አንቀልባ

ባላደኩ..

ትላንትን ካላስረሳ ማደግ ምን ሊረባ?

ኖዎር እና ነውር..በሕይወት ግርግም ስር ምንና ምን ናቸው?

……….

አስራ አምስት ቀናት በምድር ላይ አልነበርኩም። አንዳንዴም ከዛ እሰነብታለሁ። ከሕልሜ ስንሸራተት፣ በፍኖተሎዛ አሸልቤ እንደያዕቆብ የወርቅ መሰላል አላይ ስል፣ ተስፋ ያደረኩት ሲርቀኝ..ራሴን ድራሼን አጠፋዋለሁ። ራሴን ስሰውር ማንም አያስተውለኝም። ውሀ አጣጬ የወርቅ ውሃም ብትሆን አታውቀኝም።

‹አስተውለሽ ከሆነ ያልነበረውን እኔን ነበር ስታቅፊና ስትዳሪው የሰነበትሽው› ብላት ምን እንደምትመለስ ባላውቅም ለመቼም የማይፀዳ ግርታን ግን እጠብቃለሁ። እንደሰው ነኝ እኮ! ግን በከፊል አቅሌን ስቼ ነው።

በሕልሜ የተሳለ ልደርስበት የምሻው ግን ያልደረስኩበት የሆነ ስፍራ አለኝ። መንገዶቼ በሳማና ጋሬጣ ሲከለሉ የማልደርስበት እየመሰለኝ እላሽቃለሁ። ያኔ እሰወራለሁ..ድምጥማጤን አጥፍቼ ኃይል አሰባስባለሁ።

ወደመሮጫ ትራካችን ያገጠጡ ብዙ የድካም ጨረሮች አሉ። ከነዛ ጨረሮች መሐል አንዱ ሲጨርፈኝ ራሴን እሰውራለሁ። ከሰው መሐል በሀሳቤ እርቃለሁ። ከቤቴ፣ ከትዳሬ፣ ከግዛቴ ሸሽቼ አንባ እጠጋለሁ። ሀሳብ መደበቂያ ዋሻ ነው። ሀሳብ ሀገር ነው..ከዚህ ወደዛ ማቅኚያ። ራስን በሕልም ውስጥ እንደመሰወር የፅድቅና ገዳም አለ ብዬ አላስብም። ወዴትም ሳላገድም ከምርጦቼ አንዱ ወደሆነው ተስፋዬ እንፏቀቃለሁ። ልክነት እስኪጎበኘኝ ድረስ በሕልሜ ሽንቁር ውስጥ አጮልቃለሁ። ሰንኮፌን ገፍፌ ብቁ ስሆን በሄድኩበት መንገድ ወደጎጆዬ እመለሳለሁ። ከዝምታ፣ ከሽሽታ ወደ ሕ ይወት..

ጣሪያዬን ሸንቁሬ ጨረር አልናፍቅም። በሬንና መስኮቴን እከፍታለሁ እንጂ። ልባችን ለግሞ እንጂ አልከፈት ያለ በርና መስኮት የለም። በሬን ኦና አድርጌ ንፋስ አላስገባም..ጓዳዬን አላስቃኝም። በንፋሱ ልክ በሬን እገረብባለሁ እንጂ። ጨረቃን ለማየት በቀን አላንጋጥጥም ሲመሽ እወጣለሁ እንጂ። ፀሐይን ለመሞቅ በምሽት አልባዝንም እኩለ ቀንን እጠብቃለሁ። ለፈካ ብርሃን ላምባዬን አልደፋም..ኩራዜን አልሰብርም መላ እዘይዳለሁ እንጂ።

ያለቦታችን ቦታ የለንም። የቆምንበት የእኛ ካልሆነ እንሸራተታለን። የእኛ ከሆነ ደግሞ ማንም አይገፋንም። ለፊት ለፊት ከሆነ የታጨነው ከኋላ ብንቆም እንኳን ወደፊት መምጣታችን አይቀሬ ነው። ኋለኞች ከሆንም ፊት ብንገተርም ማፈግፈጋችን ያመነ ነው።

……….

አንቀልባ የሕይወት ከፈኔ…

ከተፈጥሮ ኩሬ ስር በደም እርጎ ስንፎለፎል፣ እንደመሐረብ ለገላዬ የተሰጠኝ ብጣቂ ጨርቄ ላይ ሕልሜ ታትሞበታል። በቀራንዮ በጨርቋ ላይ የጌታን ፎቶ እንዳስቀረችው ቬሮኒካ ምስሌ ቀርቷል። በማርያም ስም፣ በእልልታ በእናቴ ደረት ላይ በልጅነት ሳርፍ የነበረውን እያለምኩ ማደግን ጠላሁት። እስካልገባን ድረስ ልጅነት ነውራችን ነው እስከገባ ድረስ ማደግ ውርደታችን ነው። የሕይወትን አሳማሚ አርጩሜ ወደንና ተገደን የምንቀምስበት የቅጣት ክፍለዘመናችን ነው..ማደግ።

በብርሃን ሽርጥ አንዳንዴም በጉም ባተቶ ታጅባ በምስራቅ ሽንቁር ስር ፀሐይ ትወጣለች..በምዕራብ ትጠልቃለች..ዓለም አዲስ ነገር የላትም። አዲስ ነገራችን ከእናታችን ጀርባ..ከእቅፏ ስር የቀረ ነው። ነፍስ ማወቅ በሚሉት ፀጋ ገፋፊ ብሂል ካጠላብን የተፈጥሮ ጥላ እየራቅን ወደተሲያት መንሸራተት። ዳዴ ማለትና በአትያዙኝ ስም ራሳችንን ችለን መቆም ስንጀምር የሚጀምር መከራ እንጂ ድሎት የለም።

ሕልማችን ልጅነታችን ጋ ቀርቷል..አብሮ ከስሟል። ከእናት ጀርባ ስንወርድ፣ አፋችንን በስድብ የፈታን እለት፣ ሰባት ዓመታችንን ስናከብር፣ ትምህርት ቤት ለመግባት ጆሯችንን ስንነካ ያኔ ላይመለስ ጥሎን ሸሽቷል። ለማቆጥቆጥ..ለመለምለም ሥራችን ህብስት አልቀበል እስኪለን ድረስ ዳክረናል። ችግር፣ መከራ፣ መውጣት መውረድ፣ ረሀብ እርዛት ከሽንቋጤአቸው ጋር እስኪተዋወቁን ድረስ ከአንቀልባ ወደባቅላባ የሁሉም ሰው ምኞት ነው። ማደግ እፎይን ካልሰጠን አለማደግ በስንት ጣሙ?

ከመከራዬ ለማምለጥ የእናቴን ጉያ እሻለሁ…ከነምናምኔ ውሽቅ ማለት። የሆነ እለት ሌሎች ሀሳባችንን ወርሰውልን ሀሳብ አልባዎች ነበርን። የሆነ እለት በእኛ በገዘፉ ተጠለን ተሲያት አልነበረንም። ዓለማችን በዓለማቸው ተሰፍቶ ዓለም የለሾች ነበርን። በማደግ ስም ከሰነበትንበት ጉያ ወጣን..ያን እለት ፀሐይን ተዋወቅናት። ዓለምን ዋጀናት። ተፈጥሮን ለመድናት..ከነመከራቸው።

ረሀባችንን ተርበው፣ ትካዜያችንን ተክዘው ነፃ ያወጡን ግዙፎች ዛሬም አሳቢያችን ቢሆኑም እንደያኔያቸው በልካቸው ሊያበጁን ግን የታደሉ አይደለም። በማደግ ስም እንቢታን ወርሰናል..በዘመን ስም ሀፍረትን ተከናንበናል። በተፈጥሮ በኩል ሌላ መልክን ተዋወቅናል። ለማንም የማይጋሩ ስሜትና ስሌት ሰለባዎችም ነን። ስለሆነም ድሮን ናፋቂ ቀኝ ዘመም ሕልመኛ ነኝ።

ልጅነቴ ጀምሮ ያበቃበት እሱ ስፍራ ሕይወቴ ጀምሮ ያበቃበት ነው። ዳዴ እንደከዳቸው እንደአራስ የዶሮ ጫጩት ከሽሌ ውስጥ ራሴን ፈልፍዬ እናቴ ጀርባ ላይ ማስቀመጥ ያምረኛል። ለመኖር ክንፋቸው እንዳልጠና ተንደፋዳፊ እፆች በእንፉቅቄ ሄጄ ሕልሜን ማስመር እንዲሁ። በልጅነት ልቤ ከኅዋ ተገንጥለው ወደቤት ሲያጮለቁ የማያቸው እነዛ የብርሃን ፍርግርጎች..አግድም ዘንበው የቤታችንን ለዋገን ያራሱ ውሽንፍሮች..እንደሙዚቃ ቆርቆሮ ላይ ሲያርፉ የሚሞዝቁት የዝናብ ራሶች..ባላደግኩን ነፍሴ ላይ ያሳርፉብኛል።

ትላንት ከዛሬ ዘገር ማምለጫ ዋሻችን ነው። ባላደግን ከሚል ምኞት አሽሽቶ ወደጥንተ ቡረቃችን የሚጥለን። ባላደኩ የብዙ ሰው የአሁን እንጉርጉሮ ነው። በትካዜያችን ሰሞን የሚይዘን እጅ ሲጠፋ፣ ተስፋ ያደረግነው ሲከዳን ያን ዘመን እንናፍቃለን። በወፌ ቆመች መቆም ያለመደንን፣ መሄድ ያስቻለንን እጅና ልብ።

በእሽሩሩ መቀመጫዬን እየጠበጠበ ጀርባዋ ላይ ያስተኛኝ፣ ከማህጸን እኩል ውበት ባለው በሆነ ዓይነት የሙዚቃ ድምፀት ወደእንቅልፍ የሄድኩበት የአባብሎት ዜማ፣ ዛሬም ድረስ ያላባራሁትን መሻት ያስታቀፈኝ የፀጉሯ ሸርታቴ በሆነች ሴት ተቀይሮ እማዬን ቢያስረሳኝ..ድሮዬን ቢያስጠላኝ..ልጅነቴን ቢቀማኝ አሊያም በዛ ሕልሜ ምትክ እሽሩሩ ባይ ቢሰጠኝ የሚለው ከሰነበቱ ምኞቶቼ መሐል ቢሆንም ድሮን ከማለም አልታደገኝም። በዶቃና በዛጎል ያጌጠው፣ በተራመደች ቁጥር እየተቅጨለጨለ እንደእሽሩሩዋ የሚያጅበኝ የእቅፌ አንቀልባ የነፍሴ የሙዚቃ ባንድ ሆኖ ባላደኩኝ ያስመኘኛል።

የእናቴ የአደሷ ጠረን የተዋረሰበት አንቀልባዬ፣ ከእርምጃዋ እኩል እንደጽናጽል የሚቅጨለጨሉት እነዛ ዛጎልና ዶቃ ውሕድ ድምፆች.. ጀርባዋ ላይ በተነሰነሰ ፀጉሯ ላይ ተደላድዬ ተኝቼ፣ ዛሬም ድረስ በሚገርመኝ ብልሀት በግራ ጎኗ በኩል አሳልፋ ጭኖቿ ላይ አስቀምጣኝ በፀጉሯ ሰንበር ያወጣ ጉንጬን እየጠነቆለች ስትስመኝ…ከጡጦ ወደጡት እየተገላበጥኩ፣ ነጭ ሳቀረሻ፣ በልቼ እንዳጋሳ ጀርባዬን ስትመታኝ፣ ስቅታዬ እንዲተወኝ አናቴ ላይ እፍ ስትልብኝ፣ የአናቴ ትርትር አንዳች እንዳያርፍበት ስትሸሽገኝ..የእጆቼን መዳፍ ከጎኗ አርቃ ስሯ ስትገነድሰኝ የነበረውን የሚደልዝ..እንዳልነበረ የሚያደርግ ምን የዘመን ሞገስ አለ? ባላደኩ…

ባላደኩ..

ማደግ ቅጣት ነው..በሥጋ ደልቦ በመንፈስ መኮሰስ። አለመወለድ እኩያ የሚሆነው ከመጥናት ጋር ነው። ነፍስ ማወቅ ነፍስ መሳት እንደሆነ ሳይገባን ማደግን እንናፍቃለን። ማደግ የብኩርና ፀጋን ገፎ ክፉና ደጉን የሚያሳውቅ ነው..መጨረሻው ግን እንደአዳምና ሄዋን ውለታ መብላት፣ በብዙ ርግማን ከርስት መፈንቀል ነው። አዳምና ሄዋን ኩነኔ ባልነካው በልጅ ሀሳብ ከክብር ጋር ነበሩ..አወቅን ባሉ ሰዓት የሀሳቦቻቸው አፎት ፈጃቸው። አፎቶቻችን ሀሳቦቻችን ናቸው..ቀንድ አውጥተው የሚወጉን፣ ጥርስ አውጥተው የሚነክሱን። ባላደኩ.. ከዘመን ባልተደባለኩ። ጊዜ አኩርፎኝ በበቀል ድሮ ላይ ቢወረውረኝ። እያቀረሻሁ፣ ሳላስብና ሳላመዛዝን፣ ክፉና ደጉንም ሳለይ እናቴ ሀሳብ ገነቴ ላይ በሰነበትኩ። ባላደኩ..

ትላንትን ካላስረሳ ማደግ ምን ሊረባ?

ማደግ መርሳት ነው..መርሳት ካልሆነ ግን ማደግ ማበድ ነው። ማደግ መፍራት ነው..ማፈር ነው..ካልሆነ ግን መዛል ነው። የዛሬ ቀለሞች የነገን ውበት ካልማረኩ..ካልሰወሩ..ካላደበዘዙ ወይም ካላስረሱ ማደግ መውደም ነው።

ኖዎር እና ነውር..በሕይወት ግርግም ስር ምንና ምን ናቸው?

ከእንግዲህ እንደልጅነታችን የምናቀረሽበት የእድሜ ወሰን የለንም። ሁሉም ጅላጅልነት በኖዎር ተቀይሯል። ኖዎር የማደጋችን ላቅ ሲልም የመብሰላችን ማረጋገጫ ነው። በነውር ቀይረን መደዴ ሲወጣን በሕይወት ግርግም ስል በትዝታ መሬት እንጭራለን።

ኖዎር የብስለት..ነውር ደግሞ የክስረት ማኅተሞች ሆነው ለእያንዳንዳችን የተሰጡን የእድሜ ዘውዶች ናቸው። ማፈርና መታፈር..

ልጅነቴ የሆነ መልክ ከሆነ ሀሳብ ጋ ስሏል። ዛሬም ድረስ የሚታየኝ ያ መልክና ሀሳብ ነው..

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 24/ 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You