
– በሲሚንቶ፣ በድንጋይ ከሰልና በሌሎች ማዕድናት ልማት አበረታች ለውጦች ታይተዋል
መንግሥት ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለበት ሁኔታ ተጨባጭ ለውጦችን ማሳየት ጀምሯል። ይህንንም መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት አስታውቋል፤ በማዕድን ልማቱ የተሠማሩ አምራቾችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ወደ ውጭ ኤክስፖርት ከሚደረጉ ማዕድናት የሚገኘው ገቢ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡
ለዚህ ለውጥ በተለይ ከወርቅ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይገለጻል። ማሻሻያው ለሕገወጦች ተዳርጎ የቆየው የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ እያስቻለ ከመሆኑ በተጨማሪ ወርቅ አምራቾችም ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት በማዕድን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ የማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የእቅድ አፈፃፀሙን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት የተጠቀሰውም ይህንኑ ያመላክታል። በሪፖርቱ በማዕድን ዘርፍ በስምንት ወራቱ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆናቸው ተጠቁሟል። በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚሹ ጉዳዮችም አጽዕኖት እንዲሰጥባቸው ተመላክተዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት በማዕድን ዘርፉ ከኤክስፖርት አንድ ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ተናግረዋል። በማዕድን ዘርፍ ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት አቅም በመጠቀም የበለጠ መሥራት እንደምትችል እንደሚያመላክት ገልጸዋል። የአፈጻጸሙ ውጤታማነት ፖሊሲዎችን በመቀየር የሀገር ኢኮኖሚን በሚገባ ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን የማዕድን ሀብት በጥራት በማምረት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ ነው። ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ካሉ ማዕድናት መካከል ወርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በስምንት ወራት ስድስት ቶን ወርቅ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ፤ 22 ነጥብ 5 ቶን ወርቅ ማቅረብ ተችሏል፤ ይህ ትልቅ ስኬት ነው። በ2013 ጀምሮ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ወርቅ መጠን ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው። ምርታማነቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በዓመት ከ33 ቶን በላይ ወርቅ ማምረት ይቻላል።
ይህም ሀገሪቱን ከፍተኛ የወርቅ ምርት ለውጭ ከሚያቀርቡ የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ሊያሰልፋት እንደሚችልም ተናግረዋል። ወርቅ ከሌላው ማዕድን የተለየ ባሕሪ እንዳለው ጠቅሰው፣ በዓለም ላይ ተፈላጊና የውጭ ምንዛሪ መወዳደሪያ ጭምር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ወርቅ በኩባንያዎችና በባሕላዊ መንገድ እየተመረተ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተመረተው ወርቅ 95 በመቶ የሚሆነው ግን በባሕላዊ መንገድ የተመረተ መሆኑን አመላክተዋል። በወርቅ የታየውን ስኬት በሌሎች ማዕድናት ላይም ለመድገም መሠራት እንዳለባትም አስገንዝበዋል፡፡
በዓለም ላይ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመዋዥቅ ሁኔታ ሲኖረው ሲገጥመው፣ የማዕድናቱ ገበያም አብሮ የሚዋዥቁበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የወርቅ አቅርቦት በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል። ይህም ቀደም ሲል ሀገሪቱ ከወርቅ ማግኘት የነበረባትን ብዙ ጥቅም ማጣቷን ያመለክታል። ከማሻሻያው በኋላ ብሔራዊ ባንክ ለአነስተኛ ወርቅ አምራቾች ተጨማሪ ማበረታቻ በመስጠቱ በአንድ ወር አራት ነጥብ ሦስት ቶን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ አድርጓል። ይሄ ውጤት በጣም የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ገና ብዙ መሥራት እንዳለበትም ያስገነዝባል።
ሚኒስትሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግንባታው እየተካሄደ ስላለው ኩርሙክ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካም ማብራሪያ ሰጥተዋል። ፋብሪካው በሀገሪቷ በዓይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነም ጠቅሰው፣ በሚቀጥለው ዓመት ተመርቆ ወደ ሥራ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል። የወርቅ አቅርቦታችን የተዛባ እንዳይሆን እነዚህ ፕሮጀክቶች የራሳቸው አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ሦስት አነስተኛ ደረጃ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውንም ጠቅሰው፣ የወርቅ ምርት ወደ አስተማማኝ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን አመልክተዋል። በቅርቡ የተመረቀው የኢትኖ ማይንግ አነስተኛ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ዘመናዊ የሚባል የወርቅ ማምረትን ያሟላ መሆኑን ተናግረው፣ ሥራውን የጀመረ ቢሆንም ገና አስተማማኝ የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል። በሚቀጥሉት ጊዜያት አቅሙን ተጠቅሞ ወርቅ በተሟላ መልኩ ማምረት ይጀምራል ሲሉ አብራርተዋል።
በጸጥታው ምክንያት ሥራ አቆመው የነበሩ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የኢዛናና ቱሉካፒ አነስተኛ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች ለሙከራ ማምረት መጀመራቸውንም ጠቅሰው፤ በቀጣዩ ወር ሙሉ ለሙሉ ወደ ማምረት እንደሚገቡም ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ዋይኤምጂ ጎልድ አነስተኛ የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከክምችቱ ጋር ተያይዞ ያጋጠመውን መስተጓጎል በመፍታት ወደ ማምረት ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
በመተከል የሚገኘው ሜድሮክ የወርቅ ፋብሪካ ሥራ በተሟላ መልኩ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረው፣ እነዚህ አዳዲስና ነባር የወርቅ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ወርቅ ወደ ማምረት ሲገቡ የወርቅ ምርትና ምርታማነት ያድጋል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ የድንጋይ ከሰል አፈጻጸሙንም ጠቅሰዋል፤ እሳቸው እንዳብራሩት፤ በሀገሪቱ ሦስት ዘመናዊ የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እየሠሩ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ባለፈው ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ኢቲሚኒራልስ ነው። ናሽናል ማይኒንግም ሥራ ለመጀመር ዝግጁ ሆኖ በተወሰነ መልኩ ሲያመርት ነበር። ሌላው ፋብሪካ ጋሞ አካባቢ ከሁለት ወር በኋላ የማምረት ሥራ ይጀምራል። ቀደም ሲልም ከእነዚህ ውጭ በተወሰነ መልኩ የድንጋይ ከሰል አምርቶ የሚያቀርብ ፋብሪካ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እነዚህ አራት ፋብሪካዎች ፕሮስስ የተደረገ ጥራት ያለውና ፋብሪካዎች ሊጠቀሙት የሚችሉት የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ናቸው። ቀደም ሲል የሚመረተው የድንጋይ ከሰል ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን ጥራት አያሟሉም ነበር። እነዚህ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በሀገር ደረጃ በዓመት የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን 300 ሚሊዮን ዶላር ያስቀራሉ፤ የድንጋይ ከሰል ፍላጎቱንም ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ያስችላል።
በአነስተኛ ደረጃ የድንጋይ ከሰል የሚያቀርቡ አምራቾች ምርቱን ፕሮስስ ለሚያደርጉ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት የገበያ ትስስር እንደሚፈጠር ጠቅሰው፤ ከዚህ በኋላ ያልታጠበና ጥራት የሌለው የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ ለፋብሪካዎች እንደማይቀርብ አስታውቀዋል።
የድንጋይ ከሰል የሲሚንቶ ግብዓት የሚውል እንደመሆኑ የጥራት ጉድለት በሲሚንቶ የምርት አቅርቦት ላይ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ጠቁመው፤ የድንጋይ ከሰል በብዛት እየተመረተ ቢሆንም ከፋብሪካዎች ፍላጎት የተጣጠመ ምርት ስለማይመረት ከፍላጎት በላይ እየተመረተ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን ይገልጻሉ። ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲመረት እየተሠራ ነው ሲሉ አስረድተዋል። የተሻለ ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስችል ስትራቴጂክ ፕላን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌሎች ማዕድናት ዘርፍም እንደ ወርቅም ባይሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ መጠነኛ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰው፤ በተለይ እሴት የተጨመረባቸው ማዕድናት ለውጥ እየታየባቸው መሆኑን ይገልጻሉ።
ማዕድናት በአብዛኛው በጥሬ እንደሚላኩ ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም የወርቅን ያህል ብዙ ገቢ አያመነጩም ብለዋል። እሴት የመጨመሩ ሥራ ገና ብዙ እንደሚቀረው አንስተው፤ አሁን ያለው ጅምር አበረታች ቢሆንም፣ ካለው ሀብት አኳያ ገና ብዙ ልንሰራበት እንደምንችል ያሳያል ብለዋል።
ተኪ ምርቶች ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው ሲሚንቶ በተያዘው በጀት ዓመት የሚታይ ለውጥ የመጣበት ሌላው ሲሚንቶ መሆኑን ሚኒስትሩ ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሲሚንቶ አንደኛ በባለፉት ጊዜያት መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎች በተለያዩ ምክንያቶች በሙሉ አቅማቸው አያመርቱም ነበር፤ ሁለተኛው በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ እጥረቶች ነበሩ፤ ሦስተኛ ገበያውም እንዲሁ ችግር ነበረበት። በአጠቃላይ እነዚህ ሦስት ምክንያቶች በአቅርቦትም ሆነ በዋጋውም ከፍተኛ ለውጥ ነበራቸው።
በግንባታ ላይ የነበሩ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት ሥራ የጀመሩበት ሁኔታ አለ፤ ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሁለት ዓመት ባለሟላ ጊዜ ውስጥ በመንግሥት ከፍተኛ እገዛ እውን ተደርጓል፤ እነዚህ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ሆነ ችግር መፍታት ተችሏል። ይህም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ የሰሚንቶ ከፍተኛ ሀብት እንዳላትና 25 በመቶ ያህል የሀገሪቱ የቆዳ ስፋት በሲሚንቶ ግብዓት የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ብዙ በማምረት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ የማዕድን ዘርፉ ሌላው ሀብት ብረት ነው፤ ብረት አቅልጠው ወይም በከፊል አቅልጠው የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች ምርቱን እያቀረቡ ይገኛሉ፤ የብረት አቅርቦት እጥረት የለም። ይህ የሆነው የብረት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ በመድረጉ ነው።
ሚኒስትሩ የግብዓት የአቅርቦት ችግር እንዳለም ጠቅሰዋል። ግብዓቱን ከውጭ ለማስመጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እያጋጠመ መሆኑን ያመላክታሉ። እነዚህ ፋብሪካዎች ያለቀለት ብረት ከውጭ እያመጡ ብረት እንደሚያመርቱ አመልክተው፣ በተያዘው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ጠቁመዋል። የአይረ ኦርን ለማምረት የተሻለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ከሀገሪቷ ከ40 ያላነሱ የከበሩ ማዕድናት ዓይነቶች እንዳሉም የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በተሳሳቱ ግንዛቤዎችና በዘርፉ ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ በቂ የማበረታቻ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ እንዲሁም የገበያ ሥርዓቱ የተዛባ በመሆኑ የተነሳ ማዕድናቱ ብዙም ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ ይገልጻሉ።
ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ በተለይ የወሎ አካባቢ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ በኦፓልና በሌሎች ማዕድናት የበለጸገ እንደመሆኑ የወሎ ዩኒቨርሲቲም በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ በርካታ ሥራዎች ይሠራል፤ በቅርቡም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ዘርፉ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትግበራ እንዲገባ ይደረጋል። የግብይት ሥርዓት ችግርንም ለመፍታት ልክ እንደ ቡናና ሌሎች ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እስካሁን በማዕድን ዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች መረጃ በተበታተነ መልኩ ተቀምጦ እንደሚገኝ አመልክተው፣ ይህን በአንድ ቦታ በማዕከል በሀርድ ኮፒና በሶፍት ኮፒ በመሰብሰብ አሰባሰቦ ለመያዝ የሚያስችል የኢትዮጵያ የማዕድን መረጃ ማዕከል ግንባታ ሥራ መጀመሩንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ዘርፉ ብዙ የማስተዋወቅ ሥራ የሚፈልግ እንደ መሆኑ በየዓመቱ በሚዘጋጀው ማይን ቴክ ኤክስፖ ብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማሳተፍ የማስተዋወቅ ሥራው እየተሠራ ይገኛል። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካና ዓለም በማዕድን ዘርፍ የሚገናኙበት የመገናኛ ቦታ በመግባት ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡
በማዕድን ዘርፉም ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ፈቃድ በመስጠት ረገድ በክልሎች በጣም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ፍቃዶች መሰጠታቸውን የሚጠቅሱት ሚኒስትሩ፤ ተቋማቱ ግን ይህንን ማስተናገድ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል። ይህንን ለማስተካከል የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በማዕድን ዘርፉ አቅምን በዘላቂነት በመገንባት፣ የተቋማትን፣ የሰው ኃይላቸውን፣ ቴክኖሎጂንና የአሠራር ሥርዓትን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። የማዕድን ዘርፉ ከሁሉም የኢኮኖሚ ምሶሳዎች ውስብስብ ችግር እንዳለበት ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታትም ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሀገሪቷን የሥነ ምድር የመረጃ ሽፋን በጥራትም በተደራሽነትም ማስፋትንና ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። መንግሥትም በማንኛቸውም መሠረተ ልማቶች ላይ ኢንቨስት እንደሚያደርገው ሁሉ በሥነ ምድር መረጃዎች ላይም ከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ማድረግ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለማዕድን ዘርፉ የሀገሪቱ ሥነ ምድር መረጃ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የማዕድን የተረጋገጠ መረጃ ካለ የትኛውም ኩባንያ መረጃውን ወስዶ ኢንቨስት ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማሉ። የዚህ መረጃ እጦት የሀገሪቱ ዋና ችግር መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የማዕድን ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴም ይህን የሚኒስቴሩን የ2017 ዓ.ም የስምንት ወራት አፈፃፅም ሪፖርት ገምግመው አስተያየት ሰጥተዋል፤ በቀጣይ መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫዎች አመላክተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም