የግብርናውን ዘርፍ በገንዘብ ለመደገፍ በተለይም ባንኮች የብድር አገልግሎት ለዘርፉ አለማመቻቸታቸው በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ በዘርፉ እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንዲሁም በመንግስትም ዘንድ በተደጋጋሚ ይገለጻል:: የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ግብርና የፋይናንስ አቅርቦት ትኩረት ሳያገኝ ባንኮች ባለሀብቶች በከተሞች ለሚገነቧቸው ህንጻዎች በማበደር ላይ ብቻ መጠመዳቸውን ሁሌም እየተተቸ ነው:: ሀገሪቱ ለግብርናው ዘርፍ ፋይናንስ የማይቀርብባት ተብላም በግብርናው ዘርፍ ባለሙያዎች ትጠራለች::
ግብርናው በባንክ ብድር አለመደገፉን በተመለከተ የወጪ ንግዳቸውና የተለያየ ምርታቸው በግብርና ምርት ላይ የተመሰረተው ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ፤እንደ ሀገር ግብርናውን ፋይናንስ የማድረግ ፍላጎት ዝቅተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ:: ‹‹ባንኮች የብድር ማስያዣና የሚያምኑት ደንበኛ ይፈልጋሉ የሚሉት ባለሀብቱ፣ የግብርና ሥራ ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ ወቅትን ጠብቆ መከናወኑና የመስኖ ልማትም አለመጠናከሩ የግብርናው ዘርፍ ከባንክ ብድር እንዳያገኝ አመኔታ እንዳይኖር ያደረገ አንዱ ምክንያት ሆኖ ይወሰዳል ሲሉ ያብራራሉ::
ምርትን በመጨመር ካፒታልን ማሳደግ እንደሚቻል ባለሀብቱ ጠቅሰው፣ በሙሉ አቅም ያለማምረትና ለእርሻ የሚውለውን መሬት ሁሉ ለግብርና ሥራው ያለማዋል ክፍተት ለምርትና ምርታማነት አለማደግ አንዱ ምክንያት መሆኑንም ያመለክታሉ::
እንደ ባለሀብቱ ገለጻ፤ በግብርና ሥራ ብቻ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ቢደረግ እንዲሁም ሁለትና ሶስት እጥፍ ማምረት ቢቻል የግብርና ውጤትን ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ ይቻላል:: የቅባት እህል የሚመረትባቸው አካባቢዎች በፀጥታ ምክንያት የምርት መስተጓጎል አጋጥሟቸው እንኳን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ መገኘት መቻሉ ግብርናው ምን ያህል ኢኮኖሚውን እንደሚያግዝ አንዱ ማሳያ ነው:: በመስኖ የማልማት ጥረቶች ቢኖሩም ከፍተኛ ውጤት በሚያስገኝ መልኩ ባለመከናወኑ ምርታማነቱ የሚፈለገውን ያህል አልሆነም:: በመስኖ የማልማቱ ባህል ቢጠናከር ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል::
ለአብነት ቡናን ወስደው ሲያብራሩም ቡናን በመስኖ ማልማት ቢቻል ከተለመደው የልማት ዘዴ ከሁለት እጥፍ በላይ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ተሞክሮዎች ይጠቁማሉ ሲሉ ይገልጻሉ:: የመስኖ ልማቱ በተፈጥሮ የሚከናወነውን የግብርና ሥራ ማገዝ ከቻለ ምርትና ምርታማነት ከፍ እንደሚልና ለካፒታል እድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል:: ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ብድር የሚገኝበትን ዘዴ ማመቻቸትም ከመንግሥት እንደሚጠበቅ ነው ያመለከቱት::
የግብርናው ዘርፍ በፋይናንስ በሚፈለገው ልክ አለመታገዙና በተለይም ከባንክ ብድር አለማግኘቱ ለምን ይሆን? በሚል ጥያቄ ያቀርብናላቸው የምጣኔ ሀብት እና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አላት:: በውሃ ሀብቷ የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ የውሃ ቁንጮ በሚል ትታወቃለች:: በየአመቱ ከ120 ቢሊየን ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር በላይ በአማካይ በሀገሪቱ አራት አቅጣጫዎች ወንዞች ይፈሳሉ:: ወደ72ሚሊየን ሄክታር የሚሆን ለእርሻ የሚውል መሬትም አላት:: የህዝብ ቁጥሯም እየጨመረ ነው::
ሀገሪቱ የውሃና የመሬት ሀብቱ እንዲሁም የሚሰራ የሰው ኃይል እያላት የምግብ አቅርቦት እንደ ችግር ሊነሳ አይገባም ነበር ሲሉ ይገልጻሉ:: የፋይናንስ አቅርቦት ግብርናውን ለማሳለጥ ዋና መሠረት መሆኑንም ይጠቁማሉ::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በመጥቀስ ሲያብራሩ እንዳሉት፤ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝት ግዛት ዘመን ያዳበሩት ሥርዓት አላቸው:: ለአብነትም ዚምባቡዬ የዶላር ምንዛሬ ዋጋ ሲጨምርና የተለያየ ችግር ሲያጋጥም የምግብ ጉዳይ ግን ሀገሪቱ ውስጥ እንደችግር ተነስቶ አያውቅም:: ሀገሪቱ የግብርና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ታገኛለች:: ችግሮችም ኖሮው በሀገሪቱ የምግብ አቅርቦት ችግር አለመፈጠሩና በወጪ ንግዱ ላይም ተጽዕኖ አለመፈጠሩ የግብርና ሥራው የተስፋፋ በመሆኑ ነው:: የግሉ ዘርፍም በሀገሪቱ በስፋት ይንቀሳቀሳል::
የኢትዮጵያ ግብርና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችንም ጭምር ለተቃውሞ ያነሳሳ እንደነበር ጠቅሰው፣ ለዚህም የተማሪዎችን የመሬት ላራሹ ጥያቄ በአብነት ያነሳሉ:: ባለፈው ስርአትም መንግሥት አራት ሚሊየን ሄክታር መሬት በሊዝ ለኢንቨስተሮች ለመስጠት ውሳኔ በማሳለፍ ወደ እንቅስቃሴ ገብቶ እንደነበርም አስታውሰው፣ ውሳኔው ግን የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም፤ ከባድ ችግር ነው ያጋጠመው ይላሉ::
ኢንቨስተሮቹ ከልማት ባንክ ገንዘብ ወስደው ገንዘቡን ለሚፈለገው ዓላማ ሳያውሉት በመቅረታቸው በባንኩ ላይ ችግር መፍጠራቸውን ጠቅሰው፣ በእርሻ ሥራ ላይ ለመሰማራት ከልማት ባንክ ብድር የወሰዱ የሀገር ውስጥ ባሀብቶችም ቢሆኑ፣ የእርሻ ሥራን የማያውቁ ስለነበሩ ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው ነው ያዋሉት ሲሉ ያብራራሉ::
በፋይናንስ አጠቃቀም ላይ ክፍተቶች ቢኖሩም፣ አሰራርን ማስተካከል እንጂ ፋይናንስ ለዘርፉ አስፈላጊ ነው የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች የብድር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ያስፈልጋሉ ብለዋል :: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ለውጭ ባለሀብቶችም ሆነ ለውጭ ባንኮች ዝግ እንደሆነም ተናግረው፣ ይህም አንዱ ችግር መሆኑን ነው ያስታወቁት:: የግብርናው ዘርፍ በፋይናንስ ተጠቃሚ ሲደረግም የማስተዳደር አቅም ሊኖር እንደሚገባም ነው ያመለከቱት::
የግል ባንኮች እስካሁን ለእርሻ ልማት ወይንም ለኢንዱስትሪ ያመቻቹት ብድር ወይንም ፋይናንስ በማድረግ የሰጡት አገልግሎት ይኖር እንደሆን ቢጠየቅ ምናልባት አንዳንዶች ይኖሩ እንደሆን እንጂ መልስ ለማግኘት እርግጠኛ ለመሆን ያስቸግራል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ባንኮቹ የልማት ሳይሆኑ ለአክሲዮን ባለድርሻዎቻቸው የሚያገለግሉ እንጂ የፖሊሲ ባንኮች አይደሉም ነው የሚሉት::
በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ ተብሎ የተቋቋመ የእርሻና የኢንዱስትሪ ልማት ባንክ የሚባል እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ለግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ አገልግሎት በማቅረብ በኩል ልማት ባንክ ብቻ እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ:: እርሱም ቢሆን ከፍተኛ ኢንቨስትመንትና ዩኒየኖች ላይ እንደሚሰራ ተናግረው፣ ምክንያቱ ደግሞ የሚያስይዙት ሀብት ስላላቸው መሆኑን ይናገራሉ:: አርሶ አደሩን በአነስተኛ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል በወረዳ ደረጃ ለማገዝ ጥረት ካልተደረገ በስተቀር አሁን ያለው አሰራር በዚህ መልኩ የተደራጀ ነው ይላሉ::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማስተካከል በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በብሄራዊ ባንክ ደረጃ የሚደረጉ ጥረቶች ስለመኖራቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች ሲተላለፉ እንደሚሰማ አመልክተው፣ ከእነዚህ መካከል አንዱ የካፒታል ገበያ መቋቋም፣ሌላው የውጭ ባንኮች ካፒታል ይዘው ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ያብራራሉ::
እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች የተለየች መሆን የለባትም:: ጅቡቲ፣ኬኒያ ታንዛኒያ፣ዩጋንዳ ደቡብ ሱዳን፣የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸው ሀገራት ናቸው:: በኢትዮጵያ ግን ሀገር በቀል ባንኮች እንዲስፋፉ ነው የሆነው:: በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አልተካሄደም:: እንደ ቻይና፣ዱባይ የመሳሰሉ ሀገራት የዕድገታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ተሞክሮአቸውን ማየትና መፈተሽ ይቻላል::
ከውጭ በግዥ ወደ ሀገር የሚገባውን የስንዴ ምርት ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ለውጭ ገበያም በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን መንገድ ለማሳካት የሚቻለውም በመሥራትና ለግብርናው የሚያስፈልገውን በማሟላት ነው ይላሉ::
የመሬት ጥያቄን በተመለከተም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በትንታኔያቸው፤የመሬት ጥያቄ ከፖለቲካ ጋር የማያያዝ ነገርም ስላለው ውስብስብ እንዲሆን አደርጎታል ይላሉ:: እርግጥ አነስተኛ እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮች መኖራቸው ለአካባቢ ዘላቂነት ጥሩ ነው:: ነገር ግን የህዝብን ፍላጎት ማሟላት ወይንም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ::
አርሶ አደሩ መሬት ካለውና ካመረተ፣እንስሳትም ካለው ይህን ሀብቱን በማስያዝ ከባንክ የብድር አገልግሎት ማግኘት ያልቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ ያነሳንላቸው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እያሉ መንግስት አርሶ አደሩ መሬቱን አስይዞ ከባንክ መበደር የሚያስችለው መመሪያ ወጥቶ እንደበር አስታውሰው፤ አሁን ባለው አሰራር መሬት የገበሬው አይደለም ::መሬት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው በሚል በአዋጅ ተቀምጧል:: በአዋጅ ያልተፈቀደ መሬት ይዞ ባንኩ የብድር አገልግሎት ቢሰጥና ብድሩ ባይመለስለት መሬቱን ሸጦ ብድሩን ለማስመለስ ህጉ አይፈቅድለትም ይላሉ::
የፕላን ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባዘጋጀው በአዳማ ባካሄደው ስለ ኢትዮጵያ መድረክ ላይ የአርሶ አደሩን የመሬት ሰርተፍኬት አስመልክተው የሰጡት ግን ከባንክና መሬት ጋር የተያያዘው የአርሶ አደሩ ችግር እየተፈታ የመጣ መሆኑን ያመለክታል::
መንግስት መሬትን የኢኮኖሚ መሳሪያ ለማድረግ ባከናወነው ተግባር አርሶ አደሩ የመሬት ሰርተፍኬት እንዲያገኝ መደረጉን ሚኒስትሯ ገልጸዋል:: አርሶ አደሩ ሰርተፍኬቱን አስይዞ ከባንክ እንዲበደር እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ የግብርና ስራውም የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመከተል እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል:: እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ለምርትና ምርታማነት እድገት ትልቅ የሚባል ለውጥ እንደሆነም ነው ያስታወቁት::
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አርሲና ባሌ ላይ ‹‹የጭላሎ አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ዩኒት ካዱ›› ተብሎ የሙከራ ፕሮጀክት ሥራ እንደነበር ያስታውሳሉ:: አርሲና ባሌን የስንዴና የገብስ አምራች ያደረጋቸው በወቅቱ የተቀረፀው ፕሮጀክት እንደሆነም ተናግረው፣ በወቅቱ ፕሮጀክቱ አራት ሚሊየን ዶላር ብቻ እንደወጣበትና ከስዊድን ሀገር በተገኘ እርዳታ የተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል::
ሌላ ፕሮጀክት ዋዱ ተብሎ ወላይታ አግሪካልቸራል ፕሮጀክት ዩኒት ተብሎ ሊስፋፋ ሲል የወታደራዊ ደርግ መንግሥት ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ተቋርጦ መቅረቱን ጠቅሰው፣ እንዲህ ያሉ ውጤት የሚያስገኙ ተሞክሮዎች እያሉ እንደ አዲስ ጥናት ማካሄድ አስፈላጊነቱ እንዳልታያቸውም ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው የሚናገሩት::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ‹‹ዛሬ የአርሲ ገበሬ ትራክተርና ኮምባይነር ይከራያል:: ካመረተ በኋላ ነው ክፍያ የሚፈጽመው:: በአካባቢው ላይ እንዲህ ያለ ሥርዓት ተዘርግቷል::›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህን ተሞክሮ ማስፋት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ:: ዝናብ ጠብቆ የሚያርስን ገበሬ በፋይናንስ ልደግፍ ብሎ የሚነሳ ባንክም ሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያ አይኖርም ይላሉ::
ሀገሪቱ ከታክስ፣ከእርዳታ፣ከብድርና ከተለያየ ምንጮች የምታገኘው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግሥት ሁሉንም ፋይናንስ በማድረግ ለመደገፍ አቅም አይኖረውም ይላሉ:: የግሉ ዘርፍ ገብቶ ሲሰራ ግን የመንግሥትን ጫና እንደሚቀንስ ይገልጻሉ:: ግብርናውን ፋይናንስ በማድረግ በኩል አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ለእዚህም ከውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይገባል፤ ይህም ኢንቨስትመንት አምራች እንዲሆን የውጭ ባንኮችና የካፒታል ገበያ በሀገር ውስጥ መደራጀት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት::
ኢትዮ ቴሌኮም ላይ የተወሰደውን እርምጃ በአብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም፣ መንግሥት አገልግሎቱን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ሲያደርግ ሳፋሪኮም ኩባንያ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራው መግባቱን ይገልጻሉ:: ወደዚህ መንገድ ለመሸጋገር ብዙ ጊዜ ቢወስድም መጀመሩ በጥሩ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል::
በሙስና በኩል የሚስተዋለው ችግር አንዱ ማነቆ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደሳለኝ ኃይለማርያም በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን፣ወጣቱን በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት መንግሥት ወደ አስር ቢሊየን ብር መድቦ ለምን ጥቅም እንደዋለ ግልጽ ሳይሆን እንዲሁ መቅረቱን አስታውሰው፣ ገንዘብ መመደብ ብቻ ሳይሆን ገንዘቡ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉም ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፤ ለግብርናው ዘርፍ የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮች መዘርጋት ያስፈልጋል፤ የፋይናንስ አቅርቦቶቹ ከውጭም ከሀገር ውስጥም መሆን ይኖርባቸዋል፤ በብድር የተገኘ የፋይናንስ አጠቃቀም ላይ ባለፉት ጊዜያት የታዩ ስህተቶች እንዳይደገሙም ፋይናንስ ማስተዳደር ላይ አቅምን ማጎልበት ይገባል:: የግብርናውን ዘርፍ ተሞክሮዎችን ከሀገር ውስጥም ከውጭ ባለሀብቶችም ሆነ ከሀገሮች ወስዶ መስራትም ሌላው የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ የሚያደርግ ተግባር ነው::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 9/2014