ጌታቸው ሙላቱ የተባሉ አንድ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ ህወሓት አጭር ታሪክ›› በሚል ዘለግ ያለ ግጥማቸው እንዲህ ሲሉ ነበር በመጀመሪያዎቹ ስንኞች ላይ የሰደሩት፡፡
ህወሓት ወያኔዎች፣ ደደቢት ተነሱ፣
ከዚያት ጥቂት ቆዩ፣ አፈር እየላሱ፣
ካሉበት በርሃ፣ በሕዝብ እየተመሩ፣ እየገሰገሱ፣
በሕዝብ የተጠላውን፣ ደርግን አፈረሱ፣
ምኒልክ ቤተመንግስ፣ ገቡና ነገሱ።
እንግዲህ በዚህ ግጥም መግቢያ ላይ ከተጠቀሰው ሃሳብ ለመረዳት እንደሚቻለው የአሸባሪው ህወሓት ትርክት ስልጣን እና ስልጣን ስለመሆኑ፤ ከደደቢት እስከ አራት ኪሎ የደረሱትም በጀግነንታቸው ሳይሆን በህዝብ እየተመሩ ስለመሆኑ እንጂ በሚዲያ እንደሚደሰኩሩት አለመሆኑ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር ቢኖር ግን በቀጣይ ህወሓት ደደቢት ተፈጥሮ ደደቢት የመቀበሩ እውነታ አሁን አሁን ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡
በርካታ ህወሓታውያን በአንድም ይሁን በሌላ በሕይወት ዘመናቸው ከቡድኑ ውጪ እንዳይሳቡ በመደረጉ ቡድኑን እንደጣዖት የመመልከት እርግማን ውስጥ ገብተዋል። ይህ ከትግራይ ህዝብ መንፈሳዊ፣ባህላዊና ማህበራዊ የልቦና ውቅር የተጣላ አስተሳሰብ ከነሱ አልፎ የትግራንም ህዝብ ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
ቡድኑን እንደ ጣዖት የሚመለኩ ግለሰቦች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ ባይሆንም፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ መድረክ ውስጥ አንድን ቡድን ጣኦት አድርጎ የመቀበሉ አውነታ በብዙ መልኩ ከማሳዘን አልፎ የሚያሳፍር፤ ከዘመን ጋር በዓደባባይ ተጣልቶ መገኘትን አመላካች ነው ።
ኃይል አምላኪነት የተጠናወተው፤ ከውልደቱ ጀምሮ የጦርነት ከበሮ በመደለቅ በትግራይ ወጣቶች ደም የሚቆምረው ይህ ቡድን በፕሮፓጋንዳው ዛሬም የትግራይን ወጣት ለዳግም እልቂት እያነሳሳ ይገኛል። ለሰላም የተሰጠውን ዕድል ትርጉም ለሌለው እብሪት አሳልፎ በመስጠት የትግራይን ህዝብ እንደህዝብ ያልተገባ ዋጋ ለማስከፈል የጦርነት ከበሮ እየደለቀ ይገኛል። ለዚህ አስገዳጅ በሆነ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ቢቢሲ ግንቦት 04 ቀን 2022 በሠራው ዜና እንዲህ ብሎ ነበር ርዕስ ሰጥቶት ነበር፡፡ ‹‹ህወሓት ለመዝመት ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን እያሰረ መሆኑ ተነገረ›› ይላል፡፡ ህወሓት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ልጆቻቸው ያልዘመቱ ወላጆችን እያሰረ እንደሚገኝ የቤተሰብ አባላት ለቢቢሲ ተናገሩ በሚለው ዜናው፤ ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ የትግራይ ተወላጅ፣ልጆች ለመዝመት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ወላጅ አባቱ እና አጎቱ ታስረዋል፡፡ ‹‹ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ውትድርና መላክ አለበት፤ መዋጣት አለበት የሚል ሕግ አለ›› ይላል ታዳጊው።
ይህ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ ክልል ውጪ የሚገኘው ወጣት፤‹‹አባቴን ልጅህን አምጣ አሉት። ማምጣት ስላልቻለ ለአንድ ወር አሰሩት። ከዚያ ደግሞ ወንድሜን እንዲያመጣ ብለው ለቀውት ነበር። አሁን ያለበትን ሁኔታ ባላውቅም ለመጨረሻ ጊዜ በስልክ ሳገኛቸው አባቴን አስረውት ነበር››በማለት በዚያ አካባቢ ያለውን ሰቆቃ አስረድቷል።
ወጣቱ እንደሚለው አዋቂ የሆነው ወንድሙ በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት የለውም። ‹‹ወንድሜ እኮ ትልቅ ነው። ከፈለገ የአባቴን ፍቃድ ሳይጠይቅ ይሄድ ነበር። የያዙት ግን አባቴን ነው›› ሲል የትግራይ ወጣት ለእሳት ለመማገድ ደፋ ቀና የሚለው አሸባሪው ህወሓት የሚይዘው የሚጨብጠው ሁሉ እንደጠፋው ያሳያል፡፡ ልጆቻቸውን ወደ ጦር ሜዳ ባለመላካቸው አጎቱም ጭምር ለእስር ተዳርገዋል፡፡ 18 ዓመት ያልሞላቸው ታዳጊዎችን ጭምር ወደ እሳት ማግዱ እየተባሉ እየተገደዱ ስመሆኑ እጃቸውን ለአማራ ክልል ፀጥታ ኃይሎች፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ የሰጡ የትግራይ ተወላጆች ይናገራሉ፡፡ ቡድኑ ከሠላማዊ ህይወት ይልቅ የጦርነት ጥማት ያለበት ቡድን ነው ፡፡ የቀደመ ታሪኩም በአብዛኛው የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
በፌደራል መንግስት ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመት በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ በመሆን ህዝቡን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ሊነጥለው ሞክሯል፡፡ በሐሰት ትርክት ጀግና ለመመስል እና እንደእርሱ የነበዙ ጀግኖችን ለመፍጠር ሲቃዥ ቆይቷል፡፡ ከቡድኑ የአሸባሪነት ባህሪው በመነሳትም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሥጋት ስለመሆኑ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ህወሓት ኢትዮጵያን ማቃናት ሳይሆን ኢትዮጵያን እየቦጠቦጠ ራቁቷን ያስቀረ ነው፡፡ በህገወጥ የንግድ ስርዓት በመሰማራት በሀገሪቱ ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በባህር ላይ ውንብድና ሆነ በሌሎች ህገወጥ ተግባራት ውስጥም ሹማምንቶቹ ተሳትፈው ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በገንዘብ ሚኒስቴር እና ብሄራዊ ባንክ ከሚዘወረው በላይ በህገወጥ ደላሎችና ኢኮኖሚውን ያለአግባብ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ኪራይ ሰብሣቢዎችም የህወሓት ቁንጮ ሰዎች ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚው፣ የሀገሪቱ ማህበራዊ ስሪትና ፖለቲካው ህጋዊ ከመሆን በላይ ከህግ ውጭ አፈንግጦ በደባና ተንኮል እንዲመራው ህወሓት ጠንሳሽ ዋነኛ ተዋናይ ነው፡፡
በመንግስት ስልጣን ከለላ በማድረግ ከኢኮኖሚው ከአቅም በላይ የመጠቀምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር በማድረግም የአንበሳውን ድርሻ ይዞ የቆየ የማፍያ ቡድን ስለመሆኑም የጥቃቱ ሰለባዎች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ቅሌት የነወረው ይህ ማፍያ ቡድን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በተኛበት ጥቃት በማድረስ የመጨረሻ የተባለውን የሀገር ክህደት ፈጽሟል፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ በመንግስት በተካሄደው የህልውና ዘመቻ አብዛኞቹ የቡድኑ አመራሮች ሙት ሆነዋል፡፡ ከፊሎቹም በቁጥጥር ስር ውለው የፍርድ ሄደታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
