መንግሥት በአስር አመቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሪ እቅዱ ላይ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብሎ ከለያቸውና በትኩረት እየሰራባቸው ከሚገኙ ጥቂት የኢኮኖሚ አምዶች አንዱ የማዕድን ዘርፍ ነው::
ይህን የማዕድን ዘርፍ በተደራጀ መልኩ አልምቶ ሀገራዊ እቅዱን ማሳካት ከሚጠበቅባቸው መካከል ክልሎች ይጠቀሳሉ:: ይህን መነሻ በማድረግ በኦሮሚያ ክልል ስለሚገኙ የማዕድን አይነቶች፣ የማዕድን ሀብቶቹን በተደራጀ መልኩ አልምቶ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተደረገ ስላለው ጥረትና ስለተገኙ ለውጦች ከኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለሥልጣን ኃላፊ ከአቶ ተስፋዬ መገርሣ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል::
አዲስዘመን፡- የክልሉን የማዕድን ሀብቶች በየዘርፋቸው ለይቶና አደራጅቶ ለማልማት ምን እየተሰራ ነው? ዋና ዋና የሚባሉ የማዕድን ሀብቶችን ቢገልጹልን::
አቶ ተስፋዬ፤ በክልሉ ሰፊ የማዕድን ሀብት አለ፤ በጥናት በተደገፈ ሁኔታ መጠኑንም ሆነ የማዕድን አይነቶቹ በየትኛው የክልሉ አካባቢ እንደሚገኙ መግለጽ አለመቻሉ ግን አንድ ክፍተት ነው:: ይህም የቀድሞው መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረት አናሳነት ጋር ይያያዛል:: በወቅቱ የማዕድን ሥራው የሚከናወነው በወሰኑ ባለሀብቶች ነው:: ለዘርፉ የሚመደበው በጀትም አነስተኛ ነበር:: የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሚባለው ተቋም ካልሆነ፣ በዘርፉ ላይ አተኩረው ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ነበሩ ማለትም አይቻልም::
አዲስ ዘመን፤ በክልሉ በጥናት የተደገፈ የማዕድን ሀብት መኖሩ ካልተረጋገጠ ሀብቱ ስለመኖሩ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ክፍተቶቹ አሁንም ቀጥለዋል ማለት ነው?
አቶ ተስፋዬ፤ የቀድሞውን አሰራርና በአሰራር ምክንያት የተፈጠረውን ክፍተት ያስቀደምኩት ከሀገራዊ ለውጡ በኃላ ያለውን እንቅስቃሴ በንጽጽር ለማሳየት ነው:: ከአራት አመታት ወዲህ በተደረገው እንቅስቃሴ በአሮሚያ ክልል የተቋም አደረጃጀት ለውጥ ተደርጓል:: የማዕድን ዘርፉ በክልሉ በባለስልጣን ደረጃ ራሱን ችሎ ተቋቁሟል:: የተቋመውም ሶስት ዓላማዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ነው:: አንዱ አላማም ክልል ውስጥ የሚገኘውን የማዕድን ሀብት ተደራሽ የማድረግ፣ ቆጠራዎችን ማካሄድ፣ በጥልቀት የመለየትና ማጥናት ነው:: በዚሁ መሠረትም ማዕድኖቹን በአይነትና በመጠን መለየት ተችሏል::
ሁለተኛው ዓላማ በጥናት የተለዩት ሀብቶች እንዴት ጥቅም ላይ ይዋሉ የሚል ነው:: ሶስተኛው ደግሞ የማዕድን ልማቱ በተፈጥሮና በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ማድረግ ነው:: በዚህ መልኩ ባለፉት ሶስት አመታት ሲሰራ ቆይቷል::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ስለነበር ውጤቱም አጥጋቢ አልሆነም:: ከሀገራዊ ለውጡ በፊትም ዘርፉን የሚመሩ በየክልሉ አደረጃጀቶች ነበሩ:: ችግሩ የአሰራር ሥርአት አለመዘርጋቱ ነው? ወይንስ ዘርፉ ከቢሮ ደረጃ ከፍ ብሎ አለመመራቱ ወይንም አለመደራጀቱ ላይ ነው?
አቶተስፋዬ፡- አንደኛ በክልሉ ራሱን ችሎ የተደራጀ ቢሮ አልነበረም:: ወጥ የሆነ አደረጃጀትም አልነበረም:: አንዴ በቢሮ ደረጃ ይዋቀራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጥምረት አንድ ክፍል ሆኖ እንዲሰራ ይደረጋል::
በክልል ደረጃም የማዕድን ሥራዎች አዋጅ አልነበረም:: ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮሚያ የማዕድን ሥራዎች አዋጅ ጨፌ ኦሮሚያ ላይ ቀርቦ የፀደቀው በ2011ዓም ከሀገራዊ ለውጥ በኃላ ነው:: የክልሉ የማዕድን ሀብት በፌዴራል ደረጃ ሲወጡ በነበሩ አዋጆች ነው ሲመራ የቆየው::
አንዱ ችግር ተቋማዊ አደረጃጀት ነው:: ሌላው በክልል ደረጃ ፖሊሲና አዋጅ አለመኖር ነው:: ሶስተኛው ደግሞ እስከታችኛው እርከን የተዘረጋ መዋቅር አለመኖር ነው::በአጠቃላይ ከላይ እስከታች የተደራጀ ነገር አልነበረም:: ብዙ ሥራዎች ቢቀሩም አሁን እነዚህ ነገሮች በመቀረፍ ላይ ናቸው::
አዲስዘመን፡- የአደረጃጀት ክፍተቶቹን ለመቅረፍ ጥረት ከተደረገ ወዲህ ስለተከናወኑት ተግባራት ቢገልጹልን?
አቶ ተስፋዬ፡– የተቋም አደረጃጀቱ ከተፈጠረ በኃላ ክልሉ ውስጥ ያሉትን የማዕድን አይነቶች የመለየት ሥራ ተከናውኗል:: ለዚህ ሥራም አስፈላጊውን በጀት በመመደብና በማዕድን ዘርፍ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ሀብቱን ለመለየት ተሰርቷል::
በዚህም ወደ 48 የሚደርሱ የማዕድን አይነቶች ማግኘት ተችሏል:: ከዚህ በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜም በኦሮሚያ ውስጥ በጥናት ታግዞ በተከናወነ የመለየት ሥራ የተገኘውን የማዕድን አይነት ለማስተዋወቅ ኤግዚቢሽን ተካሂዷል::
ባለስልጣኑ እነዚህን በጥናት የተደገፉ ሥራዎች ለማከናወን ወደ ሥራ ሲገባ ኤክስፖሎሬሽን የሚባል ወይንም ማዕድናቱ መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ክፍል አዋቅሯል:: በዚህ ክፍል በተከናወነ ሥራም አዳዲስ ማዕድናትን ማግኘት ተችሏል::
እስካሁን ባለው ሥራም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ማዕድናት መኖራቸውን ለማረጋገጥ ተሰራ እንጂ በመጠንና በአይነት ዝርዝር ሥራዎች በቀጣይ ይከናወናሉ:: ባለስልጣኑም ገና በአዲስ የተዋቀረ በመሆኑ ጠለቅ ያለ ተግባር ውስጥ አልገባም:: ጥልቅ በሆነው ሥራ ላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የማመቻቸቱ ሥራ ቀጣይ ተግባር ይሆናል:: በቀላሉ ሊለሙ በሚችሉት ደግሞ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርባቸው ጎን ለጎን ይሰራል::
አዲስ ዘመን፡- ከ48ቱ የማዕድን አይነቶች ዋና ዋና የሚባሉትን ቢጠቅሱልን?
አቶ ተስፋዬ፡ ዋና ዋና ማእድናቱ ወርቅ፣ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ኒኬል፣ ክሮማይት እንዲሁም እንደ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ ታንታለም የመሳሰሉ የጌጣጌጥ ማዕድናት ናቸው:: አብዛኞቹ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙም ናቸው:: ከማዕድናቱ መካከል ኢትዮጵያን ከዓለም አስረኛ ደረጃ ላይ ሊያስጠቅሳት የሚችለው ታንታለም የተባለው አንዱ ነው፤ ይህ ማእድን በጣም አብረቅራቂና ውብ ነው::
ማዕድኑ በኤሌክትሪክ ኃይል ለሚሞሉ ተሸከርካሪዎችና ለተንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ ግብአት የሚውል መሆኑ ተረጋግጧል:: ማዕድኑ በክልሉ ጉጂ ዞን ሰባቦር በሚባል ወረዳ በስፋት መኖሩ ታውቋል:: ማዕድኑ ፊትም ይመረት እንደነበር መረጃዎች ቢኖሩም፣ አሁን ላይ ጥሬውን ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ እንዲቀርብ በማድረግ የበለጠ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን፡ እነዚህ ዋና ዋና የማዕድን አይነቶች በክልሉ በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚገኙ ተለይቷል?
አቶ ተስፋዬ፡– በሁለቱ የጉጂ ዞኖች፣ ቦረና እና ሶስቱ የወለጋ ዞኖች እንዲሁም ኢሊባቦር ወርቅ፣ ብረትና ብረት ነክ የሆኑ ማዕድናት ይገኙባቸዋል:: ማዕከላዊ ወይንም ሸዋ ዞኖች ላይ ደግሞ ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ግብአት ሊውሉ የሚችሉ፣ ጅማ አካባቢ ደግሞ የድንጋይ ከሰል የሚገኙባቸው ናቸው:: እነዚህ በዋናነት ተጠቀሱ እንጂ በክልሉ 21 ዞኖችም የተለያዩ የማዕድን አይነቶች ይገኛሉ::
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ዘርፉን ክልልን አካባቢንና ሀገርን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ክልሉ ያለው ቁርጠኝነት እንዴት ይገለጻል ?
አቶ ተስፋዬ፡– አንዱ ትኩረት የማግኘት ጉዳይ ነው:: ትኩረት ከተገኘ በኃላ ደግሞ ዘርፉን ወደላቀ ተጠቃሚነት ማሸጋገር ነው:: ይህን ለማድረግ በእውቀት ላይ ተመስርቶ መሥራት ይጠበቃል:: እንደ ሀገር ያለብን ክፍተት አንዱ የአቅም ውስንነት ነው:: ሌላው የእውቀት ማነስ ነው:: እነዚህን ውስንነቶች ለመቅረፍ እየተሰራ ነው:: የዘርፉ ሥነምግባር የሚጠይቀውን አሟልቶ ለመንቀሳቀስ ከዩኒቨርስቲዎች ጋር እየተሰራ ሲሆን፣ዩኒቨርስቲዎቹ የልህቀት ማዕከል እንዲኖራቸው በተለይም በጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል ላይ ትኩረት አድርገው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ:: ባለስልጣኑም አብሮ እየሰራ ነው::
በዚህ ረገድ በመስራት በኩል በተለይም ከወለጋ ዩኒቨርስቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመናል:: ጉጂ ውስጥ ከሚገኘው ቡሌሆራ ዩኒቨርስቲ ጋርም ለመፈራረም ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው::
ማዕድን ላይ ስንሰራ ፖሊሲ፣ህግና መዋቅሮች ላይም ፍተሻ በማድረግ መስተካከል ያለባቸውን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል:: ለሚቀጥሉት አስር አመታት ዘርፉ በምን ሁኔታ መመራት እንዳለበት ፍኖተ ካርታ (ሮድማፕ) ተዘጋጅቷል:: በፍኖተ ካርታው ላይም አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው ተቀምጠዋል::
የመጀመሪያው ተግባር የሀብት ልየታ ሥራ ሲሆን፣ የክልሉን ሀብት በካርታ ማመላከት (ሪሶርስ ማፕ መሥራት) ነው:: የሚገኘውን የሀብት አይነትና መጠን የሚያሳይ ሥራ መሰራት እንዳለበት ነው አቅጣጫ የተቀመጠው::
እንደ ማዕድኑ ባህሪ ተለይቶ እንዴት ጥቅም ላይ ይዋል የሚለው ደግሞ ሌላው አቅጣጫ ነው:: ይህ ከቴክኖሎጂ ጋር ይያያዛል:: በግዥ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለመተካት ምን አይነት ዘዴዎችን መጠቀም አንደሚገባ የሚያመላክት አሰራር ነው::
ሶስተኛው ተግባር ሀብቱ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተጠቃሚነት ጉዳይ ነው:: ይህ ጉዳይ ህብረተሰቡም የሚያነሳው በመሆኑ ምላሽ ማግኘት አለበት:: የኢንቨስትመንት ተሳትፎም በተመሳሳይ ይነሳል:: ተጠቃሚነት፣ኢንቨስትመንትና የአካባቢ ደህንነት ጉዳዮች ከማዕድን ልማቱ ጋር እንዴት ተጣጥመው መከናወን አለባቸው የሚለው ትኩረት ተሰጥቶታል::
ሶስተኛው የትኩረት አቅጣጫ ፍቃድ አሰጣጥ፣ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ላይ ከትትልና ቁጥጥር ማድረግ የሚሉትን ይመለከታል:: የማዕድን ዘርፉ የግለሰቦችን ኪስ ብቻ ከሚያደለብ ይልቅ የሀገር ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዴት መሥራት አለብን ብለን እየሰራን ነው:: ፍቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን የዚህ ባለስልጣን ድርሻ የሰጠውን ፍቃድ በአግባቡ የማስተዳደር ግዴታም ስላለበት በዚህ ታሳቢነት ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን::
የማዕድን ዘርፉ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽእኖ ለመቀነስ መሰራት አለበት:: ይህም አራተኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው:: ልማቱ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለማዕድን ፍለጋ የሚካሄድ ቁፋሮ ካለቀ በኃላ ጉድጓድ ክፍት የሚተውበት ሁኔታ ይታያል:: ይህን መሰሉ ተግባር መታረም ይኖርበታል::
ህብረተሰቡ አብሮ የሚለማበት ሁኔታ መፈጠር አለበት:: መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቷል:: ሥራዎች መሰራት ያለባቸው መንግሥት የሰጠውን ትኩረት ሊመጥን በሚችል ተቋም ነው፤ ይህን መገንባት መቻል አለብን በሚል በትኩረት እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ማዕድኑን በቁፋሮ ከመሬት ውስጥ የሚያወጡት የድካማቸውን ዋጋ እንደማያገኙና ትኩረትም እንዳልተሰጣቸው ቅሬታ ያቀርባሉ:: በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- ዘርፉ የሥራ ዕድሎች የሚፈጠሩበት ማድረግም ሌላው የቤት ሥራችን ብቻ ሳይሆን ግብችንም ነው:: በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉ ማዕድናት ላይ ማህበረሰቡን ማዕከል ባደረገ መልኩ ልማቱ እንዲከናወን ታቅዷል:: ለእዚህም የደለል ወርቅ ማምረት በአብነት ይጠቀሳል:: ህብረተሰቡ እነዚህን ማእድናት በቀላሉ ሊያለማቸው ይችላል፤ መጠነኛ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀም ለማድረግ ግን ይሰራል::
ካፒታል በሚጠይቁ ልማቶች ላይም ቢሆን ማእድኑ ያለበት አካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ተመቻችቷል:: ይህም በድንጋይ ከሰል ልማት ላይ በተግባር ተከናውኗል:: ይህ የሚደረገው አንድም ህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ለማድረግ ነው::
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ማዕድን የሚያዘዋውሩ ግለሰቦች ላይ ባለስልጣኑ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል:: በቅርቡም ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር የተሳተፉበት ህገወጥ ተግባር ተደርሶበት 22 ህገወጦችን ተይዘው ለህግ ቀርበዋል::
አዲስ ዘመን፡- በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ይደረጋል ሲባል ምን ማለት ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ዓለም የሚጠቀምበትን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ነው ጥረቱ:: ለአብነትም በባህላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ ጉልበታቸውን ከማባከናቸው በተጨማሪ በቁፋሮ ያወጡትን ማዕድን በአግባቡ እያጣሩ አይደለም::
ከአንድ ኪሎ አፈር ውስጥ መቶ በመቶ ማዕድኑን ማውጣት እየተጠበቀባቸው አነስተኛ መጠን ያለው ወርቅ ነው የሚያወጡት:: ይሄ ብክነት ነው:: ወርቁን ከአፈር ውስጥ የሚያጣራ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ችግሩን ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት ይሰራል::
ቴክኖሎጂውን መንግሥትም የግሉም ዘርፍም ለወርቅ አምራች ማህበራት ማቅረብ ይችላሉ:: አቅርቦቱንም ፕሮጀክት ቀርጾ መተግበር ይቻላል:: ዓለምአቀፍ ድርጅቶችም ሊተባበሩ ይችላሉ:: በአሁኑ ጊዜም አንድ የካናዳ ድርጅት ወደ ስምንት የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖች አቅርቦልናል:: አምራቾቹ ስልጠና ወስደው መጠቀም ከጀመሩና ጥቅሙንም ከተገነዘቡ በኃላ በራሳቸው ለመግዛት ይነሳሳሉ::
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በ2014 በጀት አመት በማዕድን ልማት በኢኮኖሚ ላይ ስላበረከተው አስተዋጽኦና የ2015 በጀት አመት እቅድ ቢገልጹልን?
አቶ ተስፋዬ፡– በወርቅ ማዕድን ብቻ ወደ 4ሺ680 ኪሎግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ ተደርጓል:: ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው በማህበራት ነው የተመረተው:: ከዚህም ወደ 314 /ሶስት መቶ አስራአራት / ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል:: ወደ 461ሺቶን የድንጋይ ከሰል ለፋብሪካዎች ቀርቧል::
በዘርፉ ለ156ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በእቅድ ተይዞ ከዚህ ውስጥ ለ126ሺ ዜጎች ሥራ ተፈጥሯል:: በአጠቃላይ በዘርፉ በወጭ ንግዱም ሆነ በሀገር ውስጥ ግብአትን ለመተካት በተደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል::
ዘርፉ ኢኮኖሚውን ከፍ በማድረግ ረገድ ድርሻው ትልቅ እንደሆነ ማሳየት ተጀምሯል:: በቀጣይ እቅድ መልካም አፈጻፀሙን ማስቀጠል ክፍተቶችን ደግሞ በማረም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይሰራል:: በተለይም እሴት የተጨመረበት ሥራ በመሥራት የውጭ ንግዱን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ላይ በትኩረት ይሰራል:: የሥራ ዕድል መፍጠር ላይም እንዲሁ ይሰራል::
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ መጠይቁ ላደረጉልኝ ትብብር አመሰግናለሁ::
አቶ ተስፋዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 13/2014