ቦታው የአይን ህክምና አገልግሎት መስጫ ቦታ ነው። አገልግሎት ፈልገው የተሰበሰቡት ሰዎች ወረፋቸውን እየጠበቁ ነው። በወረፋቸው መሰረት ወደ ህክምና ክፍል የገቡ እናት ከሀኪሙ ጋር ናቸው። ሀኪሙ እንደተለመደው “ይህቺ ፊደል አቅጣጫዋ ወዴት ነው?” እያለ ይጠይቃል፤ እርሳቸውም ይመልሳሉ። አሁንም ሌለ አቅጣጫ ጥያቄ፤ እርሳቸውም ሌላ ምላሽ። ከትልቁም፤ ከመካከለኛውም፤ ከትንሹም ፊደል እያደረገ አቅጣጫውን እየፈተነ ዘለቀ። እማማ “ህክምና ነው የመጣሁት ወይንስ ምን?” እያሉ በውስጣቸው እያጉረመረሙ፤ ማሽን ላይ እንዲቀመጡ ታዘዙና ወደ ማሽን ሄዱ። በማሽን ወደሚደረግ ምርመራ።
ህክመናውን ጨርሰው ከቤታቸው ሲደርሱ ውሏቸውን ለቤተሰባቸው አባል ሲናገሩ የመጨረሻው ልጃቸው በጥሞና ታደምጣለች። እንደተለመደው ከቤተሰቡ ውሎ ተነስታ ጽሁፍ ልትጽፍ። ሁሉም የቤተሰብ አባል ስለ እይታ፤ ስለ አይን ምርመራ፤ ስለ ህክምና የየራሳቸውን ሃሳብ እየሰጡ አመሻሹ፤ ታዳጊዋም ስለምትጽፈው ጽሁፍ እያሰበች።
በነገታው ልጃቸው “የእይታ ልክ” ብላ የሰየመችውን አጭር ልብወለድ አዘጋጀች። ጽሁፉንም ለቤተሰቡ አባላት አነበበች። አባት በልጃቸው የስነጽሁፍ አቅም ተገረሙ። የእይታ ልክ ትልቅ ቦታ ለመድረስ አስባ ተነስታ በየጊዜው የሚገጥማትን ተግዳሮት አልፋ መዳረሻዋ ላይ ደርሳ ታሪኳን ለልጆቿ የምትተርክ እናት ታሪክ ነው።
ልጅቱ በሥነ-ጽሁፍ ነገሮችን የምታይበትን ፍልስፍናዊ መንገድ ታሳያለች። በማህበረሰብ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር በጥበብ አድርገን ማቅረብ መቻል እንደ ማህበረሰብ ልንቀርጽ የሚገባውን እሴት ለመቅረጽ ይረዳል ብላም ታምናለች። እይታው ትልቅ የሆነ ማህበረሰብ በመደበኛ ትምህርትም፤ በኪነጥበብም እንዲሁም በሚዲያ ይዘቶች ይቀረጻል የሚልም እምነት ይዛለች።
አባትም እንደወትሮው ለልጃቸው “ልጄ እውነትሽን ነው የእይታ አቅም ብዙ ነገር ማለት ነው። በአይናችን አማካኝነት ብዙ መረጃዎችን ወደ ውስጣችን አስገብተን አብላልተን ለውሳኔ ሰጪነት እንደምንጠቀምበት እንዲሁ ህይወትን የምናይበት መንገድም ለአጠቃላይ ለህይወት ጉዞችን ወሳኝ ነው።” በማለት ተናገሩ። አባት ንግግራቸውን በመቀጠል “ልጄ የአድዋ ድልን በእይታ ውስጥ ስታይው ብዙ ያስተምረናል። አድዋ ተራሮች አናት ላይ ስለ እይታ የተጻፈ ታላቅ ገድል አለ። ይህን ታላቅ ክስተት ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክተሸ በብእርሽ አድርገሽ የምታቀርቢው መልእክት የአድዋን መንፈስ በሰዎች ውስጥ ይፈጥራል። ጣሊያን በቂም ዳግም የወረረችን ታሪክንም እንዲሁ በተለያየ አቅጣጫ ልታይው ትችያለሽ። በመጀመሪያው የተሸነፈች በኋለኛው ያሸነፈች አድርገሽ ልታቀርቢው ትችያለሽ። ነገር ግን መሸነፍ ማለት እጅ ሰጥቶ መቀመጥ ከነበረ ደግሞ እንዳልተሸነፍን ይገባሻል። አየሽ ልጄ የእናትሽን አይን ጤንነት ለማወቅ የአይን ሀኪሙ ከተለያየ አቅጣጫ እንደመረመረ እንዲሁ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ በመመልከት እይታን ማስተካከል ይቻላል። ሰዎች ስለ እኛ በተለያየ አቅጣጫ የሚሉትን ሰምተን ምናልባትም በተሳሳተ ሳጥን ውስጥ ራሳችንን እንዳንጨምር የእይታ ጥራት የግድ ነው።” እያሉ የተለመደውን ማበረታቻቸውን ቀጠሉ።
“ልጄ ብርጩቆውን ተመልከቺው፤ ግማሽ ብርጭቆ ውሃን ይዞ ይታያል። በብርጭቆ ውስጥ ያለውን ውሃ የምታይበት አተያይ ግን እንደ እይታሽ ልክ ነው። አንዳንዱ ግማሽ ብርጭቆ ውሃ ሲታየው ሌላው ግማሽ ባዶ ብርጭቆ ሊታየው ይችላል። ሁሉም እንደ እይታው የሚለው ይኖረዋል። እይታ የህይወት አቅጣጫን የመወሰን እድሉ ከፍተኛም የሆነው ለእዚህ ነው። ሰዎች የልቦናቸው አይኖች በርተው ምርቱን ከገለባው ለይተው ማየት ካልቻሉ ኪሳራ ውስጥ ዘመናቸውን ይጨርሳሉ። የመጣው ነገር ሁሉ የሚወስዳቸውም ይሆናሉ። የሚመጣው ነገር ሁሉ ራሱን አሳምሮ እንደሚመጣ መሆኑን ይረሳሉ።
አንቺን ለፍቅር ህይወት የሚፈልግ ሁሉ ሲመጣ ራሱን መልአክ አድርጎ፤ አንደበቱን አስተካክሎ ወዘተ ነው የሚመጣው። ነገርግን በጠራ እይታ ነገሮችን መርምረሽ ውሳኔ ማሳለፍ የአንቺ ኃላፊነት ነው። ዛሬ በተንሸዋረረ እይታ የህይወትን መስመር የሳቱ ብዙ ሰዎች አሉ። ህይወትን በገንዘብ ውስጥ ብቻ አይተው ስለ ገንዘብ በማይሆን መንገድ ውስጥ ገብተው ከዓላማ መስመር የወጡ። ህይወትን በዝና ውስጥ ፈልገው ዝናው እጃቸው ሲገባ ወጣ ወጣና እንደሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የሆኑም አሉ። ሁሉም እንደ እይታሽ ነው፤ እይታሽ የጠራ ካልሆነ ግን ህይወትሽ በጨለማ ውስጥ ይዳክራል። ህይወትን እንዲህ ግለጪያት። ፈጽሞውኑ ህይወትን በደፈረሰ እይታ ውስጥ የመምራትን አደገኛነት አስተምሪ።” አሉ።
በዚህ ጽሁፍ ስለ እይታ ልክ እናነሳለን። ትልቅ እይታን የያዙ ሰዎች የሄዱበት እርቀትን ተመልክተን በትንንሽ እይታ በቆሙበት ቦታ ላይ ስለቀሩትም በማስታወስ። ትልልቅ እይታ ከትልልቅ ስፍራዎች ሳይሆን ከራስ ልብ የሚነሳ መሆኑን ልብ በማለት።
ኮሌጅ ያልተገኘው
ወደ ኮሊጅ የገባ ተማሪ እውቀትን ይዞ ሊወጣ የወሰነ መሆኑ ጥርጥር የለውም። እውቀትን ሸምቶ፤ እውቀትን የራሱ አድርጎ መፍትሔን ፍለጋ በሥራው አለም የሚሰማራ። ሊያሳኩ የፈለጉትን ነገር ኢላማ አድርገው፤ ትኩረታቸውን በልባቸው ይዘው ዳር ለማድረስ የተጉ አያሌ አንቱታን ያተረፉ ሰዎች በኮሌጅ በር ላይ አልፈዋል። እኒህ በስራቸው አንቱታን ያተረፉ ሰዎች የሚያዩትን በተግባር ለማየት በብዙ የደከሙ መሆኑን የተራመዱት እያንዳንዱ ቀን ምስክር ነው። በኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አያሌ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰው መመረቃቸው ጸድቆላቸው ይወጣሉ። ከተመራቂዎቹም መካከል ከፍተኛውን ነጥብ ያመጡት ኮሌጁ ያዘጋጀውን ሽልማት ተሸልመውም ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ለማመን የሚከብድ ውጤት ይዘው ሲወጡ ሚዲያዎች የገጾቻቸው ማድመቂያ አድርገዋቸውም እናነባለን። ለትምህርት ቦታ መስጠት ለነገ የሚባል አለመሆኑንም እንረዳለን፤ እንዲህ በመሰለ መንገድ ጎበዝ ተማሪዎች መሸለማቸውንም እንዲሁ እናነሳለን። ነገርግን የዓለማችንን ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ኮኮብ ተማሪዎች ግንባር ቀደም ሆነው የመታየታቸው ነገር የጠበበ የሆነበትን እድልም ጎን ለጎን እንፈትሻለን።
በተለምዶ ውጤታማ ተማሪዎች መገለጫ አድርገን በምንመዝንበት መመዘኛቸው መሰረት በትክክል ተጽእኖ መፍጠር መቻል ወይንም ውጤታማ መሪ ሆኖ መመዘን አስቸጋሪ ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ በ500 ትልልቅ ድርጅቶች ላይ በተሰራ ጥናት ከ 50% በላይ የሚሆኑት የድርጅት ስራ-አስፈጻሚዎች የኮሌጅ ውጤታቸው በ C የሚገለጽ ሆኖ የተገኘ ነው። 75% የሚሆኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የትምህርት ቤት ውጤታቸው በመካከለኛ ተማሪነት የሚገለጹ እንጂ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ (በተለምዶ ሰቃይ ተማሪዎች) ከሚባሉት መካከል አይደሉም። ከግማሽ የማያንሱ በጥናቱ የተካተቱ ሚሊዬነር ስራ ፈጣሪዎች ኮሌጅ የጨረሱ ሆነው አልተገኙም። እኒህ ተራ የሚባሉ ሰዎች ሀገር ለመምራት እንዲሁም ሚሊዬነር እንዲሆን ያደረጋቸው የእይታ ልካቸው ነው፤ ትልቅ አይተው ትልቅ ቦታ ደርሶ፤ ትልቅ በማየታቸው በውስጣቸው የተፈጠረው መቀጣጠል ያዩትን እንዲጨብጡ አደረጋቸው። እይታ ጤናማ ሲሆን፤ እግር በአግባቡ ሲራመድ፤ እጅም ሊሰራ የሚገባውን ሲሰራ ግብ ካደረጉት ተራራ ላይ መድረስ ይቻላል።
በምን አወቅናቸው?
በዓለማችን ውስጥ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገው ያለፉ ሰዎችን በምን አወቅናቸው ብለን እንጠይቅ። እከሌን በእዚህ አወቅኩት፤ እከሊትን በእዚህ አወቅናት ስንል የምናነሳው ተጨባጭ ውጤት አለ። ጋንዲን በሰብዓዊ መብት አወቅነው ዊንስተን ቸርችልን ስለ ነጻነት በሄዱበት እርቀት፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ እኩልነት በጉልህ የፊትለፊት ሰው ሆኖ በከፈለው ታላቅ መስዋእትነት፤ ቢልጌት በቴክኖሎጂ አብዮተኛነቱ አወቅነው። እንዲህ እያልን ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን። እኒህ ግለሰቦች አንድ ግለሰብ ሆነው ሳለ ለዓለም ባበረከቱት አስተዋጽኦ የታወቁ ሆነው አገኘናቸው። እይታቸው ይዟቸው ከወጣበት ከፍታ ላይ ቆመው ዓለም አያቸው፤ ወደ ከፍታው ለመድረስ ያለፉበት መንገድ ትልልቅ መጽሐፍ ይወጣዋል።
ዛሬ ሰዎች እንዲያውቁን ከመድከም የጠራ እይታ ኖሮን፤ ተፈጽሞ ልናይ የምንወደው ሆኖ እንድናይ እንመላለስ። ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የሚከተሏቸውን ሰዎች ለማብዛት ትኩረት ሳቢ በሆነ እንቅስቃሴ የተጠመዱ ሰዎችን እናገኛለን። እኛም ከእነርሱ አንዱ ሆነን እንደሆነ በፍጹም አንድከም፤ ስራችን ስለ እኛ መናገር ሲጀምር ሰዎች እንዲከተሉን ሳንጠይቃቸው የሚከተሉን ሆነው እናገኛቸዋለን።
የጠራ እይታ በያዝን፤ በያዝነው እይታ መሰረት በግለት ለመልካም ስራ በተጋን ቁጥር ለውጥ እናመጣለን። የምናመጣው ለውጥ ውስጣችን በተቀጣጠለው እሳት ልክ በተሰማራንበት ዘርፍ ውስጥ ወደ ፊትለፊት ይዞን ይወጣል።የተቀጣጠለው እሳትም ነዳጅ ሆኖን ልንሆን ያሰብነው ጋር እንድንደርስ ያግዘናል። ወደ ውስጣችን ብንመለከት በአንዳች ጎልቶ በወጣ ነገር ውስጣችን ሲቀጣጠል ልናገኘውም እንችላለን።
በታሪክ መዝገብ ውስጥ ስለ ሰው ልጆች መልካም ይሆን ዘንድ በብዙ የተጋደሉ ሰዎች መደበኛ ህይወት ኖረው ካለፉ ሰዎች በተጨባጭ የሚለዩ ናቸው። ይህ በሁሉም ዘርፍ ተመሳሳይ ነው። ጠንካራ የውስጥ ፍላጎት የጠራ እይታን ሰጥቷቸው በጠራ እይታ ወደ ተራራው የደረሱ። ደካማ ፍላጎት ደካማ ውጤት ነው የሚያመጣው። ትንሽ እሳት ትንሽ ሙቀት እንደሚፈጥር ማለት ነው። ትልቁ የውስጥ እሳት ግን አንዳንዴ በትንሽ ነገር እንዳይጋረድ ጥንቃቄን በሚሻ አካሄድ።
ትንሽዋ ሳንቲምና የተራራው ምሳሌ
ወደ ትልቁ ተራራ የሚደረገውን ጉዞ መገዳደር በተመለከተ የትንሿ ሳንቲምና የተራራው ምሳሌ በአስተውሎት እንመልከት። ተራራው ገዝፎ የሚታይ እሩቅ ሆኖ እይታ ውስጥ መገባት የሚችል ነው። ከእርቀት የሚታየውን ተራራ ግን ትንሿ ሳንቲም ወደ አይናችን ባስጠጋን ቁጥር እየጋረደችው ትመጣለች። ሳንቲሙ ወደ አይናችን አብዝቶ ከተጠጋ አብዝቶ የተራራው ምስል እየደበዘዘ ይመጣል።
እይታ በትንሽ ነገር ከተጋረደ ትልቁን ምስል ማየት የማንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ትልቁ ምስል ከተጋረደ እለታዊ እንቅስቃሴያችን ትንሽ ይሆናል፤ አይናችንን በቀረበው ነገር ልክ ይያዛል። ዛሬ ከእይታ ውስንነት የተነሳ እንቅስቃሴያችን በሰፊው የተገደበ እንደሆነ እናስተውላለን። የፖለቲካ ስሪታችን እንዲሁም አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ጉዟችን የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ ሆኖ ይታያል። በመቀራረብ አቅምን አሰባስቡ ድምር ውጤቱ ሁሉንም አሸናፊ ከሚያደርግ ጉዞ ይልቅ ሁሉም በጋራ ተሸናፊ የሚሆንበት መንገድን የመረጥን ይመስላል።
ተቃርኖው መቆሚያው የት እንደሆነ እርግጠኛ ባንሆንም የእይታ ልክ ግን የሚሰራው ስራ ስለመኖሩ አንዳች ጥርጥር የለንም። ትንሿን ሳንቲም ከአይን ላይ አንስቶ የሚሆን እይታ።
የአይን ህክምና ሰዎች የአይንን የማየት አቅምን ተመልክተው የእይታ ደረጃችን ላይ አስተያየት እንደሚሰጡ ሁሉ በሀገራችን እየተገበርናቸው ባሉት ፖሊሲዎችና መሰል ተግባራት እይታችንን በመመርመር ወደ መፍትሔ መራመድ አለብን። ትንሽዋ ሳንቲም የጋራደችውን ተራራ ተመልክቶ ወደ ተራራው የሚደረገውን ጉዞ ከማደናቀፍ በተራራው ስር ያለውን ሃብት አውጥቶ መጠቀም ተገቢነት እንዳለው አምኖ እይታን ማስተካከል።
በትንሿ ሳንቲም የሚወከል እይታችንን የጋረዱትን ነገሮች ለማንሳት ብንሞክር የምናገኘቸው እውነታዎች በዙሪያችን ያለውን ሁኔታ አግዝፈን በማየት አልችልም ማለታችን፤ በዙሪያችን ያሉ ተስፋ አስቆራጭ ድምጾችን አድምጠን መቆማችን፤ ትናንት ሞክረው ያልተሳካለቸው ሰዎችን ምክር ሰምተን ከጉዞ መታቀባችን፤ ደጋግመን አንኳኩተን ያልተከፈተውን በር አጥብቀን ከማንኳኳት መመለሳችን፤ ከእለት ወደ እለት እየደቀቀ ያለ ኢኮኖሚ የሚፈጥረው ተስፋ ቢስነት ህልማችንን እንደ ቅዠት መቁጠራችን ወዘተ ናቸው።
አንባቢው እንዲረዳው የሚያስፈልገው ነገር በመነሳሳት ወይንም በተቀጣጠለ ልብ ውስጥ አንዳች ነገር ለማሳካት የሚነሱ ሰዎች ተቀምጠው ተግዳሮትን ከሚያወሩ በየትኛውም መንገድ የተሻሉ መሆናቸው ነው። ዛሬ በልባችን ውስጥ ያለውን ድምጽ በሚገባ አድምጠን መሄድ ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ መራመድ እንድንችል ከልብ መነሳሳት ያስፈልገናል። ከሁኔታው በላይ መራመድ የሚያስችልን አቅም ከውስጣችን ፈልገን ከፈጣሪ ጋር ለመነሳት የእይታ ምልከታችን ወሳኝነት አለው።
በእይታችን ልክ የምንወርሰውን ተራራ እንመልከት። ተራራው ግዙፍ ነው፤ ተራራው በመካከል ካለው የትኛውም ተግዳሮት በላይ ልናየው የተገባም ነው፤ ተራራው ላይ ደርሰን ከፍታውን በተቆጣጠርን ጊዜ አካባቢውን በሚገባ መቃኘት የምንችልበትም ስፍራ ነው።
ከተራራው ማዶስ
እይታውን ተራራው ላይ አድርጎ ጉዞን የጀመረ ሰው ከተራራው ጋር ሲደርስ ስኬቱን ያከብራል። በጉዞው የገጠሙትን ተግዳሮቶች እንዴት በድል እያሸነፈ እንደ ዘለቀ ከትዝታው ማህደር እያወጣ ደስታውን ያጣጥማል። ተራራው ጫፍ ጋር ደርሶ መቆም አንድ አመራጭ ሲሆን ሌላው አማራጭ ከተራራው ጫፍ ተነስቶ ሌላኛውን ተራራ ጫፍ መመልከት ነው። ወደ አዲስ ተራራ፤ ወደ በለጠው ከፍታ። ሁኔታ በተግባር ህይወት ውስጥ ቀላል አይደለም፤ ነገርግን የእይታ ሰዎች መገለጫ ነው።
በኢኮኖሚክሱ የሰው ልጅ ፍላጎት በቀላሉ የማይረካ መሆኑን እንረዳለን። በምድር ላይ ያለው ሃብት ውስን ቢሆንም የሰው ልጅ ፍላጎት ግን የሚቀጥል ነው። አንድ ሰው በህይወት ጉዞ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ እሴትን መያዝ አለበት። ከአንድ ተራራ ወደ ሌላ ተራራ በጽናት የመጓዝ በስተመጨረሻም በአሸናፊነት ማማ ላይ ለመድረስ።
ከተራራው ማዶ ሌላኛውን ተራራ መመልከት ውስጥ ጽናት አለ። እይታን አጥርቶ የመጓዝ ጽናት። ልጆች ማሳደግ ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን ልጆችን በማሳደግ ህይወት ውስጥ ያለፉ ያውቁታል። ሰዎችን መምራት ምን ያህል አስቸጋሪ መሆኑን በመሪነት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ይናገራሉ። አንዳንዱ ወደ ግራ እንሂድ ሲል ሌላው ወደ ቀኝ ሲል በመካከል በሚፈጠረው መሳሳብ አማካኝነት የሚሆን አስቸጋሪነት። ከተራራው ማዶ የሚያዩ ሰዎች የተግዳሮቱ ምንጭ ምንም ይሁን እያንዳንዱን ቀን በእሴት የተሞላን ኑሮን በመኖር ወደ ውጤት ይደርሳሉ።
በህይወት ጉዞ ውስጥ ከአራቱም አቅጣጫ የሚመጣውን ተግዳሮት ተቋቁሞ ወደ ውጤት መድረስ እንዲቻል የእይታ ልክ ወሳኝነት አለው። ነገሮችን በልካቸው ማየት፤ ያየነውን ትልቁን ምስል ጠብቀን መራመድ፤ በብርቱ መነሳሳት።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014