አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከመጪው መጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በዘላቂ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ እንደምታካሂድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ለአዲስ ዘመን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ለሦስት ቀናት በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የሚካሄደው ኮንፍረንስ በጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር አዘጋጅነት ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማትና ከዓለም አቀፉ የገንዘበ ትብብር ጋር በመተባበር ነው፡፡
እንደ መግለጫው ከሆነ፤ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች በዓለም ዙሪያ ለኢንዱስትሪና ለቴክኖለጂ ልማት ዋነኛ ሞተር የመሆናቸውን ያህል የአካባቢ ሀብቶችን ያለአግባብ በመጠቀማቸውና በአካባቢ ላይ በሚያደርሱት ብክለት ይወቀሳሉ፡፡ ‹‹ዘላቂ የኢንዱስትሪ አካባቢዎች›› በሚል ፅንሰ ሃሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው ኮንፍረንስም አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በማመጣጠን ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲኖር በማበረታታት ለወቀሳው ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
‹‹በዘንድሮው ኮንፍረንስ በኢንዱስትሪ ሽግግር፣ ኢንዱስትሪ ፖርኮችና በክላስተር ልማት የተገኙ የአገራት ዓለም አቀፍ ተመክሮዎች ይቀርባሉ›› ያለው መግለጫው፤ በተለይም የውጭ ባለሀብቶችን ወደ አፍሪካ ለመሳብና የሥራ እድሎችን ለማሳደግ በሚያስችሉ መንገዶችና አገራቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚያስችላቸው መንገዶች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ውይይት ያካሂዳሉ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ፣ ለሥራ እድል ፈጠራና ለአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነታቸውን ያረጋግጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡
ኮንፍረንሱ በኢኮኖሚ ብልፅግና ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ እድገትን ለማሳካትና አካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችንም ከግምት ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል ትክክለኛ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የሚያስችል ብቻ ሳይሆን በመንግሥትና በኢንዱስትሪዎች በኩል ያሉ ውሳኔ ሰጪዎች በየአገሮቻቸው የኢንዲስትሪ መዋቅራቸውን በቀጣይ እንዴት መቀየስ እንደሚችሉ የሚገፋፋ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል፡፡
ኮንፍረንሱ ከአሁን ቀደም በህንድ፣ ቻይና፣ ኢንዶኔዢያ፣ ቱርክ፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮና ግብጽ የተካሄደ ሲሆን፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ለስምንተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከአፍሪካ፣ አውሮፓና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ከ300 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይሳተፉበታል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