‹ትሁት..አንቺ ትሁት..› በእንቅልፍ ልቤ የእናቴን ድምጽ ሰማሁት:: እናቴ በእውኔ ብቻ አይደለም በህልሜም ያለች ሴት ነች:: በህይወቴ የትም ቦታ አለች:: በሴትነቴ ጉራንጉር፣ በሰውነቴ እንጦሮጦስ ውስጥ የትም አገኛታለው:: ብዳብሳት የትም የማላጣት ሴት ናት:: ከእማዬ በቀር ተኝቼ የማልመው ህልም የለኝም:: የቀን ታሪኮቻችንን እያለምኩ ነው ከእንቅልፌ የምነቃው..የምነቃውም እንዲህ እንደዛሬው በጥሪዋ ነው:: በህልሜ የማይመጣ ፊት፣ የማላየው ገጽ የላትም:: ቤታችን ካለችው መደብ ላይ ቁጭ ብላ እየፈተለች አሊያም እንዝርቷን እያሾረች ህልሜ ይጀምራል:: የህልሜ መቋጫ ጥሪዋ ነው:: ከእውኔም በህልሜም ሴትነቴ ውስጥ ተሰንቅራ የትም አያታለው::
በእናቴ ጥሪ ከእንቅልፌ ተቀሰቀስኩ:: ህልሜን ሳልጨርስ አልሜያት ሳላበቃ:: አልነጋም እኮ አባዬ ለገና የገዛው ከመታረድ የተረፈው የቤታችን አውራ ዶሮ ከጮኸ አልቆየም:: ለምን በዚህ ለሊት ተነስታ እንደምታስነሳኝ ሊገባኝ አልቻለም:: ጥሪዋ ቢሰማኝም እንቅልፌን ስላልጨረስኩ አቤት ማለት አልቻልኩም:: እንቅልፍ ጨርሶ ጠዋት መነሳት ምን እንደሚመስል አላውቅም:: እንደ መርዶ ነጋሪ ለማኝ ሳይፀዳዳ በውርጩ ነቅቼ የቤታችንን እዳሪ ነፍስ የምዘራበት እኔ ነኝ::
‹እስከ አሁን ተዘፍዝፈሽ..ቀኑን ሙሉ ተኝተሸ ልትውይ ነው እንዴ?..በይ ተነሽ› ብላ ጆሮ ግንዴ ላይ አንባረቀችብኝ:: እንቅልፌ ብቻ አይደለም ቀልቤም ትቶኝ ሄደ:: እናቴ የቤታችን ሰይጣን ናት:: አባቴ ደግሞ የቤታችን መላዕክ:: በነዘሲህ ሁለት መንፈሶች የምሰቃየው ደግሞ እኔ ነኝ:: ታላቅ ወንድሜ አግብቶ ከእናቴ ሰይጣንነት ተገላግሏል:: እኔም መች ይሆን ከዚህ ቤት ወጥቼ ከእናቴ ሰይጣንነት የምገላገለው ስል አስባለው:: አግብቶ የሚወስደኝ፣ ከእናቴ የሚገላግለኝ አንድ ወንድ ማጣቴ ይቆጨኛል:: የሴት ልጅ ተስፋዋ ወንድ መሆኑን ሳስብ እናደዳለው:: ሴት ልጅ ከእናት አባቷ ቤት ለመውጣት ከማግባት ውጪ ምንም አማራጭ አንደሌላት ሳስብ ሴት መሆንን እኮንናለው:: ወንድ ብሆን የእናቴ ሰይጣንነት ባልተሰማኝ ነበር እላለው:: ከእናቴ ሰይጣንነት ለመገላገል ስል ወንድነትን እናፍቃለው:: አጠገቤ እንደ መላዕክ በዝምታ የሚኖር አባት ስላለኝ የእናቴ ሰይጣንነት ጠልቆ አይሰማኝም::
እናቴ የኔን መተኛት ቀኑን ሙሉ አለችው:: እናቴ ቀንና ሰዐት እንዴት እንደምትቆጥር አላውቅም:: ገና እኮ ከለሊቱ አስራ አንድ ሰዐት ነው:: ገና እኮ አውራ ዶሯችን መጮህ አላቆመም:: ይሄን ከእኩለ ቀን ያመለጠ ለሊት ቀን ሙሉ አለችው..እስካሁን ተዘፍዝፈሽ አለችኝ:: ተነሳሁ..ከዚህ በፊት እንደነቃሁባቸው ማዕልቶች እየተነጫነጭኩ..እያጉረመረምኩ:: ከአባቴ ዝምታን ከእናቴ ጉርምርምታን ወርሻለው:: በሰይጣንና በመላዕክት መሀል መኖር ምን እንደሚመስል እኔ ናሙና ነኝ::
ገና እኮ የለሊት ልብሴን አልቀየርኩም..ገና እኮ ደጅ አልወጣሁም..ገና እኮ ፊቴን አላጸዳሁም ‹ዛሬ የአመቱ ገብርኤል ነው፣ አዲሱን ነጠላዬን አውጪልኝ ቤተክሲያን ስሜ ልምጣ› አለችኝ:: ጉስቁልናዬ ጀመረ:: ባደፈ ፊትና ገላ ከነለሀጨ የእናቴን አዲስ ነጠላ ፍለጋ ጀመርኩ:: ከግማሽ ሰዐት ፍለጋ በኋላ አዲሱ ነጠላዋ ተገኘ:: እናቴ እቃ ስታስቀምጥ በግራ እጇ ነው መሰለኝ ቶሎ አይገኝም:: እናቴ አስቀምጣው ቶሎ የምታገኘው እንዝርትና ጥጧን ነው:: ከምትቀመጥበት መደብ ውጪ የትም ስለማታስቀምጠው በቀላሉ ታገኘዋለች::
አዲሱን ነጠላዋን አቀበልኳት:: ‹ስመለስ የምጠጣው ቆንጆ ቡና አፍልተሽ እንድትጠብቂኝ› ከምትል ቀጭን ትዕዛዝ ጋር ነጠላዋን ተቀበለችኝ::
‹ቆንጆ ቡና እንዴት ነው? አልኳት::
‹ቆንጆ ቡና ሳታውቂ ነው ሴት የሆንሽው? አለችኝ::
ጥሎብኝ ሙያ የለኝም..ሙያ የለሽ መሆኔን ደግሞ ከአባቴ በቀር ድፍን ሰፈራችን ያውቀዋል:: እናቴ ‹ምን ይሆን የሚጣፈጥልሽ? ብላኝ ታውቃለች:: አባቴ ግን ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔ ካላፈላሁለት ቡና አይጠጣም:: እኔ ምግብ ካልሰራሁለት አይበላም ለምን ስለው ያንቺ ሁሉ ነገር ያስደስተኛል ይለኛል:: አባቴ መላዕክ ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል? እማዬ የምታዘኝን ከአባቴ ጋር ለሁለት ሰርተን እናውቃለን:: አይደለም ሊያዘኝ..አይደለም በሌሊት ሊቀሰቅሰኝ ቀርቶ በእማዬ ትዕዛዝ ውስጥ አብሮኝ የሚለፋ አጋሬ ነው::
‹ስሚ አንቺ ረኸጥ..›አለችኝ እናቴ::
ልሰማት ቀና አልኩኝ..
‹ቆንጆ ቡና ማለት ያልወፈረ፣ ያልቀጠነ ያልመረረ ቡና ነው:: ስመጣ አሁን ያልኩሽን ቡና አፍልተሸ እንድትጠብቂኝ› ስትል ነጠላዋን እያጣፋች ገላመጠችኝ:: ከአጠገቧ ስሄድ ‹ይብላኝ ሴት ናት ብሎ ለሚያገባሽ› ስትለኝ ሰማኋት::
ምን ረስታ እንደሆነ እንጃ ደግሞ ወደ ሳሎን ተመለሰች:: እናቴ መንቆራጠጥ ልሟዳ ነው..ያንቆራጥጣታል:: ከሄደችበት ተመልሳ ‹ምናለ ዛሬ እንኳን ቤተክርስቲያን ብትሄድ? አለችው አባቴን::
አባቴ ዝም አላት..ከየት እንዳመጣው እንጃ ለእናቴ የሚሆን ብዙ ዝምታ አለው::
‹በመቁረቢያ እድሜህ እዚህ ተጋድመህ..አንተን ብሎ ወንድ› ስትለው ሰማሁ:: በአባቴ እንደዛ መባል ስቅጥጥ አለኝ:: እናቴ አባቴን አታከብረውም:: የሴት ልጅ ውበቷ ምኗ ነው ላለኝ የምመልሰው ብዙ መልስ አለኝ:: ከእናቴ ነውረኛ ሴትነት ውስጥ የቀሰምኩት:: አባቴ አሳዘነኝ..ቀና ብዬ ሳየው በወትሮ ዝምታው ውስጥ ነው:: በዝምታው ውስጥ ምን እንደሚያስብ ባውቅ እላለው::
ከአባቴ ወደ እኔ ዞራ..‹እንደ ነገርኩሽ ስመጣ መራራ ቡና እንዳታጪኝ፣ አንቺ እንደሆነ ልብ የለሽም› ብላኝ ወጥታ ሄደች:: እናቴ ሳርፍ አትወድም..የሆነ ነገር ፈጥራ የሆነ ነገር ትለኛለች እንጂ እሷ እየፈተለች እኔ እያወራኋት አጠገቧ እንድቀመጥ አትፈልግም:: የምትፈትለውን ጥጥ አጠገቧ ሆኜ ስፈለቅቅላት እንኳን ያገዝኳት አይመስላትም:: ‹እዚህ ከምትዘረፈጪ እስኪ ሂጂና ለእግሬ ውሀ አሙቂልኝ ትለኛለች:: ውሀውን አሙቄ አግሯን አጥቤያት አጠገቧ ቁጭ ስል:: እንግዲህ መጣሽ በወሬ ልታደርቂኝ..ሂጂና ትላንት የዘፈዘፍኩትን ልብስ አጥበሽ ስቀይ ትለኛለች:: የተዘፈዘፈውን ልብስ አጥቤ ሰቅዬ ቤት ስገባ ‹ከእትዬ ተዋበች ቤት ነገ የሚመለስ አንድ ስኒ ቡና ተበድረሽ ነይ ትለኝና ወደዛ እሄዳለው፡: እናቴ አጠገብ ሆኜ እናቴ ትናፍቀኛለች:: እንደ ልጅ አጠገቧ ቁጭ ብዬ የሆዴን ያወራኋት ግዜ የለም:: ለነገሩ እሷም አርፋ አታውቅም..ስትፈትልና ስትደውር ሸማኔ ቤት ስትመላለስ ነው የምትውለው:: ሰፈሩ ውስጥ ፈትላ ጋቢ ያላለበሰችው አንድም የለም:: የዛሬ አመት የተዳረው ታላቅ ወንድሜ እንኳን በእናቴ ጋቢ የተዳረ ነው:: እኔ ብቻ ነኝ ውጤት ሳይመጣልኝ ቤት የእናቴ ተላላኪ ሆኜ የተቀመጥኩት:: ዩኒቨርሲቲ የሚማረው ታናሽ ወንድሜ በእናቴ ጋቢ ላለመመረቅ ከአሁኑ ማስጠንቀቂያ እየላከልን ነው::
አባቴ በዝምታ የሚያምን ዝምታ ነው:: ከእናቴ ጫጫታ ይልቅ የአባቴ ዝምታ በእግዜር ፊት የሚሰማ ይመስለኛል:: ዛሬ ከነጋ እንኳን እኔንና ተከራዮቹን ስንት ግዜ በማይሆን ነገር ተቆጣችን:: እንግዲህ ይቺ ናት እናቴ..በዚህ ልብና ነፍሷ ነው ለተማጽኖ እግዜር ቤት የምትሄደው::
እንደ ምትፈለቅቀው ጥጥ፣ እንደ ምታሾረው እንዝርት እጇ ላይ ነኝ:: እንደ ቋጨችው ሸማ፣ እንደ ፈተለችው ድርና ማግ ከታሪኳ አልጠፋም..ከታሪኬ አጠፋም:: እኔና እናቴ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ነን..ዘውድና ጎፈር:: የጥፍሬ ጥፍረ መጥምጥ ናት..የመዳፌም አይበሉባ:: የመረቧ አሳ ነኝ..የጣቶቿም ጓንት::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2014