መንግስት የቡድኑ እብሪት በትግራ ህዝብ ላይ ያስከተለው እና ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት) ሠላማዊ ህይወት እንዲመሩ፤ የዘር ጊዜም እንዳያመልጣቸው (በሚል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከክልሉ እንዲወጣ ቢያደርግም የቡድኑ ርዝራዥ ዳግም በመሰባሰብ በአፋር እና አማራ ክልል ወረራ በመፈፀም ዳግም ዳግም ወደ አራት ኪሎ ያደረጉት ጉዞ በብዙ ኪሳራ ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በወቅቱም በቡድኑ ላይ ከደረሰው መጠነ ሰፊ ኪሳራ የተነሳ ከፍባለ ድምጽ ስለ ሰላምና ድርድር እንዲጮህ ያስገደደው ቢሆንም ፤ውሎ ሳያድር ተመልሶ የጦርነት ከበሮ ወደመጎሰሙና የትግራን ወጣት ለእልቂት ወደ መመልመሉ ተመልሷል። መንግስት ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር ለመግባት ለደረሰበት ውሳኔም ቅድመ ሁኔታዎችን ወደ ማስቀመጥ ሄዷል።
ከፍጥረቱ ጀምሮ በሰላማዊ ንግግርና ድርድር የማያምነው አሸባሪው ህውሓት ፤የመንግስትን የሰላም መሻት ጊዜ መግዧ ለማድረግ እየመከረ ነው። ለዚህ ደግሞ በህግ መላው የትግራይ ወጣት መሳሪያ አንስቶ ለቡድኑ ህልውና እንዲሞት እያስገደደ ይገኛል። በቅርቡ የቡድኑ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ‹‹ለጦርነቱ ጥሪ ምላሽ የማይሰጥ ወጣት ወደፊት በሚወጣ ህግ የሚያጣቸው መብቶች እንዳሉ በአደባባይ አሳውቋል።
አሸባሪው ህውሓት ለድርድር ያስቀመጣቸው / ሊያስቀምጣቸው የሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሊኖሩ አይችሉም። ‹‹ላም አለኝ በሰማይ፤ወተቷን አላይ›› ከልሆነ በስተቀር ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ የሚያስችል ወቅታዊ ቁመናም የለውም፡፡
ትልቁ ነገር የህወሓት ርዝራዧች አሁንም ወደ ጦርነት በመግባት የትግራይን ወጣት ለዳግም እልቂት ሊዳርጉት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ እንደቀደሙት ወቅቶች አልጋ በአልጋ የሚሆን አይደለም። የትግራይ ወጣት ትርጉም አልባ ለሆነ ጦርነት እራሱን የመስዋእት በግ አድርጎ የሚሰጥበት የንቃተ ህሊና ውድቀት ውስጥ አይደለም።
በከበሮ ድለቃና በሆሆይታ ዘፈን ሕይወቱን ዘመን ላለፈባቸው፤ ዛሬም በትግራይ ወጣት ደም ነገዎቻችውን ተስፋ ለሚያደርጉ፤ በንጹሀን ደምና በትግራይ ህዝብ ተስፋ ለደለቡ መስዋእት አድርጎ አይሰጥም፡፡ ለዚህም ነው ለህወሓት የጦርነት ጉሰማና ቅስቀሳ ጆሮ በመንፈግ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ወደ አጎራባች ክልሎች እየፈለሱ ያሉት፡፡ ሕይወታቸው ከቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ትርክት በላይ ዋጋ እንዳለው በተጨባጭ እያሳዩ ያለው።
የተቀረው ቢሆን እዚያው ትግራይ ክልል ውስጥ ሆኖ እንቢታውን እየገለፀ ነው፡፡ይህ የዛሬው የትግራይ ወጣት እንቢታ፤ የነገውን የትግራ ህዝብ እጣ ፈንታ የሚቀይር ፤ህዝቡ እንደ ህዝብ በሰላም የመኖር ተፈጥሯዊ መብቱን የማስጠበቅ አልፋና ኦሜጋ ነው። ይህን አጠናክሮ መቀጠል ደግሞ እውነተኛ የሆነውን የነፃነት ቀን ማፍጠን ነው።
ትልቁ እውነት አሸባሪው ህወሓት ትግራይን በሰላማዊ መንገድ ሊመራ ቀርቶ ራሱን ማዳን የማይችልበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ የትግራይ እናቶች፣አባቶችና ወጣቶች በጀመሩት መንገድ እንቢታቸውንም ማቀጣጠልና ህወሓትን እስከመጨረሻቸው ማሠናበት አለባቸው፡፡
ትግራይ ሠላምን እንጂ ፀረ-ሠላሞችን የምትሸከምበት ጫንቃ እንደሌላት ታሪክ በመሥራት ማሳየት አለባት፡፡ ከእንግዲህ ከህወሓት በኩል ለሚሰነዘር ጥቃት ዝምታን የሚመርጥ ኢትዮጵያዊ መኖር የለበትም፡፡ የአሸባሪው ህወሓት ታሪክም ደደቢት ተጀምሮ ደደቢት ስለመፈፀሙ በትክክል ማረጋጥም የመላው ኢትዮጵውያን ትልቅ ኃላፊነትና ታሪካዊ ድርሻ ነው፡፡
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም