ከወላጆቼ ቤት ትዳር ይዤ እንደወጣሁ ነው ያረገዝኩት። እርግዝናው አስቤበትና ፈልጌው ነው የመጣው። የአብራኬ ክፋይ የሆነ የራሴ ልጅ እንዲኖረኝም በብርቱ እመኝ ነበር። ትዳር የመሰረትኩበት የመጀመርያ ዓላማዬም ልጅ መውለድን መሰረት ማድረጉን አስታውሳለሁ። እንዳለምኩትም ልጅ መጸነሴ ተነገረኝ። ደስ አለኝ።
ተከታታይ የወሊድ ክትትል ለማድረግ ለመጀመርያ የሄድኩት ካዛንቺስ ጤና ጣቢያ ነበር። እናት ልሆን በመሆኑ ልቤ በደረቴ ተፈጥርቆ እስኪወጣ ደስ ብሎኝ እንደነበርም አልዘነጋውም። ክትትሉን ለመጀመር የሚያስችለው ቅድመ ምርመራ ሲደረግልኝ ሁሉ ሁለመናዬ ጥርስ በጥርስ ነበር። ሆኖም አብሮ አንድ ጉድ ተነገረኝ። በደሜ ውስጥ የኤች ኤቪ ቫይረስ መኖሩን።
መርዶው ሲነገረኝ ዙርያ ገባው ጨለማ ሆነብኝ። መሬት ተከፍታ ብትውጠኝም ወደድኩ ስትል ታሪኳን ያጫወተችን የዛሬ እንግዳችን ገነት መላኩ ናት። (ስሟ የተቀየረ)
በራሷ አንደበት ታሪኳን ያወጋችን ገነት ኤች አይቪ አለብሽ ስትባል በፍፁም ዕውነታውን ልትቀበል አልቻለችም። ምክንያቱም ባለቤቷ ሹፌር ቢሆንም መስክ የሚያስወጣ ሥራ የለውም። በቤተሰቡ ላይ ማግጦ እንዲህ ዓይነት ችግር ያመጣልም ተብሎ የሚታማ ሰው አልነበረም። ሆኖም ለብዙ ጊዜ እንዴት መጣና ማን አመጣው እየተባባልን ተፋጥጠን ቆይተናል ትላለች።
አንዳችን አንዳችንን ብንጠረጥርምና ሺህ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ብንወያይም ቫይረሱ በማናችን ሳቢያ እንደመጣ ማወቅ አልቻልንም። ቆይቶ የሰፈር ልጆች ተሰባስበን የምናግዘው አንድ ወጣት እንደነበረ ትዝ አለኝ። ነፍሱን ይማረውና ወጣቱ ለእናቱ አንድ ነው። በተኛበት አልጋ ላይ የምናደርግለት እንክብካቤና ድጋፍ ይሄን ሰብኣዊነት ታሳቢ ያደረገ ነው። ሆኖም በፍፁም የደም ንክኪ እንዳልነበረን እርግጠኛ በመሆኔ ወጣቱን መጠራጠሬን አቆምኩ።
ሆኖም ሁኔታውን መቀበል ስላልቻልኩ መሬት ላይ ተንበርክኬ ፀጉሬን እየነጨሁ አለቅሳለሁ፤ የአርባ ቀን ዕድሌን በፀጋ መቀበል አቅቶኝ ሌሊት ሁሉ አሸዋ ላይ ተንበርክኬ ሳነባው ኖሬያለሁ። በእጅጉም በሕይወት በመኖሬ ተስፋ ቆርጫለሁ።
የካዛንቺስ ጤና ጣቢያ የምክር አገልግሎት ባለሙያዎች በቀላሉ ሊያረጋጉኝ ባይችሉም በሪፈር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ልከውኝ ነበር። ሆስፒታሉ በፊናው ንጋት በተሰኘና አሁን የት እንዳለ የማላውቀው ፕሮጀክት ውስጥ እንድታቀፍ አደረገኝ። ይሄኔ ሲዲ ፎሬ 900 በመሆኑ መድሃኒት አላስጀመሩኝም። ፈጥኖ መድሃት የሚጀምረው ሲዲ ፎሩ ከ500 በታች የሆነ ነው። ለነገሩ የባለቤቴ የሲዲ ፎር መጠን እዚህ መካከል በመሆኑ መድሃኒት የጀመረው ቀድሞኝ ነው። ቆየት ብዬም እኔ ሲዲ ፎሬ 900 ቢሆንም በማርገዜ ምክንያት መድሃኒት ተጀመረልኝ። በንጋት ፕሮጀክት አማካኝነት እኔን ጨምሮ 50 ቫይረሱ በደማችን ያለብን እናቶች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰባተኛ ፎቅ ላይ ልጆቻችንን ወለድን።
በየጊዜው አንድ ፌስታል ሙሉ ኪኒን ተሸክሞ መግባት ይሰለቻል። በየቀኑ እስከ 10 ፍሬ የሚደርሰውን መድሃኒት መቃሙም መፈጠርን ያስጠላል። በእርግዝና ሰዓት ዋናውን የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት ስወስድ ቆይቻለሁ። ልጄን በሰላም ተገላገልኩ፡፤ሆኖም ልጄም እንደኔው በደሟ ውስጥ ቫይረሱ መኖሩ ተነገረኝ። አምርሬ አለቀስኩ፤ከእኔ አልፎ ልጄን ለመከራ መዳረጌ እራሴን እንድጠላ አደረገኝ።
አሁን የሚያሳስበኝ የልጄ ጤንነት ነው። ቫይረሱ እንዳይጎዳብኝም ጥንቃቄ አደርግ ነበር። ከተወለደች በኋላ ጡት እያጠባኋት የምወስደውም መድሃኒት ነበር ። ልጄን እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት ብቻ እንጂ ሌላ ምንም የምትወስደው አልነበረም።
ሆኖም ጎን ለጎን በፈሳሽ መልክ የምትወስደው መድኃኒት ከባድ ነበር። ልጄ በፈሳሽ መልክ የምትወስደው መድሃኒት በራሱ ራሱን የቻለ ራስ ምታት ሆኖብኝ ቆይቷል። መድሃኒቱን ከወሰደች በኋላ ከ30 ደቂቃ በፊት ካስመለሳት የግድ ተደግሞ ይሰጣታል። በዚህ ምክንያት በምትሰቃይበት ሁኔታ በየጊዜው ለፈጣሪዬ አለቅስ ነበር። ይሄ ዘመን ለኔ ፍፁም ብርሃን የማይታይበት ጨለማ ነበር። የጨለማ ዘመን የምልበት ብዙ አሁን ከደረስንበት ጋር የሚነፃፀሩ ምክንያቶች አሉኝ። እኔ ነፍሰ ጡር ስለሆንኩ መድሃኒቱን እንድወስድ ይፈቀድልኝ እንጂ ብዙ ህሙማኖች የመድሃኒት እጥረት ስለነበር የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት ሳንወስድ በሲዲፎራችን መጠን ተገድበን ለረጅም ዓመት ለመቆየት እንገደድ ነበር።
ዛሬ ግን ማንኛውም ቫይረሱ በደሙ ያለበት ሰው ፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት ይወስዳል። ራስን ግልጽ አድርጎ ቫይረሱ በደም ውስጥ መኖሩን መናገር ይቅርና በመድሃኒት አወሳሰድና በአንዳንድ ሁኔታዎች በግል ተነሳሽነት ሐኪሞች ከሚያደርጉት ያለፈ የምክር አገልግሎት አልነበረም። አሁን ግን የምክር አገልግሎቱ ከእንክብካቤ ጋር በስፋት ይሰጣል።
ለማንኛውም ወደ ራሴ ልመለስና የትኛውንም ሐኪሞች ከመድሃኒት ጋር ተያይዞ የሚመክሩኝን ምክር ሳልተገብር ቀርቼ አላውቅም። ከራሴ አልፌ ተርፌ ልጄ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ ኖሮ እንድትወለድ ምክንያት በመሆኔ ተስፋ ብቆርጥም በኔም ሆነ በልጄ ጉዳይ ከመድሃኒት አወሳሰድ እስከ ሰዓቱና ምጣኔው የመከሩኝን ዝንፍ ሳልል ነው የምፈፅመው።
ማጥባት ያቆምኩት ልጄን በወለድኩ በዘጠነኛው ወር ነው። ከአንድ ወር በኋላም መድሃኒቱም ቆመ። በእርግዝና ሰዓት ዋናውን የፀረ ኤች አይቪ መድሃኒት ስወስድ ቆይቻለሁ። ከተወለደች በኋላ ጡት እያጠባኋት የምወስደውም መድሃኒት ነበር ። ሆኖም ጎን ለጎን በፈሳሽ መልክ የምትወስደው መድኃኒት ከባድ ነበር። በዘጠነኛ ወሩ ጡት ሳቆም አቁሜ ከአንድ ወር በኋላ መድሃኒቱ አብሮ ቆመ። ይሄኔ የመጀመርያ ምርመራ ተደረገና ልጄ ከቫይረሱ ነፃ ተባለች። ለመጀመርያ ጊዜ ከውስጠ ተደሰትኩ፤አምላኬንም አመሰገንኩ።
ከዓመት ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ ‹‹ ግራጅዌሽን›› የተሰኘውን ምርመራ ተመረመረች። በምርመራው አሁንም ከቫይረሱ ነፃ መሆኗ ተረጋገጠ። የጨለማው ዘመን አልፎ የብርሃን ዘመን መጣ። እንዲህ ከሆነ ለምን ሁለተኛ ልጅ አልወልድም አልኩ። አሁን ገና ከጽንሱ ከእናት ወደ ልጅ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የሚያደርገውን ሕክምና ተከታትየ ሁለተኛ ልጄን ወለድኩ።
መቆየት ደግ ነው። የመጀመርያ ልጄ ዘንድሮ 19ናኛ አመቷን ይዛለች። ለ12 ኛ ክፍል ማትሪክ ፈተና እየተዘጋጀች ነው። ሁለተኛ ልጄ ደግሞ ዘንድሮ ሰባተኛ ዓመቷን ደፍናለች። ሆኖም ልጆቼ እስካሁን በደሜ ውስጥ ኤችአይቪ እንዳለ አያውቁም። ልጄ ማትሪክ እንደተፈተነች ታሪኬን በሙሉ ለመንገር ወስኛለሁ። አበቃሁ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 /2014