ሆያ ሆዬ እና እዬዬ

ምድር አረንጓዴ ባተቶ ለብሳለች። ሰማዩ ሊሄድ በቃጣው የክረምት ጭጋግ ቡራቡሬ መልኩን ይዞ ከበላይ ተሰትሯል። አደይ አበባዎች በየመስኩና በየሜዳው በላያቸው ላይ ነፍሳትን አሳፍረው ይታያሉ። አዕዋፍት በበረታና ባዘገመ ፉጨት ከአንባ ሲደመጡ መስከረም ሁሌ በመጣ ያስብላል።

ጋሽ ፍሰሃ የዘጠኝ ልጆች አባት መሆናቸው የሚያስቆጫቸው በዓል በደረሰ ሰሞን ነው። መቼም ለምን የሚል አይጠፋም.. መስከረም ከነከርሱ አፍጦ፣ እንቁጣጣሽና መስቀል ፊት ቆመው አዬዬ የማይል ካለ ዳንጎቴ ብቻ ነው።

ለዘጠኝ ልጆች አባት አዲስ ዓመት የአዲስ መከራ መምጫ እንጂ የአሮጌ ዓመት መሄጃ አይደለም። አዲስ ዓመት ውበት ያለው ላለው ከሆነ ሰነባብቷል። ለሌለው የሌለው መሆኑን ከመናገርና በጎረቤት ተድላ ከመቋመጥ ባለፈ እርባና የለውም። አዲስ ዓመት እንደስሙ የአዲስ ዓመት ጅማሮ ቢሆን ጥሩ ነበር ግን አይደለም። ከአሮጌው ዘመን ጋር የሚለዋወጠው ሸርና ክፋት አለው። ያላለቁ አበሳዎች የሚያልቁበት..

‹ዘመን መለወጫ ድሮ ቀረ› የሚል ተረት አውሪ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። በስሙኒና በድንቡሎ ሙክት እያረደ ቀን የወጣው አያቴ ይሄን ዘመን በመጠየፍ ተወዳዳሪ የለውም። እናቴስ ብትሉ እናትና አባቷ ጋር የበላችውን እያሰበች፣ ከአባቴ ጋር በአፍላ ፍቅር የሆኑትን የዝብናኔ ጊዜ እያስታወሰች ይብላኝ ለእናንተ በስጋ ፈንታ ስጋት ለገባችሁና በስግብግብ ትውልድ አህያ ቄራ ለዋላችሁ ወደማለት ተሸጋግራለች። እኔ ምንም አልል..ሃሳቤን በእናትና በአባቴ ላይ ጥዬ ከርሴን እሞላለሁ።

ሰው እስከሆነ ጊዜ ድረስ ሃሳብ የሌለው እንስሳ ነው። አእምሯችን በምቾት አንቀላፍቶ ሰንብቶ ለራሳችን መኖር በጀመርንበት የሆነ ጊዜ ላይ ላለመውደቅ የምናደርገውን ትግል አይቶ የሚነቃ ይሆን? እንደዛ ይመስለኛል.. ሁሉም ሰው ለማለት በሚደፍር ንግግር እናገራለሁ አንቀላፍተን የምንነቃ ነን። ያስደገፉን ሲንሸራተቱና የያዙን ሲያፈገፍጉ ያን እለት ማሰብ እንጀምራለን። የእኔ ማሰቢያ ጊዜም የከንፈር ወዳጅ ይዤ፣ ስለእሷ ሳስብና ስለአብሮነታችን ስተክዝ እንዲሁም ጥርስ ያበቀሉ ስሜን ሸሽገው አባዬ ብለው የሚጠሩኝ ልጆች ሲኖሩኝ ያን ጊዜ ነው እላለሁ።

ስጋ ስጋት የሆነበት ዘመን፣ ሰላም ቅንጦት የሆነበት ጊዜ ለትውልዱ የሥነቃል መዝገበ ቃላት ቢሆን ምን ይገርማል? እንደአባቶቹ ዘመን ከወዳጅ ዘመድ ስቆና ተጫውቶ፣ አጋርቶና ተጋርቶ ተመስጌን ብሎ የማይቀበለው ዘመን መጣ ቀረ ምን ሊበጀው? ደግሞስ በቀይ ምንጣፍ ጉዝጓዝ ላይ እንደልብ የማይሆኑለት ዘመን ምን ዘመን ሊባል?

‹እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ› ለዚህ ትውልድ ምኑም ነው። በደህናው ጊዜ እነዘሪቱ ጌታሁን ዘፍነውታል። ጦሙን በሽሮ ለሚፈታ፣ አዲስ ዓመቱን በባዶ ሌማት ለሚቀበል ትውልድ የዘመን መለወጥ ምኑ ነው? ሁዳዴን ሆነ ትንሳኤ በጾመኞች ሀገር ነን.. እናም ይሄ ትውልድ በዘመን ላይ ተረት ሲያንሰው ነው።

ሽሮ ባቅሟ መችና የት ልብላ በሚል ፈሊጥ እቅድ ውስጥ ስትገባ አስባችሁታል..እናስ ዘመን መጣ ቀረ ምን ሊፈይድ? ያቺ ከቅቤ ጋር በየሰው ቤቱ የማይጠፋው፣ ያቺ የሰንደቅ ዓላማችንን ያክል በሁላችን ታሪክ ላይ የተውለበለበችው..ያቺ የአረንጓዴ ቢጫ፣ ቀይን ያክል የምናውቃት ሽሮ የስጋን ክብር ይዛ ከቤታችን ከጠፋች ሰንብታለች። የት እንብላ በምን እንብላ የተቀየረበት ትውልድ። ከየትና ምን እንብላ ጦም ወደማደር የዘመነባት ሀገር..አዲስ ዓመት ምን ሊሠራው?

ድሮ ሽሮ የድሃ ባንዲራ ነበረች አሁን ሽሮ መካከለኛ ገቢ ላለው ማህበረሰብ ገቢ ሆናለች። ድሃው ሳይበላ በማደርና በቀን ለአንድ ጊዜ በመመገብ ሽሮ ናፋቂ..ድሮን አድናቂ ወጥቶታል። ያቺ የተቀናጣንባት..ልጅነታችንን እንደዶቃና አንቀልባ አቅፋና ሸክፋ በእሽሩሩ ቀን ያወጣችን ሽሮ ከድሃ ድሃ ወደ መካከለኛ የማህበረሰብ ክፍል ስትመነደግ ነገን ሰጋሁት። ነገስ የባለጸጎች የማትሆንበት ምን ዋስትና አላት? ወደሞጃዎች ከአሁኑ ዳዴዋን ጀምራለች..

ሙክት የሌለበት ዘመን፣ ቅርጫና ዶሮ፣ ከጠላና ጠጅ፣ ከቤት ያፈራው ጋር የሌለበት አውደዓመት፣ ዘመድ ያልመጣበት ወደዘመድ ያልተኬደበት ጉርብትና፣ ልጆች አዲስ ለብሰው ወላጆች በክት አጊጠው በሳቅ ያልዋሉበት፣ አበባየሆይ ያላሉበት..ቄጠማና ጠጅ ሳር፣ እጣንና ሰንደል ያልጨሰበት ከሰዓትና ማለዳ እውን አዲስ ዓመት ነው? ዘሪቱ ጌታሁን ያልዘፈነችበት፣ ሀመልማል ያላዜመችበት፣ ጤና ለሰጠው ሰው እድሜውን ላደለው አውዳመት ጸጋ ነው..ስትል ማን አለሙሽ ያልተምነሸነሸችበት፣ በአስራ ሶስት ወር ጸጋ ዜማው ጥሌ ያላቀነቀነበት አውዳመት አላውቅም።

እንኳን አደረሳችሁ የሚል የወዳጅ ዘመድ መልካም ምኞት የማይሰማበት፣ የዶሮ ሽታው፣ የዳቦው መዐዛ አጥር ባልዘለለበት፣ በምነው ባልመጣ ስሜት ቤቱ መሽጎ ማግስት እስኪሆን የሚጠብቅ ጎረቤት በበዛበት ቅዱስ ዮሃነስ ትርጉም የለሽ ነው።

በዓል በሁለት ልሳን የሚገለጽ ሆያሆዬና እዬዬ ነው። ለአንዳንዱ ሆያሆዬ ለሌላው እዬዬ የሁለት ወግ ስሜት። የላመና የጣፈጠ ለመብላት ዓመት የሚጠብቁ እንደጋሽ ፍሰሀ ያሉ ቤተሰቦች የመኖራቸውን ያክል አዲስ ዓመትን ለአዲስ ፌሽታ የሚጠብቁም ጥቂቶች አይደሉም።

ድሃ አዲስ ዓመት የለውም። የጠገበ እለት አዲስ ዓመቱ ነው። እኚህ ነፍሶች ለዘመን መቁጠሪያነት እንጂ ለተለየ ተልዕኮ አዲስ ዓመትን አይፈልጉትም። ለአንዳንዶች ካልሆነ ለብዙሃኑ አዲስ ዓመት የአዲስ መከራ መምጫ ነው ስለዚህም ብዙዎች ይፈሩታል።

ጋሽ ፍሰሃ በጥበቃ ሥራ የሚተዳደሩ የዘጠኝ ልጆች አባት ናቸው። ደም ብዛታቸውን ጨምሮ በሳይንስ ያልተረጋገጡ በሽታዎችን የሚታመሙት በአውዳመት ማግስት ነው። ደህና ሰንብተው ብቻቸውን ማውራት የሚጀምሩትና አንዳንዴም መንገድ ወድቀው በቃሬዛ ቤት የሚገቡት በበዓል ሰሞን ነው። እናስ ከትውልዱ ጋር አብረው ተረት ቢተርቱ፣ በዘመን ላይ ጥርስ ቢነክሱ ምን ይደንቃል?

ከነሐሴ አጋማሽ የቡሄ ጅራፍን ተከትሎ እስከ ጳጉሜ መዳረሻ ድረስ የእዬዬ ሰሞናቸው ነው። የዘንድሮውን በዓል በሆነ መላ ካልሆነ በጥበቃ ደሞዛቸው የሚዘልቁት አልመሰላቸውም። ስለሆነም በዓልን ታኮ ለሚመጣው የልጆቻቸው የፍላጎት ጥያቄ ከወዲሁ መላ ለማዘጋጀት ከራሳቸው ጋር ሳምንት መክረዋል። ትናንት ማታ ከሥራ ውለው ወደቤታቸው ሲገቡ በሚገርም ንቃት ነበር። ይሄን ንቃታቸውን ያየች ባለቤታቸው ወይዘሮ ይመኙሻል ከእንዴት አመሹ በፊት ‹ምነው ሥራ አልገባህም እንዴ? ስትል ከመንገድ እንደተቀበለቻቸው ያስታውሳሉ። ለሊቱን ከዚህ ብልሃታቸው ጋር አድረው ነቁ።

ማለዳ የበዓል ሰሞን ላይ የሆነ የሚገዛ ድባብ አለው። ሁሉም ነገር ውብ የሚሆነው በዓል ሰሞን ላይ መሆኑ ለኔ ብቻ ይሆን የሚገርመኝ? በሚዘምሩ ወፎች፣ በሚንጣዙ ነፍሳት፣ በለመለሙ ሳሮች፣ በአረንጓዴ ቀይ፣ በብሩህ ሰማይ፣ በዘሪቱ ጌታሁን ዜማ ታጅቦ የማይደንቅ ማለዳ ይኖር ይሆን? ካለ ለጋሽ ፍሰሃና ሽሮ ለከዳቻቸው ድሆች ይመስለኛል..

በግምት ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ቢሆን ነው..ጋሽ ፍሰሃ ለቤተክርስቲያን መሳሚያ እና ለአንዳንድ ሁነኛ ጉዳይ ካልሆነ በማይጠቀሙበት ሀጫ ጋቢያቸው ጋር ወደቤት ሰተት አሉ። ከነጭ ጋቢያቸው ጋር ሲታዩ ከመላዕክት አንዱ ወደቤታቸው ጎራ እያለ ይመስል ነበር።

በማለዳ ከእኩዮቻቸው ጋር ተጠራርተው ለእንቁጣጣሽና ለሆያ ሆዬ ልምምድ ከወጡ አራት ልጆቻቸው በቀር አምስቱ ልጆቻቸው ዙሪያቸውን ከበው ስለሚገዛላቸው አዲስ ልብስ ሲያውኳቸው..ከከረመ መላቸው አንዱን መዘው ይሄን አሉ..‹ልጆቼ ለአዲስ ዓመት አዲስ ልብ እንጂ አዲስ ቀሚስ አያስፈልግም። በአዲስ ልብ ፈንታ አዲስ ልብስ እየገዛን ነው አሮጌነታችንን መሻር ያቃተን። በልብሳችሁ ሳይሆን በሃሳባችሁ አዲስ መሆንን ተለማመዱ። ይሄ ለሁላችሁም የበዓል ስጦታዬ ነው.. ከእኔ ለእናተ ከእናተም ለልጅ ልጃችሁ የተላለፈ..። በመሻገር ቀን ላይ ይሄን አይነቱን እሳቤ ማለፍ ይጠበቅብናል..› በማለት ልጆቻቸውን በየተራ አቀፉ።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም

Recommended For You