ስድስተኛው የጉማ ሽልማት ባሳለፍነው ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ተከናውኗል። ባለሰማያዊ ምንጣፉ፣ በኢትዮ ፊልም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የፊልም ሽልማት ዝግጅት፤ የፊልም ባለሙያዎች የሚገናኙበትና ደም ቀው የሚታዩበት መድረክም ነው።
በሽልማት ዝግጅቱ አዳዲስ ብቅ ያሉ የሥነ- ራዕይ (የፊልም) ባለሙያዎች ይበረታታሉ፣ ነባሮቹም ልምዳቸውን ያካፍሉበታል፤ አቅማ ቸውንም ያሳዩበታል። ከውድድሩ ማግስት፤ አሸናፊዎች ብሎም እጩዎች ይፋ ከሆኑ በኋላ ጥሩ ተብለው የተሸለሙ ፊልሞች ከያሉበት ዳግም ለእይታ ይናፈቃሉ፣ ምርጥ የተባሉ ተዋንያን ለበለጡና ለተሻሉ ሥራዎች ይተጋሉ።
ይህን እንደ አንዱ የፊልም ሽልማት ጥቅም ልናየው እንችላለን እንጂ የፊልም ሽልማቶች ለፊልሙ ዘርፍ እድገት ምን አበርክተዋል የሚለው ጠለቅ ያለ ዳሰሳ የሚፈልግ ሳይሆን አይቀርም። ጉማ የፊልም ሽልማትም በፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ መሠረቱ ተጥሎና በተለያዩ የጥበብ ተባባሪ የሆኑ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያገኘ ስድስት ዓመታትን ዘልቋል።
ጉዞን አለማቆም የመጀመሪያው ስኬት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉና፤ ጉማ እየደመቀ መቀጠሉ እንደ አንድ ስኬት የሚያዝ ነው። እንደምን ቢባል የተለያዩ ክዋኔዎች ተጀምረው እየቀሩ፣ ወረት እየሆኑና በሳምንታቸው እየተረሱ እያየን ብሎም አንድ ጭብጨባ እያዳለጣቸው የሚወድቁ ብዙዎችን እየተመለከትን በመሆኑ ነው። እናም የጉማ አዘጋጆች «ጉማ ሁሌም ይቀጥላል!» ብለው መሪ ሃሳባቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ፤ እኛም ይበል ይቀጥል እንላለን።
ወዲህ ደግሞ መለስ ብለን በዛሬው የኪነጥበብ አምድ የጉማ ፊልም ሽልማትን ጉዞ እንዲሁም የዘንድሮውን የሽልማት ስነ ሥርዓት እንዳስሳለን። እንደወትሮው በደሌ ስፔሻል በሙሉ ስፖንሰርነት በደገፈው በዘንድሮው የጉማ ሽልማት ላይ፤ በቁጥር 61 የሚደርሱ ፊልሞች ተመዝግበው 25 የሚሆኑት ለውድድር ቀርበዋል። ፊልሞቹም በኢዮሃ ሲኒማ ለዳኞች እይታ ቀርበዋል፤ ታይተውም ውሳኔ አግኝተዋል።
ፊልምና የፊልም ሽልማት
የፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ ሥነ- ራዕይ ይለዋል፤ ፊልምን። የፊልም ዘርፍ የጥበባትን ቡድን ከተቀላቀለ አንድ መቶ ሃምሳ ዓመት እንኳ አልሞላውም። ይህ ማለት ከሥነ ጽሑፍና መሰል የጥበብ ዘርፎች ጋር ሲወዳደር እድሜው እጅግ ለጋ የሚባል ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ግብዓቶቹ እድሜ ጠገብ የሆኑ ጥበባት በመሆናቸውና ወሳኙ የካሜራና ሲኒማቶግራፊ ጥበብ ደግሞ በየጊዜው እየተሻሻለና እያደገ ስለመጣ ከሁሉም በተሻለ በአጭር ጊዜ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ ዘርፍ ሆኗል። የፊልም ሽልማት መርሃ ግብራትም ለዚህ ነው ከሌሎች ጥበባዊ ዘርፎች በተሻለ፤ ከሙዚቃም በደመቀ ሁኔታ ጎልተው የሚሰማሙት። እንደሚታወቀውም በዓ ለም አቀፍ ደረጃ በመዝናኛው ዘርፍ ላይ የሚሠሩትም ሆነ የተቀሩት መገናኛ ለእነዚህ ሽልማቶች ትኩረት ይሰጣሉ። ከነ ኦስካር መንደር የዘርና የቆዳ ቀለም ጉዳይ፣ የፆታ ነገርና የታሪኮች ዓይነት ገና ከውድድሩ ቀደም ብሎ መነጋገሪያ ሆኖ ሲሰነብት ታዝበናል።
ባለሙያዎችም እንደ ጥበብ አፍቃሪ እርካታን የሚሰጣቸውን ሥራ ከመሥራት በተጓዳኝ እነዚህን ውድድሮች ታሳቢ በማድረግ በየጊዜው በሥራዎቻቸው ላይ ለውጦችን ያሳያሉ። ያም ለውጥ ማጣቀሻ (Bench mark) ሆኖ ይቀመጥና፤ ሌሎች የፊልም ባለሙያዎች ደግሞ ከዛ በበለጠና በተለየ መንገድ ለመሥራት አዳዲስ መንገዶችን ቀይሰው በሥራዎቻቸው ያስቃኛሉ።
ይህ ቅብብል ለሂደቱ ደረጃ ሆኖለት፤ ባለሙያዎቹን ከዓመት ዓመት ከፍ እያደረገ የፊልምንም ጥበብ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ማድረስ ችሏል። እንደተባለው ደግሞ የፊልም ሽልማቶች በዚህ ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። አሁንም ሻገር ብለን በጥበቡ አንጋፋ ከሆኑት የፊልም መንደሮች ስንቃኝ፤ እንደ ኦስካር እና ባፍታ ያሉ ሽልማቶች ይነሳሉ። በእነዛ ውድድሮች ላይ «በውጭ አገር ቋንቋ የተሠራ» ዘርፍ ላይ ከስንት አንዴ ከመሳተፍ ውጭ ለአገራችን የፊልም ዘርፍም እንዲህ ያለ ዕድል ቢፈጠር መመኘታችን አልቀረም።
ነገሩን የፊልም ወዳጆች የሆኑ ብርቱ ባለሙያዎች አጢነው ዝም አላሉም፤ የፊልም ሽልማቶችን በአገራችን ጀምረዋል። ለዚህ ደግሞ ጉማ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው። ጉማ የፊልም ሽልማት ለብቻው እንደ ሽልማት የቀረበ ሲሆን፤ በፊልም ፌስቲቫል መልክ ተዘጋጅተው መዝጊያቸውን ሽልማት ያደረጉ ድርጅቶችም ተፈጥረዋል። ለዚህ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፌልም ፌስቲቫል እንዲሁም የአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫልን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
ጉማ ሲጀመር
ጉማ የፊልም ሽልማት መጠሪያውን ያገኘው ከአርባ ሦስት ዓመታት ቀደም ብሎ በሚሼል ፓፓታኪስ ከተሰራው ‹ጉማ› የተሰኘ ፊልም ነው። ጉማ ሽልማት የተዘነጉትን በማስታወስ፣ ብዙ የሠሩ ግን ያልታወቁትን በማጉላት፣ ትኩረት ሳይሰጣቸው የቆየ ከፊልም ጋር የተያያዙ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ለማድረግ እንዲያስችል በመወዳደሪያ ዘርፎች ውስጥ አዳዲስ ዘርፎችን በማካተት ቀላል የማይባል ሥራ ሲሠራ የቆየ የፊልም ሽልማት ነው።
ጉማ የፊልም ሽልማት አስቀድሞም ሙያው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን እውቅና ለመስጠት ታስቦ እንደተዘጋጀ ነው በተለያየ ጊዜ ሲዘገብ የነበረው። « ታድያ የፊልም ዘርፉን ምን ጠቀመው ? » የተባለ እንደሆነ አስቀድሞ እንዳልነው መጠነኛ የዳሰሳ ጥናት ሳይጠይቅ አይቀርም። ይሁንና በግልጽ የሚታዩና ሽልማቶች ለፊልሙ ዘርፍ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አለ። ይህንን የውድድር መንፈስ መፍጠርና ባለሙያዎች በሥራቸው ለእያንዳንዱ ነገር እንዲጨነቁ የሚያደርጋቸው መሆኑ ነው።
ከሦስት ዓመታት በፊት በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ኪነጥበብ አምድ ላይ «“ጉማ የፊልም ሽልማት” ለሲኒማው እድገት ምን አበረከተ?» በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ዘገባ ነበር። በዚህም ስለ መጀመሪያው የጉማ ፊልም ሽልማት ከሰፈረው ላስታውስ። እንዲህ ነው፤ በመጀመሪያው የጉማ ሽልማት ዝግጅት ላይ ለውድድር የቀረቡት በ2004 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የቀረቡ ፊልሞች ናቸው።
በዚህ የመጀመሪያው ውድድር 33 ፊልሞች ተመዝግበው፤ ከ87 በላይ በሆኑ ዳኞች ተሳትፈው ለውድድር ከቀረቡት 33 ፊልሞች መካከል ያለፉት 23ቱ ነበሩ። በዚህ ጊዜ የውድድር ዘርፎቹም በቁጥር 17 ይጠጋሉ። ከእነዚህ ዘርፎች በተጨማሪ ውድድር የሌለው «የሕይወት ዘመን ተሸላሚ» የተሰኘ ዘርፍ ሲሆን፤ በልዩ ሁኔታና ምልከታ ነው ተሸላሚውም የሚመረጠው።
ታድያ እንዲህ ብሎ ያለ ስፖንሰርና ድጋፍ በአዘጋጁ ኢትዮ ፊልም ጥረት ብቻ አሃዱ ብሎ ጀመረ። ከዚህ ጊዜም ጀምሮ እያለ እያለ ቀጥለው በተካሄዱት የጉማ ሽልማቶች ላይ የተሳታፊ ፊልሞች ተሳትፎ ከፍ እያለ፤ መወዳደሪያ ዘርፎቹ በዓይነትና በቁጥር ብሎም በጥራት እየጨመሩ መጥተዋል። ሽልማት ሆኖ የሚቀርበው የጉማ ዋንጫም በቅርጽ ይዘቱ እየተቀየረና በባለሙያዎች እይታ እየተሻሻለ አሁን ያለበትን ቅርጽ ይዟል።
የዘንድሮው ጉማ
ስደስተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ባሳለፍነው ማክሰኞ መጋቢት 17 ቀን 2011ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ሲካሄድ በአዳራሹ የፊልም ሙያ እንቁና ፈርጦች ሁሉ ተገኝተው ነበር። የሽልማት መርሃ ግብሩ ከ17 ቀናት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል። የፊልም ባለሙያና ታዋቂ ሰዎች ባሉበት የካሜራ ባለሙያና ፎቶ አይታጡምና፤ ዝግጅቱ የጀመረው ማምሻውን አንድ ሰዓት ላይ ነው።
የጉማ ሽልማት በአያሌው የሚመሰገንበት አንድ ነገር አለ። ይህም ብዙ ሥራ የሠሩ ነገር ግን ራሳቸውን በሥራቸው ልክ ያላስተዋወቁ፤ የተዘነጉ ሰዎችን የማስታወሱ ነገር ሲሆን፤ በዘንድሮውም ሽልማት ይኸው ጉዳይ በሰፊው የታየበት መድረክ ነበር። ምንአልባትም ሸላሚ ሆነው በመድረኩ ላይ የተገኙ ባለሙያዎች ራሳቸው ተሸላሚዎችና አንደኞች መሆናቸው ለሽልማቱ ካባና ሞገስ ሳይሆነው አይቀርም።
እዚህ ላይ ልያዛችሁና በመድረኩ እጩዎችን በመግለጽና አሸናፊዎቹን ይፋ አድረጎ በመሸለም የተሳተፉትን እነዚህን ባለሙያዎች ልጥቀስ። ከባለሙያዎቹ አብዛኞቹ ያልተዘመረላቸው የሚባሉ ናቸው።
ከእነዚህም መካከል አንደኛው ብርሃኑ ሽብሩ ነው። ብርሃኑ በፊልም ሙያ ጥበብና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከአገር ውስጥ አልፎ ባህር ማዶ ትምህርቶችንና ልምዶችን የቀሰመና የሚያውቀውን ለጠየቀው ሁሉ ከማካፈል የማይቦዝን ባለሙያ ነው። እጅግ በርካታ በሆኑ ፊልሞች ላይ በሥራ መሪነት ወይም ዳይሬክተርነት ሠርቷል።
እንደዚሁ ሁሉ በማስተር ቪዲዮግራፊ በአሰልጣኝነት ለ14 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ወንድሙ ካሳዬ፣ በማስታወቂያ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በካሜራ ባለሙያነት ያገለገሉና «ባለንስር ዓይኑ» የሚባሉት የካሜራ ባለሙያ አቶ እንዳልክ አያሌው፣ በሙዚቃ ድርሰት አንቱታን ያተረፉትና በክቡር ዘበኛ በድምፃዊነት፣ ተወዛዋዥነትና አሰልጣኝነት ለ34 ዓመታት በማገልገል ብሎም በድምሩ በሙዚቃው 62 ዓመታትን ያሳለፉት አየለ ማሞ እጩዎችን ለማሳወቅና አሸናፊውን ለመሸለም ከብሔራዊ ቴአትሩ መድረክ ተሰይመዋል።
እነርሱም ብቻ አይደሉምና ልቀጥል፤ በተለያዩ የዓለማችን አገራት የሥነ ስዕል ጥበብ የደረሰበትን ደረጃ ቀስመው ወደሥራ የገቡትና በፊልም ኮርፖሬሽን በፖስተር ዲዛይነርነት ለዓመታት ያገለገሉ ሰዓሊ ዜና አስፋው፣ በረጅም ልብወለድ የመጀመሪያዋ ሴት ደራሲትና በርካታ መጻሕፍትን ለአንባብያን ያደረሰችው ፀሐይ መላኩ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በፕሮግራም ፕሮዳክሽን ክፍል፣ ፊልም ማንሳትና ላቦራቶሪ ቅንብር የሠሩ ብሎም በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችን በካሜራቸው በምስል ያስቀሩ «ተንቀሳቃሽ የምስል ላይብረሪ» የተባለላቸው የካሜራ ባለሙያ አቶ ኤልያስ ብሩም ነበሩ።
ከሃያ በላይ ቴአትሮች ላይ የተወነውና በሬድዮና ቴሌቭዥን ድራማና ትረካዎችም የተሳተፈ፤ «የእግዜር ጣት» የተሰኘውን ቴአትር የጻፈው ደረጀ ደመቀ፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ ለ28 ዓመታት በትወና እና በውዝዋዜ ያገለገለችው መርከብ ባልሔር፣ ላለፉት 38 ዓመታት በኪነጥበብ ዘርፉ ያገለገለ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ ጋዜጠኛ ተፈሪ ዓለሙ፣ ከ63 ዓመት በፊት ዘርፉን ተቀላቅላ በትወና፣ በድምፃዊነትና በተወዛዋዥነት ያገለገለችው የሺ ተክለወልድ፣ ተዋናይና የቴአትር ባለሙያ ተክሌ ደስታም በተመሳሳይ እለቱን ሞገስ ሆነውታል።
የሲኒማቶግራፊ ባለሙያና በቶም ቪድዮና ፎቶ ግራፍ ማሰልጠኛ ለዓመታት በማገልገል ብዙ ተማሪዎችን ያሰለጠነው ኢዮብ ስብሐቱ፣ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የሙዚቃ ዘርፍ ብቅ ካሉ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መካከል የሆነውና በርካታ ሙዚቃዎች ላይ አሻራው የሚገኘው አቤል ጳውሎስ፣ አምስት አልበሞችን ለአድማጭ ያደረሰችና በኮራ እንዲሁም በአፍሪማ የሙዚቃ ውድድሮች ተሳትፋ የአገራችንን ስም ያስጠራችው ድምፃዊት ጸደንያ ገብረማርቆስ አይዘነጉም።
በርካታ ፊልሞችን በድርሰትና በማዘጋጀት በጉማ ሽልማትም ብዙ ዋንጫዎችን በመቀበል ክብረ ወሰኑን የያዘችው ቅድስት ይልማ፣ የኢዮሃ አዲስ ኤግዚቢሽንና ኢዮሃ ሲኒማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አዩ ዓለሙ፣ በትወና እና ሞዴሊንግ ሥራ፤ በፊልም ዘርፍም በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበችው መቅደስ ጸጋዬ። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ባለሙያዎች በስድስተኛው የጉማ የፊልም ሽልማት ላይ ሸላሚ ሆነው የተገኙ ናቸው።
ከሽልማቱና ከዋንጫው እኩል የሸላሚዎቹ ማንነት ለአሸናፊዎቹም ሆነ ለሽልማቱ ክብር አይጨምርም ትላላችሁ? አንጋፎችን በማስታወስና በአዲሱ ትውልድ እንዲታወቁ በማድረግ በኩል ጉማ ሽልማት ድርሻውን እየተወጣ እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላልና ይህ ይቀጥል የሚባል ነጥብ ይሆናል።
ወዲህ ደግሞ ከሸላሚዎቹ ወደ አሸናፊ ዎቹ እንመለስ፤ የስድስተኛው የጉማ ሽል ማት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ናቸው። በእርግጥም ፕሮፌሰር ኃይሌ ከዚህም በላይ የሚገባቸው ባለሙያና ሙያቸውን አፍቃሪ ናቸው። የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳውም ባህርማዶ ባሉ እውቅና አንጋፋ ትምህርት ቤቶች በፊልም ጥበብ ሙያ ተምረዋል። በአሁኑ ጊዜም በሀዋርድ ጠቅላይ መካነ ጥናት የፊልም ጥበብ ፕሮፌሰር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ፕሮፌሰር ኃይሌን የፊልም ተመልካች ጤዛ በተሰኘው ሥራቸው ያስታውሳቸዋል፤ አይረሳቸውም። ከዛም ባለፈ በጥቂቱ እንጥቀስ ከተባለ «ዓድዋ»፣ «ሳንኮፋ፣ ከክረምት በኋላ»፣ «አመድና ፍሞች»፣ «ቡሽ ማማ» እና ሌሎች በርካታ ልብወለዳዊ ፊልሞችና ዘጋቢ ፊልሞችን ለእይታ አቅርበዋል። ከዚህ ባሻገር እጅግ በርካታ ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለም አገራትና የፊልም ጥበብ ዘርፍ ሸላሚዎች ተረክበዋል። በተለይም «ጤዛ» በተሰኘው ፊልም በግሪክ ታሳሎንኪ፣ በፈረንሳይ አሚየንስ፣ በቱኒዝያ ካርቴጅ፣ በሮተርዳም፣ በቡርኪናፋሶ፣ በቶሮንቶ የሥነ ርዕይ ትርዒቶች ላይ የተቀበሏቸው ሽልማቶች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
በጉማ ሽልማት ላይ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፤ ምንም እንኳ ሽልማቱን ለመቀበል በአገር ውስጥም ሆነ በአዳራሹ መገኘት ባይችሉም፤ የኪነጥበብ ባለሙያው ሙያውን እንዲወድና ሕዝቡን እንዲያከብር መልዕክታቸው ለታዳሚው ደርሷል። ከዚህ ባሻገር በነበሩት አሥራ ስድስት ዘርፎችና ሁለት ልዩ ሽልማቶች የፊልም ባለሙያዎች የድካማቸውን ፍሬ አሳይተዋል፤ ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናን ከጉማ ሽልማት ተቀበለዋል። በዚህ መሰረት «በእናት መንገድ» የተሰኘው የበኃይሉ ዋሴ /ዋጄ/ ፊልም ሦስት ሽልማት በመውሰድ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ «ሲመት»፣ «ወደ ኋላ» እንዲሁም «ሚስቴን ዳርኳት» እያንዳ ንዳቸው በሁለት ዘርፎች ሽልማቶችን ወስደ ዋል። በዘንድሮ የጉማ ፊልም ሽልማት ከመደበ ኛዎቹ ዘርፎች በተጓዳኝ በአጭር የተማሪዎች ፊልም አማኑኤል ዘሪሁን (ሙኑመ እረከበ) እንዲሁም በምርጥ አጭር ፊልም የአብስራ ዶጮ (ሌላው ጀግና) ተሸላሚ ሆነዋል። በተቀሩት ዘርፎች አሸናፊዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤
በምርጥ ድምጽ አናኒያ ኃይሉ (ድንግሉ)፤
በምርጥ የፊልም ሙዚቃ ድምፃዊ መሳይ ተፈራ፣ ዜማ አህመድ ተሾመ /ዲንቢ/ እና ግጥም ወንደሰን ይሁብ (ሚስቴን ዳርኳት)፤ በምርጥ የፊልም ስኮር ሱልጣን ኑሪ (በሲመት)፤ በምርጥ የፊልም ሜክአፕ መሰረት መኮንን (በሲመት)፤ በምርጥ የፊልም ስክሪፕት በኃይሉ ዋሴ (ዋጄ) በእናት መንገድ፤ በምርጥ የፊልም ቅንብር (editing) ልኡል አባዲ (ወደ ኋላ)፤ በምርጥ ፊልም ቀራፂ (Cinematography) እውነት አሳሳኸኝ (ውሃ እና ወርቅ)፤ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ሴት ተዋናይት ሕፃን ማክቤል (ሞኙ ያራዳ ልጅ ቁጥር 4)፤ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ወንድ ተዋናይ በኃይሉ እንግዳ (ጃሎ)፤ በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይት ዘነቡ ገሠሠ (ትህትና)፤ በምርጥ ረዳት ተዋናይ ካሳሁን ፍስሀ ማንዴላ (ወደ ኋላ)፣ በምርጥ ሴት መሪ ተዋናይት ሶኒያ ኖዌል (አንድ እኩል)፤ በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ ኤርሚያስ ታደስ (አላበድኩም)፤ በደሌ ስፔሻል የተመልካቾች ምርጫ (ሚስቴን ዳርኳት)፤ ምርጥ የሥራ መሪ (ዳይሬክተር) በኃይሉ ዋሴ (በእናት መንገድ)፣ የዓመቱ ምርጥ ፊልም (በእናት መንገድ) አሸናፊ ሆነዋል።
ጉማ ይቀጥል
የጉማ ፊልም ሽልማት በበጎ ጎን እንደ ሚነሱ ብዙ መልካም ነገሮቹ ሁሉ ቢስተካከሉ የሚባሉ ነገሮችንም በቀላሉ መታዘብ እንችላለን። ከዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው የሰዓት አጠቃቀም ጉዳይ ነው። ምንም እንኳ ይህ እንደ አገር ሁላችንም የምንወቀስበት ችግር ቢሆንም እንዲህ ያሉ ትልቅ የሚባሉ ክዋኔዎች ግን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መጠበቃችንና መጠየቃችን አይቀርም። በስፍራው የባከነ ሰዓት አለ ለማለት ባልደፍርም፤ የመክፈቻና የመርሃ ግብሩ መጀመሪያ ሰዓት ቀደም ቢል ግን ነገሩ ቀላል ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። 6ኛው የጉማ ሽልማት እንግዶቹን ከ11፡00 ጀምሮ ተቀብሎ ልክ 12፡00 ሰዓት ላይ በአጫዋች ሙዚቃዎች አቆይቶ ዋናው መርሃ ግብር የጀመረው ምሽት 1፡00 ሰዓት ላይ ነው። ሰዓቱ ቀደም ቢል ምናልባት ፎቶ የሚነሱት ባለሙያዎች ሰፊ ጊዜ ያገኛሉ፤ በዝግጅቱ ማብቂያም ላይ አዳራሹን ለቅቆ ለሚወጣ ታዳሚ ነገሩ አስቸጋሪ አይሆንበትምና ይህ ቢስተካከል እንላለን።
ተዋናይና የፊልም ባለሙያው ደሳለኝ ኃይሉ ከዚህ ቀደም ስለ ጉማ ፊልም ሽልማት ተጠይቆ ነበር። እርሱም ሲመልስ ጉማ የፊልም ሽልማት ስነ-ስርዓት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የቪዲዮ ፊልሞች ምርት መሰረት የጣሉትን ሰዎች ያስታወሰ፤ በዳኝነትም ቢሆን አንጋፋ የፊልም ተዋናዮችን ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው ብሏል።
የጉማ ፊልም ሽልማት መሥራችና የፊልም ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በበኩሉ፤ በንግግሩ ለዝግጅቱ መሳካት ድጋፋቸው ላለተለየው ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል። 5ኛው የጉማ ሽልማትን ባተተው መጽሔት ላይ በሰፈረው ሃሳቡ ደግሞ በየዓመቱ ሳይታክቱ የሽልማት ዝግጅቱን ለሚያግዙ ምስጋናን አቅርቧል። ጉማ የፊልም ሽልማት ይዟቸው የተነሳው ሃሳቦችና ግቦች በየዓመቱ እየጠነከሩ፣ እየተሻሻሉ እና እየተስፋፉ መምጣታቸውንም አንስቶ፤ «ጉማ ሁሌም ይቀጥላል» ብሏል። እኛም አልን፤ ወደፊት እየተራመደ እንጂ ስንዝር ሳይመለስ ጉማ ይቀጥል። ሠላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ሊድያ ተስፋዬ