አሸባሪው ህወሓት እድሜ ዘመኑን ክህደት የተጣባው ፤ በመታመን ኪሳራና እዳ እስከ አንገቱ የተዘፈቀ ሆኖ እያለ መንግስት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ሲል የወይራ ዝንጣፊ ይዞ እጁን ሲዘረጋለት አንድ ጊዜ ቅድመ ሁኔታ እየደረደረ ፤ ሌላ ጊዜ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ የሚያንገራግረው በምንና በማን ተማምኖ ነው። ቅድመ ሁኔታ ለመደርደርስ ምን መደራደሪያና ጫና መፍጠሪያ/leverage/እጁ ላይ አለ ፤ ጦርነትን እንደ ጣኦት ከማምለክ ውጭ ፤ የትግራይ ሕዝብ እንዲሁ በደጀንነት ፋቲግ የተሰላቸና የተዳከመ ፤ ሰራዊት የውጊያ ሞራሉ የተንኮታኮተ ፤ የትጥቅና የስንቅ እጥረት ክፉኛ ያቆራመደው ፤ ከዚህ ቀደም በለኮሳቸው ጦርነቶች ከፍተኛ የጦር መሪዎችን፣ ሰራዊቱንና የጦር መሳሪያውን በተለይ ከባድ መሳሪያውን ያጣ ፤ የሚያካሂደውም ሆነ ያካሄደው ውጊያ አላማ የሌለው፤ ለአንድ ጦርነት ወሳኝ ግብዓት የሆነው ሎጂስቲኩ አከርካሪው የተሰበረበት፤ ወዘተረፈ ሆኖ እያለ ታዲያ እንዲህ ለያዥ ለገናዥ የሚያስቸግረው ለምንድን ነው!?
በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊት የሚዋጋው ሀገሩ በታሪካዊ ጠላቶቿና እንደ ህወሓት ባሉ ተላላኪዎች እንዳትፈርስ የሚል የተከበረና የተቀደሰ ጽኑ አላማ አንግቦ ፤ በየጊዜው የሚሰለጥንና የነፍስ ወከፍም ሆነ የቡድን መሳሪያ እስካፍንጫው የታጠቀ ፤ ሰራዊቱም ሆነ አመራሩ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራና የዕዝ ጠገጉን የሚያከብር ፤ በሜካናይዝድ፣ በአየር ኃይል ፣ በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴና ድሮን የሚታገዝ ፤ አስተማማኝና ቀጣይ የትጥቅ ፣ የስንቅና የሰራዊት አቅርቦት ያለው ፤ ለሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት ሲል ተገዶ የገባበት ፍትሐዊ ጦርነት ነው ።
ከአሸባሪው ህወሓት አንጻር ሲታይ ጦርነቱን የመሸከም ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለው ፤ እንደ አባቶቹ ቀፎው እንደተነካ ንብ ለሀገሩ በአንድነት ሆ ብሎ የሚነሳ 115 ሚሊየን ሕዝብ በደጀንነት ያሰለፈ ፤ ወዘተረፈ ስለሆነ ለመደራደር አብላጫ ጉልበት/leverage/ያለው መንግስት ሆኖ እያለ ህወሓት ለምን ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል !? መልሱ ቀላል ነው ። ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በኋላ የዐቢይ አስተዳደር ለሰላም ያለውን የማያወላውል ቁርጠኛ አቋም ቡድኑ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄን የመንግስት ጥንካሬ እንደ ድክመት ቆጥሮ ነው ቅድመ ሁኔታን እየደረደረ ያለው ። ለህወሓት ለሰላም መጨነቅና መጠበብ ድክመት ነው ። የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ትግራዋይ ጦርነት ይበቃቸዋል፤ የሚያስፈልጋቸው ልማትና ብልጽግና ነው ማለት ለህወሓት እንደ ፍርሃት ነው የሚቆጠረው ።
ሀገራችን የጦርነትን ቀለበት ሰብራ መውጣት ስላለባት ፤ ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያንኮታኩት፤ ሀገርን ከልማት ከዕድገትና ከብልጽግና የሚያስተጓጉል፤ ዜጋን በተለይ አምራቹን የሰው ኃይል የሚያስጨርስ ፤ በጦርነት ዘላቂ ሰላም እንደማይመጣ፤ በተለይ የእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊ የሌለውና የዜሮ ድምር ፓለቲካ አጫፋሪ ስለሆነ ፤ ህወሓት አመጣሹ ማባሪያ የሌለው የትግራይ ሕዝብ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው መከራና ስቃይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ጽኑ ዕምነት ስላለው ፤ ከአሸባሪው ህወሓት ይልቅ መንግስት ለአለምአቀፍ ሕጎችና ለሞራል ልዕልና የሚገዛ ፤ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት መሆኑ እና ስለነገዋ ኢትዮጵያ ብሩሕ ተስፋ የሰነቀ መንግስት ስለሆነ ይህ ተስፋው እንዲጨናገፍ ስለማይፈልግ ወደ ግጭትም ሆነ ወደ ጦርነት የመግባት ምንም ፍላጎት የለውም ።
አሸባሪው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ትውልድም ሆነ ታሪክም ይቅር የማይለው ጭፍጨፋና ክህደት እስኪፈጸመ ድረስ መንግስት ህወሓትን ወደ ሰላም ለማምጣት ያደረገውን ተደጋጋሚ ጥረት የሚዘነጋ አይደለም ። ሆኖም ሰላም በአንድ ወገን ጥረትና ፍላጎት ብቻ እውን አይሆንምና ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ ውድ ዋጋ አስከፍሎናል ። መንግስት ዛሬም ህወሓትን እሽሩሩ የሚለውና ለሰላም ያለ ምንም ቅድመ ሆኔታ ረጅም ርቀት እየሄደ ያለው ጦርነትን ለማስቀረት ነው። የሚያሳዝነው ህወሓት መንግስት ምን ያህል ለሰላም ቁርጠኛ እንደሆነ ስለሚያውቅ ይሄን ክፉኛ የመንግስት መሻት ገልብጦ እንደ መደራደሪያ አቅም/ሌቨሬጅ/እየተጠቀመበት ይገኛል ።
መንግስት ለሰላም ሲል የማቀርብለትን ቅድመ ሁኔታ ሁሉ ያለ ማመንታት ይቀበላል የሚል የተሳሳተ ዕምነት ይዟል ። ለዚህ ነው መንግስት በአንድ ወገን ፍላጎትና ጥረት ሰላም እንደማይመጣ በተደጋጋሚ ገጥሞት አይቷልና ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል የሚባለው። ሆኖም ለሰላም ያሳየው ቁርጠኝነት ሁሉ በዜሮ ተባዝቷል ማለት አይደለም ። ምንም እንኳ አጥጋቢ ባይሆንም ምዕራባውያንና አለምአቀፉ ማህበረሰብ ስለ መንግስት የነበረውን ሸውራራ አመለካከት መለስ ብሎ እንዲያጤን ፋታ መስጠቱ አልቀረም ። አቋማቸው በተወሰነ ደረጃ እየተለሳለሰ መምጣቱን እየታዘብን ያለው ለዚህ ነው ። ይሁንና መንግስት ከሚገባው በላይ ለዛውም በተናጠል ነገረ ስራውና ሰራ አካላቱ ሁሉ ለሰላም መወሰዱ/obsessed/መሆኑ ከገደቡ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ።
በቅድመም ሆነ በድህረ ጦርነት ህወሓትን ሲያስፎክሩና ያዙኝ ልቀቁኝ ሲያስብሉ የነበሩ የመደራደሪያ አቅሞች አንድ በአንድ ከእጁ እየወጡ አጨብጭቦ እየቀረ ነው ። ለውጡ እንደባ’ተ ኮሽታ ሳያሰማ ጭራውን ቆልፎ ተጠራርቶና ተጠቃቅሶ ወደ መማጸኛ ከተማው መቀሌ በፍጹም ራስ መተማመንና ዕብሪት የመሸገው ላለፉት 50 አመታት ያጠመዳቸውን ፈንጅዎች ማቀጣጠያ ፊውዞች ተማምኖ ነበር ። ላለፉት አራት አመታት እነዚህን ፊውዞች አንድ በአንድ እያየያዘ የስልጣን ጥሙን ለመቁረጥ ያደረገው ጥረት ሁሉ ሲከሽፍ ደግሞ እንደ ወሼ እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል በሚለው የልቦና ውቅሩ እኔ እንደ ብረት ቀጥቅጬ የማልገዛትና የማልዘርፋት ሀገር ትፍረስ ብሎ የሄደበት መንገድም ምንም እንኳ ውድ ዋጋ ቢያስከፍለንም ተቀልብሷል ። ከህወሓት እጅ አንድ በአንድ ያመለጡ የመደራደሪያ አቅሞችን ወይም ነጮች እንደሚሉት “ሌቬሬጅስ” እስኪ መለስ ብለን በስስ በስሱ እንቃኝ ።
አሸባሪው ህወሓት ከምንም በላይ ሲመጻደቅበትና ሲኩራራበት የነበረው የውጊያ ብቃቱን ነበር ። በአደባባይና በሸንጎ በአፍሪካ ህወጋትን በጦርነትና በውጊያ ስልት የሚያክለው የለም እያለ እንደ መንደር ጎረምሳ ያዙኝ ልቀቁኝ ይልበት የነበረው ዕብሪቱ የሰሜን ዕዝ በተከዳና በተጨፈጨፈ ማግስት ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አከርካሪው ተሰብሮ ቆላ ተምቤን ሊወርድ ችሏል ። ምንም እንኳ መንግስት በተከተለው የተሳሳተ መንገድ ድሉን ማስጠበቅ ፣ ማጽናትና ማዝለቅ ባለመቻሉ አፈር ልሶ ተነስቶ ያልተገባ ዋጋ ቢያስከፍለንም ። በሁለቱም ጦርነት ከፍተኛ ፓለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ፣ ሰራዊቱን ፣ የጦር መሳሪያውን፣ የውጊያ ሞራሉን ፣ ወዘተረፈ አጥቷል ።
ዛሬ የህወሓት የውጊያ ብቃት ከአራትና ከሶስት አመታት በፊት እንደነበረው የመደራደር አቅም ሊሆን ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል ። ይህን ስል እንዘናጋ እያልሁ አይደለም ። ህወሓት ነገ ምን ፈጥሮና አድርጎ ሊያስደነግጠንና ሊያስደንቀን እንደሚችል መገመት ይቸግራልና ። ሆኖም ከህወሓት ማንነትና ባህሪ ተነስቶ የማይጠበቀውን ለመጠበቅ በስነ ልቦናም በአካልም መዘጋጀት ይገባል ። ህወሓት ለሰላም እንዲያ እግሩ ላይ ተወድቆ ሲለመን ይጓደድ የነበረበት ሌላው ምክንያት ላለፉት 50 አመታት በተለይ ደግሞ ላለፉት 30 አመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ ሲዘራውና ሲጎነቁለው የኖረው የዘረኝነት የጎሰኝነት የልዩነት የጥላቻና ቂም በቀል ፈንጂ ፊውዝን በፈለገ ጊዜ በቀላሉ አያይዞ አማራው ከኦሮሞው ፣ አፋሩ ከኢሳው፣ ሲዳማው ከወላይታው፣ ሱማሌው ከኦሮሞው ፣ አማራው ከጉምዙና ከቅማንቱ ሲባላና ሲጫረስ ሀገር ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት ስትዘፈቅ የዛን ጊዜ በአቋራጭ አገዛዝ ላይ መመለስ ነበር የቀን ቅዠቱ ።
ባለፉት አራት አመታት በዚህ የህወሓት መሠሪ ዳባ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ንጹሐን በግፍ ቢጨፈጨፉ ፣ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎ ከቀያቸው ቢፈናቀሉም በሀዘን ቅስማችን ቢሰበርም ፤ በሆነው ሁሉ ጥርሳችንን ብናፋጭም ፤ በአለም አደባባይ አንገታችንን ብንደፋም ፤ በሀዘን ከል ብንለብስ፣ በራሳችን ትቢያ ብንነሰንስም ፤ በኢትዮጵያ አምላክ ምህረት ወደ ማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት አልገባንም ፤ ህወሓትም እኛን አባልቶ ወደ አገዛዝ አልተመለሰም ። አይመለስምም ። ዛሬ ከሶስትና አራት አመታት በፊት ከነበረው በብዙ እጥፍ የተሻለ የጸጥታና የደህንነት ተቋም መገንባት ስለቻልን ፤ የህወሓት ክፉ ሀሳብ ከማይሳካበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ። የመደራደሪያ ጉልበቱ የነበረው የ50 አመት ፕሮጀክቱ በዚህ መንገድ ከሽፏል ።
አልሻባብ ፣ ሸኔ ፣ የቅማንት የጉምዝ የጋምቤላና የአገው ታጣቂዎች ሌላ የህወሓት የመደራደሪያ ጉልበቶች ነበሩ ። እነዚህን ቡችሎቹን እስፖንሰር እያደረገ ስምሪት በመስጠት አገር በአራቱ ማዕዘናት እንደ ሌጦ ስትወጠር ህወሓት የጎበዝ አለቃ ሆኖ ራሱን ለመሾም አሰፍስፎ የነበር ቢሆንም ይሄም እንደ ቀን ቅዠቱ መሻት አልሆነም ። ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደ ሞከርሁት የለውጥ ኃይሉ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ በጸጥታና በደህንነት ተቋማት ላያ ያደረገው ማሻሻያ ቆይቶም ቢሆን እየከፈለው ይገኛል ። ሰሞኑንና በአልሻባብ ላይ ያረፈው ብርቱ ክንድ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ። እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ተሞክሮ የጠራ የፓለቲካና የጸጥታ ተቋም ክልል ላይ ሲኖር ከፌደራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ ምን አይነት ተአምር ሊፈጥር እንደሚች በሱማሌ ክልል እየተመለከትን ነው ።
በአደባባይ ባያውጅም እንደ መደራደሪያ ጉልበት ወይም ሌቬሬጅ ከሚጠቀምባቸው ኃይሎች በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያኮረፉት ግብጽና ሱዳን ይገኙበታል ። ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጎን በመቆም የሚታወቀው ህወሓት የዛድባሬን ወረራ ደግፎ ከታላቋ ሶማሊያ ፕሮጀክት ጎን ተሰልፎ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም የግብጽን ሀገራችንን የማተራመስና የማፍረስ ተልዕኮ ወስዶ የሕዳሴውን ግንባታ ለማጨናገፍ ሌት ተቀን ሲማስን ከርሟል ። ለዚህ ውለታው ደግሞ የዲፕሎማሲ ፣ የፓለቲካ ፣ የሚዲያ ፣ የቅጥረኛና የፋይናንስ ድጋፍ ሲደረግለት ቆይቷል ። ይሁንና ግብጽ ይሄ መንገዷ እንዳልተሳካ የሕዳሴው የውሃ ሙሊት ለ3ኛ ጊዜ ያላንዳች መስተጓጎል መካሄዱና ከአንድም ሁለት ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ጮኽ ብለው ይናገራሉ ።
ግብጽ እንደ ህወሓት ያሉ ከሀዲ ተላላኪዎችን የትም እንደማያደርሳት እየተረዳች ስለሆነ ለእነዚህ የእናት ጡት ነካሾች ስታደርግ የቆየችው ዙሪያ መለስ ድጋፍ በነበረበት አይቀጥልም ። ህወሓት ሱዳን በግብጽ አይዞሽ ባይነት ድንበራችንን አልፋ መሬታችንን ስለወረረች የኢፌዴሪ መንግስት በደም ፍላት ጦርነት ውስጥ ሲገባ ግብጽ ከሱዳን ጎን ስለምትቆም በዚህ ግርግር ለማትረፍ ቋምጦ የነበረው ህወሓት ሳይሳካለት ቀርቷል ። እንዲህ እንዲህ እያልን ከወጭ ቀሪ ስንተሳሰብ ህወሓት ቅድመ ሁኔታ ለመደርደር እንደ አቅም የሚታይና ይህ ነው የሚባል ሌቨሬጅ እንደሌለውና ባዶ እጁን አጨብጭቦ እንደቀረ እንረዳለን ። ምንም እንኳ ከስህተቱ የመማር መርገም እንዳለበት የሚታወቀው ህወሓት ይሄን ሀቅ ተገንዝቦ ወደ ድርድሩ ይመጣል ተብሎ ስለማይጠበቅ መንግስት ለማንኛውም ነገር ቆቅ ሆኖ መጠበቅ አለበት።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም