በትግራይ ወጣቶች ደምና በትግራይ ህዝብ ተስፋ በመቆመር ዘመኑን የፈጀውና ዛሬም እየቆመረ ያለው አሸባሪው ህወሀት ከትናንት ስህተቱ መማር የሚያስችለውን እድል እየገፋ የመጨረሻ እስትንፋሱ የሚቆረጥበትን የጥፋት መንገድ ሊገፋበት ዳር ዳር እያለ ይገኛል።
በደደቢት በረሀ ተወልዶ በክፋት እና በሴራ አድጎ ፤ በንጹሀን ደም ገዝፎና ደልቦ በእብሪትና በማን አለብኝነት መንፈስ ላለፉት 50 አመታት ሀገርና ህዝብን ፤ በተለይ ደግሞ የትግራን ህዝብ ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሏል ።የትግራይን ምድር የደም ምድር ከማድረግ ጀምሮ ህዝቡን የጉስቁልና መገለጫ እንዲሆን አድርጎታል ።
ቡድኑ ለ17 አመታት በፍትህና ነጻነት ስም ባካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት የትግራይን ወጣት በርካሽ ፕሮፖጋንዳ በማነሳሳት መሳሪያ አሸክሞ የበረሀ ሲሳይ አድርጓል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለአካል ጉዳተኝነትና ለስነልቦና ቀውስ ዳርጓል። በክልሉ የትኛውም አይነት የልማት ስራዎች እንዳይካሄዱ እንቅፋት ከመሆን ጀምሮ ህዝቡ የተረጋጋ ህይወት እንዳይኖረው በማድረግ ለጀመረው ጦርነት አቅም አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል ።
ወጣቱ በየትኛውም መንገድ ተስፋ የሚቆርጥበትን ሁኔታ በማመቻችት፤ ይህንኑ የወጣቱን ተስፋ መቁረጥ የፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ የእድል ካርድ እና የጥፋት መንገዱ አቅም አድርጎ ተጠቅሟል። ከዚህም ባለፈ በረሀብ አደጋ ውስጥ የነበሩ፤ በሞትና በህይወት መካከል ጣር ውስጥ ለሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች ሲቀርቡ የነበሩ የእርዳታ አቅርቦቶችን በመሸጥ ፍጹም ኢ-ሰብአዊ ተግባር የመፈጸም ጸያፍ ታሪክ ባለቤትም ነው ።
ከተጠናወተው የመስፋፋት እብደት የተነሳም በወልቃይትና በራያ አማሮች ላይ ያካሄደው የዘር ማጥፋትን ጨምሮ የተለያዩ አሰቃቂ ወንጀሎች ቡድኑ የቱን ያህል ሰብአዊነት የሌለው፤ ለህዝብና ለህዝባዊነት የተገዛ የአስተሳሰብ መሰረት እንደሌለው በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
በብዙ ርካሽ ፕሮፖጋንዳ በበረሀ ትግል ያሰለፋቸውን፤ በትግሉ ዘመናቸውን የከፈሉ ታጋዮችንና አመራሮችን ሳይቀር በድል ማግስት በብዙ ማዋረድ እና ስም ማጥፋት ሲያባርር ሁለቴ ማሰብ ያልቻለ የጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት የተንሰራፋበት፤ የነዚህ ግለሰቦች ነውር የነገሰበት ድርጅት ነው።
ነውርን እንደ ነውር ከማየት ይልቅ ትምክህት አድርጎ የማየት ባህል ያዳበረ ፤ ከነውሮች በስተጀርባ የሚፈጠረውን የማህበረሰብ የህይወት ዝብርቅርቅ እንደ ስኬት በመቁጠር የሚኮፈስና፤ ይህንንም ለማስቀጠል የሚተጋ የነውሮች ሁሉ አባት ነው ።አምጦ የሚወልደውም ይህንኑ ነውሩን ነው።
“ሀገር ለማፍረስ እስከ ሲኦል እንወርዳለን” ከሚለው የአደባባይ ዲስኩሩ አንስቶ ፤በተግባር የተለያዩ ቡድኖችን አስታጥቆ ንፁሀንን በአሰቃቂ ሁኔታ ማስገደልን እንደ አንድ የፖለቲካ ስኬት የማየቱ እውነታ የዚሁ ማንነቱ መገለጫ ነው ። የትግራይን ህዝብ ለመጠበቅ ለሃያ አመታት በቀበሮ ጉድጓድ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ከኋላ ያደረሰው ጥቃትና ጥቃቱን ተከትሎ ያሰማው ፉከራና ቀረርቶ የዚህ ነውሩ ጥግ ነው ።
በህዝባዊ አመፅ ያጣውን ስልጣን በለመደው መንገድ በትግራይ ወጣቶች ደም ዳግም በእጁ ለማስገባት የሄደበት የእብሪት መንገድ ሀገርና ህዝብን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለና እያስከፈለ ቢሆንም፤ በቡድኑ የእብሪት ድርጊት ከትግራይ ህዝብ በላይ ለከፋ ችግር የተዳረገ የለም ።ህዝቡ በአንድ በኩል ቡድኑ በለኮሰው ጦርነት ለነገው ተስፋ ያደረጋቸውን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶቹን አጥቷል ።
ከዚህም በተጨማሪ ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ውስብስብ ለሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተዳርጓል ።ለዘመናት አብሯቸው በሰላምና በፍቅር ከኖራቸው አጎራባች ህዝቦች ጋር እንዲቃቃር ሆኗል።ይህም አጠቃላይ በሆነው የህዝቡ የእለት ተእለት ህይወት ላይ ያልተገባ ሸከም ይዞበት መጥቷል። በዚህም እየከፈለ ያለው ዋጋ ከፍያለ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት እውነታ ውስጥ ዛሬም ቢሆን ይህ አሻባሪ ቡድን በሱ እብሪትና ነውር ምክንያት የትግራይ ህዝብ እየከፈለ ያለውን ያልተገባ ዋጋ ለመመልከትና እራሱን እየሄደበት ካለበት የጥፋት መንገድ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚህ ይልቅ በለመደው ተራ የማደናገሪያና የማደንዘዣ ፕሮፓጋንዳ ዳግም የትግራይን ወጣት ለእልቂት እያነሳሳ ይገኛል ።
በአንድ በኩል አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት መንግስት የዘረጋውን የሰላም እጅ ተቀብያለሁ እያለ፤ ስለ ሰላም ከባህሪው ጋር የማይሄዱ ዜማዎችን እያዜመ በሌላ በኩል ቅደመ ሁኔታዎችን ከመደርደር አንስቶ መላው የትግራይ ወጣት በግድም ይሁን በውድ ለጦርነት እንዲዘጋጅ እያደረገ ይገኛል ።
ላለፉት አራት አመታት የትግራይን ህዝብ እንደ ህዝብ በመያዣነት እየተጠቀመ ያለው አሸባሪው ሕወሀት፤ የትግራይን ህዝብ ሕይወት ስራዬ ብሎ በማመሰቃቀል ለእኩይ አላማው ግብአት እያደረገ ሲሆን ፤ በተለይም ወጣቱ የህይወት ጭላንጭል ተስፋ እንዳይኖረው በማድረግ መሳሪያ ማስታጠቁንና ለጦርነት ማዘጋጀቱን ገፍቶበታል ።
ይህ ከቀደመው ባህሪው የሚቀዳው የቡድኑ እኩይ ተግባር ዛሬ ላይ የትግራይን ህዝብ ሊያስከፍለው የሚችለው ዋጋ ከቀደመው ዘመን ጋር ሊወዳደር የሚችል አይሆንም ። ፍጻሜውም የቡድኑ አእምሮ ቢስ አመራሮች እንደሚያስቡት ሳይሆን፤ ድንገትም የቡድኑን ግብአተ መሬት የሚያፋጥን እንደሚሆን መገመት የሚከብድ አይሆንም ።
ይህንን ሀገራዊና አካባቢያዊ እውነታ የትግራይ ህዝብ፤ በተለይም የትግራይ ወጣቶች በአግባቡ ሊያጤኑት ያስፈልጋል። ትናንት ወንድሞቻቸው በፍትህና በነጻነት ስም የከፈሉት መሰዋእትነትና ያሳለፉት መራራ ሕይወት ለትግራይ ህዝብ ምን አመጣለት ብለው ሊጠይቁ ይገባል።
ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 አመታት የትግራይ ህዝብ በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም በሚታደል ስንዴ ህይወቱን ከመምራት ፤ በተለያዩ አደረጃጀቶች ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ከማጣት ውጪ ምን አተረፈ ? ልጆቹስ ከስደትና ስደት ከፈጠረው ሞት ውጪ ምን ተፈጠረላቸው ? የትግራይ ወጣቶች ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ።
ጠበንጃ ታጥቆ ቃታ ለመሳብ ከመሽቀዳደም በፊት ቃታ የምትስብበት ሀይል በርግጥ ጠላት መሆኑንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ፤በጠላትህ ነው ትርክት የሚሳብ ቃታ አደጋውና መዘዙ ብዙ እንደሆነም ማሰብ ተገቢ ነው። የትግራይን ህዝብ ከ10 አመት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረ ሀይል ላይ ቀደም ሲል የተሳበው ቃታ ምን ይዞ እንደመጣ አሁን ላይ ማስታወስ አዋቂነት ነው ።
በዘፈንና በተራ የሆይሆይታ ፕሮፓጋንዳ ታጥኖ ወደ ጦርነት የሚደረግ ጉዞ ሊያስከፍል የሚችለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው ።ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር የትግራይ ወጣቶች እንደ ትናንቱ ዛሬም በደሙ እየቆመሩ ላሉ የህወሀት የአእምሮ ደናግልት በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።የትግራይ ወጣት የራሱን እድል በራሱ የመወሰን የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት እንደሆነ ከፍ ባለ ድምጽ ሊያሰማቸው ይገባል ። የተፈጠረው ለጥይት ሳይሆን ከፍ ላለ ሰብአዊ አላማና ተልእኮ መሆኑን በእምቢታ ሊያሳውቃቸው ጊዜው አልረፈደም!
ከመርደ ጽዮስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም