የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቅርቡ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ሰባተኛው ስለ ኢትዮጵያ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ላይ የመወያያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ በቀረበው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ ከተንሸራሸሩት ሀሳቦች የግብርናው ዘርፍ አንዱ ነው፤ የመድረኩ ተሳታፊዎችም ሆነ በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የፕላን ኮሚሽን ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ዘርፉ የነበረበትን፣ አሁን የሚገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በግብርናው ዘርፍ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፤ ጥያቄዎችንም አንስተዋል። የመድረኩ ተሳታፊ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አማንይሁን ረዳ እንደተናገሩት፤ የግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኑሮን ለማሻሻል፣ ለኢንዱስትሪዎች በቂ የጥሬ ዕቃ ግብአት ለመሆን፣ ለወጭ ንግዱ (ኤክስፖርት) በቂ ምርት በአይነት፣በብዛትና በጥራት ለማቅረብ የሚያስችል ሰፊ ዕድል እንዳለው ይታወቃል። 70 በመቶ የሚሆነው የወጭ ንግድ(ኤክስፖርት) ድርሻ የግብርናው ዘርፍ ሲሆን፣ የአብዛኛው ዜጋ ኑሮም የተመሰረተው በዚሁ ዘርፍ ነው። ህዝብ የመመገብ ድርሻውም ከፍተኛ ነው።
አቶ አማንይሁን በግብርናው ላይ የተሰራው ስራ ግን በቂ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። ግብርናው በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲያመጣ ከሚፈለገው ተልዕኮ አንጻር ሥርነቀል ለውጥ ተግባር መከናወን አለበት የሚል እምነት እንደሌላቸው ነው ሀሳብ የሰጡት።
መንግሥት ለገጠር ልማትና ለግብርናው የሚመድበው በጀትም በቂ ነው የሚል እምነት የላቸውም። አርሶ አደሩና በዘርፉ የሚሰማራው ባለሀብት የመሬት ባለመብት እንዲሆን አለመደረጉም በመንግሥት ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳም በመጠይቅ ይጠይቃሉ።
አቶ አማንይሁን ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግሥት በዘርፉ ያከናወናቸውንም ተግባራት አድንቀዋል። መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ ባለው የኩታገጠም እርሻን በይሁንታ ያነሳሉ፤ በዚህ አሰራር በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገና እንቅስቃሴውም ውጤት እያስገኘ መሆኑን መገንዘባቸውን ይገልጻሉ። መንግሥት ከዚህም በላይ በመስራት ዘርፉ ሥርነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚሉት፤ የግብርና ዘርፉ ለሀገር ዘርፈብዙ ጠቀሜታ እያስገኘ ቢሆንም፣ በመንግስት በኩል የሚደረግለት የፋይናንስ ድጋፍ አናሳ ነው። መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠው በጀትም ከፍ ማለት ይኖርበታል፤ ባንኮች ለዘርፉ የሚሰጡት የብድር መጠን ዘርፉ ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር አነስተኛ ነው። በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚለቀቅ ገንዘብ መኖር አለበት። ለዘርፉ በብድር የሚሰጠው የወለድ መጠንም ቅናሽ እንዲኖረው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።
