
አዲስ አበባ፡- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የታላቁ ህዳሴ ግደብ 2ተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
ግድቡ ኢትዮጵያውያን ተቸግረንና ከመቀነታችን ቀንሰን የገነባነው ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ አባይ የጠላቶቹን ሟርት ወደ አርት እየቀየረ ፣ አቧራውን አሻራ አድርጎ እነሆ ከ602 ሜትር ከፍታ ላይ ሆኖ እየበረረ ነው ብለዋል።
በታሪክ ውስጥ ማለፍና ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚባሉ ሁለት ነገሮች አሉ ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ በታሪክ ውስጥ ማለፍ ዕድል፣ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ግን ዕድልም ድልም ነው፡፡ ይሄ ትውልድ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ባለ ዕድልም ባለ ድልም ነው፡፡ የሺ ትውልድ ጥያቄ በሚመለስበት ዘመን ተገኝቶ ግድቡ ሲገደብ በዓይን ማየት፣ በእጅ መዳሰስ፣ በእግር መርገጥ ባለ ዕድል ሲያደርግ፤ ለግንባታው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ከለገሡት፣ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ለዓባይ ከሚከራከሩት፣ ታሪክ ሠሪ ጀግኖች ወገን መሆን ደግሞ ባለ ድል ያድርጋል ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተጋርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በመልዕክታቸው፤ ‹‹እነሆ አሁን የሕዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውሃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው፤ ከዘፈንና እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢትዮጵያን በብርሃኑ ሊያደምቃት፣ ኃይል ሆኖ ሊያበረታት ከጫፍ ደርሷል። በፈጣሪ ርዳታና በኢትዮጵያዊ ወኔ ሙሉ በሙሉ ግንባታውን አጠናቅቀን የልባችን እንደሚሞላ አልጠራጠርምና እንኳን ደስ ያለን›› ብለዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም