ልጆች እንደምን አደራችሁ፤ እረፍት እንዴት ይዟችኋል? መቼም ቆንጆ ነው እንደምትሉኝ አልጠራጠርም:: ምክንያቱም ደስ የሚያሰኙዋችሁን ተግባራት እየፈጸማችሁ ታሳልፋላችሁ:: አንዱ እንደሚመስለኝ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ነው:: ለሁላችንም ደስ የሚያሰኝና አዕምሯችንን ነጻ የሚያደርግ ጉዳይ እንደሆነ ደግሞ በደንብ ታውቃላችሁ:: ስለሆነም ዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ስለ መስጠት ነው:: በጎ በማድረግ ውስጥ ያሉ በረከቶችን እነግራችኋላሁ::
መቼም ሁላችሁም እኔ ምን አለኝና ለሌላ እሰጣለሁ የሚል ጥያቄን በአዕምሯችሁ ውስጥ እያሰላሰላችሁ ይሆናል:: ይህ ግን ትክክል አይደለም:: ስጦታ ገንዘብ ብቻ አይደለም ከዚያም በላይ ነው:: የሚፈልገው አንድናአንድ ነገርም ነው:: ይህም የመስጠትን ልብ ብቻ መያዝ:: የስጦታው መጠን መቼም ሊያሳስበን አይገባም:: ይሁን እንጂ በምንሰጥበት ወቅት ደስ እያለን። ልባችን ሀሴት እያደረገ መሆን አለበት እንጂ እያዘንን። ቅር እያለን። ጉድለት እየተሰማን መሆን የለበትም። ከእንደዚህ አይነት መስጠት አለመስጠት ይሻላልና። ስለሆነም እያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ነገር እንዳለው አውቃችሁ ያለስስት ለመስጠት ፈቃደኛ ሁኑ:: ምን ካላችሁ የሚከተሉትን ለአብነት እንመልከት፡-
ፍቅርን መስጠት፡- ፍቅር ከልብ የተተከለ የመውደድ ኃይል ነው:: የመጀመሪያው ፍቅር የቤተሰብ ፍቅርም ነው:: ስለቤተሰቦቹ የማያስብ ልጅ ካለ ፍቅር የሌለውም የማይሰጥም ነው:: ስለዚህም ፍቅር የምግባራት ሁሉ ራስ በመሆኑ እናነተ አንዱ ለሌላው የምትሰጡት ነገር መሆን አለበት:: ፍቅር ለሌሎች በመስጠታችሁ ውስጥ ክፉ የሚያስቡትን ታስቀራላችሁና አድርጉት::
መመጽወት መቻል፡- ሌላው የመስጠት አካል ነው:: ምጽዋት ሥርወ ቃሉ የግእዝ ቋንቋ ሲሆን፤ ትርጓሜውም ስጦታ፣ ችሮታ፣ ልግስና ማለት ነው:: ሰዎች በሰዎች ላይ የሚያዩትን ችግር በማገናዘብ የተቸገሩትን መርዳት ነውም:: ከፍጹም ፈቃድና ርህራኄ የሚመነጭ ሲሆን፤ ለተቸገሩት ስንሰጣቸው ምሕረትን እናገኛለን:: ምክንያቱም መተሳሰብና መረዳዳትን ከልባችን ተግብረነዋልና ነው:: በእርግጥ እዚህ ላይ ልነብ ማለት ያለባችሁ ነገር ገንዘብ ብቻ እንዳልሆነ ነው:: የተቸገሩ ልጆችን ስታገኙ የማትጠቀሙበትን ልብስ፣ ጫማ እንዲሁም መጽሐፍ መስጠትም ሊሆን ይችላል:: ከምግባችሁ ላይ ማካፈልና ያላችሁን ምክር መለገስም መሆን ይችላል::
ልጆች ደካሞችን በጉልበት፣ ያልተማሩትን በዕውቀት የሙያ ርዳታ የሚስፈልጋቸውን በሙያ መርዳትም መስጠት ነው:: ሌላው ልትረዱት የሚገባው ነገር ከተረፋችሁ ላይ ብቻ ሳይሆን ካላችሁም ጭምር መስጠትን መልመድ እንዳለባችሁ ነው:: ምክንያቱም ስንሰጥ የሚጨመር አዲስ ነገር ይኖራልና ነው:: ምጽዋት መስጠት ለአምላክ ማበደር እንደሆነም ይነገራል:: ስለዚህም ብድራችሁን ከአምላክ ማግኘት ስትፈልጉ መመጽወት አስፈላጊ እንደሆነ ትረዳላችሁ::
ሌላው ለሚጠይቁን ሁሉ ተገቢ ምላሽ መስጠት ሲሆን፤ ነገሮችን በንዴትና ምንቸገረኝ ሳንል በቅንነትና በታማኝነት መመለስ መቻል ነው:: በዚህ ጊዜ ጠቢብ ትሆናላችሁ:: ጠላት እንኳን መስለው ቢመጡባችሁ ታሸንፏቸዋላችሁ:: ምክንያቱም እናንተ መልካሙን ነገር አድርጋችኋል:: እነርሱ ደግሞ ስህተት ፈጽመዋልና ያፍራሉ:: እናም ሁልጊዜ ቅን መሆንና ነገሮችን በጥበብና በተገቢው መንገድ መመለስ መስጠት ነውና ይህንንም አድርጉ::
ለመሆኑ ልጆች መስጠት ለምን እንደሚጠቅም ታውቃላችሁ ? ስለዚህ ደግሞ ትንሽ ነገር ልበላችሁ:: አንዱና የመጀመሪያው የተሻለ የመንፈስ እርካታ እንድናገኝ ማድረጉ ነው:: በሰዎች ደስታ ውስጥ እናንተም ደስተኛ የምትሆኑበት ነው:: ምክንያቱም የቻላችሁትን ስታደርጉላቸው ከችግራቸው እንደሚወጡ ያስባሉና ፈገግ ይላሉ:: በዚህ ጊዜ እናንተም ውስጣችሁን ታስደስታላችሁ፡፡
ሌላው በልደት አለያም በበዓላት ወቅት ዘመድ፣ ጓደኛ ወይም ቤተሰባችሁን ለመጠየቅ ስትሄዱ ስጦታ መግዛት ትፈልጉና ትጨነቃላችሁ:: ለዚያ መፍትሄ የምታገኙት ደግሞ ስጦታችሁ የምትፈልጉት ሰው ጋር ሲደርስ ብቻ ነው:: ምክንያቱም በስጦታው ያ ሰው ፊቱ ላይ ደስታ ይነበብበታልና እናንተም ትክክለኛ ምርጫ እንደመረጣችሁ ታውቃላችሁ::
ሌላው የመስጠት ጥቅም ሰላማዊ እንቅልፍ እንድንተኛ ማድረጉ ነው:: ተጫውታችሁ ስታበቁ አንድ የተቸገረ ሰው መጥቶ ይህንን አድርጉልኝ ቢላችሁና ሳታደርጉለት ብትቀሩ ምንም እንቅልፍ አይወስዳችሁም:: ነገር ግን ያንን ችግሩን ፈታችሁለት ብትገቡ ስላደረጋችሁት ነገር እያሰባችሁ ደስተኛ ሆናችሁ የሰላም እንቅልፍ ትተኛላችሁ:: እንደውም ይህ በህክምና ጭምር የሚመከር እንደሆነም ይነገራል:: ስለዚህም ለሰላማዊ እንቅልፋችሁ መስጠት አንዱ መሰረት ነው ማለት ነው::
በመስጠት ሌላው የሚገኘው ጥቅም ሰዎችን በማገዝ ውስጥ የሚመጣው ረጅም እድሜ መኖር ነው:: ችግረኞችን ሲያግዝ የቆየ ሰው ደግ ነበረ እየተባለ ሁልጊዜ ይመሰገናል፤ ከበራልም:: ከዚያም አልፎ ሁሉም ሰው እንክብካቤ ያደርግለታልና ጤናማ ኑሮን ይኖራል:: ይህ ደግሞ የእድሜ ባለጸጋ ያደርገዋል:: ሌላው መስጠት ስማችንን በታሪክ ጭምር የሚተክልልን ነው:: ደግ ነበር እየተባልን ከሞትን በኋላ እንኳን እንድንነሳ እንሆንበታለን:: በሁሉም ሰው ዘንድ እንድንታወቅም ያደርገናል::
ልጆች መስጠት መልሶ የሚከፍልም ነው:: ለምሳሌ ዛሬ ተርቦ ያበላችሁት ልጅ ነገ የእናንተ ክፍል ተማሪ ቢሆንና በትምህርቱ ጎበዝ ቢሆን እናንተ ደግሞ ሰነፎች ብትሆኑ በእውቀት እንደሚደግፋችሁ መጠራጠር የለባችሁም:: እያስጠናችሁ እናንተም ጎበዝ እንድትሆኑ የቻለውን ሁሉ ያደርግላችኋል:: ምክንያቱም እናንተ የችግሩ ቀን ደራሽ ናችሁ:: ስለዚህም ብድራችሁ ተመለሰ ማለት አይደል?
በመጨረሻ የማነሳላችሁ የመስጠት ጥቅም ለራስ ያለን ግምት ከፍ ማድረጉንና የአኗኗር ዘይቤያችንን ጭምር የምንለውጥበት መሆኑን ነው:: መስጠት ከእኛ በታች ያሉ ሰዎችን አይተን የተሻልን እንደሆንን እንድናስብ ያደርገናል:: ከዚህ በላይ ብንሰራ ደግሞ እነርሱንም እኛንም እንድምንለውጥ ያስተምረናል:: አዳዲስ ሃሳቦችን እንድናመነጭም በር የሚከፍትልን ነው:: በሰጠነው ውስጥ ያለውን እርካታ እየሰበሰብን ለውስጣችን ሰላም እየሰጠን ብሩህ ቀን እንድናሳልፍም እንሆናለን:: ስለዚህም ሁልጊዜ መስጠትን ልምዳችሁ አድርጋችሁ ዛሬያችሁንም ነጋችሁንም ማሳመር አለባችሁ እሺ:: ለዛሬ ሃሳባችንን በዚህ እናጠቃልል:: በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ይዘንላችሁ እንደምንቀርብ ቃል እየገባን መልካም ሳምንት ተመኘን :: ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2014