አቶ አማንይሁን፤በምግብ እህል ራስን መቻል የሉዓላዊነት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ኢትዮጵያን ማሳደግ ማለት የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ኑሮ መቀየር እንደሆነም በመጥቀስ፣ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተወዳድራ ልታመጣ ከምትችለው ውጤት በላይ በግብርናው ዘርፍ ማሸነፍ የምትችልበት ዕድል መኖሩን በመጥቀስም፣ በግብርና ምርታማነት ላይ መስራቱ አዋጭ እንደሆነ አመልክተዋል።
ህዝብን ለመመገብ የሚያስችል ምርታማነት እንዲኖርም የሥነህዝብ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት። ባለፉት አራት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ከ11 ሚሊየን በላይ መጨመሩን ጠቅሰው፣ ይህ አሀዝ የስዊድን ህዝብ ብዛት ወይንም የቦትስዋናን ህዝብ አራት እጥፍ እንደሆነም ያብራራሉ። የህዝብ ዕድገቱ ካለው የተፈጥሮ ሀብትና የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር እንዲመጣጠን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ደበላ፤በልማት ውስጥ ምርትና ምርታማነት መጨመር አንዱ ተልዕኮ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተመረተውን ተደራሽ ማድረግ ላይ በስርአት የመመራት ክፍተት እንደነበር አንስተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነትም በቡናው ዘርፍ የሚስተዋለውን ክፍተት አንስተዋል። የምርት አቅርቦት ብቻ ሳይሆን፣ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ ለመጠቀም ያለው አሰራር ምቹ እንዳልነበር ጠቅሰው፣ የወጭ ንግድ ገቢ ላይ የተሻለ እድገት እንዳይኖር ተጽዕኖ አሳርፎ እንደነበር ያስታውሳሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በባለስልጣኑ በተወሰዱ የመዋቅርና የማሻሻያ እርምጃዎች ለውጭ ገበያ ይቀርብ የነበረውን ቡና ከሁለት መቶ ሺ ቶን አሁን ወደ ሶስት መቶ ሺ ቶን ማሳደግ ተችሏል። በቡና ላይ የተወሰደው የማሻሻያ እርምጃ ያስገኘውን ለውጥ በሌሎች የግብርና ውጤቶች ላይ በተሞከሮ በመጠቀም ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይቻላል። የነበረው የፖሊሲ አቅጣጫም የተወሰኑት ብቻ ተዋናይ እንዲሆኑ ያደርግ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች ከቀረቡት ሀሳቦች አንዱ የሰው ሀብት አጠቃቀም ነው። በግብርና ሥራው ላይ ያለው ኃይል በዕድሜ የገፋው ብቻ እየቀረ፤ወጣቱ ከገጠር እየወጣ እንደሆነ የታዘቡ አስተያየት ሰጪ ጉዳዩ ተፈትሾ ከወዲሁ እልባት እንዲያገኝ ካልተደረገ በምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ያላቸውን ስጋት ጠቁመዋል።
ያለፈው ሥርአት የግብርና መር ፖሊሲ የግብርናውን እንቅስቃሴ እንደ ጎዳውም ተጠቁሟል። አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ፖሊሲው በሀገር ውስጥ የስንዴ ልማትን እያዳከመ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርትና አገልግሎት ነበር የሚያበረታታው። በሀገር ውስጥ የቅባት እህል በየአካባቢው ይመረት የነበረውን የምግብ ዘይት በውጭ ምርት እንዲተካ ተደርጎ አቅርቦቱ በውጭ ላይ ብቻ እንዲገደብ ሆኗል። በአጠቃላይ በሀገር ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጭን በማስከተል ሀገርን በመጉዳት ተጽዕኖ አሳድሯል ሲሉ የፖሊሲውን ድክመት አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የምግብ ዘይት በማምረት፣ የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ በአጠቃላይ ሰባት በሚሆኑ የኢንቨስትምት ዘርፎች ላይ በመሰማራት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ፣ ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ፀባይ፣ሰፊ መሬት እያላት ግን በግብርናው ዘርፍ ትልቅ የሚባል ለውጥ አለማስመዝገቧንና በዚህም እንደሚቆጩ ገልጸዋል።
ባለሀብቱ በአነስተኛ ነገር ላይ በመጠመድ የሀገር ኢኮኖሚን የሚያሳድግ የግብርና ሥራ ተዘንግቷል ይላሉ። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊለውጥ የሚችለው ግብርና እንደሆነም ጠቅሰዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ መንግሥት ጥሩ የሚያሰራ ፖሊሲ ቢቀርጽም፣ ወደ መሬት አውርዶ መተግበሩ ላይ ብዙ ይቀራል። በሰሊጥ፣በቡና፣በሰብልና በሌሎችም የግብርና ዘርፎች በማልማት ላይ የተሰማራው ባለሀብት በየተሰማራበት ተደራጅቶ በመስራት መንግሥትን ማገዝ ይኖርበታል። አርሶ አደሩም ጠንክሮ እንዲሰራ ጉልበትና መሬት እንዲገናኝ ማድረግ ይገባል።
ቤንችማጂ ዞን እርሻ እንዳላቸው የጠቀሱት ባለሀብቱ፣ በቀን ከምግብ አቅርቦት በተጨማሪ አንድ መቶ ብር እየከፈሉ እንደሚያሰሩ ይናገራሉ። በተቃራኒው ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሥራ አጥ መኖሩ ግራ የሚያጋባ እንደሆነም ይገልጻሉ። የሥራ ባህል መለወጥ እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ በላይነህ፣ የፌስቡክ አስተሳሰብ ወደ ልማት መቀየር አለበት ሲሉ ምክረሀሳብ ሰጥተዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች በአስተያየትና በጥያቄ በተነሱት ነጥቦች ላይ የፕላን ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በሰጡት ማብራሪያ፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ በእቅድ የተያዙትን ነገሮች ከግብ ለማድረስ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰዋል። በታሰበው ልክ በጥራትና በፍጥነት ለማሳካት የማያስችሉ ነገሮች እንደሚያጋጥሙ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት ገልጸው፣ ስለግብርና የተሰጠውን አስተያየትና በጥያቄ የቀረቡትንም እንደሚጋሩ ነው የተናገሩት።
እርሳቸው እንዳሉት፤ እንደ ሀገር በግብርናው ላይ ለመሥራት የሚያስችል አቅም አለ። የግብርናው ዘርፍ በትንሽ የትኩረት አቅጣጫ ብዙ የሚሰጥ ወይንም ብዙ የሚገኝበት ነው። ግብርና ላይ ኢንቨስት የሚደረገው አንድ በመቶ ድህነትን በእጅጉ ለመቀነስ ይጠቅማል። እንደ ኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ህዝብ ለሚኖርባት ሀገር ግብርናው ድህነትን ለመቀነስ በእጅጉ አጋዥ ነው።
እንደ ሀገር ባለፉት አራት አመታት በዘርፉ በተከናወኑት ተግባራት ከነጉድለቱም ቢሆን ለውጥ ያስገኙ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለእዚህ በአብነትም ግብርናውን በፋይናንስ ለመደገፍ የተደረገውን ጥረት ጠቅሰዋል። የመስኖ ልማትን ጨምሮ ለዘርፉ የተመደበው በጀት ከቀደመው ከ175 በመቶ በላይ ጭማሪ እንዳለውና ይሄም ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አንዱ ማሳያ መሆኑን ያብራራሉ። በትኩረቱ ልክም ግብርናው ውጤታማ እያደረገን ነው ይላሉ።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያ ሁሉ ጦርነት ተገብቶም፣ የሰሜኑ ክፍል በተለይም የትግራይ ክልል ከማምረት ሥራ ተስተጓጉሎም በዘርፉ የምርት መጨመርን ማየት በራሱ ግብ ሆኖ ሊወሰድ ይገባል ነው ያሉት።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ግብርናውን ለማዘመን የሚረዱ ለመካናይዜሽን የሚያግዙ እንደ ትራክተር እና የውሃ መሳቢያ(ፓምፕ) ያሉ የግብርና መሳሪያዎች ከውጭ በግዥ ሲገቡ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል። ይህም ትልቅ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል።
ከአነስተኛ መሳሪያዎች ጀምሮ ከቀረጥ ነፃ በገቡ የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች በመጠቀም 30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የእርሻ መሬት ለማረስ ተችሏል። በአሁኑ ጊዜም በሀገሪቱ በቁጥር ከስድስት ሺ በላይ ትራክተሮች ይገኛሉ። ይሄ በሀገሪቱ የግብርና ሥራ ታሪክ በተለይም ባለፉት አራት አመታት ጊዜ ውስጥ ያለውን ለውጥ ብቻ በማየት ውጤቱን መገምገም ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል።
የውሃ መሳቢያ (ፓምፕ) በመጠቀም በአነስተኛ የግብርና ሥራ ውጤታማ የሆኑ አርሶአደሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር ፍጹም፣ ፓምፕ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ትላልቅ የመስኖ ግድብ መሥራት ሳያስፈልግ በፓምፕ ከወንዞች ውሃ በመጥለፍ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚቻልበት ዕድል መፍጠር እንደሚቻልና ይህም እየሆነ መሆኑን ነው ያስታወቁት። በአሁኑ ጊዜ በጸሀይ ሀይል የሚሰሩ ከ20ሺ በላይ ፓምፖች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸው፣ በጸሀይ ሃይል መስራታቸው በኃይል አጠቃቀም ላይም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሆኖ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሯ በኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ፣ የግብአት አቅርቦትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት። ይህም ለምርትና ምርታማነት መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልክተዋል። በኩታገጠም የማረስ ዘዴ የኦሮሚያ ክልል ብቻ 75 በመቶ በላይ ለመጠቀም መቻሉንና ይህም ከፍተኛ እመርታ እንደሆነ በማሳያነት አቅርበዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የመሬት ፖሊሲ ጉዳይ ብዙ የሚያከራክር ቢሆንም፣ በዚህ ረገድም ተሰርቷል። መሬት የኢኮኖሚ መሳሪያ መሆን ካልቻለ፤የፖለቲካ መሳሪያ ብቻ ሆኖ እንዲያገለግል ከተደረገ ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የመሬት ፖሊሲ ጉዳይ የሚያነጋግር ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ መሬትን የኢኮኖሚ መሳሪያ ለማድረግ ባለፉት አመታት ብዙ ርቀት ተሄዶ ተሰርቷል።
ለዚህም አርሶ አደሩ የመሬት ሰርተፍኬት (የምስክር ወረቀት) ማረጋገጫ እንዲኖረው በማድረግ የተሰራውን ሥራ ሚኒስትሯ ለአብነት ጠቅሰዋል። አርሶ አደሩ የማረጋገጫ ሰርተፍኬቱን በማስያዝ የባንክ ብድር እንዲያገኝ መቻሉ የፋይናንስ ችግሩ እንዲፈታለት ዕድል እንደሰጠውም ነው ያስረዱት።
60 በመቶ የሆነውን ከ30 አመት በታች ያለውን ወጣቱን ኃይል እንዴት የልማትና የእድገት ሚና እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻልም በፖሊሲ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ ስለግብርና ከንግግር ባለፈ ተግባራዊ ሥራ ውስጥ ተገብቷል ማለት እንደሚቻልና እየተገኘ ያለው ውጤትም በተለያየ መልኩ እንደሚገለጽ ነው የተናገሩት። ለበጋ መስኖ ልማት የተሰጠውን ትኩረት በመጥቀስም አነስተኛ የመስኖ ልማቶች ጭምር መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም በአነስተኛ የመስኖ ልማት ላይ የሚሰሩ ክልሎች እንዲበረታቱ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።ክልሎቹ የመስኖ ልማት ጥቅሙ ይበልጥ እንዲገባቸው እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። መንግሥት ለተሽከርካሪዎች ለሚውል ነዳጅ ያደርግ የነበረውን ድጎማ ወደ ግብርናው እንዲዞር ያደረገውንም ሌላው ማሳያ ነው እንደሆነም ዶክተር እዮብ ጠቅሰዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም