የዛሬው የዘመን እንግዳችን በፖሊስ ተቋም ውስጥ በርካታ ስትራቴጂክ ዲዛይን በመስራትና በመቆጣጠር ከፌደራል እስከ ክልሎች ድረስ ስራዎች ያበረከቱ የምህንድስና ባለሙያ ናቸው:: በቀድሞ አጠራር በሸዋ ክፍለ አገር ደቡብ ሸዋ ከምባታ አውራጃ አንጋጫ ወረዳ ዋሰራ ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለዱት:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ዋሰራ ቅድስት ትሬዛ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በቀድሞ ስያሜ ልጅ አበባ ወልደሰማያት ትምህርት ቤት ደግሞ ዘጠነኛ አስረኛ ክፍልን ተምረዋል:: ወደ 11ኛ ክፍል በከፍተኛ ውጤት ቢያልፉም ወቅቱ የደርግ መንግስት ሥርዓቱን ተረክቦ የእድገት በህብረት ዘመቻ አዋጅ ታወጀና ትምህርታቸውን አቋርጠው በዘመቻው ላይ እንዲሳተፉ ተጠሩ:: በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ::
በወቅቱ የዘመቻው ተልዕኮ አንድ አካል የነበረው የመሠረተ ትምህርት ማስተማር፤ ገበሬዎችን የማደራጀት፤ የድልድይ ግንባታና የመንገድ ሥራ እንዲሁም መሬት የማከፋፈሉን ሥራ ሰርተዋል:: ዘመቻውን እንዳጠናቀቁም 11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ወደ ቀድሞው ትምህርት ቤታቸው ተመልሰው የቀጠሉ ሲሆን 12ኛ ክፍልን ግን የጨረሱት አዲስ አበባ ከሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማለፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመማር ተመዘገቡ:: ምዝገባውን ካከናወኑ በኋላ በእግራቸው ወደ እሳት አደጋ አካባቢ እየተጓዙ ሳለ የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ያወጣውን የትምህርት ማስታወቂያ ተመለከቱ:: ወትሮውንም ቢሆን ለፖሊስ ሙያ ትልቅ ክብር የነበራቸው እንግዳችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ትምህርት ትተው በፖሊስ ኮሌጅ ለመማር አመለከቱ። እዛም በምክትል መቶ አለቅነት በከፍተኛ ማዕረግ በፖሊስ ሳይንስ ዲፕሎማቸውን አገኙ::
እንደተመረቁ በቀጥታ አዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ፣ ሴፍቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ ሆነው ተመደቡ:: ስድስት ወር እንደሰሩ ደግሞ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ:: አንድ አመት ያህል እንደሰሩ አምስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና ትምህርት ክፍል በማታው ክፍለ ጊዜ ገብተው መማር ጀምረውም ነበርና ጎን ለጎን በፖሊስ ኮሌጅ ተመድበውም በትራፊክ ደህንነት መምህርነት ሙያ ለአንድ ዓመት ተኩል አገልግለዋል:: በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ነፃ የውጭ ትምህርት እድል በማግኘታቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ትምህርት አቋርጠው በራሺያ በኢንደስትሪያል ሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ::
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ሲሉ የመንግስት ለውጥ በመምጣቱ የራሺያ መንግስት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ጥሩ ባለመሆኑ እዚያው እንዲቆዩ ይጠይቋቸዋል:: ሆኖም እንግዳችን የራሺያን መንግስት ጥያቄና የሚጓጓውን አማራጭ ‹‹አሻፈረኝ›› ብለው ወደ እናት አገራቸው መጡ:: እንደመጡም ባስተማራቸው የፖሊስ ተቋምም መምሪያ ኃላፊ በመሆንም ተመደቡ:: በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ የኪነ-ህንፃ ሙያቸውን በተግባር የማሳየት እድሉን ያገኙት:: ቦሌ መንገድ ላይ የለንደን ካፌን ዲዛይን ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አወጡ፤ በወቅቱ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ በፈጠረው በዚህ የኪነ ህንፃ ዲዛይን እንዲሁም ግንባታው በሚከናወንበት ጊዜ በአማካሪነት ሰርተዋል::
የፖሊስ ሰራዊት ተቋም ውስጥ በርካታ ስትራክቸራል ዲዛይን በመስራትና በመቆጣጠር ከፌደራል እስከ ክልሎች ድረስ ሰፊ ተግባራት አከናውነዋል:: በተለይም እሳቸው የሚታወቁበት የኪነ-ህንፃ ዲዛይን መሀል ሜክሲኮ ላይ የፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤትን ከአስር በላይ ዲዛይኖችን ሰርተው ካስረከቡ በኋላ አሁን የሚታየው ዲዛይን ተመርጦ እንዲገነባ የተደረገ ሲሆን ግንባታውንም በበላይ ተቆጣጣሪነት መርተዋል:: የኦሮሚያ ክልል መስሪያ ቤትንም በግንባታ ተቆጣጣሪነት ሰርተዋል:: የአፋር ርዕሰ ከተማ ሰመራ ላይ ምንም አይነት ህንፃ ባልነበረበት ጊዜ ለከተማዋ የመጀመሪያ የፖሊስ ህንፃ ዲዛይን ሰርተዋል:: አለቆቻቸው ‹‹ሻለቃ እንደልቡ›› እያሉ የሚጠሯቸው የዛሬው የዘመን እንግዳችን ሻለቃ ኢንጂነር ወልደሚካኤል ዋተሮ ናቸው:: ከእንግዳችን ጋር በሕይወት ተሞክሯቸውና በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነው ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡- ለውይይታችን መነሻ ይሆነን ዘንድ ‹‹ሻለቃ እንደልቡ›› የሚል ቅፅል ስም እንዴት ሊወጣሎት እንደቻለ ሊነግሩን ይችላሉ ?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- እኔ በሕይወቴ የምኖረው በእውነትና እንደፍላጎቴ ነው:: ሥራዬን እንደልቤ መስራት ያስደስተኛል:: በሃቅ ላይ ተመስርቼ ብቻ የምናገርና የምቃወማቸው ስለሆነ ነው አንዳንድ ሰዎች ይህንን ስያሜ ያወጡልኝ:: የማላምንበትን ነገር በገሃድ እናገራለሁ፤ ሥራዬን ግን ጠንቅቄ ነው የምሰራው:: ሆኖም እነዚህ ሰዎች ባወጡልኝ ቅፅል ስም ምንም ቅሬታ የለኝም፤ ደግሞም እንዳሉትም እንድልቤ የምኖር ሰው ነኝ:: ለዚህም ነው ወያኔ ከመጣ በኋላ 12 ዓመት አገልግዬ በኋላም ሁኔታዎች እየተበላሹ ሲመጡ በገዛ ፍቃዴ ለቅቄ የወጣሁት:: በወቅቱ ኃላፊ የነበሩት ሰዎች ማዕረጉ ስላላቸው ብቻ የማላምንበትን ነገር እንዳደርግ ሊያዙኝ እንዳማይችሉ፤ እኔን ለማዘዝ አስቀድመው እኔ የደረስኩበት የእውቀት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለባቸው በድፍረት ነግሪያቸው ነው የወጣሁት:: በመሰረቱ የፖሊስ ተቋም እየከፈለ ያስተማረኝ ባለውለታዬ በመሆኑ ነው የተሻሉ እድሎች እያሉኝ ለዚህ ሁሉ ዓመት ሳገለግል የቆየሁት::
አዲስ ዘመን፡- የሁለተኛ ደረጃ እድገት በህብረት ዘመቻን የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ ያስታውሱን?
ሻለቃ ኢንጅነር ወ/ሚካኤል፡- የ10ኛ ክፍልን እንደጨረስኩኝ የእድገት በህብረት የስራ አዋጅ ታወጀ፤ ከ10ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ አራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዘመቻው ላይ እንዲሳተፉ በሬዲዬ ተነገረና እኔን ጨምሮ 150 ተማሪዎች ከምባታ አውራጃ ውስጥ ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ አሁን ዱራሜ የሚባለውና የከንባታ ዋና ከተማ ተመድበን ሄድን:: ሸሪፋ በሚባል ሜዳ ላይ ድንኳን ተጥሎ ህዝቡ ድግስ ደግሶ ፤ ‹‹መሄዴ ነው ዘመቻ››፣ ‹‹ተነሳ ተራመድ፤ ክንድህን አበርታ›› የሚሉ ጥዕመ-ዜማዎችን እያዜሙም ነው የተቀበሉን::
በዚያ ሁኔታ እነዚያ ተማሪዎች በአምስት የተለያዩ ቦታዎች ተመድበን ቀኑን ሙሉ ስንፈጋ ነው የምንውለው:: መንገድ፣ ድልድይ እንሰራለን። ገበሬዎቹም ባህር ዛፍ ቆርጠው ተሸክመው እየመጡ ያግዙን ነበር:: ከዚሁ ጎን ለጎን የአካባቢውን ሰው ሰብስበን መሰረተ ትምህርት እናስተምራለን፤ ሴት፣ ወንድ፣ ህፃን ሽማግሌ ሳይባል ሁሉም ፊደል እንዲቆጥር ይደረግም ነበር:: በዚህም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ችለን ነበር:: በወቅቱ በዘመቻው የተሳተፍነው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተመርጠን የመጣን ተማሪዎች ብንሆንም ያለማንም ልዩነት ተቀራርበን ነበር የምንሰራው:: እኔ እንዳውም በየሳምንቱ ዘመዶቼ ቤት እየወሰድኳቸው ከፍተኛ ግብዣ ይደረግላቸው ነበር:: ይህም አብሮነታችንን ይበልጥ አጠናክሮታል:: በነገራችን ላይ የእኔን ሕይወት የቀረፀው የእድገት በህብረት ዘመቻ ነው:: ልዩ ትዝታ ነው ያለኝ:: የሚገርምሽ ‹‹ሴቶች አይችሉም›› የሚለው አስተሳሰብ የተሰበረው እዚያ እድገት በህብረት ዘመቻ ላይ ነው:: አብረውን የዘመቱ በርካታ ሴት ተማሪዎች አምበርቾ የሚባለውን ትልቁን ተራራ ሳይቀር እየወጡና እየወረዱ ከእኛ እኩል ይሰሩ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- የመሬት ላራሹ አዋጅን ተከትሎ መሬት ለጭሰኛው እንድታከፋፍሉ በዘመቻው የተሳተፋችሁ ሰዎች ኃላፊነት ተሰጥቷቸውም ነበር:: እስቲ ስለዚህ ሥራ ደግሞ በጥቂቱ ያጫውቱን?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- አዋጁ እንደታወጀ የምናስፈፅመው እኛ መሆናችን በይፋ ነበር የተነገረው:: መሬት ወርሰን የምናከፋፍለው እኛው ነበርን:: በወቅቱ በጣም የማረሳው አርሾና ሃላባ አካባቢዎች ሁለት ሰዎች የአካባቢውን መሬት በሙሉ ተቆጣጥረው ነበር:: በአካባቢው የነበሩ በርካታ አርሶ አደሮች የሁለቱ ባላባቶች ጪሰኞች ነበሩ:: እነዚህ ባላባቶች መሬታቸውና ንብረታቸው ሲወረስባቸው አካባቢውን ጥለው ወጥተዋል:: በዘመቻው ውስጥ የተሳተፉ አንዳንድ የባላባት ልጆችም ዘመቻ ጣቢያውን ለቀው የወጡበት አጋጣሚም ነበር:: በተቃራኒው ደግሞ ጭሰኞቹ የመሬት ባለቤት በመሆናቸው ከፍተኛ ደስታ ነበር የተፈጠረባቸው:: ከዚህ ቀደም ግን አመቱን ሙሉ ለፍተው ሲያበቁ የባላባቱን ኪስና ጎተራ ነበር የሚደልቡ የነበረው:: እኛም በተሰጠን ትዕዛዝ መሰረት ለእያንዳንዱ ገበሬ በስም ለይተን መሬት መትረን እንዲሰጥ አድርገናል:: በዚህም ጥሩ ሥራ እንደተሰራ አምናለሁ:: በነገራችን ላይ ባላባቶቹ የነበራቸውን የጦር መሳሪያ ጭምር እንወርስ ነበር::
በመጨረሻ ላይ ግን በዘመቻው ከተሳተፉ ሰዎች ከፊሎቹ ጥለው ጠፍተው ነበር፤ ደግሞ የኢህአፓን በራሪ ወረቀቶች በሽልኩታ እየመጡ እናነብ ስለነበር አንዳንዶቹ ስርዓቱን ወደመቃወም ገቡ:: ከእኛ ጋር የነበሩ የአራተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ ዲሞክራሲ መብቶችና አስተምሮዎችን ያስተምሩናል:: እኛም አጠና አልጋ ላይ ማታ ተኝተን በቃል እየነገሩን እንፅፍ ነበር:: በተለይ ‹‹ዲሞክራሲያ›› ትባል የነበረችው የኢህአፓን መፅሔት ከመንግስት ሰዎች ተደብቀን እንደምንም ተራ ጠብቀን እናነብ ነበር:: በአጠቃላይ ፍልስፍናን ዘመቻ ላይ ሆነን ነው አጥንተን የጨረስነው:: ካነበብን በኋላ ደግሞ ጫካ ውስጥ ተደብቀን እንወያይም ነበር:: በመካከላችን ዘመቻውን እናቋርጥና እንጥፋ፤ አንጥፋ የሚል ውዝግብም ተነስቶ ነበር:: በነገራችን ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አብሮን ከዘመቱ ወጣቶች አንዱ ነበር:: እሱ ግን የዘመተው እዛው ትውልድ ሥፍራው አካባቢ ነበር:: እኩል ብንዘምትም ግን እሱ እንደሄደ ሸፍቶ ደደቢት ነው የገባው::
አዲስ ዘመን፡- ለመሆኑ የፖሊስ ሰራዊትን የተቀላቀሉበት የተለየ ምክንያት ነበርዎት?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- ፖሊስ ሰራዊትን የተቀላቀልኩት በአጋጣሚ ነው:: ነገር ግን የፖሊስ መኮንኖች ኮፍያ እና ገበርዲን ልብሳቸውን ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር እወደው የነበረው፤ ሳየው ገና ደስ ይለኛል:: እንዳልኩሽ ከልጅነቴ ጀምሮ የፖሊስ ፍቅር ቢኖረኝም ሁለተኛ ደረጃ እንዳጠናቀኩኝ በቀጥታ ለመማር የተመዘገብኩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር:: ሆኖም ስድስት ኪሎ ካምፓስ ተመዝግቤ በአፍንጮ በር አድርጌ በእግሬ ወደ ፒያሳ እየሄድኩ ሳለ እሳት አደጋ ጋር ስደርስ አጥሩ ላይ በርካታ ወረቀት ተለጥፎ 200 የሚሆኑ ወጣቶች ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ ወረቀቱ ላይ የተፃፈውን ለማንበብ ሲንጠራሩ ተመለከትኩኝ:: እኔም ተሸሎክልኬ የፖሊስ ኮሌጅ ማስታወቂያውን አነበብኩት:: እንደአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የትምህርት ማስረጃዬን ይዤ ስለነበር በዚያው ውስጥ ገብቼ እንደሌሎቹ ልጆች ተመዘገብኩኝ:: በመሰረቱ መመዝገብ የሚችለው የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ነበር፤ እኔ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ስለነበርኩኝ መዝጋቢዎቹ እኔን ለመመዝገብ አቅማምተው ነበር:: ሆኖም ውጤቴ ጥሩ ስለነበር መዘገቡኝ:: እናም በዚያ መሰረት ፈተናውን አልፌ ሰንዳፋ ፖሊስ ኮሌጅ ገባሁና ለሶስት ዓመታት የተለያዩ የቀለም ትምህርቶችን ተከታትያለሁ፤ ሶስት ወር ደግሞ በርሃ ተልከን ወታደራዊ ስልጠና ወስደናል:: እናም በዚህ መሰረት ነው ሰልጥኜ ወደ ሰራዊቱ የተቀላቀልኩት::
በነገራችን ላይ በኢላማ ተኩስ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በማዕረግ ነው የተመረቅሁት:: እንደተመረቅሁኝም በቀጥታ አዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ፣ ሴፍቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ ሆኜ ነው የተመደብኩት:: ስድስት ወር እንደሰራሁ የትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ሆንኩ:: የሚገርመው ያ ቦታ በሙሉ መቶ አለቃ ነው የሚመራው የነበረው፤ እኔ ግን ገና ምክትል መቶ አለቃ ሆኜ ቦታው የተሰጠኝ:: ሥራው ግን ውጥረት የተሞላበትና ከባድ ነበር:: ያም ቢሆን በብቃት ነው ኃላፊነቴን ስወጣ የነበረው::
አዲስ ዘመን፡- እንግዲህ የትራፊክ አደጋ ከተነሳ አይቀር በኢትዮጵያ በየቀኑ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚመዘገብበት ምክንያት ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- እውነቱን ለመናገር እኔ በሰራሁበት ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የነበረው ተሽከርካሪ መጠን በጣም ትንሽ የሚባል ነው:: መንገዶቹም ብዙ አልነበሩም:: የነበረው አደጋ ብዛት ግን ከፍተኛ የሚባል ነበር:: አሁንም ቢሆን አደጋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም:: እኔ በነበርኩበት ጊዜ በተለይ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለውን አደጋ ለመቀነስ የተማሪ ትራፊክ ፖሊስ ማሰልጠን የሚያስችል ጥናት በማጥናት እንዲጀመር አድርጊያለሁ:: በዚያ መሰረትም ከየሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተመልምለው እንዲሰለጥኑ ተደርጓል:: ይህም አደጋውን ለመቀነስ ለምንሰራው ሥራ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልናል ብዬ አምናለሁ::
ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን አደጋው እየሰፋ የመጣው በአሽከርካሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ግዴለሽነት ያለ በመሆኑ ነው:: ይህ ብቻ ሳይሆን የእውቀት ማነስም አለባቸው:: ሹፌር የተባለ ሁሉ እኩል ሹፌር አይደለም፤ ሁሉም ደንብና ስርዓትን ጠብቆ የሚያሽከረክር አይደለም:: ብዙዎቹ በትንሽ ቦታ ላይ ፍጥነት መቆጣጠር አይችሉም:: አሁንም ድረስ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ያለው የፍጥነት ወሰን ያለመጠበቅ ችግር ነው:: ሁልጊዜም ቢሆን ፍጥነት ካለ አሽከርካሪው ሊያድነው የሚችለውን ሰው ይገጨዋል:: አሁንም እንደምናየው ብዙ አደጋ ነው በየቀኑ እየደረሰ ያለው:: ስለዚህ ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው ለማንኛውም አሽከርካሪ መንጃ ፍቃድ ከመሰጠቱ በፊት በቂ እውቀትና ግንዛቤ መስጠት ስንችል ነው የሚል ሃሳብ አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- ራሺያ ለትምህርት ሄደው እዚያው እንዲቀሩ ጥያቄ ቀርቦሎት ሳይቀበሉ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱበት ምክንያት ምን ነበር?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- ልክ ነሽ፤ ትምህርቴን በጨረስኩበት ወቅት ደርግ ወድቆ ወያኔ በትረ-ስልጣኑን ሲረከብ የራሺያ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ፖለቲካ ጥሩ ባለመሆኑ እዚያው እንድንቀርና ሥራም ሆነ አስፈላጊው ሁኔታ እንደሚመቻችልን ነግረውን ነበር:: ሆኖም ያስተማረን አገርና ህዝብ እንደመክዳት ስለቆጠርኩት አሻፈረኝ ብዬ ለመመለስ ወሰንኩኝ:: እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች ከእኔ ጋር የነበሩ ኢትዮጵያኖችንም ሳይቀር አስተባብሬ ነው ይዤያቸው የመጣሁት:: እንደመጣሁም ያስተማረኝ ተቋም አላሰፈረኝም፤ አስራ አምስት ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፖሊስ ምህንድስና ዋና መምሪያ ኃላፊ አድርጎ መደበኝ::
በዚያ ኃላፊነት ላይ መስራት እንደጀመርኩ ደግሞ የአገሪቱ አጠቃላይ ችግር ወደ እኔ መምጣት ጀመረ:: ምክንያቱም በየክልሉ ያሉ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ ቢሮ የላቸውም ነበር:: በወቅቱ አንድ ለእናቱ በሚባል ደረጃ እኔ ብቻ ነበርኩኝ በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ ዋና መሃንዲስ የነበርኩትና የግንባታ ሥራዎች ጉዳይ ሁሉ ወደ እኔ ቢሮ ነበር የሚመጣው:: በየክልሉ እየዞርኩኝ ከቦታ መረጣ ጀምሮ የፖሊስ ተቋሞችን ህንፃ እስከመስራትና ግንባታውን እስከመቆጣጠር ድረስ ኃላፊነት ተጥሎብኝ ነበር::
ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ከባድ የህንፃ ዲዛይን ስራዎች ይመጡ ጀመር:: የየክልሎቹን፤ የአዲስ አበባና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዘመናዊ ህንፃ ዲዛይኖችን እንዲሰሩ ጥያቄ ቀረበልኝ:: በዚያ ወቅት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ራሱ የራሱ ህንፃ አልነበረውም፤ ዝም ብሎ የጣሊያን ዳሳሳ ቤት ውስጥ ነበር ይሰሩ የነበሩት:: እናም አሁንም ድረስ የምኮራበትና ደስ የሚለኝ ነገር አሁን የምናየውን ትልቁን የፌደራል ፖሊስ ህንፃ ዲዛይን መስራቴ ነው:: የሚገርምሽ ይህ ዲዛይን የተመረጠው አስር ዲዛይን ሰርቼ ከእነዚያ ውስጥ ነው::
ሰመራ ከተማ ያለው የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ህንፃ ዲዛይንም እኔ የሰራሁት ነው:: የዚያ ዲዛይን መሰራት ተከትሎ ነው ከተማዋ እየተስፋፋችና እያደገች የመጣችው:: በተመሳሳይ የሱማሌ ክልል ፖሊስ ህንፃን፤ የአዲግራት ፖሊስ ማሰልጠኛን፤ የሐረር ፖሊስ ማስፋፊያ ህንፃና በርካታ ተቋማትን ህንፃ ሰርቻለሁ:: በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በሙያዬ ምክንያት አካልያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- እንደፌደራል ፖሊስ ያሉ ትልልቅ ህንፃዎች መሰራት በተለይ ለከተሞች እድገትና መስፋፋት ምን አበርክቶ አምጥቷል ብለው ያምናሉ?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- ይሄ ምንም ጥርጥር በሌለው መልኩ ትልልቅ ህንፃዎች መሰራት ከከተማ ውበት ባሻገር እድገት እንዲመጣ፤ ዘመናዊ ከተማ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ባይ ነኝ:: በተለይም እንደ ፖሊስ ያሉ ህዝባዊ ተቋማት ደረጃውን በጠበቀና እንዲህ ባማረ መልኩ ህንፃ መሰራቱ አሰራራቸውንም በዚያው ልክ እንዲያዘምኑ፤ ደህንነታቸውና ሚስጢራዊነታቸውም የተጠበቀ እንዲሆን አስችሏል:: እኔም እንደአንድ ባለሙያ ይህንን የፌደራል ፖሊስን ከነበረበት ዳሳሳ ጎጆ ወጥቶ በዚህ ያማረ ህንፃ ባለቤት እንዲሆን በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ:: በነገራችን ላይ ይህ ህንፃ ከመሬት ውስጥ ጀምሮ እስከ ሂሊኮፍተር ማረፊያ ድረስ ያለው ግዙፍ ህንፃ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖሊስ ተቋም እንዲሆን የላቀ ሚና አለው:: አሁን ቢሆን እንደጊዜው እየታየ ዘመናዊ ህንፃዎችን መገንባት አለበት:: ይህ ሲሆን ነው ከተሞችንም ሆነ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ የምንችለው::
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች የሚገነቡ ህንፃዎች ለህዝቡ የሚመቹና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን እንዲገነቡ በማድረግ ረገድ ያለው ክፍተት ምንድን ነው?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡– አንድ ከተማ አደገ የሚባለው በርካታ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ስለተገነቡ አይደለም:: በተለይም በህንፃው የሚገለገለውንም ሌላውንም ማህበረሰብ ያማከለ፤ ከአጠቃላይ የከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር የተናበበ ሊሆን ነው የሚገባው:: ከዚህ አንፃር አንቺም እንዳልሽው በተለይም በአዲስ አበባ ብዙ የሚታዩ ችግሮች አሉ:: የሚገነቡት ህንፃዎች አሁን ያለውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ትውልድ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል:: ህንፃው በተገናባበት አካባቢ የሚሰራውን ስራ ማጤን የግድ ይላል:: ህንፃ ብቻ መስራት እድገት አያመጣም፤ ጠቢባንም አያደርገንም:: ይልቁንም የሰው አስተሳሰብ መቀየርና ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አድርጎ መቅረፅ ያስፈልጋል:: ደግሞም የትኛውም መሰረተ ልማት የሚገነባው ለህዝብ ጥቅም እንደመሆኑ ከግባታው ጎን ለጎን የህዝቡን ኑሮ መለወጥ ያሻል::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ይገልፁታል?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ሁሉም ነገሬ ነው:: አገሬን ከምንምና ከማንም በላይ ነው የምወዳት:: አስቀድሜ እንዳልኩሽም ውጭ የመኖር አማራጭ እያለኝ ጥዬ የመጣሁት አገሬን ስለምወዳትና ለአገሬና ለህዝቤ የበኩሌን ድጋፍ ማድረግ አለብኝ ብዬ ስለማምን ነው:: ከልጅነቴ ጀምሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንድወድ ተደርጌ በመቀረፄ አገሬን ሲነኩብኝ አልወድም:: በሌላ በኩል ካለፉት 30 ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያዊነትን የሚከፋፍል ስርዓት በመምጣቱና ትውልዱም እኔ ብቻ ብሎ እንዲቀረፅ መደረጉ ያሳዝነኛል:: በግሌ አንዱን ብሔር ከሌላው የሚለያይ አስተሳሰብን አልቀበለውም:: ለእኔ ሁሉም የሰው ልጅ እኩል ነው:: ደግሞም ከምን በፊት ሰው መሆን ይቀድማል ብዬ ነው የማምነው::
በእኔ እምነት አሁን ያለው ትውልድ ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ አገሩን እንዲወድና በአንድነት አገሩን እንዲያሳድግ ተደርጎ አልተቀረፀም:: ይህም በመሆኑ ነው አሁን ላይ የምናየው የመከፋፈል ችግር እየተፈጠረ ያለው:: ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂ የሚሆነው ግን የፖለቲካ ስርዓቱ ነው:: በወታደራዊ ቋንቋ ‹‹ተመልከት አላማህን፤ ተከተል አለቃህን›› እንደሚባለው ሁሉ ትውልዱም እንዲህ አገር ጠልና ራስን ብቻ አፍቃሪ የሆነበት ምክንያት በፖለቲካው ስርዓትና በነበሩን መሪዎች ምክንያት ነው ባይ ነኝ:: አሁንም ቢሆን አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት የፖለቲካም ሆነ የትምህርት ስርዓቱ መፈተሽና መስተካከል አለበት ብዬ አምናለሁ:: ትውልዱንም በኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ መቅረፅ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ እስቲ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ምን ሊሰራ እንደሚገባ ይግለፁልንና ውይይታችን በዚሁ እናብቃ?
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- ልክ ነው፤ ከምንም በፊት የአገር ሰላምን ማረጋገጡ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል:: እንዳልኩሽ አሁን የምናየው መከፋፋል ቀርቶ ወደ አንድነት መምጣትና አገራችን ከገባችበት ችግር ለማውጣት መረባረብ አለብን:: ከምንም በላይ በፖለቲከኞች አለመግባባት ምክንያት እየሞተ ያለውን ንፁህ ሕይወት ዜጋ ሕይወት መታደግ አለብን:: በእውነቱ በሰሜን ኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በግፍ እያለቀ ያለው ዜጋ በጣም ነው የሚያሳዝነኝ::
በእኔ እምነት ይህ ጦርነት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል:: ፖለቲከኞች ተቀራርበው መነጋገርና ለአገር ዘላቂ ሰላም ዋጋ መክፈል አለባቸው ባይ ነኝ:: አሁን ላይ በመንግስትና በወያኔ ሰዎች መካከል እየተደረገ ስላለው ድርድር መረጃ ባይኖረኝም ግን ድርድሩ የሁሉንም ህዝብ ጥቅም የማከለ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ:: በነገራችን ላይ በዚህ ጦርነት ምክንያት ህዝብ ሳይሆን እየጠፋ ያለው ተፈጥሮም ጭምር ነው:: እንዳየነውም ከሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቱ ባሻገር ብዙ ሃብት ሊሰጠን የሚችል መሬት ሳይቀር ነው ጉዳት የደረሰበት::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ::
ሻለቃ ኢንጂነር ወ/ሚካኤል፡- እኔም ለሰጣችሁኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7 /2014