የክልሉ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሀብት ልየታና ልማት ሥራዎች

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በማዕድን ሀብት የበለጸገ ነው። የድንጋይ ከሰል፣ ዶሎማይት፣ ግራናይት፣ ብሉ አጌትንና ኳርትዝን የመሳሳሉ ማዕድናት ይገኙበታል። እነዚህን ማዕድናት በጥናት ለመለየትና ለማልማት እየሠራ ሲሆን፣ በድንጋይ ከሰልና የከበሩ ማዕድናት ልማት ላይ የሚያካሂዳቸው ሥራዎች ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ።

ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በክልሉ በጥናት የተለየና ያልተለየ የበርካታ ማዕድናት ክምችት ስለመኖሩ አመላካች ሁኔታዎች አሉ። በጥናት የተለዩ ማዕድናትን በማልማት ረገድም በርካታ አልሚዎች ፍቃድ ወስደው በልማቱ ተሰማርተዋል።

በክልሉ በስፋት እንደሚገኙ በጥናት ከተለዩት ማዕድናት መካከል የድንጋይ ከሰል አንዱ ነው። ይህንን የመሳሰሉትን ማዕድናት ለማልማት በርካታ አልሚዎች ፍቃድ ወስደው ልማቱን እያካሄዱ ይገኛሉ።

ወደሥራ ያልገቡ ጥቂት የማይባሉ አልሚዎች እንዳሉም መረጃው ያመለክታል። በክልሉ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ አልሚዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረገው እንቅስቃሴ 25 አልሚዎች ያለ አግባብ ፍቃድ መውሰዳቸው ተለይቶ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማዕድንና የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሔለን ዮሐንስ እንዳሉት፤ በክልሉ ለኢኮኖሚ እድገትና ለሥራ እድል ፈጠራ እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ለታመነበት የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል። በክልሉ የሚገኘውን የማዕድን ሀብት ለማወቅና ለመለየት በሁሉም ዓይነት ማዕድናት ላይ የአለኝታ ቦታ ልየታ ጥናት ሥራዎች እየተካሄዱ ናቸው።

በተለይ በኢንዱስትሪና በጌጣጌጥ ማዕድናት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአሌና በደቡብ ኦሞ ዞኖች የአለኝታ ቦታ ልየታ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ያመላክታሉ። በክልሉ ዞኖችም በራሳቸው አቅም እና ከክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚሠሩ ጠቅሰው፣ በዚህም የማዕድን ሀብትና አቅም የመለየትሥራዎች እንደሚያከናወኑ ያመላክታሉ።

በቀድሞው ክልል በማዕድን ዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ የወሰዱ አካላት እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ቀደም ተብለው በተለዩና በታወቁ የማዕድን ሀብቶች ልማት መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ወደ ኢንቨስትመንቱ ገብተው እንዲሠሩ መደረጉን አስታውሰዋል። በክልሉ በተለይ የድንጋይ ከሰል፣ ዶሎማይት፣ ግራናይት፣ ኳርትዝ፣ ከፍተኛ ደረጃ ጠጠር የማምረት፣ ቤሪል፣ ልዩ አነስተኛ (የጌጣጌጥ)፣ አፕታይት የተሰኙ ማዕድናትን ለማምረት 211 የሚሆኑ አልሚዎች የምርት ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመትም አልሚዎች ማዕድናትን ለማምረት ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል።

በክልሉ ከፍተኛ ክምችት ያለውና በስፋት እየተሠራበት የሚገኘው የድንጋይ ከሰል በጋሞ፣ ወላይታ፣ ቡርጂ እና ጋርዱላ ዞኖች የሚገኝ ሲሆን፣ በእነዚህ ዞኖች የድንጋይ ከሰል ማምረት ፍቃድ ወስደው ሥራውን ለመጀመር በሂደት ላይ የሚገኙ አልሚዎችም አሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ወደ ማምረት ሥራው ገብተዋል። ወደ ማምረት የገቡት የድንጋይ ከሰሉን በስፋት እያመረቱ ለኢንዱስትሪዎች (ፋብሪካዎች) ግብዓትነት እያቀረቡ ይገኛሉ። የአካባቢው ድንጋይ ከሰል በሀገር አቀፍ ገበያ ተፈላጊ መሆኑንም ወይዘሮ ሄለን አስታውቀዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዶሎማይት የተሰኘውን ማዕድን የማምረት ፍቃድ ወስደው እንቅስቃሴ የጀመሩ አልሚዎች እንዳሉም ጠቁመዋል። ግራናይት ለማምረትም እንዲሁ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ እና ጋርዱላ ላይ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ የገቡ አልሚዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ወደ ማምረት ሥራው ያልገቡትን አልሚዎች ወደ ማምረት ሥራው ለማስገባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ በማዕድን ዘርፉ ኢንቨስትመንት ልማት መሰማራት ለሚፈልጉ አልሚዎች ፍቃድ ለመስጠት ከተያዘው አቅድ በላይ ፍቃድ መስጠቱንም ምክትል ኃላፊዋ አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ በማዕድን ዘርፍ ከሮያሊቲ ክፍያ፣ ከአዳዲስ ፍቃድና እድሳት፣ ከመሬት ኪራይና መሰል ሌሎች ክፍያዎች 225 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ እስካሁን ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ተችሏል ሲሉም አስታውቀዋል። ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕድን ዘርፍ በርካታ የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ ለ25ሺ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ እስካሁን ለ16ሺ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ የማዕድን አለኝታ ቦታዎች ልየታ ጥናት በደቡብ ኦሞና በአሌ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በቦረዳ በሚገኘው የድንጋይ ከሰል ላይ በስፋት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንዳንድ ውሳኔዎች በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እየተሰጠ ወደ ልማት ሥራ ሳይገቡ የቆዩትን አልሚዎች ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ኃላፊዋ እንዳብራሩት፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው የድንጋይ ከሰል በፋብሪካዎች በጣም ተወዳጅነት አለው። የድንጋይ ከሰሉን በጣም ተፈላጊ ያደረገው ያለው ከፍተኛ የካሎሪ መጠንና ዝቅተኛ የሰልፈር መጠን ነው። ይህ የድንጋይ ከሰል ከ450ሺ እስከ 500ሺ ድረስ የካሎሪ መጠን አለው፤ የሰልፈር መጠኑም ከ0ነጥብ 5 በታች ነው።

የሰልፈር መጠኑ አነስተኛ መሆኑ የሚያመጣው ተፅዕኖ በዚያው ልክ ዝቅተኛ በመሆኑ በፋብሪካዎች ዘንድ ተመራጭ ያደርገዋል። ለዚህም ከድንጋይ ከሰል አንጻር የሚነሱ የጥራት ችግሮች አልተስተዋሉም፤ ይልቁንም የበለጠ ተፈላጊነቱ ጎልቶ ታይቷል።

በክልሉ ከቦረዳ ውጭ ያሉት እንደ ቡርጂና የመሳሰሉት አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳላቸው አመላካቾች ያሳያሉ ሲሉ ምክትል ኃላፊዋ ገልጸዋል። በጋርዱላ እና በወላይታ ዞኖችም እንዲሁ ክምችቱ እንዳለ ጠቁመው፣ ይህን ማዕድን ለማልማት አልሚዎች እንዲሠማሩና ወደ ማምረት እንዲገቡ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

አሁን እየታየ ያለው አብዛኛዎቹ አልሚዎች በሚባል ደረጃ ማዕድኑ ካለበት ቦታና ከትራንስፖርት አንጻር ምቹ ሁኔታዎች ካለመኖራቸው ጋር ተያይዞ ቦረዳ ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉበት ሁኔታ እንዳለ አመላክተው፤ በሌሎች ቦታዎች ላይ ያለውን ልክ ቦረዳ ላይ እንዳለው የድንጋይ ከሰል ለማልማት አልሚዎች ወደ ልማቱ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ።

በመሆኑም ቢሮው ያሉትን የመንገድና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት የልማት እንቅስቃሴው በሌሎቹም ቦታዎች የተፋጠነ እንዲሆን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላትና ከአልሚዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ ዮ ሆልዲንግ እና ጎል የተሰኙ ድርጅቶች የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ለመገንባት መሬት ተረክበው የግንባታ ሥራ ጀምረዋል። የእነዚህ ፋብሪካዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ በድንጋይ ከሰል ጥራት ላይ ሊኖር የሚችለውን ስጋት በመቀነስ ከሰሉን በማጠብ የጥራት መጠኑን በመጨመር ተፈላጊነቱ ከፍ ያለ የድንጋይ ከሰል ለማምረት ይቻላል። ፋብሪካዎቹ በአንድ ዓመት ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ቢሮው ፋብሪካዎቹ ተገንብተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

እነዚህ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ሲገቡ በሌሎች ዞኖች የሚታየው የድንጋይ ከሰል የጥራት ችግርም እንደሚፈታና የድንጋይ ከሰሉ ከፍተኛ ጥራት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

በተመሳሳይም በደቡብ ኦሞ ዞን ዶሎማይት የተሰኘውን ማዕድን ለማምረት አልሚዎች ፍቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ይሁንና ፍቃድ ወሰደው ወደ ማምረት ሥራው ከገቡ በኋላ ወደ ገበያው ለመግባት ስጋት ውስጥ የሚገኙበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል። ይህም ወደ ማምረት ሥራ በመግባት ላይ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን እንደሚያመለክት ጠቅሰው፤ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በተጨማሪ በክልሉ የማዕድን ሕገ ወጥ ዝውውር የሚስተዋልበት መሆኑን ተናግረው፣ ይህን ችግር ለመፍታትም ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

ደቡብ ኦሞና በኮንሶ አካባቢ ዶሎማይት፣ ግራናይት፣ አልሚዎች ፍቃድ ወሰደው ሥራው ያመረቱት ምርት በገበያ ላይ ተፈላጊነት ያላቸው እንደሆኑም ይገልጻል። የጌጣጌጥ ማዕድን የሆነው ብሉ አጌት ጋሞዞን ገረሴ በተሰኘ ቦታ እንዳለና ይህንንም ለማልማት ፍቃድ ወስደው የሚያመርቱ አልሚዎች እንዳሉ ገልጸዋል። ምርቱ እየተመረተ በመሆኑና አቅርቦትም ስላለ የገበያ ትስስር መፍጠርም ተችሏል ሲሉ ያስረዳሉ።

‹‹ማዕድን ብዙ ፍላጎቶች ያሉት ዘርፍ ነው፤ ለማልማት በሚችለውና በማይችለውም ዘንድ ሰፊ ፍላጎቶች ይታያሉ›› የሚሉት ምክትል ኃላፊዋ፤ እነዚህን ፍላጎቶች ለማስተናገድ ክልሉም አዲስ እንደመሆኑ ቀደም ሲል ጀምሮ ያሉ ፋይሎችን እየመረመረና እያጠራ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ፍቃድ ወስደው ወደ ልማት ሥራው ያልገቡትና ችግር ያለባቸው ፋይሎችን በማጣራት እንዲሰረዙ ተደርጓል። በዚህም በክልሉ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ከወሰዱት 211 አልሚዎች መካከል ወደ ሥራ ያልገቡ 25 አልሚዎች ፍቃድ ተሰርዟል። አልሚዎች ሥራ ባለመጀመራቸውና ሥራ ላይ ባለመገኘታቸው የተነሳ ሂደቱን ጠብቆ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር ባልገቡት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ተወስዷል። ቦታውን አጥረው ብቻ ባስቀመጡ ሕገወጦች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።

ፍቃድ የወሰዱና ወደ ሥራ ያልገቡ አንዳንድ ግለሰቦች በፍላጎት ብቻ ከአግባብ ውጭ በሆነ መንገድ ለመሄድ እንደሚሞክሩ ገልጸው፤ እዚህ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተናበበ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በቀጣይም ክልሉ በማዕድን ዘርፍ እምቅ አቅም ስላለው የማዕድን አለኝታ ቦታዎች የመለየቱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተጀመሩ የጥናት ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ ሌሎች ጥናቶች እንዲካሄዱ በዘርፉ አልሚዎች እንዲሠማሩ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠርም ይሠራል። በማዕድን ልማት ላይ የተሠማሩ አልሚዎች የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲሠሩ የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በማዕድን ዘርፉ ገቢ በማመንጨትና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በማዕድን ልማቱ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ የማይገቡ አልሚዎችን ፋይል በደንብ በማጥራት መሰረዝ ያለባቸውን እንዲሰረዙ፣ መቀጠል ያለባቸው እንዲቀጥሉ የሚደረግበት አሠራር መዘርጋቱንም አመላክተዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You