በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከ50 ዓመት በፊት የታተሙት ጋዜጦች ቃኝተናል። ለትውስታ ያህል በርካታ አመታትን መለስ ብለን ከተመለከትናቸው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባዎች መካከል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአውሮፓ ተወዳድረው ያገኙትን ስኬት፤ አበበ ቢቂላ በውድድሩ በቼኮዝላቫኪዊ ለ11 ዓመት ተይዞ የነበረ ክብረ ወሰን መስበሩን የሚያስታውሱ ይገኙበታል።
በወቅቱ በ 800 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሠይድ ሙሳ 2ኛ መውጣቱን ዝነኛው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ያጠናከራቸው ዘገባዎች ያሳያሉ። በወቅቱ ከተዘገቡ ወንጀል ነክ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችንም አካተናል።
፫ቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች
ሦስቱ የኢትዮጵያ አትሌቶች አበበ፣ ማሞና ሠይድ በአውሮፓ ውስጥ ማለት በስዊድን፤ በምዕራብ ጀርመን፤ በዴንማርክ፤ በኖርዌይና በቤልጅግ አገሮች ላይ እየተዘዋወሩ የኢንተርናሽናል ውድድር በማድረግ ፤፮ ሳምንት ከቆዩ በኋላ፤ ባለፈው ሳምንት አ/ አበባ መግባታቸው ቀደም ብሎ ተገልጿል።
የነዚህ አትሌቶች አሠልጣኝና መሪ ሆነው አብረው የሔዱት ሜጀር አኒ ኒሰካል ግንቦት ፳፰ ቀን በስዊድን አገር ማልም በተባለው ስታዲየም ላይ በተደረገው በየአንድ ሰዓት ሩጫ ሲናገሩ አበበና ማሞ ከመጀመሪያ ጀምረው እስከ ፲፯ኛው ኪ/ሜትር ድረስ አብረው ከሮጡ በኋላ አበበ መሪነቱን በመያዝ በተባለው ሰዓት ውስጥ ፳ ኪ/ሜትር ከ፪፻፳፮ ሜትር በመሮጥ ፩፻ ሜትር ያህል ቀድሞ ሲገባ ማሞ ደግሞ ፳ ከዜሮ ፶፮ በመሮጥ ተከትሎ ደርሷል። ፫ኛው ዴጊ ቶርነር ሶን የተባለ የዴንማርክ ተወላጅ ነው።
በአበበ የተቀደመው ፰፻፵፫ ሜትር እርቀት ሲሆን፣ ፬ኛው ምዕራብ ጀርመን ናቸው። የዚህን ርቀት ሪኮርድ ለ፲፩ ዓመት የያዘው የቼኮዝላቫኪያዊያን ተወላጅ የዛቶፔክን እርቀት አበበ በአንድ መቶ ሰባ አራት ማሞ በአራት ሜትር እርቀት እንደሰበሩ ሜጀር ገልፀዋል።
እንዲሁም በዚሁ አገር በተደረገው የ ፰፻ ሜትር ሩጫ ፩ኛ ሄርበርት ሚሲኦላ ምዕራብ ጀርመን ጊዜው ፩ ደቂቃ ከ፶፪ ሰኮንድ ነጥብ ፪
፪ኛ ሠይድ ሙሳ ኢትዮጵያ በሦስት ነጥብ ተቀዳሚነት
፫ኛ ከርት ክርስቲአንሰን ዴንማርክ ፤
፬ኛ ኤስ ኦ ኦቲሰን ስዊድን፤
ሜጀር አኒ ዜግነታቸው ስዊድን ዕድሜያቸው ፶፩ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ፲፮ ዓመት አሁን የሚሠሩት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊነት ሲሆን ለኢትዮጵያ አትሌቶች በአማተር ስም የሰጡት ትህምርታዊ አገልግሎት ከፍ ያለ ለመሆኑ አትሌቶቹ ያገኙት ውጤት ምስክራቸው ለመሆን ይችላል።
ሰለሞን ተሰማ
(ሐምሌ 12 ቀን 1954 ከወጣው አዲስ ዘመን)
መቶ ሐምሳ ሺህ የባህር ዛፍ ችግኝ ተተክሏል
ጐንደር፤ሐምሌ ፴ ቀን ፶፬ ዓ.ም የጐንደር ከተማ ከንቲባ የተከበሩ ደጃዝማች አርአያ ዋሴ ለከተማው ልማትና ለሕዝብ ምቾት ሲሉ በጐንደር አጠገብ በሚገኘው ተራራ ላይ በአዘጋጁት የተክል ሥፍራ፤ክቡር ሌተናል ጄኔራል ነጋ ኃይለሥላሴ የበጌምድርና የስሜን ጠቅላይ ገዥ በተገኙበት የከተማው ሕዝብ የፖሊስና የጦር ሠራዊት ወታደሮች የመንግሥት ሠራተኞች ፤ካህናቶችም ሳይቀሩ በበጎ ፈቃዳቸው በአንድ ኅብረት በመተባበር በዚሁ ቀን አንድ መቶ አምሳ ሺህ የባህር ዛፍ ችግኝ ተተክሎ ውሏል ሲል ወኪላችን ገልጿል።
(ነሐሴ 2 ቀን 19 54 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)
‹‹ባርቆብኝ ገደልኩት››
አበራ በቀለ የተባለ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ ባልደረባ ነሀሴ ፲፮ ቀን ትናንት ከቀኑ ፮ ሰዓት ከ፵፭ ደቂቃ ሲሆን ፤ለገሠ አደራ የተባለ ባልንጀራው እቤቱ መጥቶ ፤ለሽጉጥህ ጥይት ገዛህለት ወይ ብሎ ጠይቆኝ አዎን ገዝቼለታለሁ ብዬ መኝታ ቤቴ ውስጥ ገብተን ሽጉጡንና ጥይቱን ስናይ፤በድንገት ሽጉጡ ባርቆብኝ ገደልኩት ሲል እጁን ለ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ የሰጠ መሆኑን የ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ሻምበል አጥናፉ ወርቅነህ በሰጡት ወሬ አረጋግጠዋል።
(ነሐሴ 17 ቀን 1954 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ከጅብ አፍ ተረፈች
ሰኔ ፳፯ ቀን ፶፬ ዓ.ም. ለ፳፰ አጥቢያ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከተማ ፩ኛ ወታደር ተፈራ ገብሬ ቊጥር 1135 ፪ኛወታደር ብርሃኑ ሽመና ቊጥር 1191 የአውራጃው ፖሊስ አዛዦች ከላይ በተጠቀሰው ሌሊት የፍተሻ ማለት የፀጥታ ሥራቸውን በአውራጃው ውስጥ ሲያከናውኑ እመት በቱሬ አሜቴ የተባለች ሴት ማታ ወደ ውጭ ወጥታ ሳለች ጅብ ይዞአት ስለጮኸች ለዕርዳታው ከላይ የተጠቀሱት ወታደሮች ደርሰው ከተናጣቂው አውሬ አትርፈዋታል። ነገር ግን በሐኪም ስለተረዳች ለሕይወቷ አያሰጋትም።
የአውራጃው አዣንስ
( ጳጉሜ 1 ቀን 1954 ከወጣው አዲስ ዘመን)
17 በጐች ሲነዳ ተያዘ
ወልደ ማርያም ኃይሌ የተባለ ሰው ፪ ራሱን ሆኖ ነሐሴ ፲፮ ቀን ትናንት ከቀኑ ፱ ሰዓት ላይ በእንጦጦ ወረዳ ኪዳነ ምሕረት ቀበሌ ፲፯ በጐች እየነዳ ሲሔድ፤ ኰሎኔል ፋንታ ወልደ ገብርኤል አግኝተውት በጥርጣሬ በጐቹን ከየት እንዳመጣ ቢጠይቁት የእርሱ አለመሆናቸውን ስላረጋገጠ ፤ወልደ ማርያምና ግብረ አበሮቹ፤እንዲሁም ፲፯ ቱ በጐች በ፪ኛ ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ፤ለበዓለ ፍልሰታ በጐች አዘጋጅታችሁ የተሠረቀባችሁ ሰዎች ብትኖሩ ማስረጃችሁን እያቀረባችሁ ከጣቢያው ልትወስዱ ትችላላችሁ በማለት የጣቢያው አዛዥ ባወጡት ማሳሰቢያ ገልጠዋል።
(ነሐሴ 17 ቀን 1954 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014