት ነው። እኛ ሕዝቦች ደግሞ በ50 ዓመቱ ውስጥ መንግስትን አላሰራም ብለናል፤ ግማሻችን በትጥቅ ትግል፣ ገሚሳችን በብዕራችን ችግር ፈጣሪዎች ነበርንና እንደ ሕዝብ ደግሞ ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ ለአገር ብዙ የመጥቀሙን ያህል አብዛኛው የፖለቲካ ቀውሱም የሚመጣው በዳያስፖራው በኩል ስለሆነ በዳያስፖራውና አገር ቤት ባለው መካከልም እርቅ እንዲመጣ እንሻለን።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መሰረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብና እርስ በእርስ መግባባት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችለውን ስራ በይፋ ጀምሯል፤ የእናንተ ስራ ከእነርሱ የሚለየው በምንድን ነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- እነርሱ አላግባቡ ባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በየቦታው ህዝብን ማወያየት ለምሳሌ በኢፌዴሪ ሕግ መንግስት ላይ የማይስማማ ሰው ይኖራል፤ በሰንደቅ ዓላማ የማይግባባ አለ። በአዋሳኝ ቦታዎች የሚጣሉ አሉ። እንዲሁ ሌሎችም መሰል ጉዳዮች ይኖራሉ፤ በእነዚህ ጉዳይ ውይይት ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል። ይህም የራሱ የሆነ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ይታወቃል። በዚህ መሃል ደግሞ የሰው ልጅ እያለቀ ነው። ታድያ ውይይቱ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ በተቃራኒው ደግሞ ህዝብ እያለቀ ከሆነ ለማን ነው ውይይቱ የሚያስብለን ነገር አለ። ስለዚህ ውይይቱ ይቀጥል፤ እኛ ደግሞ የምንለው ጥርጊያ መንገዱን እንስራ ነው። ከወዲሁ አገር ማረጋጋት አለብን። እኛ ምድሪቷን ከሰማይም ከምድርም ጋር ማስታረቅ አለብን ነው የምንለው። ይህ ደግሞ ከእነርሱ ጋር የሚጣረስ ሳይሆን ይልቁንም የሚያግዛቸው ነው። እነርሱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የማግባባት እንጂ የማስታረቁ ስልጣን አልተሰጣቸውም።
በፊት የነበረው የእርቅ ኮሚሽን ይህን ሰርቶት ቢሆን ኖሮ ብዙ ጥርጊያ መንገድ በመጣ ነበር። በእርግጥ የበፊቶቹ የሚችሉትን ያህል ሞክረዋል። በአዋጅ ተቋቁመው በአዋጅ ፈርሰዋል። እርግጠኛ ነኝ እነርሱ በእጃቸው ላይ ያለውን ስራ ወደአሁኑ ኮሚሽን እንደሚያሸጋግሩ አስባለሁ። ምን ያህል ግብዓት እንደሆናቸው አላውቅም። እኛ ግን የምንሰራው እንደ እናት ነጻ ሆነን ነው። ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ነው፤ ፖለቲካዊ አባባል ነው ሌላም ሌላም ነው ሳንል ልክ እንደ እናት ነው የምንነጋገረው። ሌላውም እንዲሰማ የምንፈልገው እንደ እናት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሰው ከራሱም፣ ከፈጣሪውም፣ ከመሰሉም፣ ከአካባቢው እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው እንፈልጋለን በሚል መርህ ነው እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት፤ ይህ ምን ማለት ነው?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡– ኢትዮጵያውያን እንዳልኩሽ ፈጣሪ አለ ብለው የሚያምኑ ናቸው። ይህ በሙስሊሙም፣ በክርስትያኑም በስፋት ያለ ነው። በምድሪቱ እስካሁን በፈሰሰው ደም የተነሳ ያለው እርም ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ስለምድሪቷ እየጮኸ ነው። ስለሆነም የፍትህ አምላክ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር መታረቅ አለብን። ፍትህ እንዲመጣልን ደግሞ እግዚአብሔርን ምህረት እንጠይቅ ነው። ሌላው ከራሳችን ጋር ያልነው በደረሰብን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ጉዳት የተነሳ ቁጡዎች ብሎም አኩራፊዎች ሆነናል። ግማሾቻችን የምናኮርፈው በመንግስት ነው፤ ገሚሳችን ደግሞ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው፤ ሌሎቻችን ደግሞ በሌላ ምክንያት ነውና እሱ ነገር ቁጣ፣ ምሬት፣ እልህና ብስጭት እንዲሁም በቀል ሞልቶብናል። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ ከራስ እንደመጣላት ነውና ከራሳችን ጋር መታረቅ አለብን።
እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ ባለፉት 50 ዓመታት ያህል ሞክረነዋል፤ ቂመኛም ጸበኛም ሆነን፣ የትጥቅ ትግል ብለን፣ በከተማም መሃል ሆነን ድንጋይ ወርውረን አይተነዋል። ነገር ግን የትም አላደረሰንም፤ አያደርሰንምም። እስኪ አሁን ያልሄድንበት መንገድ ቢኖር ይህ አሁን ይዘነው የመጣነው የእርቅና የሰላም መንገድ ነውና ከአምላካችን ጋር እንታረቅ፤ እርስ በእርሳችንም እንታረቅ ነው። ያስቀየምናቸውን ጨምሮ እኛ መሳሪያ ታጥቀን ሰዎች ባንገድል እንኳ ሰዎች የሞቱባቸውን ይቅርታ እንጠይቃቸው ነው። ከተፈጥሮ ያልነው እንደሚታወቀው መንግስትም የጀመረው በጎ ተግባር አለ። ያንንን መከተልና ዛፉንም ዝም ብሎ አለመቁረጥ በራሱ ከተፈጥሮ ጋር እርቅ እንደማካሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በያዛችሁት ዓላማ መጓዝ የምትፈልጉት የት ድረስ ነው? ምንስ ሲሳካ ነው እርካታ የምታገኙት?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- እኛ እርካታችን ምድሪቷ እፎይ ስትል ነው። እርስ በእርስ መገፋፋቱ፣ መገዳደሉ አንዱ በሌላው ላይ የሚያደርሰው የአዕምሮም የስነ ልቦና ጫናው ቆሞ መተባበር፣ መግባባትና መተሳሰብ ሲኖር ነው። ይህ ደግሞ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል፤ ያለንስ ጉልበት የት ድረስ የሚያደርስ ነው ቢባል አናውቀውም። እኛ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢሆን ደስተኞች ነን። ነገር ግን ይህ እስኪሆን ድረስ እንተጋለን። ከዚህ በተረፈ ግን ብዙዎች አሁን የሐሳባችን ተካፋይ እየሆኑ ስለሆነ የተነሳንበትን ዓላማ ብዙ ሰው መደገፍ መቻሉ በራሱ የመከራችንን ዘመን ለማሳጠር ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን። በቀጣዩ ዓመት እርቅና ሰላም የሰፈነባት፣ የለቅሶ ድንኳን ሳይሆን የወጣት ሙሽሮች ድንኳን የሚተከልባትን ምድር እናያለን ብለን ነው የምናምነው፤ የምንናፈቀውና ተስፋ የምናደርገውም እሱ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምትሰሩት ስራ መንግስትን ማገዝ ነው የምትፈልጉት፤ እናንተስ መንግስት ምን እንዲያደርግላችሁ ነው የምትፈልጉት?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- በመጀመሪያ ደረጃ መንግስት ይዘን የተነሳነውን ዓላማ እንዲያምንበት እንፈልጋለን። መንግስት እንግዲህ እያልነው ነውና አቅም በሚያንሰው ቦታ ሁሉ እንዲተባበረን እንሻለን። በእርግጥ እኛ እንደ ሕዝብ መንግስትን አላሰራ ብለነዋል። ሚዲያዎችም እንዲሁ እንዲተባበሩን ፍላጎታችን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያ እናቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎ?
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- የኢትዮጵያ እናቶች ሆይ! እኛ ከዚህ በኋላ ትውልድ እንዲነጠቅብን አንፈልግምና ልጆቻችሁን ላልተገባ አካል አትስጧቸው። በየጫካው በመሆን ሰዎችን የምትገድሉብን እባካችሁ ያንን አታድርጉ፤ ልጆቻችንንም የዚያ አይነት ዓላማ ውስጥ አታስገቡብን እንዲሉ ነው የምንፈልገው። የራሳቸውን የፖለቲካ ሒደት ለማጋጋል ልጆቻቸውን የሚያሸፍቱባቸውን አካላት ይብቃችሁ እንዲሏቸው ነው የምንፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ሰዋሰው፡- አዲስ ዘመን እድሉን ሰጥቶን ይህን የእናቶች የዘመናት የሰቆቃ ድምጽ እንዳሰማ ስለፈቀደልኝ እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014