“ፍቅር ፍቅር አሉት ስሙን አሳንሰው …” እንደተባለው ሁሉ ሕይወትንም ስሙን አሳጥረን “ሕይወት” አልነው እንጂ እንደ ስያሜውና አጠራሩ ቀላል አይደለም። በኑሮ ይገለፅ ከተባለም አልጋ ባልጋ ሆኖ አያውቅም።
ሕይወት ባለ ሕይወቱን የማያደርገው የለም። ያወጣዋል፣ ያወርደዋል፤ ይሾመዋል፣ ይሽረዋል፤ ወዘተርፈ። በመሆኑም፣ “ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ” እንደተባለው ነውና ሕይወትን ለመኖር የሚከፈለው ተገቢ የሆነ ዋጋ ከተገቢነቱ ባለፈ ተገቢ አይደለም በሚል ሲያነታርክ አይታይም። የዛሬዋ እንግዳችን እንደሚነግሩን ከሆነ ግን ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ተገቢ ያልሆና ዋጋ እየከፈሉ ነውና ሕይወት ለእሳቸው ከላይ እንደ ገለፅነው አይደለም። እንግዳችንን ዋጋ እያስከፈለ ያለው “ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ” በሚለው የመጽሐፍ ቃል መሰረት ሳይሆን በግፈኞች የግፍ አገዛዝ ምክንያት ነው።
ወይዘሮ ጥሩነሽ ገበየሁ (በተለምዶ ጥሩ) ይባላሉ። ባለትዳርና የአራት ሴት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ ነዋሪነታቸው እዚሁ አዲስ አበባ፤ የካ ክፍለ-ከተማ፣ ወረዳ 01 (ቀበሌ 07) ነው።
ወይዘሮ ጥሩን ያገኘናቸው የመሀል አዲስ አበባ ዋና ዋና አደባባዮች ከሆኑት በአንዱ፣ በአራት ኪሎ፣ ድላችን አደባባይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (የተፈጥሮ ሳይንስ) ካምፓስን አጥር ተደግፈው ከሕይወት ጋር ሲታገሉ ነው።
ሕይወት ወደ ጎዳና ያወጣቻቸው፤ የስራ ቦታቸው ጎዳና እንዲሆን የዳረገቻቸው ወይዘሮ ጥሩ ሕይወት ገና ለገና ጎዳና ላይ አውጥታኛለችና እንደ ፈለጋት ታድርገኝ በማለት እራሳቸውን ለችግር አጋልጠው እጃቸውን ለልመና አልዘረጉም። በፎቶግራፋቸው ላይ እንደሚታየው እጃቸው እጥፍ – ዘረጋ እያለ ያለው ለስራ፤ ለዛውም የአገር በቀል እውቀት ውጤት ለሆነው ስፌት ተግባር፤ ለዛውም በአለላ በተንቆጠቆጠ ስፌት ነው።
ፎቶግራፍ ሆኖ እንጂ ተንቀሳቃሽ ምስል ቢሆን ኖሮ አንባቢ ወይዘሮ ጥሩነሽ ገበየሁን አድንቆ፤ በስራቸውም ተገርሞ አያበቃም ነበር። ወይዘሮዋ ብርታታቸው ገና ትኩስ ነው፤ ቅልጥፍናቸው የአራት ልጆች እናት ሊያስመስላቸው ቀርቶ ገና በኮረዳነት እድሜ ላይ ያሉ ነው የሚመስሉት። ያሳለፉት መከራና እንግልት ወደ ውስጣቸው ያሰረፀው ጥንካሬን እንጂ ስንፍናን፤ ምርኮኛነትን አይደለም። ሲሰሩ ፍጥነትና ቅልጥፍናቸው የጉድ የሚያስብል ነው። ሲያወሩ እንኳን እጃቸው ከስራቸው ንቅንቅ አይልም፤ አይናቸውም እንደዛው። ባጭሩ ፈጣሪ ለስራ የፈጠራቸው ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል። ግና ምን ያደርጋል አስቀድመን እንዳልነው … ግፍ እና የግፍ አገዛዝ እስካለ ድረስ ሕይወትና ሕያዋን ለጉስቁልና ብቻ ሳይሆን ጭራሹንም ለጎዳና ሁሉ ሊዳረጉ ይችላሉና የወይዘሮዋ እጣ-ፈንታም የሆነው እንደዚሁ ነው። ግን እጅ አልሰጡም።
ከወይዘሮ ጥሩ ጋር ጊዜ ወስደን ብዙ ተጫዋውተናል። የሆዳቸውን ሁሉ ነግረውናል። የደረሰባቸውን ሁሉ አንድም ሳይደብቁ አጫውተውናል። የተፈራረቁባቸውን ችግሮች፤ “ደረሰብኝ” ያሉትን በደል ሁሉ አንድ፣ ሁለት … በማለት ዘርዝረውልናል (ግማሾቹ ከሕግ ጋር የተገናኙ በመሆናቸው እዚህ ባንጠቅሳቸውም)። ግን ምን ያደርጋል፤ ገፃችን የጋዜጣ ነውና ሁሉንም እዚህ ማስፈር አልቻልንም። በመሆኑም፣ ዋና ዋና በደሎቻቸውና ለጎዳና የዳረጓቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥቂቶቹን ብቻ ይዘን ቀርበናል። ይህንንም፣ እራሳቸው ባለ ታሪኳ “እኔ” እያሉ ይነግሩን ዘንድ ፈቅደናልና እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የቀድሞው መኖሪያዬ ጎጃም፣ ኑንዴን ወረዳ፣ ሞጣ ጊዮርጊስ አካባቢ ነው። ተወልጄ፣ ተኩዬ የተዳርኩት … እዛው ነው። ነገር ግን በማህበራዊ ችግር፣ በተለይም በወንድሜ ሞት ምክንያት እዛ መኖርን አልፈለኩም። በመሆኑም በ1998 አ.ም መልቀቂያዬን ይዤ ወደዚህ፣ አዲስ አበባ መጣሁ። የካ ክፍለ-ከተማ፣ ወረዳ 01 (ቀበሌ 07)ም በነዋሪነት ተመዝግቤ መኖር ጀመርኩ። በ2007 ዓ.ም የቀበሌ ቤት ተሰጠኝ።
ከዛን ጊዜ ጀምሮ እንደ አንድ ነዋሪም የቀበሌ ቤት ተሰጥቶኝ መኖር ጀመርኩ። በአንድ ግቢ ውስጥ ብዙ ሆነን መኖር ጀመርን። ነገር ግን ይህ የቀበሌ ቤት ውስጥ የመኖሬ ጉዳይ ዘላቂነት ሊኖረው አልቻለም። ከዚህም ከዚያም እንቅፋቶች ገጠሙኝ።
የተሰጠኝ የቀበሌ ቤት መብራት እንኳን የለውም። ጠይቄም ሊገባልኝ አልቻለም። የሚገረመው ይሄ አይደለም፤ መብራት ሳልጠቀም የመብራት ክፈይ የሚለው ነገር መምጣቱ ነው። ያልተጠቀምኩበትን አልከፍልም ስል ያጠራቀምኩትን ብር አስያዙብኝ።
ከዚህ ከቀበሌ ቤት ጋር በተያያዘ የደረሰብኝ በደልና መንገላታት እንዲህ በቀላሉ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም። ብዙ ግፍ፣ ብዙ በደል ነው የደረሰብኝ። ይሄንን ሁሉ ግፍና በደል ያደረሱብኝ ሰዎች ናቸው፤ አሁንም አሉ።
እኔ ዜጋ ነኝ። እንደማንኛውም ዜጋ እኩል ልታይ ይገባል እንጂ ይህ ሁሉ በደል ሊደርስብኝ አይገባም። ሰው ሁሉ እኩል ነው። በመጨረሻም ከምኖርበት የቀበሌ ቤት በልማት ተነሺ ስም አፍርሰው አባረሩኝ። የተሰጠኝ ምንም አይነት ምትክ የለም። ይሄው በአሁኑ ሰአት እንደምታዩኝ ነው እየኖርኩ ያለሁት። የደረሰብኝ በደል ብዙ ነው። ቀደም ሲል በልማት ተነሺ ስም ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡
በወቅቱ መብቴን ስጠይቅ የሚመልስልኝ የለም። እንደውም እብድ ነች ተብዬ፣ የመጨረሻዋን ልጄን ነፍሰ ጡር በነበርኩበት ሰአት አማኑኤል ሁሉ በመኪና ጭነው ወስደውኛል። ዶክተሩ ነው ጤነኛ ነች ብሎ እንድመለስ ያደረገኝ። ዶክተሩ ነፃ ባያደርገኝ ኖሮ እንደ እነሱ ቢሆን ኖሮ … ይሄኔ እኔ እዛ አማኑኤል ነበርኩ።
አሁን በምን አይነት ደረጃ ላይ ነው የምትኖሪው ለሚለው እንጦጦ ማርያም አካባቢ የግለሰብ ቤት በወር 2ሺህ 800 እየከፈልኩ ተከራይቼ ነው የምኖረው።
ልጆቼ ከእኔ ጋር አይደሉም። የመጀመሪያዋ ልጄ አግብታለች። ሌሎቹ አሉ። ከአባታቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ናቸው።
የትምህርታቸውስ ነገር ለተባለው በእርዳታና ድጋፍ፤ በትምህርት ቤቶቹ ትብብር ይማሩ ነበር። ደብተርና ስክሪፕቶ የሚባል ነገር አላስብም ነበር። አሁን ያ ስለቀረ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።
ይህንን ስራ በተመለከተ ለጠየከኝ፣ ወደዚህ ስፍራ፣ ጎዳና ከወጣሁ ወደ ሶስት አመት እየሆነኝ ነው። ይህንንም ስራ ስጀምርም እንደዛው። በእርግጥ ከዛ በፊትም ሙያው አለኝ፤ እሰራዋለሁ። እዚህ አዲስ አበባ ከመጣንም በኋላ በአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት (የትኛው ክፍለ-ከተማ እንደሆን አላስታውሰውም) አደራጅቶን መስራት ጀምረን ነበር። ድንገት ሳይታሰብ ግን በተኑን፤ ተበተንን። ዳግም መልሰን ለመደራጀት አስበን አልሆነልንም። እነሱም እንደዛ አይነት ነገር ነበር የነገሩን፤ ተመልሰን እንደምንደራጅ ነበር ተስፋ የሰጡን። ግን አልሆነም። ተበተንን፤ በዛው ቀረን።
በወቅቱ ያደራጀን አካል አያያዙ ጥሩ ነበር። ብር መቆጠብም ጀምረን ነበር። እኔም በሶስት አመት ውስጥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5ሺህ 690 ብር መቆጠብ የቻልኩት ያኔ ነው። ደብተሩን አልያዝኩትም እንጂ ማየት ይቻል ነበር። ለአባይ ግድብም የአምስት ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ። በወቅቱ ይህ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ “እንዴት ልትገዛ ቻለች?” በሚል ይመስለኛል ጥሩ ስሜትን አልፈጠረም ነበር። እኔ ግን አሁንም የመግዛት እድሉን ባገኝ ባለችኝ ገንዘብ ቦንድ ለመግዛት ዝግጁ ነኝ። ለአባይ ግድብ ቦንድ መግዛቴን አላቆምም።
የስራውን አዋጭነት አስመልክተህ ለጠየከኝ ስራው ጥሩ ነው። ምንም አይነት የገበያ ችግር የለበትም። እኔ አንድም ጊዜ ገበያ አጥቼ አላውቅም። በትእዛዝ ነው የምሰራው። እንቅብ (700 ብር ነው) እታዘዛለሁ፤ ሙዳይ (500 ብር) እታዘዛለሁ፤ መሶብ (600 እና 700 ብር ነው) እታዘዛለሁ፤ እሰራለሁ። የሳሎን መሶብ (1ሺህ 300 ብር) እታዘዛለሁ፤ በቀጠሯችን መሰረትም ሰርቼ አስረክባለሁ። ሰዎች እየመጡ የሚፈልጉትን ያዙኛል፤ እሰራላቸዋለሁ። እግዚአብሄር ይመስገን የገበያ ችግር የለብኝም።
አሁን ምን ትፈልጊያለሽ ላልከው እኔ የምፈልገው እንደነከርኩህ የነበርኩበት ቀበሌ መልቀቂያዬን ሰጥቶ እንዲሸኘኝ ብቻ ነው። ሌላው፣ መንግስትንም ሆነ ሌሎችን የምለምነው በዚሁ ሙያ እንዲያደራጀኝ፤ አደራጅቶም (ሳያደራጁኝም በግሌም ቢሆን) ትንሽዬ ቦታ እንዲሰጠኝና እዛ ላይ ህጋዊ ሆኜ እንድሰራ ብቻ ነው። ይሄንን ብቻ ነው የማስቸግረው። የምሰራው ስራ በጣም ፈላጊ ስላለው ይህ ከተደረገልኝ ብዙ እንደምሰራ አውቃለሁ። ለሌሎችም እንደምተርፍ አውቃለሁ። በመሆኑም ይሄንን ብቻ ቢያደርጉልኝ በቂዬ ነው።
ለሌሎች፣ መሰል ሰዎች፣ በተለይም ጎዳናን ለመለመኛነት ብቻ ለሚያውሉት የምትመክሪው ካለ ላልከው፤ አዎ አለኝ። ሰዎች ስንባል ስራ ነው መስራት ያለብን። ያለ ስራ ምንም የለም። በመሆኑም የትም ቦታ ሆነን መስራት እንችላለን። ቦታው ሲመቸን ብቻ አይደለም ስራ መስራት የሚገባን። ሳይመቸን መስራትንም መልመድ አለብን።
መንግስት ይህንን በተመለከተ ሰዎችን እያደራጀ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ አለበት። ቅድም እንደ ነገርኩህ መደራጀት ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ሳናውቀው ባይፈርስ ኖሮ ብዙ ጥቅም እናገኝ ነበር። እ… አልኩህ እኮ ንግድ ባንክ እስከ መቆጠብ ደርሻለሁ እኮ።
መንግስት ጎዳና የወጡትንም ሆነ ሌሎችን አደራጅቶ ነይ ካለኝ ባለኝ ሁሉ ላግዘው ፈቃደኛ ነኝ። ስልጠና ከመስጠትና ልምድን ከማካፈል ጀምሮ ያለኝን፤ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ፍቃደኛ ነኝ። ሌሎችም እንደዚሁ ፍቃደኛ ሊሆኑ ይገባል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014