‹‹ልጆቼ እንደምታዩኝ ዕድሜዬ ገፍቷል። አቅሜም ደካማ ነው ።የዘንድሮ ክረምት ደግሞ እጅግ ኃይለኛ ነው። እንዳለፉት ዓመታት ልብስ መዘፍዘፊያ እየደቀንኩ፤ በታች በበር የሚገባውን ደግሞ በቁም መጥረጊያ በመመለስ ፍፁም ልከላከለው አልችልም› ይህ ድምጽ የተሰማው ከወይዘሮ እልፍነሽ ማዘንጊያ ነው።
ወይዘሮ እልፈነሽ በአረጀ እና በተጎሳቀለ ቤት ውስጥ ለዘመናት ኖረዋል። በበጋ ንፋሱና ጸሃዩ በክረምት ደግሞ ጎርፍና ጻሃዩ ሲያንገላታቸው ዘመናትን ተሻግረዋል።
የቀለም ትምህርት መቅሰም ባለመቻላቸው ዕድሜያቸውን በውል ባያቁትም አፄ ኃይለስላሴ ሲመለሱ ነው ጅባትና ሜጫ ውስጥ የተወለድኩት የሚሉት እኝህ እናት አሁን ላይ መሳለሚያ አካባቢ በቀበሌ ቤት ውስጥ ትዳር ይዘው መኖር ከጀመሩ ከ40 ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውንም ያወሳሉ።
በእነዚህ አመታት ወይዘሮ እልፍነሽ መከራና ጉስቁልና ተፈራርቀውባቸዋል። እንደ ሰው ባማረ ቤት ውስጥ መኖር ቢመኙም በዳሳ ቤት ውስጥ ከመኖር የገላገላቸው አልነበረም። በቤታቸው ጉስቁልና ስለሚሸማቀቁም የቅርብ ዘመድና ወዳጅ እንኳን መጥቶ እንዲጠይቃቸው አይፈቅዱም ። ገመናቸውን ሽሽግ አድገው ከሰው ተከልሎ መኖር ነው ምርጫቸው።
በግል ጫማ ቤት እየሰሩ ሲያስተዳድሯቸው የነበሩት ባለቤታቸው እንደዛሬ አቅማቸው ሳይደክም ቆርቆሮ ከመቀየር ጀምሮ ቤቱን በተለያየ ደረጃ ሲያድሱት መኖራቸውንም ያነሳሉ።
አሁን ላይ እሳቸውን ጨምሮ ባለቤታቸውንና አንዷ በሽተኛ ልጃቸው የሚተዳደሩበት ምንም ገቢ የላቸውም።ስለዚህም ቤቱ እላያቸው ላይ ሲፈርስ ከማየት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።
ሆኖም መቆየት ደጉ ዛሬ ነገሮች ተለውጠዋል። በወይሮ እልፍነሽ ደጃፍ ጸሃይ መውጣት ጀምራለች። መንግስት በየአካባቢው ያስጀመረው የበጎ ፍቃድ ስራ ችግራቸውን ገፎላቸዋል። ለዘመናት ያዘመመ ጎጇቸው ቀና ብሎ ግርማ ሞገስ ተላብሷል። በማራኪ ሁኔታ ታድሷል። በወይዘሮ እልፍነሽ ፊትም ላይ ደስታና ተስፋ ይነበባል።
ቤታቸው አሁን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰማሩ ወጣቶችና በአካባቢው ሕብረተሰብ ትብብር ተሰርቶላቸዋል።
ሌላዋ የዚሁ መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ነዋሪ እናት ወይዘሮ ጀሚላ አሽረቃ ናቸው። ቤቱ በላዬ ላይ ሊደነባ(ሊፈርስ) ትንሽ ነበር የቀረው የሚሉት እኝህ እናት ባለፉት በርካታ ክረምቶች ከላይ የሚወርደውን ዝናብ ማስታጠቢያ በመደቀን ለመከላከል ብዙ ሌሊቶችን ቆመው ማሳላፋቸውን ይናገራሉ።
የዘንድሮ ክረምት ደግሞ እጅግ ከባድ ነው።በመደቀን ብቻ የሚከላከሉት አልሆነም። እንኳን በውድ ዋጋ ቆርቆሮ፤ እንጨትና ምስማር ገዝቶ ማደስ ቀርቶ ከነልጆቻቸው የዕለት ጉርስ የላቸውም። ሲደግፏቸው የነበሩትን ባለቤታቸውን በሞት ከተነጠቁ ዓመታት ተቆጥረዋል።
የሃምሌ ወር ጓዙን ሰብስቦ እያስገመገመ ሲመጣ ወይዘሮ ጀሚላ እንዴት እሆን ይሆን ብለው ሃሳብ ገባቸው። ክረምቱ መግቢያ አካባቢ እርጥባን ሰብስበው ላስቲክ ሸራ ቢያስለብሱትም ፈጽሞ ሊመክተው አልቻለም። የሰኔውም ሆነ የሐምሌው ዝናብ ላስቲክ ሸራውን ብጥስጥሱን አወጣው።የወይዘሮ ጀሚላ ገመና ሊጋለጥ ሆነ። በሃምሌ ጨለማ ከነስምንት ልጆቻቸው የጎዳና ሲሳይ መሆናቸው አሳሰባቸው።
ሆኖም ሳይደግስ አይጣላም እንደሚባለው አለሁልሽ የሚሏቸው ወገኖች ደረሱላቸው። የበጎ ፍቃድ የሚሰጡ ወጣቶች እንባቸውን አበሱላቸው። ከነስምንት ልጆቻቸው በላያቸው ላይ ሊፈርስ ያዘመመውን ቤት ደርሰው አቀኑት። አቧራውን አራግፈው በብሎኬት አደሱት። የዘመመውም ህይወት ቀና አለ። በወይዘሮ ጀሚላ ቤት ደስታ ነገሰ።
ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ አይሻ አወል ናቸው። አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩ 16 ዓመታትን አስቆጥረዋል።የስድስት ልጆች እናት ናቸው። ስድስተኛውንና የመጨረሻ ልጃቸውን የወለዱት ክረምቱ መግቢያ አካባቢ ነበር። ቤቱ ቀድሞ በመፍረሱ የአካባቢው ሰው ሸራ ጋርዶላቸው ነው የአራስነት ጊዚያቸውን ያሳለፉት። ሆኖም ሸራውን የዘንድሮ ክረምት ዝናብና ዶፍ አሸነፈውና በላያቸው ላይ ሊፈረስ ተቃረበ። ከእርሳቸው ይልቅ ያሳሰባቸው የአራስ ልጃቸው ጉዳይ ነበር። ገና በጨቅላ ዕድሜው በብርድ ተጎድቶ እንዳይሞት ወይም ቀሪውን ህይወቱን በበሽታ እንዳያሳልፍ ሰጉ። የክረምቱን መግባት በስጋት ተመለከቱት። ሆኖም ኢትዮጵያ የደጋጎች ሀገር ነችና ስቃይና መከራቸውን ያዩ አንዲት በጎ አድራጊ ወይዘሮ አይሻን ከስጋት ገላገለቻቸው። በጥሩ ሁኔታ ቤታቸውን አድሰው አስረከቧቸው።
ወይዘሮ አይሻም ለተደረገላቸው በጎ ስራም የሚከፍሉት ነገር ባይኖራቸውም ‹‹ አላህ በድራቸውን ይክፈልልኝ ፤እኔማ ምን አቅም አለኝ›› በሚል በጎ ሰሪዋን አመስግነዋል።
የክረምት በጎ ፍቃድ ስራ በርካታ ሴቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው። በበርካታ ውስብስብ ችግሮችና ድህነት ውስጥ ለሚኖሩት ሴቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እፎይታ እየሰጣቸው ነው።
ወይዘሮ ፋንታዬ አትርፉ በመሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ሰላም ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው።እንደነገሩን የእሳቸውን ቤት ጨምሮ በዚህ አካባቢ የነበሩት የቀበሌ ቤቶች በሙሉ በእርጅና ምክንያት ወድቀው የነበሩ ናቸው። አብዛኖቹ ቤቶች የቀበሌ ቤቶች በመሆናቸው በጣም ያረጁና የተጎሳቀሉ ናቸው። የቤቶቹ ባለቤቶችም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮን የሚገፉ በመሆናቸው ቤት ማሳደስ ቀርቶ የዕለት ጉርሳቸውን ሸፍኖ ማደር እንኳን አቅም የላቸውም።
ብዙዎቹም በአካባቢው የሚገኙ ቤቶች እንደሳቸው ቤት ሁሉ አራት በአራት የሆኑ ጠባብ ቤቶች ናቸው። መተኛውም፤ማብስያውም ፤መብያውም ፤ማጠቢያውም ያችው አንዲት ክፍል ነች። ወይዘሮ ፋንታዩ የወታደራዊው ደርግ አስተዳደር መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣና የግለሰብ ቤት ተከራዮችን ባላችሁበት እርጉ የሚል አዋጅ ሲያውጅ በወሰነው የኪራይ ታሪፍ መሰረት ላለፉት አርባ አመታት ለቀበሌ ሲከፍሉ ኖረዋል። ሆኖም ለረጅም ጊዜ በዚህ ሁኔታ ቢኖሩም ቤታቸው በላያቸው ላይ እስኪወድቅ ድረስ ያያቸው አንድም አካል አልነበረም።
እሳቸውም ቤታቸውን እንዳያድሱ ከእርሳቸውንና ከልጆቻቸው የሚተርፍ ሳንቲም አልነበራቸውም። ይደግፏቸው የነበሩት ባለቤታቸው ከሞቱባቸው በኋላ በተለይ ከልጆቻቸውና ከአካባቢው ሰው ተደብቀው ልብስ ከማጠብና አሻሮ ከመቁላት ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየሰሩ የዕለት ጉርሳቸውን ሲያሟሉ ኖረዋል። ቤታቸውንም ቆርቆሮ እየቀያየሩ ሲያድሱና ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል። ይሄን ያየችው ልጃቸው ትምህርቷን ከሰባተኛ ክፍል አቋርጣ ወደ ቤሩት በመሄድ ጥሪት ቋጥራ መጥታ ቤታቸውን በተለየ ሁኔታ ሰራችላቸው።
ሆኖ የኔ ቤት ተሰርቷል ብለው ዝም አላሉም። በየዓመቱ በክረምት በአካባቢው ባሉ ቤቶች ላይ የሚደርሰውን ችግር ከማንም በበለጠ እሳቸው ስለሚያውቁትና ስለደረሰባቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለነዚህ ቤቶች እንዲታደሱ ጥረት ያደርጋሉ። ጥረታቸው ወጣት ልጆቻቸው በቤቶቹ ግንባታ እንዲሳተፉ ከመገፋፋት ይጀምራል። የእሳቸውም ቤት ምንም ያህል አንዲት ክፍልና ጠባብ ብትሆንም ጎረቤቶቻቸውን ቤታቸው ተሰርቶ እስኪያልቅላቸው ድረስ እሳቸው ጋር እንዲያርፉ ያደርጋሉ።
ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች የኢኮኖሚ አቅም ከእጅ አይሻል ዶማ እንዲሉት ዓይነት በመሆኑ ከዚህ በዘለለ የሚደጋገፉበት ሁኔታ የለም።አሁን ላይ እሳቸው የሚተዳደሩት በእንጀራ ንግድ ነው።የእንጀራ ንግድ ደግሞ 100 ኪሎ ጤፍ ስድስት ሺህ ብር እየተገዛ ቢሰራም አዋጭ አይደለም። ቢያዋጣ በሚል ሩዝ ጨምረው ነው የሚጋግሩት። እንዲህ ሆኖ ገበያ ካለ በቀን ስድሳ ከሌለ 30 እንጀራ ቢጋግሩም የመብራት ፍጆታው ከፍተኛ በመሆኑና በየወሩ እስከ ሦስት ሺህ ብር ስለሚከፍሉ ትርፉን ይበላዋል። ሆኖም በሰፈራቸው ባዩት በጎ ስራ ደስተኛ ስለሆኑ ችግርን ሁሉ በትብብር እንደሚያልፉት እርግጠኛ ናቸው።
ወይዘሮ ዛፌነሽ አዛገ ይባላሉ። ወይዘሮዋ በበጎ ፈቃድ ሥራ በማስተባበሩም ሆነ ራሳቸው በተግባሩ በመሳተፉ አብዝተው ይታወቃሉ ። በቀያቸው ያሉትንና በእርጅና ምክንያት ያዘመሙ የሦስት አቅመ ዳካማ ነዋሪዎች ቤት እንዲሰራላቸው ታች ላይ ሲሉ ነው የከረሙት ። እኛ ወደ እነ ወይዘሮ ዛፌነሽ ጊቢ ስንሄድ ሩጫቸው ተሳክቶላቸውም በእሳቸው አስተባባሪነት የሶስቱም አቅመ ደካሞች ቤቶች ሲገነቡ ነው የደረስነው። ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ፈርሰው ፤የጭቃ ግድግዳቸው ተደርምሶ በብሎኬት ተቀይሯል። ቤቶቹ ከቆርቆሮ መዝጊያ ወደ ብረት መዝጊያ ተለውጠዋል።
ወይዘሮ ዛፌነሽ በመጠኑም ቢሆን ስለ ሦስቱ ነዋሪዎች ስላሉበትና ስለነበሩበት ሁኔታ አጫውተውን ነበር ።የአንደኛው ቤት ባለቤት ወይዘሮ እልፍነሽ ረጅም ዕድሜ ያላቸው አቅመ ደካማ ናቸው። የአስምም ታማሚ በመሆናቸው ሽታና እርጥበት በሽታቸውን ይቀሰቅስባቸዋል።
ሆኖም ቤታቸው በእርጅና ምክንያት ለረጅም ጊዜ በመውደቁ ብዙ ክረምቶችን በዚህ ሁኔታ ለማሳለፍ ተገድደው ቆይተዋል። ዘንድሮ ግን ሙሉ በሙሉ በመፍረሱ እሳቸው የአካባቢውን ሕብረተሰብ በማስተባበር በብሎኬት እንዲገነባላቸው አድርገዋል።
የአይሻና የሦስቱ ወላጅ አልባ ልጆች መኖርያ ቤትም እንዲሁ ከእርጅና ብዛት ወድቆ ነበር። በተለይ በሶስቱ ወላጅ አልባ ልጆች መኖርያ ቤት ውስጥ ጎርፍ ይገባ ነበር። ጎርፉ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ የተቀላቀለበት በመሆኑ ለጤና በእጅጉ አደገኛ በመሆኑ አስተባብረው ሊያሰሩላቸው በቅተዋል።መፀዳጃ ቤቱ አርማታ ተደርጎ በስነስርዓት ዳግም የልጆቹ ችግር በማይሆንበት ሁኔታ እየተገነባ ይገኛል።
ወይዘሮ ሕይወት በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋዊያን ማስተባበርያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር ናቸው። ቢሮው ከተሰጠው ተግባር አንዱ እንዲህ እንደ መሳለሚያ እህል በረንዳ የዘንድሮው የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስምሪት መርሐ ግብር የነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም የአረጋዊያን እናቶችንና የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ በመሥራት ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጉን ይናገራሉ።
አሁን ላይ ከክረምት በጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በተጨማሪ የሕብረተሰቡ በግልም በጋራም የመረዳዳት ባህል እየዳበረ መምጣቱን ያስታወሱት ወይዘሮ ህይወት በዚህም ስር የሰደደው የድህነታችንና ኋላ ቀርነታችን አሻራ የሆኑ ያረጁ የአቅመ ደካማና የአረጋዊያን ቤቶችን በማደሱ ረገድ ሕብረተሰቡ በግልና በጋራ ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አድነው አበራ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደ አገር እየጎለበተ መምጣቱ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ችግር ለመቅረፍ ዓይነተኛ መሣርያ እየሆነ መምጣቱን አውስተዋል። በተለይ በዚህ በኩል ያለው የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድርሻ ያረጁ ቤቶችን ከማደስና እንደገና ከመገንባት ባሻገር በችግኝ ተከላው፤ በአካባቢ ጽዳቱ፣ በጓሮ አትክልቱ በጓሮ አትክልቱና በተለያዩ የልማት መስኮች ጭምር ውጤት መገኘቱን ይናገራሉ።
የዘንድሮው የክረምት ወራት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስምሪት መርሐ ግብር አረንጓዴ አሻራን ለማኖር ከሚያስችለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በተጓዳኝ 18 ሚሊዮን ወጣቶችን በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ላይ በማሰማራት የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየቀረፉ መገኘታቸውንም አቶ አድነው አንስተዋል።
እኛም ዜጎች ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብዓዊ አመለካከት ተነስተው እንደ አገር ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ እናቶች እየተደረጉ ያሉት ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥሉ እያልን ጽሁፋችንን በዚሁ እንቋጫለን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 /2014