
ኢትዮጵያ በጥናት የተለዩና ያልተለዩ የበርካታ ማዕድናት ዓይነቶች መገኛ ነች። የበርካታ ማዕድናት መገኛ መሆኗ ይገለጽ እንጂ ያላት አብዛኛው የማዕድን ሀብት በውል ተለይቶ ስለአለመታወቁ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል።
በጥናት ተለይተው እየተሰራባቸው ያሉት ጥቂት የማዕድን አይነቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ወርቅ፣ ጨው፣ የድንጋይ ከሰል፣ መዳብ /ኮፐር/፣ ሊትየም፣ ኦፓልና የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ ብረትና ብረትነክ ማዕድናት፣ ግራናይት እና የመሳሳሉት በርካታ ማዕድናት እንዳሉ ይታወቃል።
እነዚህን ማዕድናት አልምቶ የመጠቀሙ ሥራ በጥቂት የማዕድን አይነቶች ላይ ያተኮረ ነው። በተለይ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ የማዕድን ሀብቶቹን በማልማት የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጋ እንዳትጠቅም እንቅፋት ሆኖባት ኖሯል።
ይሁን እንጂ መንግሥት ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ተደርገው ከተለዩት አምስት ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፉ እንዲሆን ማድረጉ ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝና መነቃቃት እንዲታይበት አድርጓል።
ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት በተከናወኑ ተግባሮች በማዕድን ዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ በዘርፉ ብዙ ዜጎች ተሰማርተው እንዲሰሩ አስችሏል። ማዕድናት ይገኙባቸዋል ተብለው በጥናት የተለዩ አካባቢዎች ላይ ከፍለጋ ጀምሮ እስከ ማምረት ድረስ ያሉ ፍቃድ ወስደው የተሰማሩና ለመሰማራት የሚፈልጉ አካላት እንዲበራከቱ እያደረገ ይገኛል።
ማዕድናትን እሴት ጨምረው ለማልማት ፍቃድ ወስደው የተሰማሩ አልሚዎች ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብም ባሻገር ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። በዚህም የውጭ ምንዛሪ በማስገባትና ከውጭ የሚመጡትን ምርቶችም በመተካት ረገድ ብዙ ሥራዎች እየሰሩ ናቸው።
በመንግሥት በኩል ለማዕድን ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ለውጦችና መሻሻሎች እንዲመጡ ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በተለይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በወርቅና በመሳሳሉት ማዕድናት ላይ ለውጥ እንዲመጣና ከፍተኛ እምርታ እንዲመዘገብ ማድረጉን መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል።
የማዕድን ልማት ጉዳይ ሲነሳ በዋናነት ጉዳይ ሊሆን የሚገባው ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ የማቅረብ ጉዳይ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ማዕድናት በጥሬው ወደ ውጭ ከሚላኩ ይልቅ እሴት ተጨምሮባቸው ቢላኩ ለሀገር ያላቸው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ሁሌም ይገለጻል።
በአሁኑ ወቅትም እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ማዕድናትን በተመለከተ በተጀማመሩ ሥራዎች አበረታች ለውጦች እየታዩ ስለመሆናቸው የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በመሆኑም በሀገሪቱ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምረው ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ካሉ አምራቾች መካከል አንዱ ጉድሎ ማይኒንግ ኩባንያ ነው። የጉድሎ ማይኒንግ ኩባንያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀበን ጎሽ እንደተናገሩት፤ ኩባንያው በማዕድን ምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።
እሳቸው እንደሚሉት፡-ድርጅቱ በትግራይ ክልል ማዕድን ዘርፍ ልማት ላይ ተሰማርቶ ሲሆን፣ ከአራት ዓመት በፊት ነው የተመሠረተው፤ በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን በማልማት ለገበያ ለማቅረብ ታልሞ የተቋቋመ ድርጅት ነው። በኢንዱስትሪያል፣ ሜታሊክና ሜታሊክ ያልሆነ ማዕድናት በማምረት ለፋብሪካዎች ግብዓት ያቀርባል፤ ኤክስፖርትም ያደርጋል።
ድርጅቱ በአብዛኛው በትግራይ ባሉ ማዕድናት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትንም እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ከምርቶቹ መካከል መዳብ፣ ሊትየም፣ ኮፐር ኦር፣ ኳርትዝ እና ለጌጣጌጥ የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት ይጠቀሳሉ። ከማምረት ሥራው ጀምሮ ምርቶቹን ኤክስፖርት ማድረግ ከጀመረ ሁለት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ቆይታው በሽሬ እንደስላሌና ተንቤን አካባቢዎች ተሰማርቶ በሚሰራቸው የማዕድን ልማት ሥራዎች ጥሩ ለውጦችን እያመጣ እንደሚገኝ አቶ ሀበን አብራርተዋል።
ድርጅቱ በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ማዕድናትን የማልማት ፍቃድ ወስዶ የበርካታ ማዕድናት ክምችት ባለበት ሽሬ አካባቢ የማዕድን ቦታዎችና ባሉት የተለያዩ ሳይቶች ልማቱን እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በማዕድናት ምርቶቹ ላይ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ እያደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሀበን፤ ዋንኛ የገበያ መዳረሻውም ቻይና መሆኗን ይገልጻሉ። ድርጅቱ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ሀገሪቷ ያላት የማዕድን ሀብት ከማስተዋወቅ ባሻገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን እንድታገኝ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ መዳብ፣ ሊትየም፣ ሊድ፣ ኮፐር ኦር፣ ኳርትዝ ፣ ክሮም፣ የጌጣጌጥ ማዕድናት እና በመሳሰሉት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ያቀርባል ያሉት አቶ ሀበን፤ ‹‹ድርጅቱ ምርቶቹን እሴት ሳይጨምር ለገበያ አያቀርብም ››ይላሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት መዳብ እያመረተ ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ድርጅቱ ከሚያመርታቸው ማዕድናት መካከል አንዳንዶቹ ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓትነት እንዲውሉ እያደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ።
‹‹ምርቶቹ ተፈላጊና በጥሩ ሁኔታ እየተመረቱ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ በውጭ ኩባንያዎች በጣም ተፈላጊ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። ምርቶቹ እሴት የተጨመረባቸው ሲሆኑ ደግሞ ፍላጎቱ በጣም ይጨምራል ሲሉ ጠቅሰው፣ እሴት የተጨመረበት ምርት ጥሩ ዋጋ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል። ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት ፋብሪካ ማቋቋም እንደሚስፈልግም ተናግረው፣ ድርጅቱም ሥራዎችንን አስፋፍቶ ለመስራት ፋብሪካ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
‹‹ድርጅቱ እየሰራባቸው ባሉ ቦታዎች ላይ የማዕድናት ክምችት አለ፤ የማዕድን ማግኘቱ ላይ ምንም አይነት ችግር አያገጥመንም›› የሚሉት አቶ ሀበን፤ ለዚህም ድርጅቱ ማዕድናቱ ባሉባቸው ቦታዎች ላይ አምስት ሳይቶች እንዳሉት ጠቅሰው፣ ይህም ማዕድናቱን በሚፈልጉት መጠን ለማምረት እንደሚያስችላቸው ያመላክታሉ።
እንደ አቶ ሀበን ማብራሪያ፤ ድርጅቱ ለ107 ሰዎች በቋሚነት የሥራ እድል ፈጥሯል። ከዚህም ባሻገር አካባቢው ላይ ያሉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ከቀን ሠራተኝነት ጀምሮ በጊዜያዊነት እንዲሰሩ እያደረገ ነው። የአካባቢውን ሕብረተሰብ ያላሳተፈ የማዕድን ልማት ውጤታማ መሆን አያስችልምና ድርጅቱም መውጣት ያለበት በማኅበራዊ ኃላፊነቶች ጭምር እየተወጣ ይገኛል። ከዚህም አንጻር ክሊኒክና ትምህርት ቤቶች የመገንባት፣ ውሃና፣ መብራት ለማስገባት በሂደት ላይ ነው። ይህንንም ከሕብረተሰቡ ጋር እየሰራ ይገኛል።
‹‹ማዕድን ልማቱን የማካሄድበት አካባቢ የትውልድና እድገቴ ቦታ እንደመሆኑ ማዕድኑን ከማልማት ባሻገርም አካባቢውን ሕብረተሰብ የማልማት ኃላፊነትም አለብኝ››የሚሉት አቶ ሀበን፣ ‹‹የማዕድን ሥራ ለብቻ አይሰራም፤ ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን ከሕብረተሰቡ ጋር አብረን እጅና ጓንት ሆነን እንሰራለን›› ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ አንድን ማዕድን ከማውጣት ጀምሮ መጨረሻ ድረስ ብዙ ሂደቶችን ያልፋል። የማዕድን ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ለዚህም ድርጅቱ ብዙ ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን፣ ማዕድናቱ ወጥተው፣ በሚፈለገው ልክና መጠን ተመርተው ለገበያ እስከሚቀርቡ ድረስ በባለሙያ የታገዘ ክትትል ይደረግባቸዋል። ይህም ብዙ ጊዜ ማዕድናት ከማውጣት ጀምሮ የሚነሱ ችግሮች እንዳይነሱ ከማድረግም በላይ ጥራት ያላቸው ምርቶች እንዲመረቱ ያስችላል።
በተለይ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ስናቀርብ ገዥ ሀገራት የምርቶቹን የአመራረት ሂደት ጥራት ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ጥራት የሌላቸው ምርቶች ከሆኑ ገዥ አገራቱም ሆነ ሌሎችም አይቀበሉም። ጥራታቸውን የጠበቁ ከሆኑ ገዥዎች ፈልገው ይወስዳሉ። በቀጣይ የመግዛት ፍላጎትም ያሳያሉ።
‹‹እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች የማምረት ሂደቱን በጥንቃቄ እንፈጽማለች፤ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ምርቶቹን ከመሸጥ ባሻገር የማስተዋወቅ ሥራ እንሰራለን ›› ሲሉ ተናግረዋል።
ድርጅቱ እሴት የተጨመረባቸው ማዕድናትን ባለፉት ሁለት ዓመታት አራት ጊዜ ወደ ውጪ መላኩን ጠቅሰው፣ በዚህም ሦስት ሺ ቶን የመዳብ ምርቶችን መላክ መቻሉን ይገልጻሉ። ፍላጎቶቹና ትዕዛዝ ስላለ በቀጣይም መዳብ አጠናክሮ የመላክ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል። ሌሎች ምርቶችን እንዲሁ በሂደት ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የመዳብ ማዕድን ለውጪ ገበያ የሚላክባቸው ገዥ ሀገራት ምርቱን ለመግዛት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ዋንኛ ገዥ የሆነችው ቻይና የመግዛት ፍላጎቷ ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
እዚህ ላይ ዋንኛ ችግር እየሆነ ያለው የሀገር ውስጥ ቤተሙከራዎች/ ላብራቶሪዎች/ ዘመኑን የሚመጥኑ አለመሆናቸው ይላሉ። መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበው፣ ከዘመኑ ጋር ሊሄዱ የሚችሉ ዘመናዊ ቤተሙከራዎች ያስፈልጉናል ይላሉ።
አቶ ሀበን እንዳሉት፤ ድርጅቱ በቀጣይ የራሱ ዘመናዊ ቤተሙከራ ለመገንባት አቅዶ እየሰራ ይገኛል። የምርት የጥራት ደረጃ የሚታወቀው በላብራቶሪ ሲፈተሽ ነው፤ ለገበያውም ቢሆን ጥራቱ ያልተረጋገጠ ማዕድን ማቅረብ አይቻልም። ‹‹እዚህ ላይ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ እየጠየቅን ነው፤ እገዛ ያደርግልናል የሚል እምነትም አለን›› ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ገና ብዙ ያልተነኩና ያልተዳሰሱ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኗ ማዕድናት ላይ አልሰራንም፤ ገና በጀምር ላይ ነን፤ ገና ብዙ መስራት ይጠበቅበናል›› የሚሉት አቶ ሀበን፤ የአገሪቱን ማዕድናት ማስተዋወቅ የሚቻልባቸውን አጋጣሚዎች ሁሉ በመፍጠር ሀብቶቹ ለምተው ዓለምም አውቆ እንዲገዛቸው የሚያደርጉ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
በተለይ እንደ ማይንቴክ አይነቶቹን ትልቅ ትርጉም ያላቸው ዓለም አቀፍ ኤክስፖዎች በተለያዩ ጊዜ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አምራቹና ገዥው የሚገናኝባቸው ዓለምአቀፍ መድረኮችንና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል።
ድርጅቱ ዘንድሮ በተካሄደው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድን ኤክስፖ/ማይንቴክ/ ላይ መሳተፉን አስታውሰው፣ ከብዙ ኩባንያዎች ጋር በመገናኘት፣ የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውና የገበያ ትስስር መፍጠራቸው ድርጅቱን በእጅጉ ተጠቃሚ እንዳደረገውም ይናገራሉ። ‹‹ከኩባንያዎች ጋር በተፈጠረ የገበያ ትስስር መሠረት ምርቶቻችንን የመረከብ ፍላጎት በማሳየታቸው ዓመቱን ሙሉ ከእነርሱ እየተነጋገርን ምርቶቻችን በማዘጋጀት ለመላክ ዝግጅት እያደረግን ነው›› ብለዋል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አምስት ሳይቶች ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እዚያ አካባቢ በማዕድን ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ አምራቾችም ሆኑ ግለሰቦች አብረውን መስራት የሚችሉበት መንገድ እያመቻቸን እንሰራለን ብለዋል።
ድርጅቱ ሥራዎችን አስፋፍቶ ለመስራት ይቻል ዘንድ ፋብሪካ ለመገንባት ቦታ ወስዶ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል ሲሉም ጠቁመው፣ ሥራው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል። ከባንክ ድጋፍ ለማግኘት ጥያቄ አቅርበን በጎ ምላሽ እናገኛለን ብለ እየጠበቅን ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ የማዕድናት መመርመሪያ ዘመናዊ ቤተ ሙከራ ለማቋቋም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም