“በቃሉ ትርጉም እንስማማ!”፤
ንባበ መንገዳችንን የምንጀምረው በሃሳብ ላይ የሚደረግን ፍልሚያ አስመልክቶ ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች እንደ መርህ የሚቀበሉትን አንድ የተለመደ አባባል በማስታወስ ይሆናል። እነዚህ ተጠቃሽ ፈላስፎች የአደባባይ ሙግታቸውን፣ የግለሰብ አታካራቸውንና ቡድናዊ የሃሳብ ፍልሚያዎቻቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ፤ “ሃሳባችን እንዳይበታተን በመጀመሪያ በምንወያይባቸው የቃላት ትርጉም ላይ እንስማማ” የሚሉት ዘመን ዘለቅ ብሂል ነበራቸው ይባላል።
ቅዱስ መጽሐፍም እንዲሁ፤ “ሁለት ሃሳብ ያለውና የሚወላውል ሰው… አንዳች አያገኝም”፤ ምክንያቱም ሃሳቡን ማስከን ያልቻለ ሰው፤ “በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ይመሰላል (ያዕቆብ 1፡6 – 8) ይለናል። ስለዚህም፤ የዋናውን ርዕሰ ጉዳያችንን ሁለት ቃላት (አውሎ ነፋስ እና እብቅ የሚሉትን)፤ መዛግብተ ቃላቱ እንዴት እንደበየኗቸውና በዚህ ጽሐፍ ውስጥም ምንን ለማመልከት በውክልና እንደተመረጡ መደላድሉን ካሳመርን በኋላ ወደ ዋናው የዕለቱ ጉዳያችን ዘልቀን እንገባለን።
“አውሎ ነፋስ፡- ኩርፊት፣ ጠሮ፣ ጥቅል ነፋስ፣ አቧራን ወደ ሕዋ የሚበትን፣ ጉድፍ ይዞ የሚነሳ፣ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ኃይለኛ ነፋስ” በማለት በይኖታል። በዘርፉ ባለሙያዎች ትነታኔ መሠረትም ነፋስ የሚመደበው በአራት ባህርያት ሲሆን አውሎ ነፋስ ላቅ ብሎ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል። እናስታውሳቸው፤ ለምለም ነፋስ፡- ቀስ ብሎ የሚነፍስ ሰላማዊ ነፋስ፣ ልክስከስ ነፋስ፡- አቧራ ወደ ላይ አንስቶ ለትንሽ ደቂቃ ያህል ካንከባለለ በኋላ በቶሎ የሚሰክን፣ ወዠብ ነፋስ፡- ዝናብ ቀላቅሎ የሚነፍስ ነፋስ ተብለው ተደንግገዋል።
አራተኛው አውሎ ነፋስ (weird wind/Tornedo) እና እንደየሀገሩ በልዩ ልዩ ስያሜዎች የሚታወቀው ሞገደኛ የተፈጥሮ ክስተት ግን በኃይል እየተሽከረከረ የተለያዩ ቁሳቁሶችን፣ እንስሳትንና ሰዎችን ሳይቀር ወደ ሰማይ በማጎን ከፍተኛ የሕይወትና የንብረት ውድመት የሚያደርስ አደገኛ ነፋስ መሆኑን መዛግብተ ቃላቱና ምሁራኑ ፍቺውን አስታውቀውናል። ይህንን መሰሉን አውዳሚ አውሎ ነፋስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የጠቀሰው “አውራቂስ” በማለት ሲሆን አደገኛነቱን የገለጸውም ይጓዙበት የነበረውን ግዙፍ መርከብና ጭነቶችን እንደምን በታትኖ እንዳወደማቸው በሥዕላዊ ገለጻ በመተረክ ነው።
የአውሎ ነፋስና የእብቅ ማንጸሪያዎች፤
በአውሎ ነፋስ ለመመሰል የተሞከረውም ግራ ገብና “በረከተ መርገም” የሆኑብንን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ነው። የነገውን መተንበይ ቢቸግርም በዚህ ወቅት እንደምናስተውለው ቴክኖሎጂው ጡንቻውን አፈርጥሞ ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖትና የጂኦግራፊ ክልል ሳይገድበው የዓለምን አዳሜና ሔዋኔ የሰው ዘሮችን በሙሉ በአንድ ቅርጫት ማጎሪያ ውስጥ ለመክተት አቅም ያገኘበት ጊዜ ይመስላል። በሌላ አገላለጽ እናብራራው ካልን ቴክኖሎጂው አራቅቆ ባመቻቻቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ዓለማችን በጣታችን ጫፍ ላይ እንድታርፍ ግድ ብሏታል። በእብቅ ለመወከል የተፈለገው የዚሁ የማኅበራዊ ሚዲያ “የይዘት ምርትም” ምን ያህል የነገሮችን ሥርና መሠረት እያናጋ እጅግ የከፋ ጥፋት እያደረሰ እንዳለ ዕለት በዕለት እያስተዋልን ነው።
ይህንን ጽሐፍ የሚያነቡ የጋዜጣው ወዳጆችና ቤተሰቦች በመረጃና በ“ማዝናኛ” የሚፈርጇቸውን የየግል መሻታቸውን ለማሟላት ከዚህ ጽሑፍ ንባባቸው አስቀድሞ የእጅ ስልካቸውን ወይንም የኮምፒውተራቸውን ቁልፎች ለተለያዩ የግልና የጋራ ጉዳዮቻቸው መከወኛነት በጣቶቻቸው ሳይነካኩ እንዳልቀረ መገመቱ አይከብድም።
ቴክኖሎጂው አራቆ ባቀረበላት የመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ግዙፏ ዓለማችን ተኮማትራ ልክ እንደ አንድ የአተር ፍሬ አንሳ መዳፋችን ላይ ወድቃለች። ብዙዎቹ እንደ ሱስ ተጠናውቷቸው የገበሩለትን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና በመዳፋችን ውስጥ ስናሽሞነሙን የምንውለውን የእጃችንን ስልክ አገልግሎት በተመለከተ ረጋ ብለን ብናሰላስል ይህ አገላለጽ በሚገባ ግልጽ ይሆንልናል።
የእጅ ስልክን ጉዳይ ከጠቀስን አይቀር መራር ትዝብታችንን እንዲያለዝብልን ከጥቂት ዓመታት በፊት የግል ሲም ካርድ ለማግኘት የነበረውን ውጣ ውረድ አስታውሰን እንለፍ። የዛሬ ጀንበር አትስማንና አንዲት ሲም ካርድ ለማግኘት የመኪና ሊብሬ ወይንም የቤት ካርታ እንድናሲዝ በባለሥልጣኑ ኢትዮ ቴሌኮም (በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን) መጠየቅ ግድ እንደነበር የደረስንበትና ጣጣውን የተጋፈጥን ዜጎች የምናስተውሰው ነው። የስልክ ቁጥር የምርጫ ፕሮቶኮል እንደነበርም አይዘነጋም። ለምሳሌ፡- በ20 እና በ21 የሚጀምሩ የስልክ ቁጥሮች በአክብሮት ይታደሉ የነበረው በሀብት ለከበሩ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች፣ በሥልጣን ለመጠቁ፣ እጃቸውና የአንደበታቸው ምላስ ሹማምንቶቹንና ነጋዴዎቹን ለመደገፍ ለሚረዝሙ አቀባባይ ደላሎችና የዕለት እንጀራቸውን ከዚያው ከቴሌ ለሚያገኙ ግለሰብ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ነበር።
በ40 ቁጥር የሚጀምሩ የስልክ ቁጥሮች ደግሞ ለምሁራንና ለተመራማሪዎች በሚል መወሰኑና በዚህን መሰሉ ክፍፍል ምክንያትም ምን ያህል የተቋሙ አንዳንድ ሠራተኞች ራሳቸውን በሙስናና በማጭበርበር ውስጥ ዘፍቀው እንደነበር ያልመሸበት ትናንታችን ምስክር ነው። ይህን መሰሉን መራር ትዝታ ወደ ኋላ ዞር ብለን ስናስታውስ መገረም ብቻም ሳይሆን አምርረን ድህነታችንን እንድንጠየፍ ጭምር ግድ ይለናል፤ ስሜቱ ዛሬም ድረስ የለቀቀን አይመስልም።
ይህ ጸሐፊ የውጭ ሀገር ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሀገር ቤት በተመለሰበት ወቅት ለእጅ ስልኩ የሲም ካርድ ለማግኘት ያጋጠመው ውጣ ውረድና እንግልት የትራዤዲ ተውኔት ያህል እንደምን ስሜቱን እንዳኮመጠጠና በወቅቱ ይታይ በነበረው ብልሹ የአሰራር ዘዴ ምክንያትም ምን ያህል እንግልት እንደደረሰበት በግለ ታሪክ መጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ስለሚታወስ ወደፊት በግላጭ ይነበባል።
ሀገራዊ ገመናችን ሲፈተሽ፤
በአውሎ ነፋስ የመሰልነው የቴክኖሎጂው የዕድገት ሩጫ እንደ አትሌቶቻችን በሜትር ወይንም በኪሎ ሜትሮች በሚለካ ርቀት “ላብን አፍስሶ” የሚጠናቀቅ ውድድር እና ሪከርድ “ይሰበርበታል” ተብሎ የሚፎከርበት ጉዳይ አይደለም። በጭራሽ። ቴክኖሎጂው መሽቶ በነጋ ቁጥር በአስደማሚ ግኝቶች “እጃችንን በአፋችን ላይ እንድንጭን” የሚያስገድዱንን ብዙ የፈጠራ ግኝቶች ማምረቱን እያስተዋልን ነው። እርግጥ ነው ዘመኑ “ለቴክኖሎጂ ውጤቶች አጉራህ ጠናኝ” ብለን እንድንገብር በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታ ጭምር እንደተቆራኘን አይካድም። በአዎንታዊ አድናቆት የሚንቆለጳጰሰውንና አጃኢብ እያሰኘን የምንገረምበትን በረከቱን ለጊዜው አቆይተን ወደ አልተፈለገ የሕይወት አቅጣጫ ትውልዱን እየመራ ያለውን መርገምታዊ ጎኑን ብቻ ጫን ብለን ለመዳሰስ እንሞክራለን።
“በረከተ መርግም” ብለን ተንደርድረናልና፤ ከምንጊዜውም ይልቅ ዛሬ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በተመለከተ “አሰሩን ከጥፍጡ” እንዴት መለየት እንደሚገባን ጊዜና ፋታ ሳንሰጥ መወያየት ያለብን ስለመሰለን ይህንን ዋና ርዕሰ ጉዳይ ለዛሬው ውይይት መርጠናል። ሀገራዊና ነባር ፈሊጣዊ ብሂላችን “ነፋስ ገባው” በማለት የሚገልጻቸው በርካታ ስሜቶችን ነው። “ነፋስ ገባው”፡- ሲባል ሆዱ ጎሸ፣ አቄመ፣ ፍቅር፣ አንድነትና ስምምነት አጣ፣ ተለያየ፣ ተጠፋፋ፣ ተቀያየመ ወዘተ.” ማለት ነው። በአውሎ ነፋስ የመሰልነው የቴክኖሎጂ ግኝት የሆኑት የማሕበራዊ መድረኮችም ሀገራዊ ክፍተት ፈጥረው እንደምን “ነፋስ እንዳስገቡብን” ዝርዝር ጥናት ሳያስፈልገው በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል። ቀላል ማሳያ ሊሆን የሚችለው ግን ደጋግመን እንደገለጽነው በእጃችን መዳፍ ላይ አሳርፈን ስንግባባበት፣ ስንናቆርበትና ስንፋጅበት የምንውለውን ስልካችንን መጥቀሱ ብቻ በቂና ከበቂ በላይ ነው።
በአሸባሪዎች እኩይ ድርጊት የንጹሐን ደም እንደ ጎርፍ የሚፈሰውና በምስኪኖች ላብና ጥረት የተገኘ ሀብትና የመንግሥት ተቋማት እንዳልነበሩ ሆነው እንዲፈራርሱና እንዲዘረፉ የሚፈረድባቸው በአብዛኛው ከማሕበራዊው ሚዲያው አውድማ ላይ የሚታፈሱ እንክርዳድ ሃሳቦች በጨካኞች አናት ላይ ወጥተው ስለሚያሰክሯቸው ነው። የዘረኝነት እብቅና የጽንፈኝነት ገለባም ከመቼውም ዘመን ይልቅ በዚህ በእኛ ጀንበር እየተጫነ የሚበተነው በአውሎ ነፋስ በመሰልናቸው ቴክኖሎጂ ወለድ በሆኑ በርካታ ማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት መሆኑ ተደጋግሞ አቤቱታ ቀርቦበታል።
የሃይማኖት ተቋማት፣ መሪዎቻቸውና አገልጋዮቻቸው፣ የመንግሥት የሥራ መሪዎችና የበላዮች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚዋረዱበትና ሰብዓዊ ክብራቸው ሳይቀር የሚንቋሸሸው ለዘመናት ከዳበሩት በጎ ማሕበራዊ እሴቶች ውጭ ባፈነገጠ መልኩ በሚሰራጩና እብቅ ይዘት ባላቸው መልእክቶች አማካይነት ነው። በጨለማ አስተሳሰብ የተጋረዱና ለክፋት ተልእኮ የተማማሉ እኩይ የማሕበራዊ ሚዲያ ጀብደኞች ስማቸውንና ማንነታቸውን እየለዋወጡ የሚዘሯቸው እብቅ አስተሳሰቦች በሀገር ላይ ያደረሱትና እያደረሱ ያሉት ጥፋቶች ከብዛታቸው የተነሳ በዋጋም ሆነ በመጠን የሚገመቱና የሚመዘኑ አይደሉም።
“ምታ ነጋሪት፤ ቀስቅስ ሠራዊት” የሚል መፈክር በማስተጋባት ቀን ከሌት በሚተጉ የማሕበራዊ ሚዲያ ሠልፈኞች አማካይነት ከግለሰብ እስከ ሀገር የደረሱት ጉዳቶች ምን ያህል ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠንተው ይፋ ቢደረጉ ለበጎነት ሳይቀር የምንጠቀምበትን ማሕበራዊ ሚዲያ “ሀራም” በማለት “በውጉዝ ከመ አሪዮስ” ውሳኔ ጭርሱኑ በተፋታነው ነበር። የአውሎ ነፋስ አናፋሾቹ እውነታነት በሌለውና በፈጠራ በተቀናበረ ታሪክ የምን ያህሉን ቤት እንዳፈረሱ፣ የምን ያህሎችን ስሜትና መንፈስ እንደሰበሩና እንዳኮላሹ፣ ምን ያህሎቹን ለመከራና ለስቃይ እንደዳረጉ “ቤቱ ይቁጠረው” ብለን ካላለፍን በስተቀር ነካክተን የምንዘልቀው አይደለም።
ድንጋዩን ዳቦ ነው፣ እሬቱን ወለላ ማር ነው፣ እርኩሱን ቅዱስ ነው የሚሉ “የእብቅ ሃሳብ ነጋዴዎች” በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ የፈጸሙትን ሰይጣናዊ ተግባራት ብዙም ባይሆኑ ጥቂቶች በድፍረት አደባባይ እየወጡ ምስክርነት ሲሰጡ እያስተዋልን ነው። እብቅ ገለባ ዐይን ውስጥ ሲገባ እንደሚያስነባ ሁሉ በእብቅ የመሰልናቸው የማሕበራዊ ሚዲያ ልጥፎች የሚያስለቅሱት ሥጋዊ ዐይንን ብቻ ሳይሆን ነፍስና ስሜትንም ጭምር ነው።
የነፋስ ዓይነቶችን በተመለከተ ቀደም ብለን እንደዘረዘርነው ለሰስ ብሎ በሚነፍስ ነፋስ የሚመሰሉ ለምለም ሃሳቦችን ከማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማግኘት መቻሉ እርግጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ አነፋፈስ ጤናማ መሆኑን መካድ ስለማይገባ የምናልፈው አመስግነን ነው። በአንጻሩ አቧራ በሚያጨሱ ልክስክስና ወዠባማ ነፋሳት የሚመሰሉ መልእክቶችና አውዳሚ ሃሳቦችም የተለመዱ የማሕበራዊ ሚዲያው ክስተቶች መሆናቸው የሚካድ አይደለም።
ጽሑፉን የምንጠቀልለው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት እንደሚከተለው አቤቱታ በማቅረብ ይሆናል። የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ ሕጉ ጸድቆ ተግባር ላይ ይዋል ከተባለ ወራት ተቆጥረዋል። እስከ ዛሬ ሊተገበር ያልቻለበት ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚታወቁ ግለሰቦችና ቡድኖች “እዩን፣ ለዩን፣ ስሙን” እያሉ አዋጅ እየለፈፉ እያየንና እየሰማን ሕጉ ራሱ ለምን “በሕግ አምላክ!” ለማለት አቅሙ ተልፈሰፈሰ? መልስ ያለው መልሱን ቢያሳውቀን፣ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለልሆነውም “እምቢታውን በይፋ ቢገልጥልን” አውሎ ነፋሱ ቢያንገዳግደንና እብቁ ቢያስለቅሰንም ቁርጣችንን አውቀን “ተው ቻለው ሆዴ” እያልን በማንጎራጎር ቀኑን እንገፋ ነበር። እባካችሁ ሕዝባዊ እሪታችንን አድምጡልን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 4 /2014